Monday 16 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 4)

Please read in PDF

3.  በጋሻው “ሰው መንፈስ  ነው” ይለናል፤ ከየት ይኾን የቀዳው?
    በጋሻው የሰውን ሰውነት አያምንም፡፡ ሰው ሥጋና ነፍስ ወይም ሥጋና መንፈስ ነው፤ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በጋሻው፣ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል፡፡” በሚለው ፍጹም ክህደት ደምድሞታል፡፡ የዚህ ኑፋቄ ትምህርቱንም ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦
   “ ... በእግዚአብሔር የተፈጠረው መንፈስ የሆነው ሰው ከምድር አፈር አዘጋጀው፡፡ ... ያበጀውን፣ የፈጠረውን ያበጀው ውስጥ ጨመረው፤ መንፈስ ሥጋ ውስጥ ገባ ማለት ነው፡፡ ... ነፍስ ማለት ሦስተኛ አካል ምናምን አይደለችም … ነፍስ የተባለው ነገር ዕውቀት ስሜት ፈቃድ ናት፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ዕውቀት ወይም ትምህርት ... ለምሳሌ፦ ባዮሎጂ አካል አለው እንዴ? ... እርሷ[ነፍስ] በመንፈስና በሥጋ መካከል ሆና ላሸነፈው ላሳመነው ... እርሷን ራሱ በዕውቀት ነው የምታሳምነው፡፡ ... በተጨባጭ ነገር ካመነች ስሜት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ...
     ... ስለዚህ ሰው የራሱ ፈቃድ፣ የራሱ እውቀት፣ የራሱ ስሜት ያለው ማንም ጣልቃ የማይገባበት ለወደደው ነገር ራሱን የሚያስገዛ ማንነት ባለቤት ሆኖ ተፈጠረ፡፡ ስለዚህ ሰው ማን ነው? ከተባለ መንፈስ ነው ነፍስ አለው በሥጋ ውስጥ ያድራል ነው መልሱ፡፡ ሰው ሥጋ ነው፤ ነፍስ ነው አትልም፤ ሰው ማን ነው? ከተባለ ሰው መንፈስ ነው፤ …” 


      በጋሻው፣ በዘፍ.1፥26-27 እና 2፥7 ላይ ሲያብራራ ከተናገረው የተወሰደ ነው፡፡ በአጠቃላይ የበጋሻውን ሃሳብ ስንጨምቀው፣ “እግዚአብሔር አስቀድሞ አካል የሌላት ነፍስን[መንፈስን] ፈጠረ፤ ከዚያም ቀጥሎ ሥጋን ፈጠረ፤ የፈጠረውንም ነፍስ[መንፈስ] ባበጀው ወይም በፈጠረው ሥጋ ውስጥ አኖረው፤ ስለዚህም ሰው መንፈስ ነው” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን በጋሻው እንደሚለው “ሰው መንፈስ ነው ወይም መንፈስ ነን” ለሚለው ትምህርቱ፣ የጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይደግፈዋልን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ፣ ሙሉ ለሙሉ አይደለም የሚል ነው፡፡
    እንዲያውም ይህ የበጋሻው ትምህርት መመለስ የማይችላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ጥያቄዎች ብናቀርብ፦
1.     ሰው መንፈስ ከኾነ በዘፍ.1፥27 ላይ ጾታዊው ምደባ ለነፍስ ወይስ ወይስ ለሥጋ ተደርጎ ይኾን? መንፈስም[ነፍስም] ጾታዊ ምደባ አለው ማለት ነው?
2.    ለመኾኑ እግዚአብሔር ፍጥረትን ፈጥሮ የጨረሰው በስድስቱ ቀናት አይደለምን? ስድስተኛው ቀንስ፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን፤” (ዘፍጥ.1፥31)፣ እንዲሁም “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ” (ዘፍጥ.2፥1) እንደተባለ፣ ፍጥረት በስድስተኛው ቀን መጠናቀቁን ይነግረናል፤ እርሱ እንደሚለው እንኪያስ ዘፍጥ.2፥7 ላይ የተጠቀሰው ሃሳብ የስንተኛ ቀን ፍጥረት ይኾን?
3.    ዘፍ.1፥26 ላይ ያለው “ሰው ነፍስ እንጂ ሥጋ የለውም” ለማለት ምክንያታችን ምንድርነው? ዓውዱ ይላልን? ሌላስ የሚደግፈን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይኖር ይኾንን? እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ለእነዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች መልስ እንደማይኖራቸው እጅጉን የተገለጠ ነው፡፡
      ከዚህ በታች ሁለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለእግዚአብሔር ቃል ሃሳብ በማድላት እናብራራለን፦
ü ዘፍ.1፥26-31
    ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እግዚአብሔር ሰውን ሕይወት ካለው እንሰሳ “ይሁን!፤ ይሁን!” በማለት አለመፍጠሩን ይነግረናል፡፡ ይልቁን አክብሮና ወድዶ በልዩ ክብር በእጆቹ ማበጀቱን፣ ይህንም በመልኩ እንደ ምሳሌው መፍጠሩን እናያለን፡፡ እግዚአብሔር የእርሱን ባሕርያት፣ ማንነቱንም ጭምር እንድናንጸባርቅ ከአፈጣጠራችን ጀምሮ ባለው ፈቃዱ ገልጦታል፡፡ በዚህም ሰው ከእንሰሳ ፈጽሞ የተለየ መኾኑን እናስተውላለን፡፡
    በዚህ ክፍል “መልክና አምሳል” የሚሉት ቃላት “ሰው መንፈስ ነው” ለሚሉ ወገኖች ለክርክር አጋልጠው ሲያቀርቡ እናያለን፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናጠና[ምናችን በትክክል እርሱን እንደሚመስል ባይገልጥልንም] “መልክና አምሳል” የሚሉት ቃላት፣ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው መኾናቸውን እናስተውላለን፡፡ ጠቅላላ የክፍሉ ዓውድ ሰው ከእግዚአብሔር እንጂ ራሱ እግዚአብሔር አለመኾኑን፣ የሰው ምንጭና መገኛ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው በራሱ ቅድመ ኑባሬ የሌለው መኾኑን፣ ሰው በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተፈጠረ እንጂ ራሱ ፈጣሪ አለመኾኑን፣ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥር ሰውም ምንም በልዩ መልክ የተፈጠረ ቢኾንም የእግዚአብሔር ፍጥረት አካልና እንደሌሎቹ ፍጥረታት በየወገኑ ሳይኾን ወንድና ሴት ኾኖ መፈጠሩን፣ ሰው ለእግዚአብሔር በእግዚአብሔር መፈጠሩን … ክፍሉ በሚገባ ያስረዳናል፡፡
     “እንፍጠር” የሚለው ቃል እግዚአብሔር ከመፍጠሩ በፊት ሰውን ለመፍጠር ልዩ ምክር እንዳለው ያሳያል፡፡ በመልኩና በአምሳሉ በመፈጠሩም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አንድነትና ልዩነት መኖሩ እንጂ ፍጹም አንድነት አለመኖሩ ግልጥ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት የእግዚአብሔርን በረከት ተቀባይ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ “ተገንዛቢ”ና የፈቃዱ ፈጻሚ መኾኑን እናያለን፡፡ ስለዚህም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ተፈጠረ፡፡ የመጀመርያው የዚህ ቃል ተቀባዮችም “መልክና አምሳል” የሚሉትን ቃላት የተረዱት እውነት፣ የእግዚአብሔርን ወኪልነት(Vicegerent) እንጂ ሰው እግዚአብሔር[መንፈስ] መኾንን አልነበረም፡፡
     እግዚአብሔር የሰውን ሁለንተና ፈጥሮ የጨረሰው በዘፍ.1 ላይ ነው፡፡ ፍጥረትም ሁሉ ተፈጥሮ የተጠናቀቀው በምዕ.1 ላይ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን፤” (1፥31)፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረውም ቀን፣ “እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤” የሚለውን ባርኮት የሰጠው ለሁለቱም[ለአዳምና ሔዋን] ነው፡፡ ስለዚህም ያልተጠናቀቀውን[ሥጋ የሌለውን መንፈስ የነበረውን ሰው ብቻ] በዚህ ባርኮት ባረከው ለማለት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለንም፡፡
     በክርስትና ነገረ መለኮት ፍጥረት ተፈጥሮ የተጠናቀቀው በስድስት ቀናት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለ፡፡ እግዚአብሔርም እያንዳንዱ ነገር በራሱ መልካም መኾኑን ብቻ ሳይኾን፣ ነገሮቹ ሁሉ በአንድነት ተገኝተው እርስ በርሳቸውም ተስማምተው፣ ያለግጭት መኖር እንደሚችሉና የእግዚአብሔርን ዕቅድ እንደሚፈጽሙ “ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” የሚለው ቃል ያጸናዋል፡፡ ስድስቱ ቀናትም በምዕ.1 ውስጥ ተካትተው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ከስድስቱ ቀናት ውጪ ፍጥረት ተፈጠረ ማለት፣ “አርዮስ በተወገዘ ጊዜ ሆድ ዕቃው ተዘርግፎ ሲሞት በሆዱ ላይ ጌሾ፣ ጫት፣ ትንባሆ … በቀለ” ከሚለው የአሮጊት ተረት ጋር ስምም ነው፡፡
    እግዚአብሔር ሌሎችን ፍጥረታት በየወገናቸው መፍጠሩን እንጂ እንደሰው፣ “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ተብሎ አልተጻፈም፤ በዚህም ሰው በፍጥረት ክብሩ ከእንሰሳት በሚልቅ ክብር መፈጠሩን እናያለን፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰው የተፈጠረበትን የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል መጽሐፍ እንደሚለን፣ ጽድቅና ቅድስናን (ኤፌ.4፥24)፣ ዕውቀትን (ቈላ.3፥10) … ከማመልከቱ ባሻገር በራሳችን ሌላ ከዚህ ጋር የማይመሳሰል ትርጉም ብንሰጠው በቃሉ ላይ ጨምረናልና ሐሰተኞች ነን፤ (ምሳ.30፥6)፡፡

ü ዘፍጥ.2፥7 
     ይህ ክፍል የምዕ.1 ሌላ እይታ ወይም ማብራሪያ እንጂ ከስድስቱ ቀናት ውጪ ቀጣይ ታሪክን በራሱ የያዘ አይደለም፡፡ የፍጥረትን ታሪክ በተመለከተ ከሁለት አቅጣጫ በመመልከት የተቀመጡ እንጂ ሁለት የተለያዩ ታሪኮችና ክስተቶች አይደሉም፡፡ ይህ ደግሞ የቅዱሳት መጻሕፍት ባሕርይ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ሰው ከመሬት ተነሥቶ አራቱ ወንጌላት ይበዛሉና ይቀነሱ ቢል ጤናማ ሃሳብ ነው ብለን አንቀበለውም፤ ምክንያቱም የአንዱን የጌታችን ኢየሱስን ትምህርትና ሕይወት ከአራት ወንጌላውያን ዕይታ አንጻር አይተው አስፍረውታልና በደስታ ተቀብለነዋል፡፡ በዘፍ.1 እና 2 ላይም አንድን የፍጥረት ታሪክ በሁለት እይታ መስፈሩን ማስተባበል አንችልም፡፡ 
    አልያ ግን አሁንም ሌላ ጥያቄ ልናስነሳ እንችላለን፤ “እግዚአብሔር ፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ አልጨረሰም” ወደሚል አንድ እንግዳ ጫፍ ይወስደናል፡፡ ስለዚህ ምዕ.2 የምዕ.1 ማብራሪያ ወይም ሌላ እይታ ነው፡፡[1] ምዕ.2፥1 “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ” ብሎ ከፍጥረት መፈጠር መፈጸም በኋላ የኾነውን ነገር “ … የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው” (2፥4) በማለት ያጸናዋል፡፡
   በምዕራፍ.1 እና 2 መካከል ያለውን ፍጹም ዝምድና ቄስ ኮሊን በመጽሐፋቸው እንዲህ አስቀምጠውታል፤
     “እግዚአብሔርን በተመለከተ ምዕራፍ አንድ፥ በመፍጠሩ ልዕልናውን፥ ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ለሰው አስፈላጊውን ሁሉ ማዘጋጀቱን ያሳያል፡፡ ሰውን በተመለከተም ምዕራፍ አንድ ሰው የፍጥረት አክሊልና መጋቢ መኾኑን ሲያመለክት፥ ምዕራፍ ሁለትም ምድራዊ አኗኗርን ያሳያል፡፡ በአጭሩ የምዕራፍ አንድ ፍሬ ነገር ፍጥረት ሲሆን፥ የምዕራፍ ሁለት ደግሞ ገነት ነው፡፡ ሰው በምዕራፍ አንድ የፍጥረት ራስ፥ በምዕራፍ ሁለት የገነት ባለቤትና ጠባቂ ነው፡፡
      ምዕራፍ አንድ የሰማያትንና የምድርን ታሪክ ሲተርክ፥ እግዚአብሔር በልዕልና እየተናገረ ሁሉን ለሰው እንዳዘጋጀ ይገልጣል፡፡ ሁሉም ከተዘጋጀና ልዩ አምላካዊ ምክክር ከተደረገ በኋላ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ከፈጠራቸውም በኋላ ባረካቸው፤ በዓለም ላይ ሾማቸው፤ በዓለምም እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚገባቸው ነገራቸው፡፡”[2]
      ሁለቱም ምዕራፋት ስለአንድ ነገር የሚናገሩን ከኾነ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የአንደኛው ሌላ እይታ ወይም ማብራሪያ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምዕ.1 ላይ እንፍጠር ብሎ በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩን የሚነግረንን፣ ምዕ.2፥7 ላይ ደግሞ፣ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” በማለት “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያውን ይሰጠናል፡፡ እንዲሁም፣ “ወንድና ሴት” ተደርገው የተፈጠሩት ሰዎች እንዴት ተፈጠሩ? ብንል ሁለተኛው ምዕራፍ፣ “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ሥፍራውን በሥጋ ዘጋው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፤” (2፥21-22) በማለት ያብራራልናል፡፡
     ከዚህም የተነሣ የሰው ነፍስና ሥጋው በተለያዩ ጊዜያት መፈጠራቸውን የሚያሳይ አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልን ማንሳት አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረበት ቀን ሥጋውንም ነፍሱንም[መንፈሱንም][3] በአንድነት ፈጥሮታል፤ ስለዚህም ሰው ስንል ሥጋና ነፍስ ያለው ወይም ሥጋና መንፈስ ያለው ማለታችን ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይመሰክርልናል፡፡
ው ሥጋም አለው፤
    ሥጋ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ነገርን ሊያመለክት ይችላል፤ ከእኛ ርእስ ጋር ብቻ የሚዛመደውን ብንወስድ፣ “(1) ከአጥንት በቀር የሰው ወይም የእንሰሳ ክፍል፣ (ዘፍጥ.40፥19)፤ (2) ጠቅላላው ግዙፍ የሰው አቅዋም፣ (ያዕ.2፥26)፤ (3) የሰው ሁለንተና (ዮሐ.1፥14 ፤ 1ዮሐ.4፥2) ይህም ደካማ ነው፤ (ማቴ.26፥41 ፤ ሮሜ.6፥19) …” በማለት መዝገበ ቃላቱ[4] ያስቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ ሥጋ ስንል የሚታየውን፣ የሚዳሰሰውን፣ የሚያዝና የሚጨበጠውን፤ ውጫዊውንና ውስጣዊውን የሰውነታችን ክፍል ማለታችን ነው፡፡
     ሥጋ በእግዚአብሔር ከምድር አፈር የተበጀ ነው፤ ስለዚህም ሰው የፍጥረት አክሊል ነው፡፡ ክቡርና ከምናየው ዓለም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነትን የምናደርግበት፣ እግዚአብሔርንም ለማምለክና ለማክበር በቅድስና ልናቀርበው የሚገባን ሰውነት(ሮሜ.12፥1-3) ነው፡፡ ደግሞም ይህ ሰውነታችን፣ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ፤” (1ቆሮ.3፥16)፣ “እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና” (2ቆሮ.6፥16) በማለትም ያጸናዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሰውን ሥጋነት[ሥጋ ስለኾነው ተፈጥሮው] የሚያስረግጡ እጅግ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤  
ü “እግዚአብሔርም፦ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ” (ዘፍጥ.6፥3)
ü  “ከዝሙት ሽሹ፡፡ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል፡፡ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፤” (1ቆሮ.6፥18-20)
ü “ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም” (መዝ.38፥3)፤
ü “ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ” (ሰቆ.2፥11)
ü “በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው” (ፊልጵ.1፥23-24)
ü ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፤ (ቈላ.2፥22)
   መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሥጋም መኾኑን ቢናገርም፣ በጋሻውና ባልንጀሮቹ ግን ይህን እውነት ከዓውድ ውጪ አጥምመው የሚጠቅሷቸው ሌሎች ጥቅሶች አሏቸው፡፡ በጋሻው በዚህ ትምህርቱ እኒህን ጥቅሶች አላነሳቸውም፤ ወደፊት ግን በትምህርቱ ላይ ሰፋ ያለ ሥራ ስንሠራ እኒህን ጥቅሶች ለእግዚአብሔር ቃል ክብር በማድላት እናብራራዋለን፡፡
ው ነፍስም አለው፤
    የሰው ነፍስ፣ “ … በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (2፥7) እንዲል፣ የሰው ሁለተኛ ክፍል ኾና የተነገረችው ናት፡፡ አንዳንዶች የሰውን ነፍስ መንፈስ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ነፍስና መንፈስ[5] በየራሳቸው የተለያዩ ናቸው ይላሉ፡፡ ነፍስ የራሷ ማንነትና አካል[6] ያላት ስትኾን፣ ልክ እንደሥጋ በድካምና በኃጢአት ልትያዝ እንደምትችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስቀምጣል፤ “እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ፥ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች፤” (መዝ.78፥8)፣ “በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፥ የሚያጕረመርሙም ትምህርትን ይቀበላሉ” (ኢሳ.29፥24)፣ በአዲስ ኪዳንም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” (2ቆሮ.7፥1) በማለት መንፈሳችንም ሊረክስ እንደሚችል ነገር ግን ቅድስናን ፍጹም በማድረግ በእግዚአብሔር ፍርሃት መንጻት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡
     ከዚህም ባሻገር ነፍስም[መንፈስም] መኖርዋን የሚያስረግጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤ እኒህም፦
ü “በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤” (1ሳሙ.1፥15)
ü “አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ” (መዝ.25፥1)
ü “ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና” (መዝ.62፥1)
ü “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” (ሉቃ.1፥46)
ü “እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤” (1ቆሮ.5፥3-4)
   መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ሁለንተና ሰውነት በሚገባ አብራርቶ አስቀምጧል፡፡ የሰውን ነፍስነት[መንፈስነት] ብቻ ነጥሎ ማቅረብና ማስተማር ሰውን ለሌላና እንግዳ ለሆነ ትምህርት በሚገባ ወልውሎ፤ ወና አድርጎ ጠርጎ ማሰናዳት እንደኾነ ግልጥ ነው፡፡ ደግሞም ሥጋን መጣልና ሥጋን አልለበስኩም ማለት ለብዙ ክህደት ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ሰው ማለት ሥጋ፣ ነፍስ ወይም መንፈስ ነው፡፡ እንዲያው በምሳሌነት ብንጠቅስ፦ ሰው ሲሞት ነፍስና ሥጋው ይለያያሉ፤ ነፍሱን ብቻ ሰው አንልም፤ ሥጋውንም ብቻም ሰው አንልም፡፡ የሁለቱ በአንድነት መኾን ግን ሰውን ሰው ያሰኘዋል፡፡
    የበጋሻውን ትምህርት የሚጋሩ የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ በእርግጥ እነርሱ ሊሉ የፈለጉትን በግልጥ እስከመጨረሻው ለጥጠው ተናግረውታል፤ በጋሻው እንዲህ ለማለት መንገዱን ገና እያደላደለ ነው፤ የሰውን ልጅ ደረጃ ወደፈጣሪነት ከፍ የማድረጉ ትምህርት ጥረትና ድካሙ የፊተኛውን ስህተት በአደባባይ ለመድገም ማመቻመቻ ነው፡፡ እንዲህ በማለት፣ “ሁሉም የሚወልደው የራሱን ዓይነት ነው፤ የፈረስ ልጅ ፈረስ ነው፣ የድመት ልጅ ድመት ነው፣ … ከእግዚአብሔርም የተወለደ ሁሉ የእግዚአብሔር ዓይነት ነው፤ ማለትም እግዚአብሔር ነው፡፡ (ክሬፍሎ ዶላር እና ጆይስ ሜየር)፣ “እግዚአብሔር ራሱን ሊያበዛ ፈልጎ ነው እኛን ያመጣን” (ጆን አቫንዚኒ እና ሞሪስ ሴሬሎ) እና ሌሎችም “መንፈስ ነን” የሚለውን ትምህርት እዚህ ድረስ ለጥጠውታል፡፡
 “የሰው ነገር” ማጠቃለያ
    ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው በሁለንተናው እንጂ ሥጋ ወይም ነፍስ ብቻ ሆኖ አይደለም፡፡ በዘፍጥ.1 ላይ የተጻፈው ጠቅላላው የሰው አፈጣጠር ሲኾን፣ በዘፍጥ.2 ላይ ግን ከሌሎች ፍጥረታት በሚለይና ልዩ በሆነ ክብር የሰው አፈጣጠር “እንዴት ተፈጠረ?” የሚለውን “ሙሉ መልስ” ለመመለስ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በጋሻው በትምህርቱ እኒህን ሁለቱን ድንበሮች መለየት ተስኖት ፍጹም ሲሳሳት አይተነዋል፡፡ ቃሉንም እንደምናጠናው የሰው ሥጋ የተካደበትን የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል ፈጽሞ አናገኝም፡፡
     የበዛው የቅዱሳት መጻሕፍትም ማብራሪያ፣ ሰው “የእግዚአብሔር መልክና አምሳል ነው” የሚለውን ትርጉም ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ተመሳሳይነት[አምሳያነት] እንጂ ፍጹም አንድነት[አንድ ዓይነትነት] የሚያጸባርቅ አለመኾኑን ነው፡፡ እናም ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ነው፤ የመልኩና የአምሳሉ ነጸብራቅ ነው፤ ይህ ሰው የፊተኛውን እግዚአብሔራዊ መልክና አምሳሉን በኃጢአት ሲያበላሽ፣ እግዚአብሔር ዳግመኛ ሰውን በክርስቶስ ኢየሱስ በሥጋ ሞቱና ትንሣኤው በመልኩ ፈጥሮ አዲስ ፍጥረት አድርጎታል፤ (ኤፌ.2፥10 ፤ 4፥24 ፤ ቈላ.3፥10)፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ለኹላችን ማስተዋልና ቃሉን እግዚአብሔርን በመፍራት፤ በማንበብ የሚገኘውን ብጽዕና ለሁላችን ያድለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




   [1] አንዳንዶች ምዕ.1 እና 2ን የተለያዩ ሰዎች መጻፋቸውን ይገልጣሉ፡፡ ይህም ቢኾን እንኳ ነቢዩ የፍጥረት አፈጣጠር ሁለቱንም ታሪኮች በትክክል አስቀምጧቸዋል ማለት ነው፡፡
   [2] ትምህርተ ክርስቶስ ገጽ.16

[4] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ.66
    [5]       ሰው ስላለው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች  ዘንድ ሁለት ዓይነት አመለካከት አለ፤ ይኸውም ሰው ነፍስና ሥጋ ነው፤ ሰው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ነው የሚሉ ወገኖች ናቸው፡፡ የሰው ተፈጥሮው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ነው የሚሉ ወገኖች ከሚጠቅሷቸው የመጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ፣ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” (1ተሰ.5፥23) የሚለውን ቃል በመያዝ ነው፡፡ የነፍስና የመንፈስን ልዩነትንም ሲያስረዱ፣ ነፍስ የሰውን አእምሮ፣ ስሜትና ፈቃድን የሚያመለክት ሲኾን፣ መንፈስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በአምልኮትና በጸሎት የሚገናኘውን አመልካች ነው ይላሉ፡፡ የዚህ ትምህርት ተከታዮችም የሦስትዮሽ መላምት(Trichotomists) ተከታዮች ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሦስትዮሽን ትምህርት ተከታዮች፣ “ ሰው መንፈስ ነው” ለሚለው ትምህርት ተጋላጭ መኾናቸውን ቄስ ኮሊን ማንሰል፣
   “ … የተወሰኑት ደግሞ መንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ክፍልና ከአእምሮ፥ ከስሜትና ከፈቃድ የተለየ ክፍል እንደሆነ በማሰብ፥ መንፈሳዊ ሰው ብዙ ማጥናት የማያስፈልገው መሆኑን ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ከዚህም ጋር በክርስቲያናዊ ኑሮ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናትና ከማንበብ ይልቅ መንፈሳዊ ተመክሮና ስሜት የሚበልጡ ይመስላቸዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች “እኔ መንፈስ ነኝ” በማለት ሊፎክሩ እንደሚችሉ አይተናል፡፡” (ቄስ ኮሊን ማንሰል፣ ትምህርተ ክርስቶስ፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ.41) በማለት ተናግረዋል፡፡
   ነገር ግን የሦስትዮሽን መላምት የሚከተሉ ሁሉ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ይቀበላሉ የሚለውን እንዳልኾነ ማስታወስን እወዳለሁ፡፡
      [6]  አካል ማለት ከግዑዝ ወይም ከሚዳሰስና ከሚያዝ ነገር ጋር የሚያያዝ ሳይኾን ሰምቶ ከሚመልስ፤ ዕውቀትና ፈቃድ ካለው ነገር ጋር የሚያያዝ እንጂ እንደበጋሻው አስተምኅሮ ምናብና የማይታይ ነገር ሁሉ አይደለም፡፡ ነፍስ፣ መላእክት፣ ነፋስ፣ መለኮት  … እና ሌሎችም አካል አላቸው፡፡

12 comments:

  1. GEta Eyesus tsegana mastewalun yadilih .... bzu neger asayehn berta berta

    ReplyDelete
  2. “አርዮስ በተወገዘ ጊዜ ሆድ ዕቃው ተዘርግፎ ሲሞት በሆዱ ላይ ጌሾ፣ ጫት፣ ትንባሆ … በቀለ” ከሚለው የአሮጊት ተረት ጋር ስምም ነው፡፡I didn't understand those sentenses.is that related with the contecstual?

    ReplyDelete
    Replies
    1. እህት መስከረም እነኔ እንደተረዳሁት ፍጥረት ተፈጥሮ የተጠናቀቀው በ6ቱ ቀናት ነው፡፡ ነገር ግን በጋሻው ሰው ሥጋው ከ6ቱ ቀን ውጪ በማለቱ፡ በአርዮስ ሆድ ጫት ጌሾ በቀለ የሚሉም ከ6ቱ ቀን ውጪ ፍጥረት ተገኘ በማለታቸው ይህ አባባላቸው ኑፋቄ ነው ለማለት ይመስለኛል እንደገባኝ፡፡

      Delete
  3. Woow tebarek wendm tsega yibzalh

    ReplyDelete
  4. በጣም ያሳዝናል ጌታ ይርዳው ወንድማችንን

    ReplyDelete
  5. የሚገርም ጭካኔና ድፍረት የዚህ ዘመን ሰማዕትነት እንዲህ በግልጽ የሐሰት ትምህርትን መቃወም ነው፡፡ በርታ አቤን ጌታ ካንተ ጋር ይሁን፡፡

    ReplyDelete
  6. አንተ ውሸታም በጋሻው ወንጌል ባይሰብክም ልትወደው ይገባህ ነበር

    ReplyDelete
  7. ይህ ጽሑፍ ተሐድሶ ተሐድሶ ይሸታል

    ReplyDelete
  8. Melktu tru new gn askedimachu lemn atinegrutm? Sewoch esu aysemam silu semalaw bihonm enante ltanagrut yigebal. Egzabher yirdaw entseliyalen.

    ReplyDelete
  9. ወንድሜ ተሳስተሃል!! የክርስቶስ ወንጌል ወንድምህን እንደራስህ ውደድ ነው የሚለው፡፡ ክርስቶስ ለአንተም እርሱም እኩል ቅዱስ ደሙን አፍስሷል፡፡ ወንድምህ ተሳስቶ ከሆነ በፍቅር ሆነህ ቀርበው ምከረው፣ አወያየው "በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን" ይለናልና ቅዱስ ቃሉ፡፡ እውነተኛ ፍቅር በአደባባይ ወንድምን እንደዓለማውያን ጋዜጠኞች ለጥላቻ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ የቱንም ያህል እውቀት ቢሞላን ፍቅርን ካልኖርነው ከንቱ ድካም ነውና ይህንንም ቅዱስ ጰውሎስ በ1ኛቆሮንጦስ ምእራፍ 13 መልእክቱ የክርስቶስን ባህሪ አመላክቶናል፡፡ ፍቅርን ሳንኖረው ክርስቲያን ነን ብንል ከንቱ ነው፡፡ የክርስቶስን መንገድ አልያዝክም፡፡ ጌታ እንዳስተማረን ሁላችንም መጀመሪያ "የአይናችንን ጉድፍ ማጥራት ይገባናል፡፡" በነገራችን ላይ ወንድሜ ይህ አስተያየቴ አንተን ብቻ ሳይሆን እኔንም ይመለከታል፡፡ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡

    ReplyDelete
  10. ወንድሜ ተሳስተሃል!! የክርስቶስ ወንጌል ወንድምህን እንደራስህ ውደድ ነው የሚለው፡፡ ክርስቶስ ለአንተም እርሱም እኩል ቅዱስ ደሙን አፍስሷል፡፡ ወንድምህ ተሳስቶ ከሆነ በፍቅር ሆነህ ቀርበው ምከረው፣ አወያየው "በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን" ይለናልና ቅዱስ ቃሉ፡፡ እውነተኛ ፍቅር በአደባባይ ወንድምን እንደዓለማውያን ጋዜጠኞች ለጥላቻ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ የቱንም ያህል እውቀት ቢሞላን ፍቅርን ካልኖርነው ከንቱ ድካም ነውና ይህንንም ቅዱስ ጰውሎስ በ1ኛቆሮንጦስ ምእራፍ 13 መልእክቱ የክርስቶስን ባህሪ አመላክቶናል፡፡ ፍቅርን ሳንኖረው ክርስቲያን ነን ብንል ከንቱ ነው፡፡ የክርስቶስን መንገድ አልያዝክም፡፡ ጌታ እንዳስተማረን ሁላችንም መጀመሪያ "የአይናችንን ጉድፍ ማጥራት ይገባናል፡፡" በነገራችን ላይ ወንድሜ ይህ አስተያየቴ አንተን ብቻ ሳይሆን እኔንም ይመለከታል፡፡ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡

    ReplyDelete