ከሰሞኑ የአሜሪካን ምድር የናጠ አንድ በአብላጫው “የዝሙት መረጃን” ያጨቀ፣ ከአንድ ግለሰብ የመረጃ ቋት “አፈትልኮ” ወጥቶአል፤ መረጃው ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ፤ ከአውሮፓ እስከ ኤስያ የሚገኙ የአገር መሪዎችን፣ “የታወቁ ሰዎችን”፣ ለምድር የከበዱ የሚባሉትን ኹሉ በአንድም በሌላም መንገድ የሚነካካ ነው። እጅግ አሳዛኙ ተግባር፣ ለነዚህ ሰዎች የዝሙት ማገዶነት የሚቀርቡት ሴቶች ኹሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ “አካለ መጠን” ያልደረሱና ሕጻናነት ናቸው፤ ነገሩ አባት ከገዛ ልጁ ወይም አያት ከሚኾናት ሕፃን ጋር የ”መተኛት” ያህል ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ለወንጌል ምስክርነት በመጣበት
ወቅት፣ የቆሮንቶሳዊነት አንዱ መገለጫ የነበረው “አመንዝራነት” ነበር ብንል ግነት የለበትም፤ በዚያን ወቅት በቆሮንቶስ ከተማ በነበረው
ቤተ ጣዖት በአንድ ቀን ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ለጣዖቱ የዝሙትን መሥዋዕት ማቅረብ የተለመደ ተግባር ነውና። ለዚህም ተግባር
ሴቶቹ ራሳቸውን በመገላለጥ፣ የአያሌ ወንዶችን ትኵረት በመሳብ ለዝሙት ያጠምዳሉ፤ በዝሙት ይጥላሉ፤ ያረክሳሉም፤ ይረክሳሉም።
ጌታ እግዚአብሔር እንደ ማኅበረሰብ ለቀደመው ኪዳን ሕዝብም
“አታመንዝር” የሚለውን ሕግ ሲሰጥ፣ ዝሙት ጤና አቃዋሽ፤ ሥጋን አፍራሽ፤ ነፍስን አርካሽ፤ መንፈስን አጠልሽ መኾኑን አውቆ ነበር።
ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በተደጋጋሚ የወደቀበት ኀጢአትና ነውር ቢኖር ዝሙት ወይም አመንዝራነት ነበር። በዝሙት የወደቀ ማኅበረ
ሰብ ርስ በርሱ እንደሚተላለቅ የመሳ. 19 በአንድ ሌዋዊ ሚስት ላይ ለተፈጸመው ዝሙት፣ የብንያምን ነገድ ለማጥፋት የደረሰ የርስ
በርስ ፍጅትን መመልከት በቂ ነው፤ እስራኤል በበለዓም እርግማን ሳይሸነፍ፣ የተዋረደውና የተንኮታኮተው ግን በሰጢም ማመንዘሩ እንደ
ኾነ ዘኊ. 25 ይመሰክርልናል።
እንደ ግለሰብም ዳዊትን የሚያህል ብርቱ አገልጋይ፤ ሰለሞንን
መሳይ አስተዋይና ጥበበኛ፣ ሶምሶንን የመሰለ ምርጥ ናዝራዊ፤ “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ
ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር” የተባለለት ሎጥና ሌሎችም በዝሙት ወድቀዋል። በርግጥ ስለ ዝሙት፣ “የጋለሞታ ዋጋ እስከ
አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች። በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም
ላይ የሚሄድ፥ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም።” (ምሳ.
6፥26-29) ተብሎ በግልጥ ተነግሮአል።
በዘመናችንና በአገራችንም ዝሙት የጌጥ ያህል ተወድዶአል፤
አመንዝራነት የማር ያህል ጣፍጦአል፤ በዝሙት ሰበብ ትዳር አያሌ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበታል፤ ብዙ ስብራትና ንቃቃት በትውልዳችን ውስጥ
የሚታየው ዝሙት ከሚባል ኀጢአት ከሚመነጭ ምንጭ ነው። የመጠጥ ማስታወቂያ የተከለከሉ የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎች፣ “አመንዝራነትን”
ግን ከነግሳንግሱ ወደ ሰው አእምሮ ይደፋሉ ብሎም ያራግፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዝሙት የሰው ሕይወት ወጥመድ መኾኑን ነግሮናል!
ስለዚህም መፍትሔውን ሲያስቀምጥልን፣ በአጭር ቃል ከዝሙት
ከመሸሽ በቀር ሌላ መፍትሔ እንደሌለ በመንገር ነው፤ ማንም ቆሞ ታግሎ ዝሙትን ያሸነፈ የለም፤ እንደ ዮሴፍ ሮጦ የሸሸ ግን ነፍሱንም፤
ሥጋውም ከዕድፈት አስመልጦአል፤ ወጣቶችና ጐልማሶች ለዝሙት ወለል አድርገው በር ከሚከፍቱ ወንድና ሴት ጋለሞቶች ብቻ ሳይኾን፣ በእጃችሁ
ካለው “smart” ስልኮች ሽሹ፤ ነፍሳችሁን በጽድቅና በቅድስና ሸልሙ፤ እንዲህ ያለ ወሬ ከሚወድዱ፣ አመንዝራነትን እንደ መወደድና
የፍቅር መለኪያ አድርገው ከሚያስቡ “አለሌዎች” ራቁ! ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ብዙ ጊዜ በማሳለፍ ራስን የመግዛት የጽድቅ ፍሬ አብዙ
እንጂ ቆማችሁ ከዝሙት ጋር አትታገሉ!

No comments:
Post a Comment