መግቢያ ፪
የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ሰጊጎት
የሠራባቸው ቃላት
ካለፈው የቀጠለ …
ቀጥታ ወደ መጽሐፉ ምዘና
ከመሄዳችን በፊት፣ በመጽሐፉ ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከአማናዊት ኦርቶዶክሳዊት[1] እምነት ወይም
እይታ ውጪ፣ ትርጉም ስለ ተሰጣቸው ቃላት መመልከቱ እጅግ ጠቃሚ መስሎ ታይቶናል። በተለይም በመግቢያ ላይ ካለው፣ ከመዳን ትምህርት
ጋር ተያይዘው የተነገሩትን ቃላት መመልከት፣ ብዙ ሳንደክም የ“መድሎተ ጽድቅን”፣ መድሎተ ስሑትነት በሚገባ እንድናስተውል ይረዳናል።
ጸሐፊው ቃላትን በማጣመም ለራሱ ትምህርት ተጠቅሞባቸዋል። እንዲያውም በአንዳንድ የነገረ መለኮት ቃላት ላይ አንዳች ግንዛቤ የለውም
ወይም ኾን ብሎ ያምታታል።
ነገር ግን ማንም፤ ምንም
ዓይነት መጽሐፍ ቢጽፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተቃራኒና ተቃዋሚ ዐሳብን ሊጽፍ አይገባውም።[2] እንዲያውም፣
“ከወንጌል ቃል የተለዩ … በበር በኩል ያልገቡ አንዳንድ ጉሕልያዎች የሰረቁዋቸው ናቸው ብለን እንሰርዛቸዋለን እንጂ አሜን ብለን
አንቀበላቸውም”።[3]
ሌሎችን ቃላትና መጽሐፍ
ቅዱሳዊ ትርጕማቸውን በሚቀጥሉት ጊዜያት የምናቀርብ መኾኑን እየገለጥን፣ ለዛሬ በምሳሌነት፣ ጥንተ አብሶንና (Uncestral
Sin) የውርስ ኀጢአትን (original sin) ጸሐፊው የተረዳበትን መንገድ ማንሣቱ አንድ ማሳያ ነው።
ጥንተ አብሶ፦ ጥንተ አብሶ (Adam’s sin, Uncestral sin)
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ስለ አዳም ውድቀትና ውጤቱ የሚያስተምሩት ትምህርት ነው። የትምህርቱ ጅማሮ በአጭሩ፣ አዳም ኀጢአት
በመሥራቱ ምክንያት የባሕርይ ጕስቁልናና ብልሽት (fallen Nature) ገጠመው፤ ከዚህም የተነሣ የሞት አደጋ አገኘው የሚል ትምህርት
ነው። በዚህ ትምህርት ተከታዮች መሠረት፣ ሰው ኀጢአት የሚሠራው ኀጢአተኛ ኾኖ ስለ ተወለደ ሳይኾን፣ የባሕርይ ጕስቁልና ስለ ደረሰበት፣
መላለሙም ከደረሰበት ጕስቁልና የተነሣ ብልሽትና የሥርዓት ቀውስ ገጠመው ብለው ያስተምራሉ።
በአስተምህሮው መሠረት
ሞት የተጋረጠ ወይም መላውን ዓለም የገጠመ አደጋ ነው። ትምህርቱ ከጥንትም በመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያንም የነበረ መኾኑን አያሌ
አበው ይመሰክራሉ። የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ ዮሐንስ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ሊቀ ጉባኤ አበራና አቡነ መልከ ጼዴቅ እንዲህ በማለት
ይጽፋሉ፣
“ማንም ማን ኃጢአት የሌለበት
ባይኾን ኃጢአትን ለመሥራት ባሕርይ የሚለወጥ አይደለም፤ አስቀድመን እንደ ተናገርን ኃጢአት የሕሊና እንጂ የባሕርይ ናት ልትባል
አይገባም።”[4]
“የአዳም ኀጢአት ካባት
ወደ ልጅ መውረዱ አዳምን መስለው ተከትለው በሚሠሩት ብቻ ነው እንጂ በማይሠሩትና በሚነቅፉት እንደ ሄኖክ በሚጸየፉት በልጆቹ ኹሉ
አይደለም።”[5]
“‘ጥንተ አብሶ’ ይኸውም
የመጀመሪያው በደል ወይም ኃጢአት የተባለው በዘር የተላለፈውን፥ በሰው ልጆች ላይ የሚገኘውን የኃጢአት ሁኔታን የሚያመለክት ቢኾንም
የኃጢአት ውጤትና ዋጋ የኾኑት ፍዳና ሞት፥ መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ፥ እንዲሁም የሥጋ ምኞትና የዓይኝ አምሮት፥ ምድራዊ መከራና
የሰይጣ ፈተና አይለዩትም። … ስለ ኾነም የመጀመሪያው ሰው ኃጢአት ወደ ዓለም ስለ ገባ ሰዎችን ኹሉ ኃጢአተኞች አድርጓቸዋል።”[6]
“ከጥንተ አብሶ የተነሣ
ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ፤ ራሱ ሰው ከእግዚአብሔር
ይሸሽ ይርቅም ጀመረ። … ከዚህ ኹሉ በኋላ የአዳም የልጆቹም ዕድል ኀዘን መከራ ተስፋ መቁረጥ ኾነ።”[7]
አውግስጢኖስ[8]ና አንሰልም የውርስ
ኀጢአትን ሃሳብ ይዘው እስኪነሡ ድረስ፣ በጥንት ቤተ ክርስቲያን ነባሩ ትምህርት፣ የጥንተ አብሶ ትምህርት እንደ ኾነ በብዙ የነገረ
መለኮት ተማሪዎች ዘንድ ይታመናል።[9] ከእነዚህም
መካከል በጥቂት ሃሳቦች ቢለያዩም የሰሜን አፍሪካዋ ካርቴጅ ተወላጁና የነገረ መለኮት ሊቅ ተርቱሊያን(155-240 ዓመተ እግዚእ)፣
የሚላኑ ጳጳስ አምብሮስ(340-397 ዓመተ እግዚእ) እና ሌሎችም ይህን ትምህርት ይከተላሉ።
የውርስ ኀጢአት (Original
sin) - ይህ ትምህርት የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው። የትምህርቱ ጅማሮ አዳም በሠራው መሠረታዊ ኀጢአት[10] ምክንያት፣ የሰው
ልጅ ኹሉ ኀጢአተኛ ኾኖ ይወለዳል፤ ሲወለድም ጀምሮ ኀጢአተኛ ነው የሚል ነው። ይህ ትምህርት፣ አዳም በሠራው ኀጢአት መላለሙ ኀጢአተኛ
እንደ ኾነ ብቻ ያይደለ፣ ሲወለድም ኀጢአተኛ ኾኖ እንደሚወለድና በኀጢአት ርኩሰትም የተበከለ እንደ ኾነ ጭምር ያስተምራል።
ከዚህም የተነሣ፣ መሠረታዊውን
ጽድቅ ማጣት ብቻ ሳይኾን ኃጢአትን ለመሥራት ዝንባሌና ፍላጎትንም ጭምር ተሸክሞአል።[11] ለዚህ ትምህርት
መጽሐፍ ቅዱሳዊው መሠረትን ሲጠቅሱ፣ “ኃጢአት
በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” (ሮሜ 5፥12፡
18-19 የሚለውና 1ቆሮ. 15፥22፤ 2ቆሮ. 5፥21) ስለዚህም ትምህርቱ፣ ሰው የአዳምን ኀጢአት በውርስ ይቀበላል
ወይም ያገኘዋል፣ እናም በአዳም ምክንያት አዳምን ያገኘው የሞት ቅጣት መላለሙን ያገኘዋል ብሎ የሚያስተምር ትምህርት ነው።
“የኀጢአት ውርስ በተለይ
በኹለት ነገሮች ይታያል። የመጀመሪያው … የአዳም በደል ለዘሩ ኹሉ በመቈጠሩ ነውና ውጤቱ ሞት ነው። ኹለተኛው የሰው ጠባይ በኀጢአት
ተበክሏልና ከዚህ የተነሣ ኀጢአት እየሠራ ይኖራል። … ሰው ኹሉ ከአዳም የወረሰው ኀጢአታዊ ጠባይን ነው። ይህ ውስጣዊ የኀጢአት
ጠባይ የኀጢአት ኹሉ ምንጭ ነው። ብዙዎች ውርስ ኀጢአት ሰው በአዳም የሚቈጠርበትን የሰውን በደለኛነት እንደሚያካትት ያስተምራሉ።”[12]
የመድሎተ ጸሐፊ ግልጥ ስህተት
“‘ጥንተ አብሶ - original sin’ የሚለው ቃል ከጥንቱ ሲጀመር አንሥቶ
በአውግስጢኖስ የተጀመረና በአብዛኛው ምዕራባውያን የተጠቀሙበት ቃል ነው።”[13]
የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣
የመዳን ትምህርት ስህተት ከዚህ ይጀምራል፤ እርሱ እንደ ተናገረው ሳይኾን፣ የጥንተ አብሶ ትምህርት አቀራረብ (approach) የምሥራቃውያን
ሲኾን፣ የውርስ ኀጢአት ትምህርት ደግሞ የምዕራባውያን ትምህርት አቀራረብ ነው።[14] የነገረ መለኮት
ቃላትን ትክክለኛ ፍቺ ዐሳብ ሳይረዱ፣ ሌላውን ለመመዘን መቀማጠል ከግብዝነት ባለፈ ያሳፍራል። ነገረ መለኮታዊ ቃላትን አሳስተን
ከተረጐምን፣ የምናስተምረው ነገረ መለኮታዊ ትምህርትም የተሳሳተና ከእውነት ፈጽሞ አፈንጋጭ መኾኑን መዘንጋት የለብንም። በአንድ
ሌላ ስፍራ ግን ጥንተ አብሶንም፤ የውርስ ኀጢአትንም አንድ አድርጎ[ደባልቆ] ሲጠቅስ ደግሞ እንመለከተዋለን፤
“በፕሮቴስታንቶች ዘንድ
በአብዛኛው መዳን ሲሉ ግን ከኃጢአት ቅጣት ነጻ መሆንን፣ ከእስራት መፈታትን ብቻ ነው። የመዳን አስተምህሯቸው በአውግስጢኖሳዊ የቅድሚያ
ምርጫ (Predestination) እና በጥንተ በደል(አብሶ) (Original sin) አስተሳሰቦች የተቃኘና የተመሠረተ ነው።”[15]
እንዲሁም፣ የውርስን ኀጢአት
ትርጕም ተከታይ መኾኑን ሳይገልጥ፣ “መዳን”ን ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ሲተረጕም እንዲህ ይላል፤
“የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን
ትእዛዝ በማፍረሱ ምክንያት የደረሱበትን ተደራራቢ ውድቀቶች፣ ቅጣቶች፣ ከጸጋ መራቆቶችና የባሕርይ መጎሳቆሎች …”[16]
በዚህ ትርጉም ውስጥ ወደፊት
እንደምንመለከተው፣ “ቅጣት” የሚለው ቃል የውርስ ኀጢአትን ትርጉም የሚከተል ሲኾን፣ የባሕርይ መጎሳቆል የሚለው ግን ከጥንተ አብሶ
ጋር ተያይዞ የሚነገር ዐሳብ ነው። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ግን፣ ኹለቱንም በአንድነት ሰፍቶ በማቅረብ በተሳሳተ ትርጓሜ፣ የአንዱንም
ለሌላው እየሰጠ ግራ ቀኙን ሲተናኰል እንመለከተዋለን። ጸሐፊው የውርስ ኀጢአትን ትርጕም ወይም የጥንተ አብሶን ትርጉም በትክክል
አለመተርጐሙ ሳያበቃ፣ የቱን እንደሚከተል ሲናገር አንሰማውም። ይህ ኹሉ የጸሐፊውን ከፍ ያለ ግራ መጋባትና በትክክል ትምህርቱን
የመረዳት ችግር እንዳለበት ማስተዋል ይቻላል።
አንባቢ እንዲያስውል የምንሻው፣
በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ኹለቱም ምልከታዎች እንከን እንዳለባቸው ነው። የኹለቱ ትምህርቶች አቀራረብ ደግሞ፣ በየራሱ የየራሱ ሥረ ምክንያት፣
ውጤትና ትምህርታዊ መሠረትም አለው። የምሥራቅና የምዕራብ አቀራረብ ተብሎ እስኪከፈልና አንዱ ሌላውን መናፍቅና ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
ብሎ እስኪወራረፍ ድረስ ትምህርቶቹ ሲሰጡ ይስተዋላል። ዳሩ ግን የጥንተ አብሶ ተከታዮች አኹናዊ መዳንን ለመቀበል ሲቸገሩ፣ የውርስ
ኀጢአትን የሚከተሉ ደግሞ የመዳንን ሂደታዊነትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ባሕርይ ሲዘነጉ እንመለከታለን። ሰፊውን እንከኖቻቸውን
ወደ ፊት በምናነሣባቸው ስፍራዎች የምንመለከት ይኾናል።
ይቀጥላል …
[1]
ኦርቶዶክሳዊነት የአስተምህሮን ትክክለኛነት የምንጠቀምበት መኾኑን መዘንጋት አይገባም። ደኅናውን፣ ጤናማውን
መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት ለመናገር የምንጠቀመው ቃል መኾኑን መዘንጋት አይገባም።
[2]
ኅሩይ ወልደ ሥላሴ(ብላቴን)፤ ጎሐ ጽባሕ፤ 1919 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤
አሳታሚ ገጽ 24
[3]
ገብረ ሥላሴ ብርሃኑ፤ መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት፤ 1989 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አክሱም ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 147
[4]
ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ፤ ምዕ. 52 ቊ. 16 ገጽ 169
[5]
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፤ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤
ገጽ 25
[6]
አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 90
[7]
አባ መልከ ጼዴቅ(ጳጳስ)፤ ትምህርተ ክርስትና ፪ኛ መጽሐፍ፤ 1984 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት። ገጽ
30
[8]
አውግስጢኖስ (354-430 ዓመተ እግዚእ) የሰሜን አፍሪካ ተወላጅ ሲኾን የሂጶ
ሊቀ ጳጳስም ነበር። የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ምልከታ በአብዛኛው “የተቃኘው” በእርሱ ነው። አውግስጢኖስ “The
City of God, On Christian Doctrine, and Confessions” በሚለው መጽሐፉ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። በተለይም፣ “ሰው ከራሱ መልካም ነገርን ማድረግና በእግዚአብሔር ፊት ትሩፋትን
(ወሮታን) መቀበል አለመቻሉን በማስተማሩ ይታወቃል።
[9] ነገር ግን የሮም ሊቀ ጳጳሳት የነበረው አቡሊዲስና ሌሎችም ከዚህ
ትምህርት በተለየ መንገድ የውርስ ኃጢአትን ትምህርት የሚደግፍ ሃሳብን መጻፋቸውን መዘንጋትም አይገባም። “ከአዳም አንሥቶ እስከ
ሙሴ ሰዎችን በአዳም በደል አምሳል ያልበደሉ ሌሎችንም ሞት እንደ ገዛቸው ተናገረ፤ መጀመሪያ የበደለ አዳም ነው፤ አዳምም በበደለ
ጊዜ የሚመስሉትን ያን ጊዜ ወለደ።” (ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ፤ ምዕ. 42 ቊ. 9 ገጽ 135)
[10]
ዌይን ግሩደም፤ ስልታዊ ነገረ መለኮት፤ 2003
ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ኤስ አይ ኤም አሳታሚ፤ ገጽ 555-561
[11]
ሉውስ በርክኾፍ(ፕሮፌሰር)፤ የትምህርተ መለኮት ጥናት፤ 1989 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ
117
[12]
ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ 1998 ዓ.ም፤ ገጽ
64፡ 95
[13]
መድሎተ ጽድቅ፤ ገጽ 118፡ 122
[14]
ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ ገጽ 101
[15]
መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 1፤ ገጽ 109
[16]
ዝኒ ከማኹ፤ ገጽ 84
አንተ እኮ አመልካለሁ ትላለህ እንጅ በማንም ማመን እንደማታም አየንልህ አትሮንስ ያልገጨህ ዝምበል! ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል አሉ በመፅሀፍ ቅዱስ ስትመዘን ባዶነትህ ታየልህ እኮ
ReplyDeleteበመጀመሪያ ደረጃ ስለምትተቸው ነገር እንኳን እውቀት የለህም :: በደረቅ መደናቆር የመጽሀፉን ስህተት ለማስረዳት ትሞክራለህ :: መጀመሪያ ምን እያወራሁ ነው ብለህ እራስህን አጥራ we know every ተሀድሶነን ባይ reformist ይህ መጽሀፍ እንደ ሰማይ እንደሚከብዳችሁ :: አይደለም ለአቅመ ትችት ለአቅመ ውይይት ያልደረሰ ቁንጽል ሀሳብ :::
ReplyDeleteመድሎተ ጽድቅ ለመናፍቃን ምንፍቅና መልስ የተሰጠበት መፅሀፍ ነው
ReplyDeleteስለ አንተ እግዚአብሔር ይክበሪ አንተም ተባረክ በኢየሱስ ስም
ReplyDeleteMay Glory God bless you my dear brother thank you for the anointing word of God
ReplyDeleteራሳችሁ የሆነ ነገር ስለሌላችሁ በመክሰስ ላይነው ጉልበታችሁ የሚፀናው
ReplyDeleteበሚመጣው ዘመን ሥር ሰደን በሥሙ ጸንተን ስንተጋ ለሚያገኘን ጌታችንና አምላካችን ክብር ይሁን አሜን::
ReplyDeleteትግልህ ሁሉ ከሚዛን በላይ ይሆንና እየተፈጠፈጥክ አለክ ! እኔ ግርም የሚለኝ የሰዎችን ግሩም ስራ መተቸትህን ትተህ ለምን ለራስህ ታሪክ አትሰራም ? መጽሐፍ ቅዱስ እኮ ለተጠቀመበት ዓለም ዘለዓለም የሚጻፍ የሚተነተን የሚማሩትና የሚያስተምሩት ነው ። አንተ ግን ባክቴሪያ እንደጎበኘው በቆሎ ቀንጭረህ መቅረትህ ነውና ።የራስህን ስራ ስራና ታሪክህን ለተከታዮችህ አስቀምጥላቸው ባይድኑበትም ምን አልባት ከትችት ወጥተው የራሳቸውን ህይወት ማስተካከል ከቻሉ ማለቴ ነው ።
ReplyDeleteቃላት ከሚተነትኑት በላይ አፍ ኖሯቸው ያለ ማንም ሰባኪ አስፈላጊነት ብቻቸውን የሚናገሩ ሃብቶቻችን ናቸው።ጅል አትሁን
ReplyDeleteእድሜ ልክህን በኦርቶዶክስ ላይ ከምታለቅስ አንድ ቀን ለንስሀ ብታለቅስ ይሻልሃል
ReplyDeleteአቤኔዘር ብሂል እብን ሥምን መላክ ያውጣዋል ይሉሀል አቤኔዘር
ReplyDeleteየጸጋው ባለቤት ጌታ ይባረክ
ReplyDeleteጌታ ይመስገን እሄን ትምርት ስለገለፀልህ።
ReplyDeleteEterna Life = Faith X Deeds
ReplyDeleteSubject to : Faith >= 0; Deeds >= 0
---> If either Faith or Deeds are Zero (0), then the output, savation, becomes zero (multiplicative, not additive). Of course, salvation is a free gift. Whatever we do, it does not equate to what Jesus has done and will do for us. Please also note that you could lose the gift if you don't live within the framework or contraints of the gift. Do you know the devil believes in Christ? However, he does not have eternal life because he is evil in thoughts and deeds. I believe in tsega throgh Christ, but I also believe that faith without deeds is like an empty kettle. I don't want ot be an empty kettle.