Friday, 21 November 2025

የትውልድ ነቀርሳ - የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ (የመጨረሻው ክፍል)

 Please read in PDF

የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ፦

6.    በልምምዱ ጥንቁልናና አስማትን ያበረታታል፦ ኮከብ ቈጠራ እና ጥንቈላ፡ ለራስ ለውጥ እና ማስተዋል የሚያገለግሉ ሟርት አክል መሣሪያዎችን በጽኑ ይደግፋሉ። በራሳቸው ይህን ቢደግፉና ቢቀበሉ ማንም አይቃወማቸውም፣ ምክንያቱም “የትኛውም ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን የሮንዳ በርንን፣ የቦብ ፕሮክተርን፣ የድፓክ ቾፕራንና የኤካርት ቶልን፣ የማሪያን ዊልያምሰን፣ የባርባራ ማርክስ ሁባርድ፣ የኒሌ ዶናልድ ዋልሽ፣ የባርባራ ዴአንጀሊስ፣ የላቫር በርተን፣ የሪቻርድ ካርልሰን፣ የቤቲ ኢዲ፣ የኬን ፎሌት ወይም ደግሞ የእንቅስቃሴው አባቶች የሚባሉትን የአሊስ ቤይሊ፣ የቴይልሃርድ ዴ ቻርዲን፣ የሮበርት ሙለር፣ የዴቪድ ስፓንገር እና የቤንጃሚን ክሬም የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተምህሮን እያቀነቀኑ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ማለት ፈፅሞ አይቻልም።”


ጌታሁን ሄራሞ እንደሚለው፣ “እንዲያውም የአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ዋናው ዕቅድ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም የይሁዲና የክርስትናን እምነቶችን በሂደት ማክሰም ነው፤ ምክንያቱም በአዲሱ ዘመን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች በአንድ አምላክ መኖር የሚያምኑ በመሆናቸው የ"Low vibration" ባለቤት ናቸው ተብለው ይታመናሉ።” ነገር ግን የእንቅስቃሴው አማኞች በምትኩ፣ ጥንቈላንና ምዋርትን፤ አስማትና ድግምትን ያበረታታሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን በግልጥ፣

አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል። አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ኹን።” (ዘዳ. 18፥9-13)

ይላል።

እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለሙ አምላክና ገዢ ነው፤ እግዚአብሔር ኀጢአትን ጭምር ከወሰኑ ሳይወጣ ይቈጣጠረዋል፤ ሰይጣንም እንኳ በእግዚአብሔር ቍጥጥር ሥር ይገዛል፤ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ በአማኝ ልጆቹ ላይ ሲራገም፣ ሲጣላ ቢውል፣ አንዳችም ስንዝር መጠጋት አይችልም፤ “በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም።” (መዝ. 91፥7) እንዲል።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ጽኑ ጥበቃና መግቦታዊ እንክብካቤ ስላለው፣ “በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።” (ዘዳግ. 32፥10) እንደ ተባለው፣ “ከበበው ተጠነቀቀለት” ሲል፣ የእግዚአብሔርን ጫጩቶቿን ለመመገብና ለመንከባከብ እንዲሁም ከአደጋ ለመንከባከብ እንደ ምታንዣብብ ወፍ ያለ ጽኑ ጥበቃና ትድግናን የሚያመለክት ነው።

ይህ እግዚአብሔር ዛሬም ያህዌ ኤሎሂም ነው፤ ፈጥሮ የሚንከባከብና ጠብቆ ወደ ፈቃዱ በሰላም የሚያደርስ አምላክ ነው። በአዲስ ኪዳንም፣ “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴ. 9፥36) ተብሎ ለጌታችን ኢየሱስ እንደ ተነገረው እንዲኹ፣ ለሚያምኑት እጅግ የሚራራ፣ በጭንቀታችንና በንቀት በመተዋቸው የሚያዝንልን ጌታ አለን! ኢየሱስ ሕዝቡን ከአጋንንት እስራት ይፈታና ነጻ ያወጣ፣ ከለምጻቸው ያነጻ የነበረው፣ ሳይታክት ይፈውሳቸው፣ ያስተምራቸው የነበረው … ሕዝቡና የሚድኑ ወገኖቹ ስለ ኾኑ ነው። ይህንም የሚያደርገው ለሕዝቡ ካለው ርኅራኄ የተነሣ ነው። ለኢየሱስ ሕዝቡ ዘወትር እንደ ጠፉ በጐቹ ሲኾኑ፣ እርሱ ደግሞ የማይታክት የዘላለም እረኛው ነው።

እውነተኛው ክርስትና ለጠንቋይም ለአስጠንቋይም ስፍራ የለውም፤ ጥንቍልና የአጋንንት ሥራ ነው ብሎ በይፋ ይቃወማል፤ ሃይማኖተኞች ግን በክርስትና ስም ሊጠነቁሉም ሊያስጠነቁሉም ይችላሉ። እናም ለኹሉም አንድ ጽኑና የታመነ ስብከት አለን! ኢየሱስ ክርስቶስ ከየትኛው የአጋንንት እስራት ይፈታል፤ ይቤዣል፤ ይታደጋል፤ ነጻ ያወጣል፤ እናም ተደገመብን፣ ይደግሙብናል፤ ያስመትቱብናል ለሚሉትም ለሚደግሙትና ለሚያስመትቱትም እነሆ! ወደ ጌታ ኢየሱስ ኑና ከሃይማኖትና ከሰው የባርነት ትምህርት እስራት ተፈቱ ልንል እንወዳለን!

7.    ተግሳጽና ምክር ጥዩፍ “በአምልኮተ ውዳሴ” የተለከፈ አስተምኅሮ ነው፦ የሰው ሞት፣ የተገለጠ ስህተት፣ የአደባባይ ነውር፣ ጥፋትና ውድመት ጨርሶ እንዲነሣ አይፈልጉም፤ ይህን እንደ “Negative Potential” ይመለከታሉ፤ በአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ ውስጥ፣ “አሉታዊ አቅም” የሚለው ሐረግ በአጠቃላይ የሚያመለክተው አሉታዊ አስተሳሰቦችን፣ ስሜቶችን ወይም ኹኔታዎችን ወይም ድርጊቶችን በሕይወቱ ውስጥ ሊገለጡ የሚችሉበትን አቅም ኹሉ ነው። ይህ ፅንሰ-ሀሳብ የተመሠረተው የአንድ ግለሰብ ዐሳቦች፣ ስሜቶች እና አጠቃላይ “ንዝረት” እውነታቸውን የሚፈጥሩት በመሳብ ሕግ ወይም ተመሳሳይ መንፈሳዊ መርሆች ነው ከሚል እምነት ነው።

በዚህ ዐውድ ውስጥ የ“አሉታዊ አቅም” ቊልፍ ገጽታዎች፣ለምሳሌ፦ በአሉታዊ አስተሳሰብ ውስጥ መሳተፍ፣ እንደ ፍርሃት፣ ቊጣ ወይም ቅናት ያሉ ስሜቶችን ማቆየት ወይም እምነትን መገደብ “ዝቅተኛ ድግግሞሽ” ተመጣጣኝ አሉታዊ ልምምዶችን ወይም ኹኔታዎችን እንደሚስብ ይታመናል ወይም ደግሞ ካልተረጋገጠ ዕድል ጋር በማያያዝ የማይቀር ነገር ግን በማስተዋል ጥረት ሊወገድ ወይም ሊለወጥ ይችላል ብለው ያምናሉ። ከዚህም የተነሣ ግለሰቦች አሉታዊ ድምጾችን ችላ ብለው ይህንን እምቅ ችሎታቸውን ቢጠቀሙ ለመለወጥ ኃይል እንዳላቸው ይታመናል።

ጥፋት እያየን በዝምታ ሊያሞኙን፣ ደም መፍሰስና ርኩሰት እየተመለከትን “በጎ አይወጣችሁም” በሚል ማሸማቀቂያ “ሊያኮማትሩን”፣ ሥር የሰደደ የፍትሕ እጦት እያስተዋልን “ከትላንት አይብስም” በሚል የእባብና ዕንቁላሉ ንጽረት እያቀረቡልን፣ “ፍቅር ፍቅር፣ ልማት ልማት፣ ደስታ ደስታ፤ ጤና ጤና፤ ስኬት ስኬት ብቻ” እንዲወራ መፈለግ “እልል ያለ” የወጭት አጥሪ ግብዝ ጠባይ ነው።

የእግዚአብሔር ተግሳጽ ግን ያሳድጋል፤ ያስተምራልም (2ሳሙ. 22፥36፤ መዝ. 18፥35)፣ የሰሎሞን የምሳሌ መጽሐፍ ሙሉውን ማለት በሚያስደፍር “ተግሳጽ”ን መናቅ ድህነትና ነውርን መውደድ፣ በስንፍና መታሰር፣ የራስን ነፍስ መናቅ እንደ ኾነና ተግሳጽን መውደድ ግን ዕውቀትንና ጥበብን መውደድ፣ እንደ ባለ አእምሮ ልጅ በሕይወት መንገድም መመላለስ እንደ ኾነ በተደጋጋሚ ይመክራል፤ ምሳ. 1፥7፤ 6፥23፤ 10፥17፤ 12፥1፤ 13፥1፡ 18፤ 15፥32፤ 19፥20)።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከዚህ ከፍ ባለ መንገድ፣ ኀጢአተኝነትና መንገዱን መግለጥና ማሳየት ብሎም ሰዎች አለመቻላቸውንና ድካማቸውን ተመልክተው ወደ ኃያሉ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ፊት ለፊት ኀጢአተኛውን ዓለም በስብከትም፤ በሕይወትም በግልጥ ይወቅሳል። ዓለም ያለ ክርስቶስ ሞት ተፈርዶበታል፤ ይህ “Negative Potential” ሳይኾን የዘላለም እውነት ነው፤ ከሞት ማምለጥ የሚቻለው በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በማመንና በሕይወቱ በመመላለስ ብቻ ነው። በአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ውስጥ የተዘፈቃችሁ ኹሉ ከዚህ የጥፋ ትምህርት ታመልጡ ዘንድ እነሆ! እንለምናችኋለን፤ ፊታችሁን ወደ ሞተላችሁና መዳንን ወደ ፈጸመላችሁ ጌታ ትመለሱና ትድኑበት ዘንድ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16፥22)

ተፈጸመ በረድኤተ እግዚአብሔር!

4 comments:

  1. “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16፥22) amen amen

    ReplyDelete
  2. Egizabher yebarekeh 😊😊🤲🤲

    ReplyDelete
  3. ክብሩ ለኢየሱስ ይሁን።

    ReplyDelete