Wednesday, 4 October 2017

የበጋሻው ደሳለኝ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” አማኝነትና ኑፋቄያቱ (ክፍል 2)

በክፍል አንድ ላይ ለተሰጡ አስተያየቶች “ሚጥጥዬ መደምደሚያ”
    የተሰጡት አስተያየቶች ሁለት መልክ ያላቸው ናቸው[ሦስተኛውን የስድብ ክፍል መጥቀስ ባልሻም]፤ አንደኛው ቀድሞ በግል መምከርና ማናገር ይገባ ነበር እና አንተ ራሱ ማን ኾነህ ነው እርሱን “የምትኰንነው?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ለአስተያየቶቹ መልስ መስጠትን ባላምንበትም፣ በአብዛኛው በዙርያዬ ያሉ ሰዎች ያዘነቡትን ስድብና[በተለይ በኢሜይል] አስተያየት ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እጅግ ስለወረደብኝ፣ የትምህርቱን ኢ ክርስቶሳዊነት ለሚረዱት የማጥራት ሥራ ለመሥራት፣ ትምህርቱን አምነው ለተከተሉት ደግሞ በክርስቶስ ትምህርት ላይ ለሚመጣው የትኛውም ሰውም ኾነ ማኅበር ጭካኔዬን ለማሳየት ነው፡፡ አንድ ነገር ማስታወስ እወዳለሁ፤ አሁን እየተቃወሙ ካሉ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ግብረ ሰዶማውያን አገልጋዮች በግልጥ ተደርሶባቸው እንዲመለሱ ብዙ ተመክረው አልመለስ ሲሉ፣ ከአደባባይ ነውራቸው አልመለስ ብለው ልባቸውን ሲያደነድኑና እውነታውን ለማድበስበስ ሲጥሩ በአደባባይ ሰዎች እንዲጠነቀቋቸው ስጽፍ የተቃወሙኝ መኾናቸውን አሁንም ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡
    በጋሻውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ማውራቴንና በዚህ ትምህርት ማመን አለማመኑን ስለመጠየቄ፣ እርሱም ስለመናገሩ ያልጻፍኩት፣ ብዙም አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው፤ አስፈላጊና ሁሉ ማወቁ የግድ ተገቢ ነው ከተባለ ግን እንዴትና ምን ብዬ እንዳወራሁት፤ እርሱም በዚህ ትምህርት ዙርያ ያለውን አቋሙን ምን ብሎ እንደነገረኝና ይህን የሐሰት ትምህርትም ሊለውጠውም እንደማይፈቅድ የመለሰልኝን በዚህ ጽሁፍ ማብቂያ ላይ ለመግለጥ ቃል እገባለሁ፡፡

   ሁለተኛውን ሃሳብ ግን ለመቀበል ፈጽሞ እቸገራለሁ፤ በጋሻው “አዲስ አስተምህሮ” መከተሉን ከሰማሁበትና ለማጣራት ከጀመርኩበት ቀን ጀምሮ በዙርያው ያሉ ሰዎች ሲከላከሉለት የነበረው [በወንጌል የበረቱ ወንድሞችና አባቶች እንዳያገኙትም ጭምር የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ] እንዲህ ያለውን ነገር በመናገር እንጂ በጋሻውን ከዚህ የክርስቶስ ጠላት ከሆነ ትምህርት ለማዳን ብዙ ከመጨነቅና ከመራራት አንጻር አልነበረም፡፡ እኔ የበጋሻው ተከታዮቹ እርሱን እንደሚያዩት አላየውም፤ የበጋሻው ነፍስ ከሌላው አማኝ ነፍስ በምንም አትበልጥም፤ ነገር ግን እንደአገልጋይነቱ “ብዙዎችን ስለሚያሰናክል” በአደባባይ ለሠራው ስህተት በአደባባይ ከዚህ ኑፋቄው ንስሐ ገብቶ እንዲመለስ፣ አልያ ግን እርሱን መቃወም ከቅዱሳን ሐዋርያት የተማርኩት ነው፡፡
     በተረፈ ለግብረ ሰዶማውያን “አገልጋዮች” ያልራራው ብእሬ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና ቤዛነቱን ለሚዘልፍ ትምህርት እንዲራራ መመኘት ከሁሉ የሚያንስ ምስኪንነት ነው፡፡ ደግሞም ኀጢአትን ደረጃ አውጥተንለት የአገልጋይና የአማኝ ብለን፣ የአገልጋይን “ብዙ ስላገለገለ[አገልግሎት የአደባባይና የጓዲያ ተብሎ መከፋፈል ተጀምሮ ይኾን?]፣ ከሌሎች ይልቅ መከራም ስለተቀበለ[መከራም ደረጃ እየወጣለት ይኾን?]፣ ታዋቂ ስለኾነ … ከምዕመን ኃጢአት ጋር እኩል ሊታይ አይገባም” የሚለውን አገልጋይ አግናኝ፤ አማኝ አንኳሳሽ ትምህርት ከጌታም ከሐዋርያትም ስላልተማርኩት አልቀበለውም፡፡ የእባብ መርዝ የትንሹም እባብ ኾነ የትልቁ እባብ መርዝ፤ ያው መርዝ ነው፤ ኀጢአትም ማንም ይሥራው ማን ኃጢአት ነው፤ ንስሐ ገብተን በክርስቶስ ደም ስንታጠበውና ስንጠራ፤ ስንነጻም ብቻ እንጂ በአደባባይ ክርስቶስን የሚኮንን ትምህርት እያስተማርን በአደባባይ ልንወቀስ አይገባንም የሚለውን “ሙሾ” መስማት ለእኔ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ [ለክርስቶስ ትምህርት ለምታደሉ ሁሉ! በአደባባይ ኀጢአትን ሠርቼ ብዙ እድል ተሰጥቶኝ ለመመለስ ከመውደድ ይልቅ ብዙዎችን በማሰናከሌ ከቀጠልኩ ለእኔም እንዳትራሩልኝ]፡፡
የበጋሻው ደሳለኝ ግልጥ የእምነት እንቅስቃሴ አስተምኅሮዎች
1.     በጋሻው ከማንም ምንም አልተማረም፤ መማርም አይፈልግም፡፡ የሕይወቴ ምስክርነት ብሎ በተናገረውና በራሱ አንደበት “በአዋሳ ከተማ” ተገኝቶ ተከታዮቹን ባስተማረው ትምህርቱ ላይ በራሱ አንደበት እንዲህ ሲል ተናግሯል፣
 
“ ... በዚህ ዓመት መጀመርያው ላይ(2009 ዓ.ም) በሁለተኛው ወር በአንድ ቅዳሜ ምሽት በገዛ ቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ ለራሴ የጌታ መንፈስ አገኘኝ፡፡ ማንም አላገኘኝም፤ ማንም አልመሰከረልኝም፤ ማንም እጁን አልጫነብኝም ... በቤቴም ሳለሁ ላፕቶፕ ላይ አንድ ጽሑፍ እያነበብኹ ሳለ አንድ ትልቅ ከባድ እንደደመና ያለ ነገር እላዬ ላይ ወደቀ ... እስከ ለሰባት ሃያ ጉዳይ አከባቢ ድረስም ስታገል ቆየሁ፤ ... ለአንድ ሠላሳ ደቂቃ ያህልም “shake” አደርግ ነበር፤ ከዚያም ተኛሁ፤ ራሴንም አላውቅም ነበር፡፡
 ከዚያ ጠዋት ስነቃ ያ የሌሊት ድካሜ ታጥቦ ወይም ስፖርት ሠርቶ  “fresh” ብሩህ የኾነ የደስታ ስሜት አገኘኝ፡፡ እናም ያን ጊዜ ነው ነገሩ የገባኝ ማለት ነው፡፡ እና በወቅቱ ምን ዓይነት ስሜት ነው አልኩ፤ አሁን ግን ኢየሱስ የተቀባበት የደስታ ዘይት ነው፡፡ ...
     ... ከዚያን በኋላ ብዙ የጸሎት ጊዜያቶች ከወንድሞች ጋር ምናምን ኖረውናል፡፡ ከዚያኔ ጀምሮ በትክክል እጁ መጥታ ሳትነካኝ ያለፈችበት ጊዜ የለም ማለት ነው፡፡ እና አሁን ደግሞ እየጨመረ ለሃያ አራት ሰዓት ሰባት ቀን ማለት ነው፤ ጸሎት ላይ ብቻ ምናምን ሳይኾን በማንኛውም መንገድ ከእኔ ጋር ነበር ...  ”
ማለት የራሱን የሕይወት ምስክርነት ሰሚዎቹ በመንፈስ እንዲነቃቁበት በማለት በድፍረት ተናግሯቸዋል፡፡
    በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን ነቢያትም ኾኑ ሐዋርያት ስለተገለጠላቸው ጌታና ስለገለጠላቸው ነገር መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ለእነርሱ የተገለጠበትም አገላለጥ ውስብስብና አደናጋሪ ሳይኾን ግልጥ የኾነና አሻሚ ያልነበረ ነው፡፡ አንድ እውነት አለ፤ ያለእግዚአብሔር መገለጥ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም፡፡ ወይም እግዚአብሔር ራሱን ካልገለጠልን በቀር ፈጽሞ ልናውቀው አንችልም፤ (ኢሳ.55፥8 ፤ 1ቆሮ.2፥14 ፤ 2ቆሮ.4፥4)፤ የገለጠልንም ኹሉንም ያይደለ የሚረባንንና የሚጠቅመንን ብቻ ነው፤ (ዘዳግ.29፥29)፤ በፊተኛው አጠቃላይ መገለጥ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረቱ (ሮሜ.1፥19 ፤ ሐዋ.14፥17)፣ በኅሊናና በታሪክ መግለጡን ታላቁ መጽሐፍና ስለነገረ እግዚአብሔር ያጠኑ አባቶች ይነግሩናል፡፡
    ዳሩ ግን አጠቃላይ መገለጥ በቀጥታ ሰውን ወደእግዚአብሔር ማድረስ ባለመቻሉ እግዚአብሔር ልዩና ታላቅ መገለጥን ሊያመጣ ወደደ፡፡ ስለዚህም፣ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤” (ዕብ.1፥1-2 ፤ 1ጢሞ.3፥16) በማለት የዕብራውያን ጸሐፊ ከመግለጡም ባሻገር፣ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ.1፥18) በማለት የመገለጦች ዳርቻ ክርስቶስ ኢየሱስ መኾኑን በትክክል ይናገራል፡፡
   በክርስቶስ የተወሰነውንና የዘጋውን መገለጥ እናብራራዋለን እንጂ፣ አዲስ መገለጥና ትምህርት በማምጣት ቅጣይ ልናበጅበት አንችልም፡፡ በክርስቶስ ለእኛ ያልተገለጠና ቀረ የምንለው አንዳች ምስጢር የለም፡፡ እርሱ ዳርቻችን፣ ዋናው ወሰናችን ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንኳ ሲመጣ የሚያስተምረን፣ የሚያስታውሰን፣ የሚመክረንና የሚገስጸን ክርስቶስ ከተናገረው ከዚያው ቃል እንጂ፣ አዲስና ልዩ መገለጥን በመስጠት አይደለም፤ (ዮሐ.15፥26 ፤ 16፥8 ፤ 12-15 ፤ 1ቆሮ.2፥11 ፤ ዕብ.2፥4)፡፡ እግዚአብሔር የሃይማኖትን ትምህርት ፈጽሞ ገልጧልና አሁን እኛ አማንያን በዚሁ በተገለጠው ትምህርት ጸንተን መቆም እንጂ ሌላ መግለጫ መፈለግና ወይም መከታተል አይገባንም፤ (ኤፌ.3፥5 ፤ 6 ፤ ይሁ.3 ፤ ራእ.22፥18-19)፡፡
   የግል ሕይወትን በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ ለግል ሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንድናውቅ፣ እንድናስተውል ይመራናል፤ (ሮሜ.8፥14 ፤ 1ቆሮ.14፥26 ፤ ገላ.2፥2)፡፡ ይህ መገለጥም በክርስቶስ በስሙ ለምናምንና ዘወትር ከእርሱ ጋር በቅድስና ለምንኖር ኹላችን እንጂ “የአገልግሎት ካባ ለደረቡ አገልጋዮች ብቻ” አይደለም፡፡ እንደውም አንዳንዴ “ለአገልጋዮቹ ሐዋርያት” ሳይገለጥ “ለሌሎች” ከመንፈስ ቅዱስ የመጣውን ምሪት የሚናገሩበት ሂደት እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ በሐዋርያት ዘመን የነበረውን ነቢይ አጋቦስ የተባለውን ሰው ማስታወስ እንችላለን፤ በአንድ ወቅት በመላው ዓለም ስለሚነሳው ረሃብና ጳውሎስ ስለሚደርስበት መከራ በትክክል ተገልጦለት ተናግሯል፤ (ሐዋ.11፥28 ፤ 21፥10)፡፡
    መምህራንና ነቢያት በአንድነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገለግሉ ነበር፤ (ሐዋ.13፥1 ፤ ኤፌ.2፥20)፡፡ በዚህ የአገልግሎት ዘመናቸውም የሚሠሩት ሥራ እንደቃሉ ሊመጣ ያለውን እንደነቢዩ አጋቦስና ቅዱስ ዮሐንስ(ራእ.1፥19) መግለጥ፣ ቤተ ክርስቲያንን መምከር፣ ማጽናትና ማነጽ (ሐዋ.15፥32 ፤ 1ቆሮ.14፥3) ነው፡፡ “አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ … በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ? … እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም” (1ቆሮ.14፥6 ፤ 22) እንዲል፣ መገለጥና ትንቢት አስፈላጊ ቢኾንም በሥርዓትና በአገባብ ሊነገር፣ ከተነገረውና ከተገለጠው ቅዱስ ቃል ጋር የተስማማና አንድ የኾነ መኾኑን በትክክል መመርመር ይገባናል፡፡
    የእምነት እንቅስቃሴ አማኞችና አገልጋዮች በትምህርቶቻቸው ኹሉ፣ “የመገለጣችንና የትምህርታችን ምንጩ እግዚአብሔር ብቻ ነው” በማለት፣ ጌታችን ያስተማረውን ቅዱስ ወንጌል፣ የሐዋርያትን ትምህርትና በብዙ ትጋት ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ውስጥ ማለፍን ፈጽመው አይደግፉም፤ አይፈልጉምም፡፡ ቅዱስ ቃሉ ግን ፣ “ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው፤” (1ጢሞ.4፥9)፤ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ፤” (2ጢሞ.2፥15)፤ በሚለውና በሌሎችም የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት ውስጥ ድካምና ትጋት የሚሉት ቃላት የተገለጡት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋልና በጸሎት ልብ ለማጥናትና ለመመርመር ላብን[ወዝን] ጠብ እስኪል ያለውን ድካምና ትጋት የሚያሳይ ነው፡፡
    ጌታ ኢየሱስ አይሁድ ብሉይ ኪዳንን በሚገባ ባለማወቃቸው፣ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን?” (ማር.12፥24) በማለት ወቀሳቸው፡፡ ቅዱስ ቃሉ የተሰጠን ለእኛ ከኾነ በትክክል ማጥናትና በቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ኾነን ዘወትር ልናነበው ይገባናል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ቢኾን እንኳ ይህ እውነት ቋሚና የማይለወጥ ነው፤ ምክንያቱም ለትምህርትና ለሥነ ምግባር አስፈላጊ የኾነው ነገር ኹሉ በሐዋርያት ለቤተ ክርስቲያን ተሰጥቷል፤ (ገላ.1፥8 ፤ ይሁ.3)፡፡
     በጋሻው፣ ትምህርቱን[አዲስ ማንነት እያለ በተደጋጋሚ የሚጠራውን] የኢየሱስን የደስታ ዘይት ከቀባው ከራሱ ከመንፈስ ቅዱስ እንጂ ከማንም እንዳልተማረው ሲናገር ሰምተነዋል፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ደግሞ ቴዲ ከሚባለው ልጅ ጋር በስልክ ሲናገር እንደተደመጠው፣ የየትኛውም “የኔታ እጅ” እንዳልገባበት አፉን ሞልቶ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን በጋሻው ይህን ትምህርት የሚናገረው እንዲኹ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ልምምዱን የወሰደበትና እንዲህ አይነት ግልጥ ልምምድ ያላቸው አካላት ስላሉ እንጂ፡፡ በተለይም ኹሉም የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን “ከራሱ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሌላ ከማንም እንዳልተማሩ” በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል የሚመስል፣ ነጭና እጅግ አንጸባራቂ ልብስ የለበሰ ተገልጦ ከፊት ለፊቴ ቆመ”፣ “ኢየሱስን ፊት ለፊት አየሁት፤ ተገልጦልኝም ተናገረኝ፤ በእጁም ዳሰሰኝ፤ ልክ ከሐዋርያት እንደአንዱም ሁሉንም ነገር አስተማረኝ” ብሎ በድፍረት መናገር የዚህ ትምህርት አራማጆች ዋና መገለጫ ነው፡፡
  በጋሻውም፣ ይህን ይበል እንጂ እኔ ካነጋገርሁት በኋላ፣ እንደእርሱ ከሚያገለግል ከቀድሞ አገልጋዮች መካከል ስለበጋሻው ቅድስና ከሚከራከሩለት አንዱ፣ እርሱን በማናገሬ እጅግ ተናድዶ፣ “በጋሻውን ለመሞገት ምንም አይነት የነገረ መለኮት ብቃትና ትምህርት እንደሌለኝ፣ በጋሻው ከደረሰበት መገለጥ እንዳልደረስሁ በቁጣና በብስጭት ተናግሮኝ ነበር፡፡ ስለዚህም “ልዩ መገለጥ እንዳለው” አምነው የተቀበሉለት ብዙ እንዳሉ አስተውያለሁ፡፡ እንዲሁም በጋሻው ራሱም፣ ‘አቤንኤዘር እኔን ለመሞገት ለመኾኑ ከየትኛው ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ወጥቶና ተምሮ ነው?’ ብሎ በብስጭት መናገሩንም ሰምቻለሁ፡፡
   የቃል እምነት እንቅስቃሴ መምህራን የሚሰሟቸውን ሰዎች ለክርስቶስ ደቀመዛሙርት የማድረግ ዓላማ የላቸውም፤ ዘወትር የእነርሱን መገለጥና ከራሱ ከእግዚአብሔር አገኘነው የሚሉትን “እንጭጭ ስብከታቸውን ብቻ” እንዲሰሙላቸው ይፈልጋሉ፤ በሌላ ንግግር ዘወትር ሰሚዎች እንዲኾኑ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲኾኑ አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ስብከት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከሰሚዎቹ መለየት ካልቻለ በእኛ ሕይወት የክርስቶስ ሃሳብ አልተከናወነም ወይም እንዲከናወን አልፈቀድንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የትኛውም አስተምኅሮ በቅዱስ ቃሉ ሚዛንነት መመዘን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የእምነት እንቅስቃሴ መምህራኑ ይህን መንገድ ፈጽመው ይጠየፋሉ፤ ምክንያቱም ሥውር ሴራቸውን ፈጽሞ ያፈራርሰዋልና፡፡
    እንግዲህ እኛ እነርሱን ስንሞግታቸው፣ ምን ያህል የነገረ መለኮት ዕውቀት እንዳለን እንጠየቃለን፣ እነርሱ ግን ነገረ መለኮትን አሽቀንጥረው ጥለው፣[ነገረ መለኮትን ማጥናት እግዚአብሔርን ለማወቅ ዋና መንገድ ነው ብዬ በግል አላምንም፤ እግዚአብሔር የሚፈሩ ነገረ መለኮታውያን ግን ትልልቅ ሥራዎችን መሥራታቸውን ከልብ አምናለኹ] “ከጌታ መንፈስ በቀጥታ ተምረናል” የሚሉትን “እንቶ ፈንቶ” ማስረጃ ሲጠየቁ፣ አሻፈረኝ ሲሉ እያየን ነው፡፡ በእርግጥ ግን እንዲህ በለበጣና በድፍረት መናገር የአማኝነት ዋና መመዘኛና መሥፈርት ሊኾን ይችላልን? እንኳን የዚህ ዘመን መምህራንና ተገለጠልን የሚሉ አካላትን አይደለም፣ የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ይሰሙ የነበሩት የቤርያ ክርስቲያኖች የሐዋርያውን ትምህርት ይሰሙት የነበረውን ቀጥታ እንደወረደ ሳይኾን፣ “እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ[2] ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ፣” (ሐዋ.17፥10) ነው የሚለን፡፡ 
    በጋሻው ከተናገራቸው ሁለተኛው የስንፍና ቃላት አንዱ፣ “ … ከዚያኔ ጀምሮ በትክክል እጁ መጥታ ሳትነካኝ ያለፈችበት ጊዜ የለም ማለት ነው፡፡ እና አሁን ደግሞ እየጨመረ ለሃያ አራት ሰዓት ሰባት ቀን ማለት ነው፤ ጸሎት ላይ ብቻ ምናምን ሳይኾን በማንኛውም መንገድ ከእኔ ጋር ነበር ...  ” ይላል፡፡ እንዲህ ያለ የፍጽምና መንገድ በትክክል የተገለጠውና የታየው በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት ብቻ ነው፡፡ “የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም … ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ” (ዮሐ.8፥29) ያለውና ማለት የሚቻለው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንጂ ከሰው ወገን ማንም ሊኾን አይችልም፡፡ ይህንም በመናገሩ ሰዎች ያመኑት ጌታችን ኢየሱስን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ አንዳች እንከን ያልተገኘበት፣ ፍጹም ጻድቅ ሰው ነው፤ (ማቴ.27፥54 ፤ ዮሐ.8፥46 ፤ 2ቆሮ.5፥21 ፤ 1ጴጥ.2፥22)፡፡
   እኛ ግን ፍጹም ባልተዋጀው ዓለም እያለን፣ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም፤” (1ዮሐ.1፥8-10) በማለት ቃሉ በግልጥ ያስረዳናል፡፡ “ሃያ አራት ሰዓት፣ ሰባት ቀናት” ጌታ በማናቸውም መንገድ ከእኔ አልተለየም የሚለው ቃል፣ “አልተሳሳትኩም፣ የእኔ መገለጥና ራእይ ትክክል እንጂ እንከን የለበትም” ወደሚለው የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን መደምደሚያ ላይ አያደርሰንም በሚል ሞኝነት አንያዝም፡፡ በጋሻው የዚያ መንደርደሪያ ላይ ነው ያለው ብንል አልተሳሳትንም፤ ምክንያቱም እያየናቸው ያለነው ፊት ለፊት ይህን ሲሉ እየሰማን ነውና፡፡
    እኒህ መምህራን ሁሉንም ትምህርቶቻቸውን “በቀጥታ ከእግዚአብሔር ተማርነው እንጂ ከሰው ወገን ከማንም አልተማርነውም” የሚሉበት ዋና ምክንያታቸው፦
      ሀ. ቃላቸውን ልክ እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንድንቀበለውና ሥልጣናዊ ቃል መኾኑን እንድናምነው ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉም ቃላቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍት እንደአንዱ እንድንቀበልላቸው ከመሻት የተነሣ ነው፡፡
      ለ. የሚያስተምሩትን አደገኛ ኑፋቄ ትክክልና መለኮታዊ ትምህርት ነው ብለን እንድንቀበላቸው ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ክህደታቸውን እንደቃሉ አስማምተንም እንድንቀበልም ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ከእኛው ጋር ተመሳስለው ወንጌሉን እንደጨበጡ በማስመሰል ሲያስተምሩ የምናየው፡፡
     ሐ.  በዚህ እምነት ሥር ያሉ የሐሰት መምህራን ትምህርትንና የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶችን የሚያጥላሉና እጅግ የሚነቅፉ ናቸው፤ ምክንያቱም በቀጥታ ከእግዚአብሔር ተምረናል፤ ከመምህርም ኾነ ከትምህርት ቤት መማር አያስፈልገንም ስለሚሉና ከማን እንደተማሩ ምንጮቻቸውን መግለጥ ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ውስጥ ያለውን ፈሪሃ እግዚአብሔራዊ ጥናትን ይንቃሉ፤ ያጣጥላሉ፤ ራሳቸውን ብቻ የትምህርታቸው ምንጭና ልክ እንደቅዱስ ጳውሎስ “ሐዋርያዊ ሥልጣንን” በራሳቸው መሾም ይፈልጋሉ፡፡
    እንዲህ ብለው መናገር ካልቻሉ በቀር፦ “ሰው መንፈስ ነው፣ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል”፣ “ሰው መንፈስ ስለኾነ ኢየሱስ ሰውን ሊያድን የሰይጣንን አካል በመልበስ ሰየጠነ”፣ “በመስቀል ላይ በሥጋ መሞት ለኀጢአት ክፍያ ዋጋ መኾን ከቻለ ሁለቱ ሌቦችም የኃጢአት ዋጋችሁን ከፍለውላችኋል ማለት ነው፤ ዋናው ነገር ግን የኢየሱስ ወደሲዖል ወርዶ የሰይጣንን አካል ለብሶ፣ በሰይጣን እጅ መከራን ተቀብሎ፣ ተሰቃይቶ፣ ለሰይጣን ካሳ ከፍሎና ከእግዚአብሔር ተለይቶ መቆየቱ ነው”፣ “የከፈለውም መሥዋዕትነት ሰይጣናዊ እንጂ እግዚአብሔራዊ(atonement) አይደለም”፣ “የምንናገረው ቃል፣ የምናምነው እምነት ልክ እንደእግዚአብሔር ቃል አድራጊና ፈጣሪ ነው”፣ “እግዚአብሔር ራሱ ልክ እንደእኛ ያምናል” … የሚለውንና ኁልቆ መሳፍርት የሌለውን ክህደታቸውን ሊግቱን አይችሉም፡፡ ይህን ሁሉ ክህደታቸውን ጸጥ፤ ለጥ ብለን እንድንቀበል በጋሻውና ባልንጀሮቹ “ሁሉን ከእግዚአብሔር ከራሱ ተቀበልን፤ ተማርን፤ እርሱም ሃያ አራት ለአንዲት ቅጽበት እንኳን አልተለየንም” ይሉናል፡፡
     ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስፈልገንን ሁሉንም ነገር ነግሮናል፤ ያልነገረንና አሁን እንደአዲስ ከፍጡር ወገን የምንጠብቀው አዲስ ትምህርትና መገለጥ የለንም፡፡  የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ይዞ የሚመጣውን እንጂ ማንንም እንዳንቀበል ጽኑ ሰማያዊ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም ከጌታችን ኢየሱስ በቀር የምንሰማው፤ ከቅዱስ ቃሉ፣ ከመንፈስ ቅዱስና ከቅዱሳን ሐዋርያትም የበለጠ አንዳችም ምስክር የለንም፤ እንዲህ እናምናለን፤ እንታመናለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




    [1] “የእምነት እንቅስቃሴ”[ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የቃል እምነት በመባል የሚጠራው] በመባል የሚታወቀውን መናፍቃዊ ትምህርት ጠንሳሽ ናቸው የሚባሉት፣ በ1879 ዓ.ም በኒው ዮርከ ከተማ የተወለዱት ዊሊያም ኢ. ኬንየን ናቸው፡፡ ኬኒየን የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን የነበሩ ሰው ቢሆኑም፣ በ1892 ዓ.ም ላይ ዲበ አካላዊ መናፍቃን (Metaphysical Cults) በመባል የሚታወቁት[በዚህ ትምህርት በዋናነት የሚታወቀውፊኒያስ ኩዎምቢ ሲሆን ከእርሱ ተከታዮች በዋናነት የክርስቲያን ሳይንስ አማኟ ሜሪ ቤከር ኤዲ በዋናነት ትጠቀሳለች] መናፍቃዊ እንቅስቃሴዎች ከፈለቁበትና ቦስተን ከተማ ከሚገኘው ኤመርሰን ኮሌጅ በመግባት፣ “አዲሱ አስተሳሰብ” (New Thought) በመባል የሚታወቀውን ትምህርት ተማሩ፡፡ ይህ ትምህርት መሠረት ያደረገው፣
“በቈሳዊ ነገሮች ላይ ለሚከሠቱት ነገሮች ሁሉ ምንጫቸው፣ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እውን የሆነው ነገር ሲሆን … አዎንታዊ ቃል በመናገር እንደጤንነትና ሀብት ያሉትን ቍሳዊ ጥቅሞች እውን ማድረግ(ማግኘት) ይቻላል፡፡”

በሚል አስተምህሮ ላይ የተጠነሰሰ ነው፡፡ (Charles E. Hummel, Fire in the Fire Place (Ivp, 2nd ed,1993), 25. 
    [2] “እየመረመሩ” የሚለው ቃል በግሪኩ “አናክሪኖ” ተብሎ የተጠቀሰ ሲኾን፣ ይኸውም ወደላይና ወደታች እያደረጉ ማበጠርን፣ የምንሰማውን ኹሉ በቃሉ ሚዛንነት መመዘን እንደሚገባን የሚያመለክት ነው፡፡ ማንኛውንም ትምህርት ኾነ ስብከት ወዲያው ያለምንም የቃሉ ሚዛንነት መቀበል አግባብ አይደለም፡፡ አማኝ ስንኾን ክርስቶስንና የተናገራቸውን ትምህርቶቹን ኹሉ ማመን፣ እንዲሁም ትምህርቶቹን ደግሞ በግል ልናጠናቸው፣ ልንመረምራቸው፣ በልባችን ልናሰላስላቸው፣ ልናወጣና ልናወርዳቸው ይገባናል፡፡ 

5 comments:

  1. እናመሰግናለን። ያላወቅነውን አሳውቀኸናል።

    ReplyDelete
  2. thank you very much. this is good to know

    ReplyDelete