በሥጋችን ምግብና ውኃ ስናጣ መራብና መጠማት የጤነኝነት ምልክት ነው፤ እኒህን ስናጣቸው አለመራብና አለመጠማት ጤነኝነት አይደለም። ራብና ጥም የሌለው ሰው፣ በጽኑ ደዌ ወይም ለሞት በሚያበቃ ሕመም ለመያዙ ምክንያት ሊኾን ይችላል። ስለዚህ ራብና ጥም ለሰውነታችን አንዳች ረብ ያለው ነገር እንደሚያስፈልገን ኹነኛ ምልክት ነው።
ፊተኛው
አዳም በመብል መታለሉን እንመለከታለን፤ የሰይጣንን ምክር ሰምቶ በመታለልና የእግዚአብሔርን ክብር በማጉደል ለራሱ ጥቅም ሲል
ያልታዘዘውን ምግብ ለራሱ በላ። የኪዳኑ ሕዝብ እስራኤልም በእግዚአብሔር መግቦት ወደ ምድረበዳ ቢመራም፣ በእግዚአብሔር መግቦት
ላይ ከመተማመን ይልቅ በምግብና መጠጥ ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረመ።
ራብና
መጠማት የጤናማነት ምልክት ነው ማለት፣ መመገብና መጥገብ ደግሞ ዘወትር የጤነኝነትና የመልካምነት ምልክት አይደለም ማለታችንም ነው።
ፈታኙ ሔዋንን፣ “በውኑ
እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” ብሎ የተናገረውን የስህተት አሳች ጥያቄ መጠየቁን እንዳንዘነጋ። ፈታኝ እንዲበሉ ሲፈትን፣ ጌታ እግዚአብሔር ግን
እንዳይበሉ አዝዞአቸው ነበር። መብላት፤ አለመብላቱ ትርጉም የሚሰጠው፣ የእግዚአብሔር ቃል ከመጠበቅና ካለመጠበቅ ወይም ለሰይጣን
ቃል ከመታዘዝና ካለመታዘዙ ላይ ነው። ሴቲቱ የአሳቹን ቃል ሰምታ ብትበላ፣ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝዋን ታሳያለች፤ ባትበላ ግን
እግዚአብሔርን አክብራ ትከብራለች።
እስራኤልም
የአምላክን ቃል ባለመስማት ቢበላ፣ መብሉ መቃብሩን አፈጠነና በልቶ የረከሰበት ስፍራ፣ “የምኞት መቃብር” ተባለ።
የእግዚአብሔርን መግቦት እንዲፈልግ የተሰጠው ራብና ጥም፣ ለመውደቁና በምድረ በዳ ለመቅረቱ ምክንያት ኾነው። ሔዋንም እስራኤልም
የእግዚአብሔርን ቃል በመጠራጠር ወይም ችላ በማለት የተሰጣቸውን ተስፋና ኪዳን እንዲዘነጉ በማድረግ ጠላት “አሸነፋቸው”።
ቅዱስ
ቃሉ፣ “ሰውም
ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት አይኖርም” ቢልም፣ ብዙዎች ግን
ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለራብና ጥማቸው የሚመልሱት ምላሽ ሌላ ነው። እውነተኛ ራብና ጥም የሚመለሰውና የሚታገሠው በራሱ
በእግዚአብሔር ብቻ ከመርካት እንደሚጀምር አለማስተዋል ምስኪንነት ነው።
እግዚአብሔር
ዘወትር እንድንፈልገውና እንድንራበው፤ እንድንጠማውና እንድንናፍቀው አብዝቶ ይፈልጋል፤ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና
ይጠጣ።” ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ
ትናፍቃለች።”፣ ነቢዩ በሌላ ስፍራም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣
በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።” (ዐመት)።
ሰው ሲጾም ምግብን
ብቻ ከተራበ ከንቱ ነው፤ ይልቅ እየራበው የሚጾመው ሰው ራቡ በጥጋብ የሚረካውና ፤ ጥሙ በመጠጣት የሚቆረጠው በጾም በሚያመልከው
በራሱ በእግዚአብሔር ብቻ ነው። የፆመ ሰው ፍላጎቱና ናፍቆቱ መንፈሳዊ ምግብን መመገብ እንጂ
ሥጋዊ ምግብን መመገብ፤ አለመመገቡ አይደለምና። ስትጾሙ ምን ይርባችኋል፤ ምንስ ይጠማችኋል?
እንደ
ሔዋንና እንደ እስራኤል ናፍቆትና ራባችሁ መብል ብቻ አይኹን፤ ይልቁን ከተራባችሁና ከጾማችሁ፤ ከናፈቃችሁና ከተመኛችሁ ራሱ እግዚአብሔርን
ተራቡ፤ እናም የማይነጥፍ ወንዝ ከኾነው ከቅዱስ ቃሉ ውስጥ በመጥለቅ፣ ከቅዱስ ቃሉ ጠጡ፤ ደግሞም በመቁረስ እየተራባችሁ ጥገቡ፤
እየጠገባችኹም ዘወትር ተራቡ!
No comments:
Post a Comment