የክርስቶስ የመስቀል ሥራ በመላለሙ የናኘውና ሰዎች ኹሉ ወደ መስቀሉ ሥራ ፊታቸውን ዘወር ያደረጉት፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። አብ ለእኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠልን ወልድ በመስቀል ላይ ባሳየው ፍጹም መታዘዝ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ይህን እውነት ለሰው ልጆች ኹሉ በማቅረብ የታመነ ነው። ስለዚህም ክርስቶስን ያለ መንፈስ ቅዱስ፤ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ ያለ ክርስቶስ ልንረዳ አንችልም። ከዚህም የተነሳ ያለመንፈስ ቅዱስ ኀይል መስቀሉንና ሥራውን ልንሰብከው፤ ልናውጀው፤ ብሎም ሰዎች አምነው እንዲድኑ ማድረግ አይቻለንም።




