Saturday 31 August 2024

“ኑ ወደ ኦርቶዶክስ ተመለሱ!” ለምትሉን!

 Please read in PDF

ኦርቶዶክሳዊው ተሐድሶ እያየለና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ ሲመጣ፣ በቃላት በማባበል፣ በጥቅምና በክብር በማማለል፣ መልሰን አናወግዛችሁም በሚል የተስፋ ቃል በመስጠት … እየቀረበልን ያለው ጥያቄ፣ “ኑ! ወደ ኦርቶዶክስ ተመለሱ!” ሚል ነው። ከዚህ በታች የምናስቀምጣቸው ጠንካራ ምክንያቶች የመመለስና ያለ መመለስን ጥያቄ ትርጕም ይሰጡታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ኋላ ስለ መመለስ በማስጠንቀቂያ አዘል ከተጻፉ መልእክቶች አንዱ፣ የዕብራውያን መልእክት ነው። የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናጠና እንደምናስተውለው፣ አስቀድሞ ክርስትናን ለተቀበሉ አይሁድ የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ዓመታት እጅግ አስቸጋሪዎች ነበሩ። በእነዚህ ጊዜያት ክርስትና በአጭሩ የአይሁድ ሃይማኖት ኾኖ ነበር። ከ120ው የጌታ ቤተ ሰቦች (ሐ.ሥ. 1፥15) ጀምሮ ኹሉም በአንድነት ያመልኩና ያገለግሉ የነበረውም በአይሁድ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበርና፤ (ሐ.ሥ. 2፥46፤ 3፥1፤ 5፥42)።

Sunday 18 August 2024

የ“ታቦር” ስብከቴን ቀይሬአለኹ!

 Please read in PDF

ጌታችን ኢየሱስ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት፤ ማንነቱን ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየበት የክብሩ ተራራ እውነት እጅግ አስደናቂ ነው። ጌታ፣ በፊልጶስ ቂሣርያ፣ “ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና፦ ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ኾንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።” (ሉቃ. 9፥18) ደቀ መዛሙርቱ ሲመልሱ፣ የነቢያትን ስም በመጥራት እንዲኹም ከነቢያት አንዱ ነህ ይላሉ ብለው መለሱ። ቀጥሎም፣ “እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።” (ሉቃ. 9፥20) “ጴጥሮስም መልሶ፦ ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ።”ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ታላቅ እውነት በመመለሱ፣ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” (ማቴ. 16፥17) በማለት የጴጥሮስን ዕድለኝነት ጌታችን መሠከረለት።