Tuesday, 22 April 2025

“ነይ ነይ እምዬ ማርያም… ቤዛዊት ዓለም … ስህ-ተ-ት ነው” (አባ ገብርኤል)

Please read in PDF

ከሰሞኑ በጣም ያከራከረ አንድ ርዕሰ ጉዳይ አለ፤ ነገረ ቤዝወት። “ቤዝወት” ታላቅ ነገረ መለኮታዊ ዕሳቤን በውስጡ የያዘ አስደናቂ ቃል ነው። በብዙዎች አንደበት የሚጠቀስ ቃል ቢኾንም፣ ቃሉ በትክክል ስፍራውንና ትርጕሙን አጊኝቷል ብዬ ግን አላምንም። ጥቂት ስለ ቃሉ እናውጋ እስኪ!

ቤዛነት ምንድር ነው?

“ቤዛ” የሚለው ቃል፣ ከግዕዝ ቋንቋ የተወሰደ ሲኾን፣ ሰውን ከባርነት ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ ወይም አንድን  የተያዘን ወይም የተወሰደን ነገር ለማስመለስ የሚከፈል ዋጋን፣ ካሳን አመልካች ነው። ቤዛን የመክፈል ሥራ ደግሞ፣ ቤዛነት ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶአል። ቤዛነት፣ በበደለኛው ሰው የተወሰነውን ትክክለኛ ፍርድ ተመጣጣኙን ዋጋ ከፍሎ ነፃ ማውጣት ነው። ስለዚህም ቤዛ ማለት፣ “በቁሙ ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ፣ ምትክ፣ ዋቢ፣ ዋስ፣ መድን፣ ተያዥ … የመሰለው ኹሉ። [በደቂቅ አገባብ] ደግሞ፣ ስለ፣ ፈንታ፣ ምክንያት”[1] በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ያብራሩታል። ከዚህ በመነሣት፦

  1. በብሉይ ኪዳን ሰዎች እንሰሳትን ከመታረድ፣ በድኅነት ምክንያት የተሸጠውን ርስት መሬታቸውን ወይም ቤታቸውን ወይም በባርነት የተያዘባቸውን ሰው ለማስለቀቅ ተመጣጣኙን ዋጋ ይከፍሉና ይቤዡ ነበር፤ (ዘጸ. 13፥13፤ ዘሌ. 25፥24-34፤ ሩት 4፥4፤ ኤር. 32፥6)፣ ለዚህም በምሳሌነት፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽና ከባቢሎን መቤዠቱን ይናገራል፤ (2ሳሙ. 7፥23፤ ነህ. 1፥10)፣
  2. በአዲስ ኪዳን ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑበት ኹሉ፣ ቤዛና መድኀኒት ኾነላቸው፤ (ማር. 10፥45፤ ኤፌ. 1፥7፤ 1ጢሞ. 2፥5፤ ዕብ. 9፥12)፤ ይህንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነትን ከሙታን ትንሣኤ በኋላ አረጋገጠው፤ (ሮሜ 8፥23፤ ኤፌ. 4፥30)።[2]

ጌታችን ኢየሱስ ለምን ቤዛ ኾነን?

1.   ሰው በደለኛ ስለ ኾነ፦ ሰው በደለኛና ኀጢአተኛ ስለ ኾነ፣ ለራሱ ቤዛ መኾን አይችልም። ቤዛ ለመኾን ከሚቤዥበት ነገር፣ ተቤዢው ነጻ መኾን መቻል አለበት። ከዚህ አንጻር በደል አልባ የኾነ ሰው፤ ለሰው እጅግ ያስፈልግ ነበር፤ ምክንያቱም ኹሉም የአዳም ዘር፣ ከኀጢአትና ከበደል በታች ተከስሶ ተዘግቶበት ነበር፤ (ሮሜ 3፥9)። ስለዚህም ክርስቶስ ኢየሱስ፣ “ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” (ቈላ. 1፥13-14)።

2.   በኀጢአት ምክንያት የሕግ እርግማን ያገኘንን፣ እርሱ የሞትን መውጊያ ሰብሮ፣ የሲዖልን ኃይል ድል ነሥቶ ተቤዠን፤ ዋጀን፤ ዐርነትን ሰጠን። የሕጉንም እርግማን ከእኛ ላይ አስወገደው፤ (1ቆሮ. 15፥56፤ ገላ. 3፥10)። ስለዚህም ከእርሱ ተነሣ ቅዱሳንና አለነውር ኾንን።

ክርስቶስ አንዳች በደል ስለሌለበት ስለ በደላችን ብቸኛ ቤዛ ኾነልን። ራሱም ሲናገር፣ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ” እንደ መጣ ተናገረ፤ (ማቴ. 20፥28፤ ማር. 10፥45)፤ እኛም በክርስቶስ በኩል በኾነው ቤዛነት፣ የበደላችንን ስርየት አገኘን፤ ከሕግ እርግማንም ዋጀን፤ (ሮሜ 3፥24፤ ኤፌ. 1፥7፤ ገላ. 3፥13)።

3.   ከዚህም የተነሳ ለዋጀን ጌታ ብቻ እንኖርለታለን፤ ቤዛና ዋጆ በዐሳብ ደረጃ ተዛማጅ ትርጉም አላቸው፤ በቤዛነት ክርስቶስ የራሱ ገንዘቦች እንዳደረገን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመሰክራል፤ “በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።”፣ “በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ።” (1ቆሮ. 6፥16፤ 7፥23)።

የዳንነውና ክርስቲያን የተባልነው ወይም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን የተጠራነው፣ ክርስቶስ ያለ አንዳች በደልና ነውር ቤዛ ኾኖ በደሙ፣ የኀጢአታችንን ዕዳ ኹሉ ስለ ከፈለልን ነው። በዋጋ የገዛን እርሱ ነውና የእርሱ ብቻ ነን! ወደፊት የምንኖረውና የምንኖርለት በክርስቶስ ለክርስቶስ ብቻ ነው። ዐርነት የወጣንበት እውነት (ዮሐ. 8፥32)፣ ጸድቀን ጻድቃን የተባልንበት ጽድቃችን ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ (1ቆሮ. 1፥30-31)።

ቤዛነትን ፍጹም በኾነ መንገድ፣ አንድን ነገር የራስ ገንዘብ ማድረግ ነው። ልክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ፣ ገዝቶ፣ ተቤዥቶ የራሱ ገንዘቦችና ውድ ዕቃዎቹ እንዳደረገን እንዲህ ነው። የፈጠረንና፣ “ሁሉን በሥልጣኑ ቃል የደገፈው ክርስቶስ ኢየሱስ፥ ኃጢአታችንን ደግሞ በራሱ አንጽቶአልና” (ዕብ. 1፥3)። 

ቤዛነት፣ አምላክነትን ብቻ ያይደለ፣ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መኾንን ይሻል። በፍጹም አምላክነቱ ዓለማትን የደገፈው ያው ጌታ፣ ከቅድስት ድንግል ተወልዶ በፍጹም ሰውነቱ አድኖናል፤ ለኀጢአታችን በደሙ ስርየት ኾኖአል፤ “መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን አድርጎአልና፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (ራእ. 1፥6)።

ቅድስት ማርያም፣ ኀጢአትን በተመለከተ ለሰው ልጆች ኹሉ ቤዛ መባል ወይም መኾን አትችልም፤ ምክንያቱም ቅድስት ማርያም ቤዛዋን ወለደች እንጂ፣ በራስዋ ቤዛ ለመኾን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት ያሻታል። ቅድስት ማርያም እንዲህ ናት የሚሉ፣ ቅድስት ማርያም ለነርሱ አራተኛ “ሥላሴ” ናት ማለት ነው። ነገር ግን ለኀጢአታችን ቤዛችን ናት ማለትም፤ “እርሷ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ናት” የማለት ያህል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ የተገለጠ ኑ-ፋ-ቄ ነው። 

ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ ቆሞ፣ ቤዛነት ከስቅለት ጋር አይገናኝም የሚሉም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በቀጥታ ከስቅለቱና ከደሙ ጋር በማያያዝ እንዲህ ይላል፦ “በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን” (ኤፌ. 1፥7) ይላል። ዘበነ ሆይ! “በደሙ የተደረገ ቤዛነት” የተባለው የመስቀሉ ሥራ አይደለምን?!

ቤዛነት፣ ክርስቶስ በሰውነቱ ወይም በሥጋ ሞቱ የከፈለልን ፍጹም የመስቀሉ ሥራ ነው፤ ይህም ብቃት ያለውና አንዳች ተጨማሪ ነገር የማያሻው ነው፤ የትኛውም ኀጢአተኛ ይህን በማመን ይድናል። ይህ መንገድ ኹለተኛ ሌላ አማራጭ የለውም፤ የዳንበትና የምንድንበት የቤዛነት ሥራ አንድና አንድ ብቻ ነው። ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ እንዲህ ብለዋል፤ 

“አዳም መለኮታዊ ሕግን በመተላለፉ፣ በደል በመፈጸሙ የሞት ቅጣት ተፈርዶበታል፤ አዳም ከዚህ ዘላለማዊ ቅጣት ለመዳን የሚችለው በፍርድ መንገድ እንጂ በሌላ ሁኔታ መዳን አይችልም። ቅጣቱ በፍርድ እንደ ሆነ መዳኑም በፍርድ ይፈጸማል። ስለዚህ ነው ጌታ ሥጋ ለብሶ ማለት ሰው ሆኖ የአዳምን የሞት ፍርድ በራሱ ሰውነት ተቀብሎ ያዳነው፤ “ወአድኃነነ በፍትሕ ጽድቅ ወርትዕ” ተብሎ እንደ ተጻፈው መዳናችን በፍርድ እንደሆነ እናስተውል (መቅድመ ወንጌል)። ፍርድም የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው። እንግዲህ በመስቀል የመዳናችን ነገር አማራጭ የሌለው በእግዚአብሔር የተመረጠ ብቸኛ የጽድቅና የፍትሕ የርትዕ መንገድ እንደሆነ እናምናለን።

ከመስቀል ሌላ የመዳን አማራጭ አለ ብሎ ማሰብ ከእውነትና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ መሆንን ያመለክታል። መስቀል አያስፈልገንም ከነ ኃጢአታችን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንችላለን ማለት ዘበት ነው፤ ሐሰት ነው፤ ከእግዚአብሔር ተለይቶ መቅረት ካልሆነ በስተቀር የእግዚአብሔር የቅድስና መለኮታዊ ባህርዩ የሚያቃጥል እሳት ስለሆነ በክርስቶስ መስቀል በኩል ካልሆነ ማንም ሊድንና ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ አይችልም። … ደም ካልፈሰሰ የኀጢአት ሥርየት የለም (ዕብ. 9፥22)። የኀጢአት ሥርየት ከሌለ ሰው ከእግዚአብሔር አይታረቅም።[3]

ማጠቃለያ

ከላይ በርዕስነት የመረጥኹትን “መዝሙር”፣ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለኹ፣ “ከዘመሩ፣ ካስዘመሩ” መካከል እኔ ፊተኛው ነኝ። ባለማወቅ ለብዙዎች የመሳሳት ምክንያት ኾኜ ነበር፤ ዛሬ ላይ በአደባባይ ይህ “ዝማሬ” ስህተት እንደ ኾነ ከሚናገሩት መካከል አንዱ ነኝ። ከላይ ባስቀመጥነው ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መዝነን የቤዛነት ትምህርት በትክክል ከተረዳን፣ “የማርያም ቤዛ አለመኾን” አይደንቀንም!

እናም ቤዛነት በክርስቶስ ብቻ የተከናወነ፣ የሰው ልጆች ኹሉ የዳኑበት ታላቅ፣ ዘላለማዊና ሕያው ሥራ ነው። ኀጢአተኞች ኹሉ በዚህ ጽድቅና ቤዛነት በመታመን ቢመጡ፣ “ከአባቶቻቸው ከወረሱት ከከንቱ ኑሮአቸው” (1ጴጥ. 1፥18-19)፣ ከኀጢአት ባርነት (ዮሐ. 8፥34)፣ ከጨለማ ሥልጣን (ቈላ. 1፥13)፣ ከሞት ፍርሃት (ዕብ. 2፥14) ነጻ በመውጣት ይድናሉ፤ ቤዛነቱ ለመላለሙ፤ መዳኑ ደግሞ ለሚያምኑበት ነውና። እንዲህ ያዳነን ጌታ ይባረክ፤ አሜን።

አባ ገብርኤል ምንም እንኳ አቀራረባቸውን በጥቂቱ ባልደግፈውም፤ በትምህርታቸው ግን ሙሉ ለሙሉ የምስማማ ነኝና፣ ትጋቱን ይጨምርልዎ ማለትን እወዳለሁ!

 “ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።


የቴሌግራም አድራሻ - https://t.me/ebenezertek

የጡመራ መድረክ አድራሻ - https://abenezerteklu.blogspot.com/2020/05/blog-post_24.html

 



[1] ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ ገጽ 266

[2] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 116

[3] ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ገጽ 116


No comments:

Post a Comment