Friday, 24 July 2026

“ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል… አለች።”

 

ጽዮን በባቢሎን ምርኰ በተያዘችና ለሰባ ዓመታት ያህል በግዞት በዘገየች ጊዜ የተረሳችና የተተወች መሰላት፤ በተለይም የመቅደሱ መፍረስና ከቅድስቲቱ ምድር ሙሉ ለሙሉ መነቀላቸው ተስፋቸውን ይበልጥ አጨለመው። እግዚአብሔር ግን ሕዝቡ ተስፋ እንዲቈርጥ አይፈልግም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ታማኝ፤ ጽኑ ፍቅር፤ የማያቋርጥ ኪዳናዊ ቊርኝት ያለው፤ ጨርሶ ሊዘነጋ የማይችል ልብ አለውና። ይህን እውነት እግዚአብሔር በበደልና በኀጢአት ለወደቀችው ለጽዮን፣ በነቢዩ አንደበት በግልጥ ይናገራል፤ እንዲህ በማለት፣

“ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።” (ኢሳ. 49፥14-15)

በዘመኑ በነበረው ባህል እናት ለምትወልደው ሕፃን ጠንካራ ፍቅር፤ ጽኑ ስስት እንደ ነበራት ያሳይ ነበርና፤ በዚህ ምስያ እግዚአብሔርም ለጽዮን በሚያጽናና ቃል ይናገራል። ምርኰ ፍጻሜ አይደለም፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ምድሩ ይመልሳል። በልጅነት ወድዶአታል (ሆሴ. 11፥1)፣ በመራራትና አንጀቱ እስኪታወክ ድረስ እንደሚወድዳት ተናግሮአታል (ኤር. 31፥20)። ይህን ሁሉ ግን ጽዮን ዘንግታለች።

በርግጥ አንዳንድ እናቶች ልጆቻቸውን ችላ ሊሉ ይችላሉ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ርኅራኄ ከልጆች ወላጆች እጅግ የላቀ ነው። በእጁ ላይ እንደ ምልክት፣ ወይም በክንዱ ላይ ማኅተሙ፣ እነርሱን ሁልጊዜ እንደሚያስታውሳቸው ያሳያል። ከዚህም በላቀ መንገድ የእግዚአብሔር ፍቅር ከተፈጥሮአዊ የማኅፀን ፍቅር በላይ እጅጉን የሚልቅ ነው። በርግጥ በዚህ መንገድ የተናገረው በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ከዚህ የሚበልጥ ውድ የፍቅር መገለጫ ሌላ ስለሌለ ነው።

አዎን፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጨርሶ ሊተው አይችልም፤ ፍቅሩ ከተፈጥሮ ሕግጋት በላይና ጥበቃው በማናቸውም መንገድ ውስጥ ብናልፍም እንኳ አብሮን እንዳለ የሚያመለክት አስደናቂ መልእክት ያለው ነው። ተወዳጆች ሆይ፤ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” እንዲል፣ በእግዚአብሔርም ተስፋና ክብር ደስ ይበለን፤ ደግነቱ አይታክትምና፤ ፍቅሩ ሕያው ነውና!

“ጽዮን ግን” ሲል፣ እዚህ ያለው ቋንቋ ቅሬታ ነው፣ ​​እና በብዙ አደጋዎች፣ መከራዎች እና ፈተናዎች መካከል የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጥልቅ ስሜት ይገልጻል። ጽዮን የተረሳች ቢመስላትም እንኳ፣ እግዚአብሔር በመለኮታዊ መግቦቱ፤ በሉዓላዊ ጥበቃው አይለያትም፤ አዳኙን መሲሕ በብዙ ናፍቆት ለሚጠብቁ፣ የጽዮንን ምርኮ መመለስ በብርቱ ለሚፈልጉ፣ የመቅደሱን እንደገና መሠራትና የኢየሩሳሌምን እንደገና መታደስ ለሚጓጉ ይህ ቃል እጅግ የሚያጽናና ተስፋን የሚያበረታ ነው።

በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠው ያህዌ ኤሎሂም ዛሬም በዚህ ጠባዩ አለ፤ አልተለወጠም፤ የማይለወጥ ኪዳኑ፣ ፍጹም የኾነው አባታዊና እናታዊ ርኅራኄው ለቤተ ክርስቲያንና ለአማኞች፤ ለሚፈሩትም ኹሉ እንደ ተትረፈረፈ አለ፤ (መዝ. 103፥13)። የምናልፍበት መንገድ ምንም ይኹን ምን፣ እግዚአብሔር ከነ ጭንቃችንና መከራችን ፈጽሞ አይተውንም፤ ያስብልናል፤ ይራራልናል።

የመተው ወይም የተረስቻለሁ ስሜት፣ ጠንካራና እጅግ አደገኛ ነው። ከፍ ላለ ጭንቀትና ለድብርት ጭምር የሚያጋልጥ ነው። እግዚአብሔር ግን እንዲህ እንዲሰማን ስላልወደደ፣ አንድያ ልጁን ክርስቶስ ኢየሱስን ሰደደልን፤ ድካም ለሚያስጨንቀን “ድካማችንን ሊሸከምልን፤ ደግሞም በድካማችን ሊራራልን፤ ከምንለምነው አብልጦ መልካምን የሚያደርግልን” የታመነ ሊቀ ካህናት አለልን። እጁ አይጥልም፤ ክንዱ ዝሎ አይለቅቅም፤ ጨርሶ ሊዘነጋ የማይችልም ርሱ ብቻ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ያለ ብርቱ የመጽናናት ቃል ተናግሮናል፤

“አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ።” (ሉቃ. 12፥6-7)

1 comment: