Saturday, 20 September 2025

የትውልድ ነቀርሳ - የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ (ክፍል - ፩)

 Please read in PDF

ጥቅስ የጠቀሰ፤ መስቀል ያነገተ፤ ነጠላ ያመሳቀለ፤ አትሮንሱን ወይም ዓውደ ምሕረቱን ይዞ የሚሰብከው ኹሉ ሰባኪ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ስላለመኾኑ በዘመናችን አያሌ ምስክሮች አሉ።  ጥቅሶች የሚጠቀሱት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚገለጡት ለእግዚአብሔር ክብር፣ ክርስቶስን ለማላቅ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት፣ የሰውን ኀጢአተኝነት ገልጠው ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ለማቅረብ ... እንዳይደለ ከአደባባይ ያልተሠወረ ምስጢር እንደ ኾነ ሰነባብቶአል።



የስህተት መምህራን ጥቅስ መጥቀስ፤ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስም ጥቅስን ከዓውድ ነቅሎ ማቅረብ አልያ ያልተባለን እንደ ተባለ አድርጎ ማቅረብ የተካኑበት ሙያቸው ነው። ዛሬ ይህን የሚያደርጉትም ሁሉ፣  የሚያደርጉት አዲስ አገር አይደለም። “ድንጋይ ዳቦ እንዲኾን የጠየቀው” ሰይጣን አሳችነቱ ሲገለጥበት፣ ወዲያው ጥቅስ መጥቀስ እንደ ጀመረ አንዘነጋም። ግማሽ እውነት የብዙዎችን ቀልብ መሳቡና ማሳሳቱ አቅሙ ቀላል አይደለም።

ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን መግቦታዊ በረከትና ጸጋ፣ የኹሉ ነገር መፈጸሚያ መሣሪያ[ሎሌ] ማድረግ በዚህ ዘመን አስቂም፤ አሳዛኝም ነው። ሰጪውን ከሥጦታው ውስጥ የመፈለግ ርካሽነት በዚህ ዘመን መወደዱ “የትውልዳችንን” ቅጥ ያጣ አገበስባሽነትን ያሳየናል። እግዚአብሔር ብቻውን የሚመለክ፤ ሌላ ርሱን መሳይ “አቻ አማልክት” የሌሉት ልዑል ነው። ፍጥረት እግዚአብሔር አይደለም፤ እግዚአብሔርም የፍጥረት አካል አይደለም። በፈቃዱ ለፍጥረት የተገለጠ መጋቢ ቢኾንም፣ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ውስጥ የሚኖር ጥልቅና ምስጢር ነው።

እንግዲህ የትውልዳችን ነቀርሳ የኾነው የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ፣ ይህን መስመር በማጥፋት “እግዚአብሔርን ሁሉ ነው፣ ሁሉም አምላክ ነው፣ ሁሉም አንድ ነው።” በሚል ቅንብብ ውስጥ ሲዶል እንመለከታለን። በተጨማሪም ቅዱሳት መጻሕፍት፣ “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሐ.ሥ. 17፥26-27) የተባለውን ያህዌ ኤሎሂምን ክደው፣ አጽናፈ ዓለሙ የሚንቀሳቀሰው በካርማ ሕግ እና በ"reincarnation" ትምህርት ነው ብለው ያምናሉ።

ለቅዱሳት መጻሕፍት እንግዳና ባዳ የኾኑ ቃላትና ትምህርት ይዘው “ጥቅስ እየጠቀሱ የሐናን ለወለተ ሐና እያከናነቡ ክርስቲያን ነን” ሲሉም ይስተዋላሉ።

የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ግብ

1.   በአንድ ጽንፍ ሰው በውስጡ ወዳለ አምላክነት እንደሚያድግ ወይም አምላክነትና ኹሉን ቻይነት በውስጡ እንዳለ እንዲያስብና አምኖ እንዲቀበል ማድረግ። በሌላ ጽንፍ ደግሞ እውነትን አንጻራዊ በማድረግ እምነቶችን ኹሉ በአንድ ጎራ ማሰለፍና አንድ ወጥ ሃይማኖትን ማዘጋጀት ትልቁ ግቡና ትልሙ ነው።

2.   ይህም የሚኾነው በመንፈሳዊ የዝግመት ዕድገት ውስጥ የሚገኘውን ኃይል በሥጋ ውስጥ በመጠቀም ራስን “ብቁ” ማድረግ ነው፡፡ አዲስ አገሮች እንደዚህ አይነት እውቀትን ለማግኘት እንደ ኮከብ ቆጠራ፣ አስማት፣ የሥነ-አእምሮ ፈውስ፣ ከአካል ውጪ የሆኑ ልምምዶች፣ የተለያዩ ቤተ እምነቶችን መልካም እሴቶችን መጠቀምና እና ማሰላሰል ብሎም በቀጥታ መናፍስታዊ ድርጊቶች ውስጥ ይሳተፋሉ። ይህን አደራረግ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ቃል፣  

3.   በአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ማሰላሰል ውስጥ፣ አኹን ያለንበትን ኹኔታ መካድና አለመቀበል ተገቢ እንደ ኾነና ሰዎች ከውስጣቸው ያለውን ኃይል መጠቀም እንደሚገባቸው በጽኑ የሚያበረታታ ነው፡፡

4.   በመጨረሻም፣ አዲስ አገሮች በአለም አቀፍ ሰላም፣ ብልጽግና እና ፕላኔታዊ ለውጥ የሚታወቀው የመጪውን “የNew world Order” ራዕይ ይጋራሉ። የመጨረሻ ግባቸው እንደ ዓለም አቀፋዊ መንደር እና ፕላኔታዊ ንቃተ ኅሊና ባሉ በተያያዙ ሐረጎች ውስጥ ተካትቷል። ነገርየው ባለ ብዙ ገጽታ ያለው የማይዛመድ ደግሞም በቀላሉ የተገናኘ ግን ራሱን የቻለ ለዓለማውያንም፤ ለመንፈሳውያንም ምቹ ኾኖ የቀረበ የጥፋት ሰፊ መንገድ ነው።

መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፣

ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳ. 14፥12)፤ ክርስቶስን ከማያከብርና ከማያገንን፤ እግዚአብሔርን ከመፍራት ይልቅ ራስን ከሚያልቅ ትምህርት ተጠበቁ፤ ተጠንቀቁ!

ይቀጥላል …

3 comments:

  1. እግዚአብሔር ይመስገን🙏🙏🙏

    ReplyDelete
  2. የሚያንፅ መልዕክት ጌታ ይባርኮ!!

    ReplyDelete
  3. Thank you, Jesus, for everything. What a blessing article.

    ReplyDelete