ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ለመቅደስ
አገልገሎት የሚያስፈልጉ ንዋያተ ቅድሳት እንዲያዘጋጅ በዝርዝር ተናግሮታል። እንዲዘጋጁ ከተናገራቸው ንዋያተ ቅድሳት መካከል አንዱ፣
በአሮን ወይም በሊቀ ካህናቱ ጥምጣም ላይ በጕልህ መንገድ እንዲታይ ከወርቅ ሰሐን የተሠራው ጽሑፍ ነው። ጽሕፈቱ ጕልህ በመኾኑና
እይታን በመሳቡ ምንያት ለኹሉ የሚታይ ነው። “በመጠምጠሚያው ፊት በሰማያዊ ፈትል በመጠምጠሚያው ላይ የሚሰፋውና በአሮን ግንባር
ላይ የሚኾነው”፣ “ቅድስና ለእግዚአብሔር ወይም ለጌታ የተቀደሰ” የሚል ከንጹሕ ወርቅ ቅጠል ሥራ ወይም በወርቅ ሳህን ቅርጽ የተቀረጸና
በጥምጣሙ ላይ የሚደረግ ነው።
የወርቁ ሳህን ከአንደኛው ጆሮ እስከ ሌላኛው ጆሮ እንዲገናኝ
ስለሚደረግ፣ ሙሉ ለሙሉ ግንባርን የሚሸፍን ነው። በሳህኑ ኹለት ጥጋጥ ላይ ባሉት ቀዳዳዎች ደግሞ ሰማያዊ ፈትል እንዲገቡበት ተደርጎ
ጽሐፍቱ በሚገባና ለኹሉ እንዲታይ በግንባር መሃል ላይ ይቀመጣል። ይህ እጅግ አስደናቂ ተግባር ነው።
ካህኑ በዚህ አለባበሱ፣
1.
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለውን ፍቅር ይገልጣል፦ አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዲህ
በሎ ተናግሮአል፣ “እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዓይኖችህም መካከል እንደ
ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ።” (ዘጸ. 13፥16) ልክ እንዲኹ፣ በሊቀ ካህናቱ ግንባር ላይ ያለው የወርቁ ሳህን
እግዚአብሔር ለእስራኤል ያለውን ፍቅር ሁል ጊዜ እንዲያስታውስ የሰጠውን ትእዛዝ የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ታዳጊና
ከውርደት የሚያወጣ መኾኑን፣ ኀጢአታቸውንም ጭምር ይቅር የሚል አምላክ መኾኑን ዘወትር የማይዘነጉበት።
እግዚአብሔር ዘወትር ለሕዝቡ እዲህ መታየትና መገለጥ
ይሻል፤ መሃሪና ይቅር ባይ፤ ተወዳጅና ታዳጊ አባት ኾኖ መታየት ይፈልጋል፤ ይህ ተወዳጅ አምላክ ለሙሴ ራሱን ሲያስተዋውቅ እንዲህ
ብሎታል፣ “እግዚአብሔር፥
እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን
ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ …” (ዘጸ. 34፥6-7) እግዚአብሔር ይህን የተናገረው በሙሴ እጅ የነበሩት ኹለቱ ጽላቶች በተሰበሩ ጊዜ
ነበር። አምላካችን መሐሪና ይቅር ባይ፤ ዘወትርም በተሰበረ ነገራችን ላይ የይቅርታና የምሕረት ዘይት የሚያፈስስ ሞገስ ያለው ነው፤
አሜን።
2.
“ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚለውን የወርቅ ጽሕፈት ያለበትን ጽሑፍ ያደረገው ሊቀ
ካህናት በዋናነት የእግዚአብሔር አገልጋይ እንጂ የሰው እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው። ስለዚህም ይህን ጥምጣም በሄደበት ኹሉ እንዲያወልቀው
አልተፈቀደለትም። ቅድስና ዘወትር እንድንኖረው የተባለ እንጂ፣ ስንወድድ የምንተወው፤ አልያ የምናነሳው አይደለም። እንዲያውም ጽሕፈቱ
ከወርቅ ጋር በመያያዙ በቀጥታ ከሕይወታችን ጋር ተዛምዶ አለው፤ ቅዱስ ቃሉ፣ ወርቅ የመፈተንና የመጥራት ምሳሌ እንደ ኾነ ገልጦአል።
እምነታችን የሚጸናው እንደ ወርቅ ስንፈተንና ፈተናውን ድል በመንሣት ስንጠራ ነው። ወርቅ ተፈትኖ በጠራ ጊዜ ለኹሉ እንደሚታይ እንዲኹ፣
ቅድስናም ሊሸሸግ አይችልም። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት ይከብራል።
3.
አገልግሎትና አምልኮ ያለ ቅድስና ሕይወት ከንቱ ነው፦ ከላይ እንደ ተናገርነው፣
ሊቀ ካህናቱ “ለጌታ የተቀደሰ ወይም ቅድስና ለእግዚአብሔር” የሚለውን ጽሕፈት ከቶ ከራሱ መለየት የለበትም። ምክንያቱም፣ አገልግሎት
ከቅድስና ሕይወት የሚመነጭ ነው፤ ቅድስና ደግሞ ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ፍጹም ከመታዘዝ ጋር የማይነጠል ነው። በኀጢአት እየተመላለስን፤
በሚታይ የቅድሰና ሕይወት ባንታይ ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ ነው። ወደሚታይና ተግባራዊ ፍቅር የማይመራ አገልግሎትና አምልኮ ዕርባና
ቢስ ነው። እግዚአብሔርን በቅድስና ማገልገል ይብዛልን፤ ይትረፍረፍልን፤ አሜን።
ኢየሱስን በማይጠፋ ፍቅር ለምትወድዱ
ኹሉ ምሕረትና ጸጋ ይብዛላችኹ፤ አሜን።

No comments:
Post a Comment