Friday, 5 June 2026

ጳውሎስ የሰማው የሞት ድምጽ! (2ቆሮ. 1፥9-11)

 Please read in PDF

ቅዱስ ጳውሎስ ኹለተኛውን ቆሮንቶስ እየጻፈ ያለው፣ በአንደኛ መልእክቱ ላይ በታላቅ ተግሳጽ የገሰጻቸውንና ንስሐም በመግባት የንስሐ ፍሬ ያሳዩትን ቅዱሳን ወገኖቹን ለማጽናናትና ለማበረታታት ነው።

አንደኛውን መልእክት ሲዘጋ፣ የወንጌል ሥራ በር እንደ ተከፈተለትና ነገር ግን የዚያኑ ያህል ደግሞ እጅግ ተቃዋሚዎች እንደ ተነሱም ተናግሮአል (1ቆሮ. 16፥8-9)፤ ምናልባት ተቃዋሚዎቹ ከባድ ስደት አልያም ከፍ ያለ እንግልት አድርሰው ሊኾን ይችላል።

ይኹንና የደረሰባቸው መከራ ለሞት ጭምር ሊያጋልጣቸው እንደሚችልና የሚሞቱም እንደ መሰላቸው ይናገራል። የኹኔታውን ክብደት ሐዋርያው ሲናገር፣ “እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።” ብሎአል።ሁኔታው በጣም አስጨናቂ ስለነበር ጳውሎስና ጓደኞቹ በሕይወት የመቆየት ችሎታቸው ላይ ሙሉ በሙሉ “ተስፋ ቈርጠዋል”። ይህ ማለት ሙታንን በሚያስነሣው አምላክ እንዲታመኑ ተገደዱ።

አቅመ ደካሞች ነበሩ እናም ሁሉንም ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲያደርጉ እንኳን ተገደዱ። መከራ በማንኛውም አማኝ ላይ ተመሳሳይ የኾነ ስሜትን ይፈጥራል። በሐሰት የምንጠብቀውን ማንኛውንም ነገር አስወግዶ ሙሉ ተስፋችንን በምንታመንበት ኃያል አምላክ ላይ እንድናሳርፍ ያደርጋል።

አኹንም፣ ጳውሎስ መከራውን ከኢየሱስ መከራ ጋር አገናኘው። ኢየሱስ የሞት ፍርድ የተቀበለው ከሮማውያን ሲኾን፣ ጥላቻንና፣ ንቀትንና ስድብን ጠግቦ የተቀበለው ከገዛ ወገኖቹ አይሁድና የሃይማኖት መሪዎች ነው። ጌታችን ግን በዚህ ኹሉ መከራ ውስጥ፣ “በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥” ደግሞም፣ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤” (ዕብ. 5፥7፡ 8)፤ አሜን።

የዳነ አማኝ ዘወትር ባለማቋረጥ ወዳዳነው ጌታ መቅረብ አለበት፤ አምነን የመዳናችን ትልቁ ግብ ወደ ጌታ ፍጹም መጠጋትና በርሱ ጥላ ሥር መከለል ነውና። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “… ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤” (2ቆሮ. 1፥9-11) አለ።

አሜን ዛሬም ከዘላለም ሞት የዳንን እኛ፣ በዙሪያችን ካለው ከብርቱ ሞት ድምጽ ያድነናል፤ ይታደገንማል።


1 comment:

  1. በዚሁ ሁሉ ዘመን ኢየሱስ ጌታ ነው ትላንትና ዛሬም ለዘላለም ያው ነው አሜን አሜን!!

    ReplyDelete