Friday, 17 July 2026

ለባህለ ትምህርት አልባ “ተሐድሶዎች”

 

ወንጌል የማይለወጥና ዘላለማዊ መልእክት ቢኖረውም፣ የራሱ ባህል ግን የለውም፤ ወንጌል ለየትኛውም ሕዝብ፤ ለኹሉም ነገዶች፤ በኹሉም ቋንቋዎችና ባህሎች መሰበክና መነገር ያለበት የእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅ ምሥራች ነው። ለዚህ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ዋና ምሳሌአችን ነው። ጌታችን ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለገሊላና ለይሁዳ መንደሮች ያቀረበበት መንገድ፣ እጅግ ጠቃሚ የኾኑ የባህል ተዛማጅ መመሪያዎችንና ልምምዶችን ያስተምረናል።

ጌታችን ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል በመወለዱ፣ ፍጹም አይሁዳዊነቱን ይገልጣል፤ ምንም እንኳ በዘር ግንዶቹ ውስጥ ከአሕዛብ ወገን የኾኑት እነ ሩት፣ ቤርሳቤህና ረዓብ በመጠቀስ መሲሑ የመላለሙ ቤዛና መድኀኒት ቢኾንም፣ “የትውልድ ሐረጉ” ግን የሚመዘዘው ከቤተ እስራኤል፤ ከቀደመው ኪዳን ተቀባይ ሕዝብ ነው። በዚያ ባህል ውስጥ በጠባብ ደረት፤ በአጭር ቁመት ተወስኖ ተመላለሰ፤ እናም ጌታችን ኢየሱስ ሲሠራና መልእክቱን የእግዚአብሔርን መንግሥት አዋጅ ሲያውጅ የምንመለከተው በተወሰነ ባህል ውስጥ ነው። የምናገለግለውን ሕዝብ ባህል ለመረዳትና ለማክበር በመፈለግ ጉዳይ የጌታችን ኢየሱስን ተመሳሳይ ምሳሌ መከተል አለብን።

ከዚህም የተነሣ ኢየሱስ በዕብራይስጥና በአራማይክ ቋንቋዎች ተናግሮአል አስተምሮአል፤ በነዚህ ቋንቋዎች ከብዙ ሰዎች ጋር ተነጋግሮአል። የእርሻውን፣ የመክሊቱን፣ የእርሾውን፣ የዓሳ ማጥመድን፣  የድሪሙን፣ የዘርና የዘሪውን ምሳሌ ሲናገር ሰዎች በሚረዱትና በሚገባቸው ቋንቋ ተናግሮአል። ስለ ሠርግ በሕዝቡ ባህል ምሳሌነት ተናግሮአል፤ እንደ ባህላቸው በሠርግና በልቅሶ ቦታ ተገኝቶአል።

ጌታችን ኢየሱስ፣ ሳምራዊቷን ሴት ሕይወቷን እንድታስተካክል ሲመክራትና ሲወቅሳት ወይም የአይሁድ አለቃ የነበረው ኒቆዲሞስ ከርሱ ጋር ከመነጋገሩ በፊት ከሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲወጣ አልጠየቀም። በዚያው ባሉበት የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል በፍቅር መሠከረላቸው። እኛም ኹሉንም ባሉበትና በባህላቸው መናገሩን ልንዘነጋ አይገባም።

ይህ እውነት ግን ዘወትር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላይቀጥል ይችላል፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ አረሞች ሊበቅሉ ይችላሉ፤ ልክ በሐዋርያት ሥራ 15 እንደ ተነገረው አይነት። አስቀድሞ ክርስትና በእስራኤል እና በአይሁድ እምነትና ባህል ውስጥ ተወለደ። አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ከመኾናቸው በፊት ከሌላ ባሕሎች የመጡ አዳዲስ አማኞች ወደ አይሁድ ሃይማኖትና ባህል እንዲቀየሩ በግልጥ ጠየቁ። ክርስትና የመላለሙ መኾኑ ተዘነጋና፣ የአንድ ወገንና የአንድ ሕዝብ ባህል ተከታይ ብቻ እንዲኾኑ ተፈለገ። ይህ ግን ፍጹም ስህተት እንደ ነበር በሳልና ተወዳጅ ከነበረው ከሐዋርያት ውሳኔ በሚገባ እንረዳለን።

[አይሁዳዊው]ቅዱስ ጳውሎስ አይሁዳዊ ያልሆኑ አማኞችን ወክሎ፣ መዳን የሚገኘውና የሚጠበቀው በክርስቶስ ጸጋ በማመንና በመታዘዝ እንጂ የአይሁድን ሕግና ባህል በመከተል አይደለም ብሎ ተናገረ፤ የሐዋርያት ጉባኤ በዚህ እውነት ተስማማ። “ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።” (ሐ.ሥ. 15፥28-29) በማለት።  ከዚህ የተነሳ ማንም ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ለመኾን የአይሁድን ባሕላዊ ቅርጽ መከተል የለበትም የሚለው አቋም እስከ ገላትያና ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ዘለቀ። በዚያ ታሪካዊ “አጋጣሚ” ወንጌሉ ወደ ኹሉም ባህሎች እንዲተረጐምና፣ እኔ እና እናንተ ባህላችንን “ሳንቀይር” ክርስቲያኖች እንድንኾን የባህላዊ አግባብነት መርህ ተዘረጋልን።

ዛሬ ላይ ግን ይህን መርሕ የማይከተሉ የወንጌል አገልጋይ ነን በዝተዋል፤ “ኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ” ነን የሚሉ ግን አንዳችም “ርቱዕ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርትና ልምምድ” የሌላቸው፤ ነጠላና ቀሚስ መልበስ፤ ካባና ላንቃ መጐናጸፍ፤ ጥምጣም መጠምጠምና ከበሮ ማንገት ብቻ ኦርቶዶክሳዊነት የሚመስላቸው ጥቂት አይደሉም፤ እንዲያው ወንጌል ተረድተው እዚያው ሌሎችን እንዲደርሱ ከመርዳት ማስኮብለል ጽድቅ፤ ከዚያ ማውጣት ታላቅ መንፈሳዊነት የሚመስላቸው “አጀብ ወዳዶች” ቤት ይቊጠራቸው።

እኔ ሐዳሲ ነኝ፤ ልኹንና የሕዝቤን ባህለ ትምህርት አስቀድሜ ለማወቅ ጥራለኹ፤ አለባበሱን፣ አመጋገቡን፣ አለቃቀሱን፣ ሠርግ አደጋገሱን፤ የኑሮ ዘይቤውን እረዳለታለሁ፤ በዚያው በሚኖረው ባህል ውስጥ ንፁሑን፤ ርቱዑን፤ በየትኛውም ባህል ውስጥ አልፎ አሸናፊውና ድል ነሺውን፤ ኀጢአትን የሚጠየፈውንና ከኀጢአት እስራት ነጻ የሚያወጣውን የድል ነሺውን የክርስቶስን ወንጌል እሰብከዋለሁ፤ እነግረዋለሁ። የቱም ቋንቋ፤ የትኛውም የአኗኗር ዘይቤ፤ ማናቸውም ባህል ወንጌል ለመስበክ ደንቃራ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት አሰናካይ አይኾንም።

እናም እባካችሁ፤ ሐዳሲ ነን ካልን የኢየሱስንና የደቀ መዛሙርት ሐዋርያትን ፈለግ እንከተል፤ ኦርቶዶክሳውያንን “በመጥላትና በማጥላላት፤ በማጣጣልም” ወንጌል አንድረስ። ባህለ ትምህርት አልባ ሐዳሲ ከመኾን፤ ባህለ ትምህርት የጠነቀቅን “የኹሉ ወገንተኛ፤ ለክርስቶስ ወንጌል በእውነት ቀናተኛ እንኹን”፤ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን።” እንዲል።

1 comment:

  1. ጌታ አብዝቶ ይባረከ ወንድም አቤነዘረ

    ReplyDelete