የክርስቶስ የመስቀል ሥራ በመላለሙ የናኘውና ሰዎች ኹሉ ወደ መስቀሉ ሥራ ፊታቸውን ዘወር ያደረጉት፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። አብ ለእኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠልን ወልድ በመስቀል ላይ ባሳየው ፍጹም መታዘዝ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህን እውነት ለሰው ልጆች ኹሉ በማቅረብ የታመነ ነው። ስለዚህም ክርስቶስን ያለ መንፈስ ቅዱስ፤ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ ያለ ክርስቶስ ልንረዳ አንችልም። ከዚህም የተነሳ ያለመንፈስ ቅዱስ ኀይል መስቀሉንና ሥራውን ልንሰብከው፤ ልናውጀው፤ ብሎም ሰዎች አምነው እንዲድኑ ማድረግ አይቻለንም።
ለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ
የኹለንተናዊ ነገራችን ማዕከል የሚኾነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስንና የጸጋ ስጦታዎቹ መራብና መጠማት፣ መፈለግና ከቶውንም
መናቅ እንደሌለብን ሲናገር እንዲህ ይለናል፤
· ተጠሙ፦ “ኢየሱስም... ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ።
በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው
ስለ መንፈስ[መንፈስ ቅዱስ] ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና።” (ዮሐ. 7፥37-39)።
የክርስቶስ የቤዝወት ሥራ
ሲፈጸም መንፈስ ቅዱስ ይህን የቤዝወት ሥራ ለመላለሙ ሊያድል፣ ለሰው ልጆች ኹሉ ተሰጥቶአል። ፍጥረት ሲፈጠር ፍጥረትን በውበትና
በድንቅ የሠራው መንፈስ ቅዱስ፣ አኹን ደግሞ የመስቀሉን ሥራ በመናኘት ለሰው ልጆች ኹሉ አጽናኝና ብርሃን ይኾናል። ስለዚህም አብዝተን
እንጠማዋለን፤ ይህንም ጥማት የሚሰጠን ራሱ ነውና ክብር ይኹንለት!
· ፈልጉ፦ “ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።
...” (1ቆሮ. 12፥31)፤ በሌላ ስፍራም፣ “ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ።
... ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት
ይሁን።” (1ቆሮ. 14፥1፤ 39-40)፣
በቆሮንቶስ መልእክት ውስጥ ከጸጋ ስጦታዎች ጋር በተያያዘ “ፈልጉ”
የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሶአል። ምክንያቱም ኹሉም የሰውነታችን ክፍሎች ጤናማ በኾነ መንገድ ካልተከበሩና ሥራቸውን ካልሠሩ፣
በሰውነታችን ላይ ችግር እንደሚከሰተው እንዲኹ፣ ስጦታዎቹም በንቃት አስተዋጽኦ ካላደረጉ በቀር ውጤታማነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
ስጦታዎቹ ከእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ የምሰጥባቸው፣ መንግሥቱን
የምናሰፋባቸው፣ ርስ በርሳችን መዋደድን የምንገልጽባቸው፣ ኅብረትን የምናጸናባቸው፣ የሰይጣንን መንግሥት የምናፈርስባቸው መንገዶችና
መሣሪያዎች ብቻ ናቸው። የመስቀሉ ሥራ በፍጥነት ምድርን ማካለል የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በስጦታዎቹ እንጂ በእኛ “ችሎታ”
ጨርሶ አይደለም።
· አትናቁ፦ “የመንፈስ ቅዱስን ሥራ አታዳፍኑ፤ የትንቢትን ስጦታ አትናቁ፤
ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ።” (1ተሰ. 5፥20-21 ዐዲሱ ትርጒም) እንዲል፣ ዛሬ ላይ የሚነገርን ትንቢት፣ ቀጥታ
እንደ ብሉይ ኪዳን ትንቢት “ተካካይ አድርገን ባቀበልም”፣ መንፈስ ቅዱስ ግን በትንቢት ለቤተ ክርስቲያን እንደሚናገርና በሕዝቡ
በኩል እንደሚናገር እናስተውላለን፤ እናም ድምፁን መቀበልን እንማራለን። ይህንም የምናደርገው ሁል ጊዜ ትንቢቶችን እየፈተሽን እንጂ
ለመፈተንና እንደ ትእዛዝ ትንቢትን በመናቅ አይደለም።
አንዳንድ ግለሰቦች ስጦታውን
አላግባብ እየተጠቀሙበት ስለ ነበር ትንቢት የተናቀ ሊመስለን ይችላል። ልክ በተሰሎንቄ ሰዎች መካከል ሥራ ፈት ሰዎች እንደ ነበሩና
(1ተሰ. 4፥11-12) ሥራ ፈትነታቸውንና የፍጻሜ ዘመን ትንቢታዊ ግምታቸውን (2ተሰ. 2፥1-5) በትንቢት ለመሸፈን እንደ ሞከሩት።
ይህን ማድረግ የጸጋ ስጦታዎቹ እንዳይሠሩ ማዳፈንና መከልከል ነው።
ደግሞም በሌሎች ዘንድ
ያለን ስህተትና ትክክል አለመኾን ተመልክተን፣ ከጸጋዎቹ ራሳችንን እንዳንከለክልና “ስጦታዎቹ ደርቀዋል፤ ቀርተዋል፤ የሉም፤ ተቋርጠዋል፤
ተሽረዋል” ወደሚል የስንፍና መደምደሚያ እንዳንደርስ፣ ቅዱስ ቃሉ “ተጠሙ፣ ፈልጉ፣ አትናቁ” ይለናል፤ ደግሞም ይህ የምክር ቃል
በአብሮነት አለ፤
“ ... እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ
ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ።” (1ቆሮ. 14፥12)።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ
ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:
Post a Comment