Sunday, 1 February 2026

እንቅልፋሙ ዮናስ!

 Please read in PDF

ወደ አሕዛባዊቷ ነነዌ የተላከው ዮናስ፣ ሕጋዊ ታሪፍ ከፍሎ ወደ ተርሴስ ኮበለለ። ቀለል አድርገን ካየነው፣ ዮናስ ሕጋዊ ክፍያ ፈጽሞ መሄዱ ችግር ላይኖርበት ይችላል፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ አላደረሰውም። እንዲያውም የተሳሳተን ነገር በትክክለኛው መንገድ ለመሥራት መጣር ነገሩን ትክክል ካለማድረጉ ባሻገር አደገኛ ያለመታዘዝ ምልክት ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድና ትእዛዝ የሚቃረን ማናቸውም ነገር እጅግ ትክክል በተባለ መንገድ ቢደረግም ኀጢአት ነው። ይህ የዮናስ አደገኛ መንገድ ነው።





እግዚአብሔርን እግዚአብሔር ደስ በማይሰኝበት መንገድ ለመታዘዝ መሞከር እንዴት ያለ ምስኪንነት ነው?!

ዮናስ እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ሌላኛው መብቱንም ተጠቅሞአል። በመርከቡ ውስጠኛው ክፍል ገብቶ ተኝቶአል። ይህ ልክ የለሽ ቸለተኛነቱን ወይም ግድ የለሽነቱን የሚያመለክት ነው። በዚያ አሕዛብ እንኳ ተጨንቀው ወደ አማልክቶቻቸው በሚጮኹበት ሰዓት ዮናስ ተኝቶአል። እግዚአብሔር እንዳያየው፤ ሰውም እንዳይረብሸው ይመስላል። መርከቡን እንደ ቤተክርስቲያን ብንወስደው፣ "የተኙ" አማኞች ልክ እንደ ዮናስና ድሪሙ በቤት ወይም በቤተክርስቲያን ውስጥ መተኛትና መደበቅ ደስ ያሰኛቸዋል። በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ያሉ ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን  ከእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ከኾነው ነገር ኹሉ ርቀዋልና አይታዘዙም።

በመርከቡ ውስጥ አሕዛብ እንኳ ለጸሎት ይጮኻሉ፤ ዮናስ ግን ተኝቷል። ዝንጉ አማኝ በጸሎት ሰዓት የተኛ ነው። ጸሎት ልመና ከኾነ፣ ዮናስ ከተጨነቁት ጋር በአብሮነት መለመን ነበረበት፤ ግን አላደረገም። ጸሎት ምልጃ ከኾነ ዮናስ መማለድ ነበረበት፤ ግን ትዝም አላለውም። ጸሎት "አድነን" የሚል የመቃተት ቃል ከኾነ ዮናስ ያን ማድረግ ነበረበት ግን አልቃተተም። ደግሞም በዙሪያው ላለው ችግር አለመጸለዩ ብቻ አይደለም፤ ችግር መኖሩንም እንኳ አያውቅም።

ዝንጉና እንቅልፋም አማኝ በዙሪያው ያለውን ችግር አያውቅም ወይም አያስተውልም፤ ብሎም ለችግሮቹ አይጸልይም። የመስጠም አደጋና ሕይወቱን ሊያጣ የሚችልበት ኹኔታ መፈጠሩን እንኳ አያስተውልም። እንዴት አደገኛ ነገር ነው!

እጅግ አሳዛኙ ነገር፣ አሕዛብ ከርሱ እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ እንኳ ዮናስ እንቅልፍ ላይ ነበር። ያላመኑ ሰዎች የኛን የአማኞች ምስክርነትና እርዳታ እየፈለጉ እኛ ከተኛንና በዝንጋኤ ውስጥ ከኾንን እንዴት ያለ ምስኪን ነን?! መጽሐፍ እንዲህ ላለው አገልጋይና አማኝ እንዲህ ይላል፦

“ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።” (ኤፌ. 5፥14)፤ እናም እንቅልፋሙ ሰው ከኀጢአቱ የተነሣ ሙት ሊኾን ይችላል። ለዚህም መጽሐፍ፦ "ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አኹን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።" (ሮሜ 13፥11-12) ይለናል።

ንቁ!


No comments:

Post a Comment