Friday, 6 February 2026

ነነዌ ተቀጥታለች!

 


የዮናስን የትንቢት መጽሐፍ ስናነብ፣ የነነዌ ኀጢአት ይቅር መባሉን እናውቃለን። የናሆምን የትንቢት መጽሐፍ ስናነብ ደግሞ የነነዌ የታወቁ ኀጢአቶች ምን፤ ምን እንደ ኾኑ እናስተውላለን። ነቢዩ ናሆም የነነዌ ኀጢአት በዝርዝር ሲገልጥ፣ በእግዚአብሔር ላይ ማሴር ወይም በክፉ ማሰብ (1፥9፡ 11)፣ ጣዖትን ማምለክ በተለይም ምናሴ የጣዖትን አምልኮ ከነርሱ ወርሶአል (1፥14)፣ የተለያዩ የሰዎችን አካላት በመቁረጥ ጭካኔ የተሞላባት ቅጣትን መፈጸም(3፥19)፣ ውሸት፣ ንጥቂያ ወይም ቅሚያ (3፥1)፣ አስማት፣ ጥንቆላና ዝሙት[ግልሙትና] (3፥4) የታወቀችበት ኀጢአቷ ነበር። ይህ ኹሉ ሲኾን የአሶርዋ ነነዌ ምንም ነገር እንደማያገኛት አስባ ተዘልላና ኮርታ ተቀምጣ ነበር።

ምክንያቱም ኀጢአቷን ያለ ከልካይ ትፈጽማለች፤ የማይታዘዟትን ሥልጣንና ገንዘብ በእጇ ነውና አይቀጡ ቅጣት ትቀጣለች፤ ያለ ከልካይ የትኛውንም የዝሙትና የግልሙትና ኀጢአትን በመፈጸም ምድርን ታረክሳለች። የእግዚአብሔር ፍትሐዊ ወፍጮ በዝግታና እጅግ በቀስታ ቢፈጭም፣ አልሞና አድቅቆ መፍጨቱን ግን አያቆምም፤ ፍጡራን ብዙ ጊዜ ይህን ይዘነጋሉ። የእግዚአብሔር ፍትሕ በምድር ላይ የማይሠራ የሚመስላቸው ብዙ ናቸው። ዛሬ በምድራችን ላይ አገራችንን ጨምሮ በኹሉም ስፍራ ጦርነት፥ ድኅነት፣ ፍትሕ-አልበኝነትና ክፋት አለ። ኃጢአተኞች እንዲሳካላቸውና ኑሮ እንዲሰምርላቸው ጉቦን፥ ዛቻንና ሰውን ማሠቃየትን ይጠቀማሉ። ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግጋት በግልጽ ከሚጥሱ ሰዎች ይልቅ ጻድቃን የበለጠ ሥቃይ የሚቀበሉ ይመስላሉ። እንዲህ ባሉ ጊዜያት እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ በመኾኑ፥ እያንዳንዱን ሰው ወይም አገር እንደየሥራው ይቀጣዋል ወይም ይሸልመዋል የሚለውን አሳብ የማጣጣል ፈተና ያጋጥመናል።

ከሰሞኑ አንድ ጄፍሪ ኤፒስተን የተባለ ግሐሰብ የታወቀ የዝሙትና የግልሙትና ተግባሩ በየሚዲያው ተጠቅሶአል። ሰውየው በዘመኑ በካበተ ሃብቱና ከታወቁ ታላላቅ የዓለም ባለሥልጣናት ጋር ባለው ቅርርቡ አይነኬ ኾኖ አካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ለዝሙትና ለግልሙትና የሚማግድ፤ ይህን ተግባሩንም በመረጃ እየቀዳ ባለሥልጣናትንና "ታዋቂ" ሰዎችን በማስፈራራት ባሪያው አድርጎ የሚያኖር ሰው ነው። ሰውየውን ማንም ለመክሰስ አይሞክርም፤ ምናልባት ለይስሙላ በአንድ ወቅት ተከስሶ 13 ወራት ቢፈረድበትም፣ ሥራውን በ"ነጻነት" ከማከናወን አልታቀበም ነበር። ቢፈረድበትም የማይታሠር አምባገነን ግለሰብ ነበር። ነገሩን እምብዛም ማራቅ ሳይገባ፣ በአገራችንም ተመሳሳይ ግለሰቦች አሉ። ከመንደር እስከ ዩኒቨርስቲ ሕፃናትንና አካለ መጠን ያልደረሱ ወጣቶችን ለባለሥልጣናትና ለ"ታወቁ" ሰዎች እንደ ዕርድ እንሰሳ የሚያቀርቡ ጥቂት ግለሰቦች አይደሉም።

የአሦርዋ ነነዌም የታወቀችው በጭካኔዋና ሌሎች ሕዝቦችን በቁጥጥር ሥር በምታውልበት የማስፈራሪያ ኃይሏ ነበር። በተጨማሪም በነነዌ ላይ ለማመፅ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ፍጻሜው መራራ ቅጣትና የማይገመት መአት ነበር። ኤፒስተንም ቢኾን በጊዜው ገናናና አይነኬ ቢመስልም፣ በፍጻሜው ግን ምንም ራሱንም እንዳያጠፋ ኾነ ሌሎች እንዳይገድሉት በግራ በቀኝ ካሜራ ቢደገንበትም በራሱ አልያም በሌሎች ከመገደል አላመለጠም፤ ነውረኛ ሰው በነውረኞች ጭካኔ መውደቁ አይቀርምና።

"ኀጢአት ከኀጢአተኛው መውጣቱ"፣ በደልም በደለኛውን ማዋረዱ አይቀርም። እግዚአብሔር ግን ምሕረትን ይሰጣል፤ ይህ ምሕረት ተሰጥቶአትና ይቅር ተብላ ነገር የእግዚአብሔርን ምሕረት ላቃለለች ነነዌ እንዴት ያለ ጽኑ ፍርድን ያመጣ ይኾን?! ምክንያቱም የናሆም ትንቢት እየተነገረ ያለው፣ ከዮናስ ዘመን አንድ መቶ ዓመታት በኋላ ነውና። ምሕረት ካገኘ በኋላ ወደ ኀጢአት የሚመለስ ሰው፤ እጅግ ክፉና ዓመጸኛ ነው የሚኾነው።

በእውነት መገሰጽ፤ ትክክለኛ ፍሬ የበዛበት ንስሐን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያብዛ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment