Monday, 25 May 2026

በሥጋው ያረገ ጌታ!

 Please read in PDF

ክርስቶስ ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል በነሣው ሥጋና ከሙታን መካከል ሲነሣ በለበሰው ፍጹም ሰውነቱ ወደ ሰማያት አርጓል። ምክንያቱም የመጣበት ዋነኛ ዓላማ፣ “የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነውና” (ሉቃ. 19፥10)። ደግሞም ሰውን ለማዳን ክርስቶስ እንከን አልባ ሰው መኾን ያስፈልገው ነበር። ከዚህም የተነሣ ሊያድነን በፍጹም ሰውነቱ የተሰቀለው ያው መሲሕ፣ በሰማያት መግቢያ በር ይኾነን ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ።

ርሱ የለበሰውን የሰውን ሥጋ ይዞ፣ ወደ ሰማያት በማረጉና ወደ ሰማያት በክብር በመግባቱ፣ ለአዳም ዘር ኹሉ የሰማይ ደጅ ወለል ብሎ መከፈቱን አበሠረልን። ሰው በቀደመው አዳም ምክንያት ከሰማያት ተሰደደ፣ በኹለተኛው አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ ግን ወደ ገነት ተመለሰ፤ ርሱ ፍጹም በደል አልተገኘበትምና፤ የዕብራውያን ጸሐፊ፣ “... እንግዲህ ሰማያትን ዘልቆ ወደ ላይ ወደ ሰማይ የወጣ ታላቅ የካህናት አለቃ ስላለን እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ፤ የካህናት አለቃውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው።” (ዕብ. 4፥14 ዐት) ሲል፣ በዕርገቱ ወደ ሰማያት የገባው ጌታ፣ የእምነታችን ርቱዕ መሠረት መኾኑን አጽንቶ ይመሠክርልናል።

ዕርገቱ የእምነታችን መሠረት ነው ስንል፣ የእኛ ጉዳይ የዘላለም ጉዳይ ኾኖአል እያልን ነው፤ ምክንያቱም በሥጋው እንደ ቅድስና መንፈስ የተነሣው ያው ጌታ (ሮሜ 1፥4) ደግሞ በፍጹም ሰውነቱ ወደ ሰማያት በማረግ፣ መቃብርና ሙስና ይዞ የሚያስቀር የነበረው ማንነታችንን አኹን ወደ ሰማያት ከፍ አድርጎ በአብ ቀኝ እንቀመጥ ዘንድ ወድዶአልና። መድኃኒታችንን ክብር ይግባው፤ አሜን።

የመጀመሪያዪቱ ቤተክርስቲያን ለዚህ ነው በጥንት ዝማሬዋ እንዲህ በማለት የዘመረችው፣

“የሃይማኖታችን ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር፦

“ሰው ሆኖ ተገለጠ፤

እውነተኛነቱ በመንፈስ ታወቀ፥

ለመላእክት ታየ፥

ለሕዝቦች ሁሉ ተሰበከ፥

በዓለም ያሉ ሰዎች አመኑበት፥

በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ” የሚል ነው።” (1ጢሞ. 3፥16 ዐት)።

እንዲህ እናምናለን፤ እንታመናለን፤ አሜን።

1 comment:

  1. ቃለህዎትያሰማልን❤❤❤❤❤❤

    ReplyDelete