Saturday, 27 April 2019

የኢየሱስ የቀብር ሥነ ሥርዓት (ዮሐ. 19፥38-42)

Please read in PDF
 ኢየሱስን በዚያ አኖሩት (ዮሐ. 19፥42)
   ወንጌላዊው ዮሐንስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ኹሉን አዋቂና ተቈጣጣሪ አድርጐ ያቀርበዋል፤ (ዮሐ. 2፥25፤ ኢየሱስ እንደሚሞት ያውቃል (ዮሐ. 12፥23፤ 13፥1)፣ እንዴት እንደሚሞት ያውቃል ( 12፥33)፣ መች እንደሚሞት ያውቃል (ዮሐ. 17፥1)፣ መከራውን ኹሉ ብቻውን መቀበል እንደሚፈልግ ፈቃዱን ገልጦአል (18፥4)፣ ጊዜው ሳይደርስ እንዳይሞትም ያውቃል (11፥54)፤ ኢየሱስ ሥጋን የለበሰ ደካማ መሲሕ ኾኖ ቢገለጥም ነገር ግን ኹሉን አዋቂና ተቈጣጣሪ ጌታ ነው። በእርግጥም የሞተው በአጋጣሚ አይደለም፣ እያወቀና ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ ስለሚወደንና ስለሚያፈቅረን ነው።




   ይህ ተወዳጅና ፍቅር የኾነ መሲሐዊ ንጉሥ በመስቀል ተሰቅሎ ስለኃጢአተኞች ሞተ፤ የሞተውም ደግሞ ከዘላለም በፊት እግዚአብሔር እንደ ወሰነውና እንደ አቀደው በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ በመሰጠት ነው፤ (ሐዋ. 3፥22-23)። እግዚአብሔር በክፉዎች አይሁድ ፈቃዱንና ዕቅዱን አከናወነ። እጅግ ክፉዎች በኾኑት እግዚአብሔር ከዘላለም በፊት ያሰበውን ዕቅዱን ፈጸመ። ማንም ሊያስተውልና ሊመረምር በማይችል ፍጹም ጥበቡ፣ የሰዎችን መዳን ሊፈጽም እግዚአብሔር ሃሳቡን በክፉዎች ማድረጉ እጅግ የሚደንቅና “እንዴት እንደሚያድን” የሚያውቅ አምላክ መኾኑን እናስተውልበታለን።
   ባለ ብዙ ሞገሱ፣ ተወዳጁ፣ ባለ ብዙ ግርማው፣ መላእክት በመራድና በመንቀጥቀጥ የሚሰግዱለትና የሚያመልኩት፣ ሰማያትን፣ ምድርንና መላዋን የፈጠረውና የሚመግበው ንጉሥ ኢየሱስ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ ከመከራው ጽናት የተነሣ የሞተው ወዲውኑ ነበር፣ ወዲያው በመሞቱም ጲላጦስ እንኳ ተደንቋል፣ (ማር. 15፥44)፤ አዎን ፍጹም ሰው የነበረው ጌታ በሰውነቱ ስለኃጢአታችን ብቻውን ሞተ፤ ሐዋርያትና ብዙዎች ተስፋ አድርገውበት ቢኾንም እርሱ ግን ፍጹም በሰውነቱ ሞተ፤ (ዮሐ. 19፥33)። ስለ ኃጢአታችን ሞትን በሥጋው ቀመሰ፤ (ሐዋ. 5፥30፤ 13፥28)። እርሱ በሥጋው ባይሞትልን ማን ያድነን ይቻለዋል? ከሞት ግርማና ፍርሃት ያድነን ዘንድ፣ ከገሃነምና ከኩነኔ ያስመልጠን ዘንድ፣ ከኃጢአት ኃይልና ጠባሳ ይታደገን ዘንድ በሥጋው ሞተልን፤ አባት ሆይ! ስለዚህ ፍቅር እንወድሃለን!!!
ኢየሱስ በሞት ሲሰናበት ቀባሪ አላገኘም ነበር፤ ኹሉም አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ፣ ደግሞም ኢየሱስ ተቀብሎት የነበረው መከራ እጅግ አሰቃቂና በሰዎች ኹሉ ፍርሃትን የፈጠረ ስለ ነበረ ማንም ሊቀብረው መምጣትን አልደፈረም። አብረንህ እንሞታለን ያሉ ብዙዎች ቢኾኑም እንኳ ከቅርብ ዘመዶቹ ጀምሮ እስከ ደቀ መዛሙርቱ ድረስ አንድም እንኳ በዚህ ቁርጥ ሰዓት አልመጣም። የሰማይና የምድር ንጉሥ ቀባሪ አጣ! እንዴት በዚህ ሰዓት ከዚያ ኹሉ ሕዝብ አንድ ስንኳ አላዘነለትም?! ተአምራት ካየ፣ በርክቶ ከበላው እንጀራና ዓሳ ከተካፈለው ማኅበረ ሰብ አንድ እንኳ እንዴት አልተገኘም። በሰማይና በምድር የተወደድን እንኾን ዘንድ ንጉሡ ኢየሱስ በኹሉ ዘንድ የተጠላ ኾነ!!!
  በዚህ ቀን ለቀብሩ የተገኙት ኹለት የስውር ደቀ መዛሙርት ናቸው። እስከዚህ ቀን ድረስ ስለ ኢየሱስ በግልጥ ያስተማሩት፣ የተናገሩት፣ ያደረጉት ነገር አልነበረም፤ ዛሬ ግን ኢየሱስ ቀባሪና አስታዋሽ ባጣበት ሰዓት እኒህ ኹለት ባለ ሥልጣንና ባለጠጋ የኾኑት ኒቆዲሞስና ዮሴፍ ጌታ ኢየሱስን ሊቀብሩት መጡ። የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ እንዲሰጠው ጲላጦስን ለመነው፤ ስውሩ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ባልተጠበቀበት ሰዓት ተገለጠ፤ በሌሊት ይመጣ የነበረው ኒቆዲሞስ ደግሞ  ለሥርዓተ ቀብሩ ማስፈጸሚያ የሚኾን መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። 
ኹለቱ ሰዎች ኢየሱስን መሸሸግ አልቻሉም፤ ኢየሱስ መሸሸግ አይችልምና፤ ማንም በኢየሱስ በቅዱሱ መሲሕ ካመነ፣ ፍቅሩን ታግሶ ዝም ማለት አይችልም። ፍቅሩ ከተራራ እንደ ተፈነቀለ ዓለት ኹሉን ነገር ማለፍ ይችላል። ሐዋርያት መከራን፣ ነቀፋን፣ መጠላትን፣ መገፋትን፣ መዋረድን፣ መሰየፍን፣ መቃጠልን ኹሉ የታገሱት ኢየሱስን በትክክል ስላመኑት ነው። ለኢየሱስ የማይመሰክሩ አንደበቶች ዲዳዎች ናቸው፤ ኢየሱስን የማያሰላስሉ ልቦች ሙት ናቸው፤ ለኢየሱስ ያልተሰጠ ማንነት ከኹሉ ይልቅ ምስኪን ነው!!!
ነቢዩ ኢሳይያስ “ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥” (ኢሳ. 53፥9) በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ በአትክልቱ ሥፍራ መቃብሩ ተደረገ። ኢየሩሳሌም የአትክልቱን ሥፍራ የረከሰ ትለዋለች፤ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም አትክልት አይተከልም፣ ምክንያቱም የአትክልቱ ማዳበሪያ ከተማይቱን ያረክሳታል ስለሚባል። ስለዚህም አትክልት የሚተከለው ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጪ ነው። እናም ኢየሱስ በ“ርኩሱ ሥፍራ” በአትክልቱ ቦታ ተቀበረ። ሞቱ ከክፉዎች ጋር ኾነ፤ ቀብሩ ደግሞ አይሁድና ኢየሩሳሌም በሚጠየፉበት ቦታ ኾነ። ኢየሱስ እኛን ለማዳን የመጨረሻውን ውርደት ተዋረደ! ወዳጄ አማኝ ክርስቲያን ሆይ! ኢየሱስ እንዴት እንደ ወደደህ አስተዋልክን?!
ባለጠጎች የሚበለጥጽጉት በክፉ መንገድ ነው፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ይልቅ በሀብታቸውና ባላቸው ይመካሉ። ኢየሱስ የተቀበረው በባለጠጋው ዮሴፍ መቃብር ውስጥ ነው፤ እርሱ ደግሞ ብዙ ምሕረትና ይቅርታን አጊኝቶ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የኾነ ነውና፣ ጽኑ ፍቅሩንና ለእርሱ ብቻ መገዛቱን በመቃብሩ ስፍራ በመገኘት ገልጦአል። እናም ኢየሱስን በዚያ እጅግ በድንጋይ በተወቀረ ባለጠጋ እንደሚቀበር ተቀበረ። ኢየሱስን በዚያ አኖሩት ሲለን መቀበሩንና ፍጹም ሰው መኾኑንም ጭምር ይነግረናል።
ኢየሱስ በተቀበረበት በዚያ ወቅት በሰማይና በምድር ፍጹም ዝምታ ኾኖ ነበር። ማንም ሊረዳው የሚችል የሌለ እስኪመስል ድረስ በኢየሱስ ላይ ኹሉም ዝም ብለዋል፤ አባቱም እንኳ ሳይቀር ዝም ብሎት እንመለከተዋለን። ይህ ግን የኾነው የማይሠራና ደካማ መስሎ ኃይለኛውንና ደካማውን እየያዘው፣ እያሰረው፣ እየቀጣው፣ እየሰበረው፣ እያዋረደው ነበር። ኢየሱስ በመቃብር ሳለ በዝምታ እየሠራ ነበር፤ እግዚአብሔር በብዙ ነገራችን ዝም ሲል የሚሠራ ሳይኾን፣ የተወንና የጣለን፣ የረሳንና በኃጢአታችን ምክንት ዘወር ብሎ ያለፈን ይመስለናል። እርሱ ግን በዝምታም እንኳ እየሠራ እንደ ኾነ ማስተዋል አለብን፤ “በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” (1ቆሮ. 15፥54-55) ተብሎ የተዘመረው ኢየሱስ እንደ ደካማና እንደ ተሸነፈ ኾኖ በመቃብር በዚያ ኾኖ ነው። አዎን! እግዚአብሔር በሰው መንገድ ያይደለ፣ ሰው ሊቀበለውና ይኾናል ብሎ በማይገምተው መንገድ እየተዋረደ፣ እየተሸነፈ፣ በመቃብር ተይዞ ሲሠራ አይተነዋል፤ ዛሬም ያ ኢየሱስ አልተለወጠም፤ እንዲህ ባለ መንገድ በሕይወታችን ስለሚሠራ ክብር ይኹንለት፤ አሜን።


5 comments:

  1. betaam astemari menfasawi ankets new. temrebetalaw.

    ReplyDelete
  2. አዎን! እግዚአብሔር በሰው መንገድ ያይደለ፣ ሰው ሊቀበለውና ይኾናል ብሎ በማይገምተው መንገድ እየተዋረደ፣ እየተሸነፈ፣ በመቃብር ተይዞ ሲሠራ አይተነዋል፤ ዛሬም ያ ኢየሱስ አልተለወጠም፤ እንዲህ ባለ መንገድ በሕይወታችን ስለሚሠራ ክብር ይኹንለት፤ አሜን። amen!

    ReplyDelete
  3. ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ይብዛልህ

    ReplyDelete
  4. አሜን አሜን ተባረክ

    ReplyDelete
  5. የአገልግሎት ዕድሜህን ያርዝምልን

    ReplyDelete