Please read in PDf
የእንሰሳቱ ደም
የእንሰሳቱ ደም
“የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና፤”(ዕብ.10፥4)
አለም ገና በኃጢአት ተይዛ ሳለ፥ ጌታ እግዚአብሔር ዋናው አካል እስኪገለጥ ምሳሌውን በማገልገል ጊዜያዊ ድኅነት(የማሥተሰርያ ሥርዐት) እንዲሰጡ ሌዋውያን አገልጋዮችን አስነሳ፡፡ ብሉይ ኪዳን በጊዜው ይሠራ ለነበረ ኃጢአት የማሥተሰርያ ሥርዐት አድርጎ ያቆመው፥ የእንሰሳትንና የአዕዋፋትን ደም ነው፡፡ በመሠዊያው ላይ የሚፈሰው የመሥዋዕቱ ደም “የተቀደሰ” ደም ነው፤ (ዘሌዋ.17፥10-14 ፤ ዘዳ.12፥23)፡፡ ምንም እንኳ በመሠዊያው ላይ የሚፈሰው የመሥዋዕቱ ደም “የተቀደሰ” ቢሆንም፥ በእግዚአብሔር አምሳልና መልክ ለተፈጠረው የሰው ልጅ ፍጽምናና ብቃት ያለው መድኃኒት አልነበረም፡፡
ዳሩ ግን ያ አገልግሎት በምሳሌነት ሲገለገል ብርቱ ጥንቃቄ ነበረው፡፡ ሕይወት የተቀደሰና ክቡር በመሆኑ፥ የሕይወት ቤዛ ምሳሌ የሆነውን ደም በክብር መያዝ እንጂ፥ መግደልና መብላት ፈጽሞ የተከለከለ ሆነ፤ (ዘፍ.9፥5 ፤ ዘኊ.35፥33 ፤ 1ሳሙ.14፥32)፡፡ እግዚአብሔር በአሮጌው የመታረቂያ መንገድ፥ አንድን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለት በእርሱ ፈንታ የሞተውንና የሚፈሰውን የእንሰሳውን ደም ያያል፡፡ ኃጢአተኛው ስለፈጸመው ኃጢአት የመስዋዕት ደም ሲፈስ በእርሱ ፈንታ ሌላ እንደሞተ፤ ኃጢአቱም በደሙ እንደተሠረየ ያመለክታል፤ (ዘሌ.5፥17-19) ኃጢአተኛው የሚያቀርበው እንሰሳ ንጹህና እንከን የሌለበትን ነው፤ (ዘሌ.1፥11)በተለይ ጠቦትና ገና የሚያሳሳ ዕድሜ ላይ ያለው እንሰሳ ለመሥዋዕትነት ይቀርባል፡፡
ከተፈጸሙት ልዩ ልዩ የደም የማሥተሰርያ ሥርዓቶች ከሐዲሱ ኪዳን ጋር መዛመድ የሚቻላቸውን ሁለት ምሳሌዎችን ብናነሳ፦
1. የፋሲካው በግ፦ የመከራው ቀንበር ሊያከትም፣ ሞት በብርቱው ጌታ ሊዋጥ፣ የግብጽ ጎበዛዝት ወድቀው የእስራኤል የበኩር ልጆች ለእግዚአብሔር ሊለዩ፣ የሞት ግርማው እየተሰማ ላያስፈራ፣ የጸናች እጁ የተዘረጋች ክንዱ በተዐምራት ልትገለጥ … የእስራኤል ልጆች በፍጻሜዋ ሰዓት አንድ ነገር ታዘዙ፡፡ “… ነውር የሌለበት የአንድ ዓመትን ጠቦት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ፤”(ዘጸ.12፥5)፡፡ ነውር የሌለበትን መሥዋዕት በማቅረብ ፋሲካን እንዲያከብሩ፡፡
ይህ የፋሲካ በግ ከጌታ ኢየሱስ መሥዋዕትነት ጋር ምሳሌያዊ ፍጹም ተዛምዶ አለው፡፡ እንዲያቀርቡት የታዘዙት መሥዋዕት ነውር የሌለበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ነውና፥ ንጹህ አምልኮን ይሻል፡፡ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው የሐዲሱ ኪዳን በግ ኢየሱስም “ነውርና እድፍ የሌለበት ንጹህ የመሥዋዕት በግ” ነው፤ (1ጴጥ.1÷19)፡፡ የቀረበውም “ነውር የሌለበት ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር አቅርቦ” ነው፤ (ዕብ.9÷14)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፥ “ኃጢአት የሌለበት እርሱ ንጹህ መሥዋዕት ራሱን አቀረበ፡፡” ብሎ በድርሳኑ ገልጾታል፡፡ (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ የኢትዮጲያ ሊቃውንት እንደጻፉትና እንደተረጎሙት ፤1987 ዓ.ም ፤ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፤ 15ኛ ድርሳን ቁጥር.120፤ ገጽ.290፡፡) በእርግጥም ክርስቶስ ኢየሱስ ነውር የሌለበት ንጹህ መሥዋዕታችን ነው፡፡ እኛም ከነውርና ከእድፈት ርኩሰት በመለየት ለእርሱ ለመሥዋዕት እንደሚቀርብ በግ በኑሮአችንና በህይወታችን ንጹሐን እንሆን ዘንድ ተጠርተናል፤ (ሮሜ.12፥1-3 ፤ 1ጴጥ.1፥15-16)
የፋሲካውን በግ በማረድና ደሙን በደጃፋቸው በመርጨት የእስራኤል ልጆች ከእግዚአብሔር ቁጣ ዳኑ፡፡ ደሙ የተቀባው ወይም የተረጨው በመቃንና በጉበኑ በውጪ በኩል ስለሆነ ለእነርሱ አይታይም፤ ለእግዚአብሔር ግን ይታያል፡፡ የእግዚአብሔርም ቁጣ እነርሱን ሳይሆን ደሙን አይቶ ያልፋል፡፡“ፋሲካችን” የሆነው (1ቆሮ.5፥7)የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በመታረዱና ደሙን በማፍሰሱ ራሱን ለእኛ ኃጢአት መስዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ (ዕብ.7÷27)
በጉ ገና መኖር በሚያጓጓበት በጠቦትነት ዘመኑ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ እንደቀረበ ጌታም እጅግ በሚያጓጓው በሠላሳ ዓመት ዕድሜው ለዓለም ሁሉ የሚበቃ መሥዋዕት ሆነ፡፡ ለእኛም የሚያጓጓው ጉብዝናችን ለትልቁ ጌታ እንዲሆን ውብና ድንቅ ምሳሌነት አለው፤ (መክ.12÷1)፡፡
ጌታ ኢየሱስ በእርሱ እውነተኛ ፋሲካነት ይህንን የአሮጌውን ፋሲካ ሊተካ በአይሁድ የፋሲካ ሳምንት ተሰቀለ(ታረደ)፤ (ሉቃ.22፥14 ፤ ዮሐ.18፥38)፡፡
2. የማሥተስረያ ቀን፦ እስራኤል እንዲያከብሩት ከተሰጣቸው ታላላቅ በዓላት መካከል አንዱ ነው፤ (ዘሌ.16÷23)፡፡ በዚህ ዕለት የሚፈጸሙ ድርጊቶች “ፍጹም” መንፈሳውያን ናቸው፡፡ በዓሉ በአመት አንዴ የሚደረግ ሲሆን ሁሉም ኃጢአታቸውን የሚናዘዙበት ዕለትም ነው፡፡ ከጌታ ጋር የሚዛመዱ ጥቂት የበዓሉን ድርጊቶች ብንመለከት፦
የበዓሉ ዋና አላማ ስለኃጢአት መልስን መስጠት ነው፡፡ ሕዝቡ ሁሉ ኃጢአታቸውን ቢናዘዙም ስለእነርሱ ግን ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ማንም ወደማይገባባት ወደሁለተኛይቱ ድንኳን ደምን ይዞ ይገባል፡፡ ሊቀ ካህናቱ ቀድሞ ስለራሱ ኋላም ስለሕዝቡ ደሙን ይዞ ወደቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባና ሁለቱ ኪሩብ ክንፎቻቸውን አጋጥመው ወደታች ወደሚመለከቱት የሥርየት መክደኛ ላይና በፊቱም በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፡፡ ቀጥሎም ከመቅደሱ ወጥቶ ከሁለቱ አውራ ፍየሎች አንዱን በማረድ ደሙን ይዞ በመግባት እንዲሁ ይረጨዋል፡፡ ያለደም የሚገባ ያለደምም የገባ የለም፡፡ የሊቀ ካህኑ ሥራ የጌታ ኢየሱስን የቤዛነትንና የማስታረቅ ሥራን በምሳሌነት የሚገልጥ ነው፡፡ እንዲሁም፦
- ሊቀ ካህኑ ህዝቡን ወክሎ ወደቅድስተ ቅዱሳኑ እንደገባ፤ ጌታ ኢየሱስም ሁላችንን ወክሎ በእጅ ወዳልተሰራችው መቅደስ ገባ፤ (ዕብ.9፥11)፤
- ሊቀ ካህኑ የእንሰሳትን ደም ይዞ በየዓመቱ ይገባ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ግን የገዛ ንጹህ ደሙን ይዞ ወደቅድስት ገባ፤ (ዕብ.9፥12)፤
- ሊቀ ካህኑ በየዓመቱ፤ ካህኑ ደግሞ በየዕለቱ ተመላልሰው ይገቡ ነበር፤ ክርስቶስ ግን የዘላለም ቤዛነት አጊኝቶ አንድ ጊዜ ገባ፤ (ዕብ.9፥12)በእርሱ ዘንድ መደጋገም የለም፡፡
- ሊቀ ካህኑ የዚህ ዓለም በሆነው መቅደስና ለዚህ ፍጥረት በሆነችው ድንኳን አገለገለ፤ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ግን በምትበልጠውና በምትሻለው ድንኳን በሰማይ ያገለግላል፤ (ዕብ.9፥1-24)
- ሊቀ ካህኑ ቀድሞ ለራሱ ኋላም ለሕዝቡ መሥዋዕትን ያቀርባል፥ ምክንያቱም እርሱም ደካማና ኃጢአተኛ ነውና፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና፤”(ዕብ.7፥26-28)ስለዚህም ድካምና ጉድለት የለበትም፡፡ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህን በእውነት ይገባናል!!!
ሁለቱ ኪሩብ ክንፎቻቸው እንደተጋጠመ ዓይኖቻቸውን በሥርየት መክደኛው ላይ በፈሰሰው ደም ላይ እንዲመለከቱ ተደርገው ይሳላሉ፣ ጌታ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ሲምር ወደሥርየት መክደኛው ደም ተመልክቶ ነው፡፡ ስለእነርሱ ያልፈሰሰውን ደም ትኩር ብለው የሚያዩና “ታርደሃልና” ብለው ድንቁን ምስጋና የሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላዕክት እንዴት ይደንቃሉ?! (ራዕ.5፥9)
ታላቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅም በድርሳኑ እንዲህ አለ፦
“የቀደመው ሊቀ ካህናት አስቀድሞ የራሱን ኃጢአት ለማስተሥረይ ከዚህም በኋላ የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሥረይ ዕለት ዕለት ይሠዋ እንደነበረ ዕለት ዕለት የሚሠዋ አይደለም … የቀደመው ላም በግ ነው የዛሬው ራሱ ነውና … የቀደመው ጧት ማታ ነው የዛሬው ግን አንድ ጊዜ ነውና …የሊቀ ካህናቱን መብለጥ መለየት ጻድቅ ንጹሕ የቀደመውን ስሑት ማለት ነውና…የቀደመው ዕሩቅ ብእሲ የዛሬው የባህርይ አምላክ ነውና …የቀደመው በደመ በግዕ ነው፤ የዛሬው በደመ ርእሱ ነውና” በማለት በድንቅ አስቀምጦታል፤ (13ኛ ድርሳን ቁጥር 178-183፡፡ገጽ.262)፡፡
ታላቁን የእስራኤልን የማስተሥረያ ቀን ሳስብ ብሔራዊ ንስሐ ትዝ ይለኛል፡፡ ምድር ሁሉ ወጥቶ ኃጢአቱን የሚናዘዝበት ልዩ የልቅሶና የመጽናናት ቀን፡፡ ወገን ሁሉ የቂም ማቁን የሚቀድበት ቀን፡፡ የፍቅር ሸማ የሚለብስበት፡፡ መች ነው ሐገሬ ከዘረኝነት፣ ከዝሙት፣ ከዘፋኝነት፣ ከጥንቆላ፣ ከምቀኝነት … ደዌዋ ለመፈወስ ብሔራዊ ንስሐ እንደየማስተሥረያ ቀን የምታውጀው? መች ነው የዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ምክንያትና አልሸነፍ ባይነትን በንስሐ ስለት ለመቁረጥ፤ ስለክርስቶስና ስለቤተ ክርስቲያን ሲሉ ተሸንፈው እንደባዕድና ባላንጣ መተያየቱን ሊተው፣ ሁለቱ ሲኖዶሶቻችን የዕርቅ ብሔራዊ የንስሐ አዋጅ ነጋሪት ድምጽ የሚያሰሙን? መቼ ይሆን?? መቼ…መቼ… ነው? ንስሐ ግቡ ባዮቹ ንስሐ የምንገባው? ጌታ ይዘበትበት ይሆን?
አቤቱ ሕዝብህን አድን፡፡ የገዛ ወገናችንን ልናስቀና ከጠላት ተወዳጅተናልና አቤቱ መልሰን እኛም እንመለሳለን፡፡
አሜን፡፡
ይቀጥላል….
Digg it deeper finally you knows.God
ReplyDeletebless you bro.
Ebbifami
ReplyDeleteGeta yibarkih
ReplyDelete