በባለፈው ክፍል እንደ ተመለከትነው፣ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ አስተማሪዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን
ሥልጣንን ጨርሶ እንደማይቀበሉና እንደሚያቃልሉ አንስተናል፤ በዚሁ ዐሳብ ላይ ጥቂት እንጨምርና ወደሚቀጥለው እንሄዳለን።
የጽድቅ መንፈስ የኾነው መንፈስ ቅዱስ ወደ ጽድቅና ቅድስና የሚመራና ደግሞም እርሱ የቅዱስ ቃሉ
ባለቤትና ደራሲ ነው፤ ስለዚህም ቅዱስ ቃሉ የሕይወታችን፣ የአምልኮአችን፣ የአገልግሎታችን፣ የአስተምኅሮና የምልልሳችን ኹሉ ማዕከልና
ቃኚ ነው። ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት በትክክል ሳንረዳ ተሳስተን ብንወድቅ፣ እኛ እንጎዳለን እንጂ ቃሉ እውነተኛና የታመነ
ነው። “ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” እንዲል (2ጢሞ. 2፥13)።