Saturday, 2 May 2026

“በወንጌል ሕይወታችን ኾነ” ከሚለው ጉባኤ የተወሰዱ ቊልፍ አባባሎች፣

 


-     “… የሰው ልጅ ኹለተኛ ባሕርይ ረቂቅ ነፍስ ናት፤ ለረቂቅ ነፍስ ደግሞ የሚሰዋላት ሕያው መስዋዕት ወንጌል ነው።”

-     “… የወንጌል ሰባኪው ራሱ ሕያው ወንጌል ነው፤ ብዙ ጊዜ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ወይም ሃይማኖታቸውን በጥልቀት የማይመረምሩ፣ ለማንበብ ጊዜ የሌላቸው ምእመናን ሁልጊዜ የሚያነብቡት የአገልጋዩን ሕይወት ነው። …”


-     “… ምዕመናን ከአገልጋዮች የከንፈር ድምጽ ይልቅ በመጀመሪያ የሚያደምጡት በዝምታ ውስጥ ጮኾ የሚናገረውን ሕይወታቸውን ነው። ምዕመናን መጀመሪያ የሚያደምጡት ዓውደ ምሕረት ቆሞ የሚናገረውን ድምጽ ሳይኾን ከዚያ ጀርባ ያለውን ጸጥ ያለ ሕይወታችንን ነው። ደምቆ ከምድር በላይ እስከ አጽናፍ የሚያስተጋባው ድምጻችን እሱ ነው።”

-     “… የሰባኪው ኃይልና ሥልጣን ለማስተማር በመረጠው ርዕስ ወይም በመድረኩ ላይ በሚያሳየው ብቃት ሳይኾን ከዓውደ ምሕረት ውጭ ያለው የሰባኪው ወጥ ሕይወት ነው። …”

-     ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ በምናኔ ሕይወት ትርጓሜው፣ “ሕይወትህ የንግግር መለኪያ ይኹን” ይላል፤ “ስለ ሰላም ስትናገር መጀመሪያ በልብህ ውስጥ ሰላም ይኑር፤ ስለ ምሕረት ስትናገር በመጀመሪያ በእጅህ ላይ ምሕረትን አሳይ፤ አንተ በአንተ ውስጥ የሌለውን በሌሎች ላይ አትናገር፤ አታድርግ።” ይላል። የሚሰብከውን በተግባር የማያውል አስተማሪ መንፈሳዊ ብክለትን ያስከትላል።…”

-     “… አንድ ሰባኪ ለሌሎች የምንግሥተ ሰማያትን መንገድ እያመላከተ፣ ራሱ በእግሩ ወደ ገሃነም የሚገሰግስ መኾን የለበትም። “መምህር በራሱ ጠባይ ከመካድ የበለጠ አሳፋሪ ነገር የለም” ይላል ቅዱስ ጀሮም።…”

-     “… ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ “On the Incarnation of the Word` በሚለው ትምህርቱ ላይ መጀመሪያ እጅህን ታጠብ ይላል። መጀመሪያ እጅህን ታጠብ፤ ከማንበብ በፊት ይታጠቡ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመመርመርና በትክክል ለመረዳት የከበረ  ሕይወት፣ ንጽሕት ነፍስና የክርስቶስ ጽድቅ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከዚያም አእምሮችን የሰውን ተፈጥሮ  በሚፈቅደው መጠን የእግዚአብሔርን ቃል ለመረዳት ይችላል፡፡…”

-     “… ሰባኪ ለምስጋናም ኾነ ለውግዘት ግድ የለሽ መኾን መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም በምስጋና ፍላጎት ከተነቃቃ ወይም በትችት ክብደት ከተሸነፈ እውነትን በድፍረት መናገር አይችልም፡፡ ቃላቱም ነፍሳቸውን ከመፈወስ ይልቅ ጆሮአቸውን ለማስደሰት እያስተካከለ ለአድማጮቹ ባሪያ ይኾናል፡፡ …”

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment