(የታማኝ ትዳር ውብ ምሳሌ)
መጽሐፍ ቅዱስ፣ እጅግ
አስደናቂ ስለ ኾኑ ሴቶች ካስቀመጠልን ሕያው ምስክር አንዷ አቢግያ ናት፤ እንዲህም የተመሰከረላት፣ “የሴቲቱም
አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፤” (1ሳሙ. 25፥3)። በተቃራኒው አቢግያ የስሙ ትርጓሜ “ጅል” ተብሎ ለሚጠራው
ለናባል ሚስቱ ነበረች፤ እርሱ በምግባሩ “ባለጌ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፤ ከካሌብም ወገን የኾነና
… ምናምንቴና ባለጠጋም ነበረ” (ቊ. 3፡ 25)። ሰውየው ባለጌ፣ ግብረ ክፉ፣ ካሌብ የስሙ ትርጉም “ውሻ” እንደ ኾነ፣ የውሻ
ጠባይ ያለው ሰው ነበረ፤ ከሚስቱ ፍጹም ተቃራኒ ሰው!
በዚያ ዘመን ዳዊት፣
ንጉሥ ሳኦል ስላሳደደው በምድረ በዳ ነበረ፤ በዚያ በሚኖርበት ምድረ በዳ ዳዊት የናባልን እረኞች ይረዳ፣ ብዙ ጊዜም ሃብቱን ከዘረፋ
ታድጎለት ነበር (25፥7-8፡ 14-17)። “ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ፦ ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ” (ቊ. 4)፤ እናም
በጎች ሲሸለቱ ብዙ ድግስ ስለሚኖር ዳዊት፣ ናባል በምግብ ይረዳው ዘንድ፣ “በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥
ስጥ።” (ቊ. 8) በማለት ለመነው፤ የናባል ምላሽ ግን እጅግ የምናምንቴና የብልግና ንግግር ነበር። ዳዊትም በናባል ቤት ያሉትን
ወንዶች ሊያጠፋ ሰይፉን ታጥቆ ተነሣ።
አቢግያ ታላቋ አስተዋይ!
አንዱ የናባል
ሎሌ ግን፣ ዳዊት እንደ አጥር ኾኖ የጠበቃቸውን የደግነቱን ሥራና ለደግነቱ ናባል የመለሰውን ምናምንቴ መልስ፣ ለአቢግያ ፈጥኖ ነገራት።
አቢግያም ወዲያው ውሳኔ ወሰነች፤ ዳዊትን ማስቆም እንዳለባት አሰበች፤ ስለዚህም ለአንድ ንጉሥ የሚገባውን ስጦታና ክብር በመስጠት፣
ዳዊትን ፊት ለፊት በመሄድ ደም ሳያፈስ ከለከለችው። ናባልም አልተገደለም፤ ዳዊትም ደም አላፈሰሰም። አቢግያ፣ ባልዋ ናባል በዚያ
ሌሊት ከግብዣው የተነሣ እጅግ ሰክሮ ነበርና ያደረገችውን አልነገረችውም፤ በነጋ ጊዜ ግን ስትነግረው፣ “ልቡም በውስጡ ሞተ፥ እንደ
ድንጋይም ሆነ፤” ተቀስፎም ሞተ፤ (ቊ. 37-38)።
ናባል በእግዚአብሔር
ተቀስፎ መሞቱን ዳዊት ሲሰማ፣ እግዚአብሔር እንደ ተበቀለለት አስተዋለ፤ ሴቲቱም እጁን ከደም እንደ ጠበቀችው ጭምር።
አቢግያ፦
·
በጥበብዋ ዳዊት በግል ቂም ተነሳስቶ ሥልጣኑን በመጠቀም፣ ሰውን እንዳይገድል
አደረገችው፣ በዚህም እግዚአብሔር ለዳዊት ተበቀቀለት፤ አቢግያ ለእግዚአብሔር ፈንታ ሰጠች፣
·
አቢግያ፣ “የእግዚአብሔርን
ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራል” (ቊ. 28) በማለትዋ፣ እግዚአብሔር ለዳዊት የጸና መንግሥት
እንደሚሰጠው አመነች። ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው ደምን እንዳያፈስ ተከላከለችለት።
·
ናባል ክፉ መኾኑን ብታውቅም፣ ነገር ግን ምንም ያህል
ክፉና ባለጌ ቢኾንም፣ በዳዊት እጅ እንዲሞት አልወደደችም፤ በርግጥ ክፉዎችን የሚበቀልና የሚፈርድባቸው አምላክ እንዳለ ታምን ነበርና።
·
አቢግያ የስሟ ትርጓሜ “የዘላለም ክብር፣ የዘላለም ደስታ”
ማለት ነው፤ ለዳዊትና ለእግዚአብሔር ደስታ ነበረች፤ አንዷ ሴት በቤትዋ ታማኝና ለትዳርዋ ቅድስት ስለ ነበረች፣ ቤትዋን ብቻ ሳይኾን
አገርንም፣ የመሲሑንም ምሳሌ ዳዊትን ታደገች፡፡ ሴቶች በትዳራቸውና በቤታቸው የሚሠሩት የትኛውም ሥራ ቤተ ክርስቲያንን አገርን መታደግ
ይችላል፤ እንዲህ ዓይነት ሴቶች ዛሬ አሉን? ጌታ ሆይ እርዳን፤ አሜን፡፡
ደግሜ ልበል፤ ዛሬስ?
እንደ ቤተ ክርስቲያንም፤
እንደ አገርም ያጣነው አቢግያዊ ልብ ያላቸውን ሰዎች ነው፤ ኹለቱም ቤት እንዳይበደሉ የሚጥሩ ሚዛናዊ ልብ ያላቸውን ሰዎች። አማኞች
ጭምር ሚዛን ስተው፣ ለእግዚአብሔር ከማድላት ይልቅ ለቡድንና ለማኅበር፣ ለፓርቲና ለፖለቲካ ባደሉበት በዚህ ዘመን፣ እንደ አቢግያ
ያሉ እናቶችና እህቶች፤ አባቶችና ወንድሞች ያስፈልጉናል። ኹለት ቤት የሚያድኑ፣ የእግዚአብሔርን ፈንታና ብድራት የሚጠብቁ፣ አስተዋይና
ጥበበኛ የኾኑ።
ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ አንተ
የቤተ ክርስቲያን ራስ ነህና እባክህን እንዲህ ያሉ ተወዳጅ ልቦችን በምድራችን ላይ አብዛ፤ አሜን።
May the SPIRIT be your guide and strength for days to come!!!!!!
ReplyDeleteአቦ ይመችህ! ተባረክ
ReplyDeleteየሰማይ:አምላክ:ይባርክህ:በመንፈሱ:የቃሉን:አብርሆት:ያበዛልህ:አምላክ:ይባረክ::
ReplyDeleteNice Exegesis. May God bless you.
ReplyDeleteI love this kind of preaching you know why ? Bcoz it's Gospel preaching not prosperity
ReplyDeleteምን አይነት መባረክ ነው
ReplyDelete