ቅድስት
ድንግል ማርያም፣ ጌታችን ኢየሱስን በመውለዷ ቅድስትና ብጽዕት ናት። የጌታ መልአክ መልአኩ ገብርኤል መጥቶ እግዚአብሔር ሊሠራ
የወደደውን ጅማሮ በርሷ መሥራት እንደሚጀምር ሲያበስራትም በመረዳት መታዘዝዋ ስለተጻፈልን፣ ለአዲስ ኪዳን አማኞችም ለጌታ ቃል
ጥንቅቅ ባለ መንገድ መታዘዝና በትክክል መረዳትም እዳለብን ከሕይወትዋ እንማራለን። ይህ ብቻ ሳይኾን፣ በዕብ. 11 ላይ እንደ
ተጠቀሱት የእምነት አርበኞች፣ የእግዚአብሔር ቃል ዕውቀትዋ በጸሎትዋ፤ ልምምድና ሥራዋ ደግሞ በተጋድሎዋ ፍንትው ብሎ
ይታያል።
ስለ
እርስዋ የተነገረው ይህና ይህን የሚመስል ኾኖ ሳለ፣ ዳሩ ግን እርስዋን ታክኮ የሚነገረው፣ “በብልሃት የተፈጠረው ተረት” እጅግ
አሳዛኝና ብዙዎችን በማሳት የታወቀ ነው። ከነዚህም ውስጥ ግንባር ቀደሙን የሚይይዘው “ሞትሽ በጥር፤ በነሐሴ መቃብር” የሚለው
አንዱ ተረት ነው። የቅድስት ማርያምን ሞት ብዙ ኦርቶዶክሳውያንና ካቶሊካውያን “ከመ ምስለ ፍቁር ወልዳ - ልክ እንደ ተወደደ
ልጅዋ” ለማድረግ ያላደረጉት ጥረት የለም። በልጅዋና በርሷ መካከል የፍጡርና የፈጣሪ ያህል ግልጥ ልዩነት መኖሩን ያልተረዱ
እስኪመስል “ትንሳኤዋን ከልጅዋ ትንሣኤ” ጋር ሲያነጻጽሩ ይስተዋላል።
ዛሬም፣
“ትንሳኤዋን እንዳዩት ሰዎች እኛም የርሷን ትንሳኤ እንመለከታለን” በማለት፣ “የፍልሰታ ጾምን” ሲያውጁ እንመለከታለን።
የፍልሰታ ጾም ቀዳሚ ዓላማው “ሌሎች የርሷን ትንሳኤ እንዳዩ ለእኛም ትታይልን ዘንድ እንጹም” የሚል ነው። ግን አንድ እውነት
አስረግጠን መናገር ይገባል፤ ከክርስቶስ መካከል ሞትን ድል ነሥቶ ከሙታን መካከል የተነሣ ሌላ በፍጹም የለም። ከርሱ በቀር
ያሉት ኹሉም፣ በርሱ ኹለተኛ መምጣት መነሣትን ይህን እውነት እንኳንና ቅዱሳት መጻሕፍት የአባቶች ትምህርትም እንዲህ ይላል፣
“ስለዚህም ጌታ … በፈቃዱ ሞተ፤ ከተነሣም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም፤ ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታ
ይህን አልተናገረም፤ ከሰውም ወገን ማንንም ተነሥ፤ ከመቃብር ውጣ አላለም፤ ዳግመኛ እስከሚመጣባት ቀን ድረስ ለሰዎች ኹሉ አንድ
ኾነው በሚነሡበት ቀን ሙታን ይነሣሉ አላቸው።”[1]
“ … ከሙታን ተለይቶ እርሱ ብቻ ስለ ተነሣ ነው እንጂ ሥጋውን ብቻ ሕያው አድርጎ
ከኹሉ አስቀድሞ በአስነሣ ጊዜ፤ በተዋሐደው ሥጋ በሞተው ሞትም የሞትን ሥልጣን በአጠፋ ጊዜ ለባሕርያችን ወደ ትንሣኤ የሚያደርስ
መንገድ እንደ ኾነ ነገሩ የተገለጠ ነው፤ …”[2]
መጽሐፍ
ቅዱስ “ዘመኑን ዋጁ” ወይም “ይህ ዘመን ክፉ ስለ ሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ።” ይላል፤ ለኢየሱስ ክብር ጊዜ ካገኘን
(ገላ. 6፥10) የትኛውንም ዕድል መጠቀም ይገባልና። ይም ትክክለኛውን ጊዜ በአግባቡና በትክክል። ቢቻል ደግሞ ከኢየሱስ “ተነጥቆ”
ለሰው ወይም ለፍጡር የተሰጠውን “ጊዜና ክብር” ለኢየሱስ ማስመለስ ወይም እንዲመለስ ማድረግ። ከዚህ የተነሳ የፍልሰታ ቀናት ለማርያም
ሳይኾን ለኢየሱስ ክብር አምልኮ እንዲቀርብ ሊመለሱለት ይገባቸዋል። የትንሣኤው በኵር፣ ጌታና ንጉሥ ርሱ ብቻ ነውና። ለሙታን ኹሉ
ተስፋና ፋና ወጊ ኾኖ በኋለኛው ዘመን በቃሉ ሥልጣን ሊያስነሣቸው የሚመጣው፣ በሞትና በሲዖል፤ በገሃነምና በዲያብሎስ ላይ ሥልጣን
ያለው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ ብሉያት፤ ሐዲሳት ብሎም መላው ኦሪትና መዝሙራት፤ ነቢያትም ጭምር ከሙታን መካከል የተነሣውና
በመምጣቱ ደግሞ ሥጋ ለባሽን ኹሉ ማስነሣት የሚቻለው መሲሑ ብቻ እንደ ኾነ በአንድነት ይመሰክራሉ፤ አሜን። መንፈስ ቅዱስ
በነገር ኹሉ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን።

No comments:
Post a Comment