Sunday, 19 June 2016

ጰራቅሊጦስ - ሌላ አጽናኛችን


Please read in PDF

     “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” (ዮሐ.14፥15-16)
     መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጆች የሚሰጥ የአብ ውብና ድንቅ ስጦታ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመርያ ጊዜ የምንመለከትበት ክፍል ይህ ከላይ ያየነው ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የመሰጠቱ ተስፋ ከኢየሱስ መሔድ ወይም ማረግ በኋላና እርሱም በዚያ ሆኖ በሚለምነው ልመና እንደሆነ፥ “እኔም አብን እለምናለሁ ... ” የሚለውን የጌታ ቃል አብነት በማድረግ ቅዱስ ያሬድ በድጓው፥ “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የእኔ ስለሆኑት ምሕረትን ወደምለምንበት ወደአባቴ ወደሰማይ ዐርጋለሁ አላቸው” በማለት በገጽ.113 ሲያሰፍር፥ እንዲሁም “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደአባቴ ዐርጋለሁ ስለእናንተ እለምነዋለሁ አላቸው” (ድጓ ገጽ 291) በማለት በግልጥ ይደግመዋል፡፡

    በእርግጥም ጌታችን ራሱ፥ “... እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” (ዮሐ.16፥7) በማለቱ ያለእርሱ መሄድ መንፈስ ቅዱስ እንደማይመጣ ተናግሯል፡፡ እንደተናገረውም በዓለ ሃምሳን ለማክበር ከአለሙ ሁሉ መጥተው በተሰበሰቡት አይሁድ ፊት ለታዘዙትና ትእዛዘቱን ጠብቀው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስን በመሙላትና ልሳንን በማናገር አረጋግጧል (ሐዋ.2፥1-4)፡፡
    በእግዚአብሔር ማመናችንን የምንገልጠው በመታዘዝ እንደሆነው ሁሉ፥ እርሱን መውደዳችንና ማፍቀራችንን የምንገልጠውም በመታዘዝና የተናገረንን ትእዛዛቱን ስንጠብቅ ነው፡፡ ጌታ የሚለምንላቸው ለእርሱ እውነተኛና ፍጹም የጠበቀ ፍቅር ላላቸውና ለሚታዘዙት ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እወድሃለሁ ማለት ቀላልና የማያደክም ሊሆን ይችላል ፤ ነገር ግን መውደዳችንን በአንደበታችን ሳይሆን ፍጹም በሆነ ሥራ ልንገልጠው ይገባናል፡፡ ቅዱስ ቃሉም፦ “እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” (1ዮሐ.5፥2-3) ይላልና፡፡
     ክርስቶስን የምንወደውና የምንታዘዘው በፈቃዳችን ወድደን ነው፡፡ አስተውሉ! እርሱን መውደድና ለእርሱ መታዘዝ ምንም የማይለያዩ ሁነታት ናቸው፡፡ እጅግ የምንወደውን ሰው እንኳ ቃሎቹን እንዴት አክብረን እንደምንሰማ አስለውሉ፡፡ ጌታ ኢየሱስን ደግሞ እጅግ እንወድደዋለን ካልን፥ ቃሎቹንና ትእእዛቱን ሁሉ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በጸጥታ ወደን ልንታዘዛቸው ይገባናል፡፡ ክርስቶስን አልታዘዝነውም ማለት ፈጽሞ አንወደውም ማለት ነው፡፡ በሌላ ንግግር መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ተገልጦ መልካሙን ሥራ አልሠራም ማለት፥ ክርስቶስን ያልታዘዝንበት አንድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ምናልባትም በሕይወታችን የልማድ ኃጢአት ወይም ሌላም ነገር ኖሮ ከሆነ ራሳችንን እንደቃሉ በትክክል ማየትና ንስሐ በመግባት በደሙ ልንነጻና ልንቆም ይገባናል፡፡
   “ብትወዱኝ ትእዛዜን ብትጠብቁ” ያለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እርሱን ወድደው ዘወትር [ዕለት ዕለት] ለሚታዘዙትና እሺ በእጄ ብለው ወደፈቃዱ ለሚያዘነብሉ ሁሉ፥ “እኔም አብን እለምናለሁ” በሚለው ቃል ኪዳኑ መሠረት፥ ለሚወዳቸውና ለሚወዱት ልጆቹ ይለምንላቸዋል፡፡ የሚለምንላቸውም እግዚአብሔር አብ ሌላ አጽናኝ እንዲሰጣቸው[ሰጠን] ነው፡፡
    ሌላ አጽናኝጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን “ሌላ አጽናኝ” በማለት ይጠራዋል፡፡ ይኸውም ሥላሴ የተለያዩ አካላት ያላቸው መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑም ባሻገር፥ ሌላ አጽናኝ የተባለው እርሱ ራሱ ሳይሆን፥ ከኢየሱስ ሌላ መሆኑን የሚያመለክት ነው ፤ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ይህን የተናገረው፦
1.     መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ሥራ የሚያስቀጥል መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ በአገልግሎት ደረጃ መንፈስ ቅዱስና ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መሞላት የምንችለው በክርስቶስ የሆነልንን ቤዛነት ማለትም፥ በመስቀሉ የተደረገልንን የደም መፍሰስና ከሙታን መካከል መነሣቱን ፍጹም ያመንን እንደሆንን ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን በቤዛነቱ አምነን ስንቀበለው መንፈስ ቅዱስንም እንቀበላለን ማለት ነው፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ አካላት ያላቸው አንድ አምላክ ቢሆኑም ሁለቱም አጽናኝ ናቸው ፤ ወይም መንፈስ ቅዱስ እንደክርስቶስ ሌላ አጽናኝ ነው፡፡
    መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ክርስቶስን ለሚወዱትና እንደፈቃዱም ለትእዛዛቱ ለሚታዘዙት የትእዛዝ ልጆቹ ብቻ ነው፡፡ ለኢየሱስ ትእዛዛት አለመታዘዝና ለፈቃዱም አለመኖር  ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግልጥ ተቃውሞ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የሚሠራውና የሚያከናውነው ጌታ ኢየሱስ በዚህ ምድር የጀመረውንና የፈጸመውን ሥራ ማስቀጠልና ማጽናት ፤ ማተምም ነውና፡፡  እርሱ ሌላ አጽናኝ ቢባልም እንደኢየሱስ የዚያው ዓይነት ሆኖ ሌላ የተባለ እንጂ እንግዳና ኢየሱስን የማያውቀው አይደለም፡፡
2.    ረዳትና አጽናኝ ስለሚሆነን፦ የመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በረዳትነቱም ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር በነበረ ጊዜ ደካሞችን ፣ ድውያንን ፣ የተገለሉትን ፣ ኃጢአተኞችን ... ይራዳ ፣ ያቀርብ ፣ ያጽናና ፣ እንባቸውን ያብስ እንደነበር እንዲሁ፥ መንፈስ ቅዱስም ኢየሱስ ወደሰማያት ከሄደ በኋላ እኛን ሊራዳ ፣ ሊያቀርብ ፣ ሊያጽናና ፣ እንባችንን ሊያብስ ፣ ድካማችንን ሊያግዘን ፣ አብሮንም በውስጣችን ሆኖ ሊቃትት ዘወትር አለ፡፡
     ጌታ ኢየሱስ በሥጋው ወራት አብሮን ኖሮ አሁን ከእኛ በመለየቱ አናዝንም ፤ ምክንያቱም ሌላው አጽናኝ ልክ እንደኢየሱስ ደም ከማፍሰስ በቀር በሚያስፈልገን ሁሉ ይራዳናልና፡፡ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድና ትእዛዛት የምንታዘዝ ነንና በውስጣችን አለ ፤ አድሮብናልም (ዮሐ.14፥17 ፤ 1ቆሮ.3፥16 ፤ 6፥19 ፤ 2ጢሞ.1፥14) ከእኛ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ ደስታችን ፣ አገልግሎታችን ብዙዎችን ቢማርክ ፣ ዕውቀታችን ፣ የተትረፈረፈው ሰላማችን ፣ አዲሱ የክርስቶስ ሕይወታችን ... ሁሉም ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የተነሣ እንጂ በእኛ ብቃት አይደለም፡፡ ክብር ይግባው፡፡ አሜን፡፡
   በተለይም ክርስቶስ ከዚህ ክፉ ከሆነው ዓለም ስላዳነን (ገላ.1፥4) ውጊያችንና ትግላችን ከሰይጣን ፣ ከሥጋ መንፈስና ከዚህ ዓለም ጋር እንደመሆኑ መጠን ትግላችንና ውጊያችን ረቂቅና ለአይን የማይታይ ነው፡፡ ስለዚህም የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መፈለጋችን የማንክደው እውነት ነው፡፡ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ እኛን ማስተማሩ ፣ ክርስቶስን ያስተማረውን ማስታወሱ ፣ ስለክርስቶስ ለእኛ መመስከሩና ወደእውነት ሁሉ እኛን መምራቱ እንዳለ ሆኖ፥ ደግሞም ከማይታዩት፥ “ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር” (ኤፌ.6፥12) በምናደርገው ፍልሚያና ውጊያ ውስጥ ሁሉ ድፍረትን ፣ መዋጋትንና ድል መንሣትንም በመስጠት ፍጹም ለእጆቻችን ሰልፍን በማስተማርና ድልን በማልበስ ይረዳናል፡፡
3.    “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ” (ዮሐ.14፥18) እንደሚለው በመከራ ፣ በሃዘን ፣ በጭንቀት ሰዓት ሁሉ መንፈስ ቅዱስ የማይተውና ዘወትርም አብሮን የሚኖር ነው፡፡ ከአባት ፤ ከእናት ማጽናናት ይልቅ የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት እጅጉን የሚቀርብና የሚያሳርፍ ነው፡፡ ወደእኛ ሲመጣም ፍጹም የቤተሰብ ስሜትና አንድነት ባለው መንፈስ ነው፡፡ በምድራዊው ኑሮ ሃዘን ሲገጥመን ብዙ ወዳጆች መጥተው እንደሚያጽናኑን፥ ከዚህ በሚልቅ ክርስቶስን በመውደድ ለታዘዝነው ታዛዥ ልጆቹ፦ “ ... ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ” (ዮሐ.14፥18) በሚለው ኪዳኑ ልጁም ፣ አባቱም ከቅዱስ መንፈስ ጋር መጥተው እኛን ያጽናኑናል ፤ በመንገዳችንም ሁሉ አብረውን አሉ፡፡ 
    መንፈስ ቅዱስ እጅግ በበረታ ጭንቀትና መከራ ውስጥ ሆነን እንኳ ያረጋጋናል፡፡ እንዲያውም ሌላ አጽናኝና የሚያረጋጋ አካል እስከማያስፈልግ ድረስ ያጽናናናል፡፡ በየትኛውም የመከራ ማዕበል ውስጥ ብናልፍም፥ በመከራው ላይ የበላይ የሆነ አጽናኝና አረጋጊ ጻድቅ አባት አለን፡፡ ለዚህም ነው የእውነተኛ ክርስቲያን ሥነ ልቦና ከብርቱ አጽናኙ የተነሳ ሁሌም የረጋና በጸጥታ የተመላ የሚሆነው፡፡

   አቤቱ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! በመጽናናትህ ስለጐበኘኸን እናመሰግንሃለን፡፡ አሜን፡፡

1 comment: