Saturday, 21 June 2025

ለኅብረት እንጠንቀቅ!

 Please read in PDF

ለመንፈሳዊ ኅብረት በምሳሌነት እንዲያገለግሉ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች መካከል፣ የሰውነት ክፍሎችን ወይም ብልቶች ናቸው። እነርሱም የተለያየ ችሎታና ተግባር ተሰጥቶአቸዋል። ልክ እንዲኹ፣ በክርስቶስ አንድ አካል የኾኑ አማኞች፣ የተለያዩ ጸጋ፣ ስጦታና ተግባር ተሰጥቶአቸዋል፤ “ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን።” (ሮሜ 12፥5) እንዲል።

ኅብረት የብልቶች ርስ በርስ የመቀባበልና በመገጣጠም አንድ የመኾን እንጂ፣ የአንድ አካል ትልቅነትን እግዚአብሔር በፍጹም በሰውነታችን ክፍሎች  ውስጥ አላስቀመጠም። ጆሮ ወይም ዓይን ከብልቶች ወይም ከአካላት ይበልጣል፤ ስለዚህ ልዩ ክብር ሊሰጠው ይገባል ማለት ጤናማነት አይደለም። በሌላም ንግግር ትንሿ የእግራችን ጣት “የእኔ አገልግሎት የመላውን እግር ያህል ነው!” ብትል ፍጹም ተሳስታለች።

ስለዚህ አንዱ ብልት ለሌላው ብልት ስጦታ መኾኑን መዘንጋት የለበትም። የሰውነታችን ክፍሎች በጋራ አንድን ተግባር በትክክል የሚፈጽሙበት እንጂ፣ አካላችን የአንድ ብልት መግነኛ አይደለም። በሌላ ንግግር አካል ጆሮ ወይም ዓይን ብቻ ነው ማለት አይደለም፤ መጽሐፍ፣ “አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና።” (1ቆሮ. 12፥14) ይላልና።

ከሌላው አማኝ እንደሚሻሉ ወይም እንደሚበልጡ ማሰብ፣ ትዕቢት ወይም ንቀት ነው። አንዱ አካል ከሌላው አካል በተግባሩና በስጦታ እንደማይበልጥ ወይም እንደማያንስ እንዲኹ፣ እኛ አማኞችን ርስ በርስ አንድ ነን እንጂ የምንበላለጥ አይደለንም፤ ሐዋርያው፣ “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።” እንዲል (ሮሜ 12፥3)።

ኹላችን አካል በኾነው በክርስቶስ ላይ የተጋጠምን ብልቶች ከኾንን፣ ኹላችንም ሕያዋንና ሥራ ያለን ነን ማለት ነው።

“… እግር የእግርን ሥራ እንዲሁም እጅ የእጅን ሥራ እንደሚሠራ ኹሉ እያንዳንዳችንም የምንሠራው ሥራ አለን። ለሌሎች ሰዎች የተሰጠውን ሥራ ለመሥራት መመኘት ግን የለብንም። ለምሳሌ፦ እግር እንዲህ ይላል ብለን እስቲ እናስብ፣ “መርገጫ በመኾኔ ደስተኛ አይደለሁም። እኔ የምፈልገው እጅ መኾን ነው። እጅ ታላቅ ሥራ ያለው በመኾኑ እጅ ካልኾንኩ የዚህ አካል ክፍል አልኾንም።”  እንደዚህ ያልንበት ጊዜ የለም? አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ብለንስ አናውቅም፣ “የኮሚቴ አባል ካላሆንኩ አላገለግልም” ወይም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ “እኔ ታናሽ ሰው ነኝ፤ ትልቅ ስጦታ የለኝም፤ ያልንበት ጊዜ የለም? እንዲህ ያለ ዐሳብ ልናስብ አይገባም።”  

እንግዲህ የተለያየ ሥራ ያላቸው የሰውነታችን ክፍሎች ቢኖሩም፣ ኹሉም ለአካሉ ጤንነት እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ናቸው። አንድነት ውስጥ ልዩነት አለ፤ ልዩነቱ ውስጥ ፍጹምና ሊነጣጠል የማይችል አንድነት አለ፤ ታላቃችንና ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ የበላዩና ልቆ ሊታይ የሚገባው፤ ትኵረትም የሚያሻው ዋናው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ ሌላው ኹሉ ወደ ጎን ወንድምና እህት ብቻ ነው!

በተለያዩ ጉባኤያት ውስጥ፣ ብዙ ብልቶችን ገድለውና አጥፍተው በአንድም ይኹን በተዘዋዋሪ መንገድ፣ አንድ ብልት ያገነኑ ጥቂት አይደሉም። ክርስቶስ፣ “ኹለትም ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ. 18፥20) ያለውን ኅብረት ለማጽናትና ለመጠበቅ፣ መንፈሳዊ የመንፈስ ኅብረት እንጂ አንድን አገልጋይ ማግነን ወይም አንድ ዐይነትነት ጤናማ አይደለም።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

3 comments:

  1. አሜን አሜን አሜን ቃል ህይወትን ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ልክ ብለሃል ዲያቆን፣ እናመሰግናለን።

    ReplyDelete
  3. አቤኒ ጌታ ጸጋውን ያብዛልህ እንደ አካል ብልቶች ተሳስረን የፈሰሰልንን ጸጋ ለተሰጠን ተልዕኮ ስምረት እንድናውለው ይርዳን።

    ReplyDelete