በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የ“ተሐድሶ አገልጋዮች” ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል፤ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ ዘሩባቤልና ኢያሱ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ሕዝቡና እነርሱ በምርኰ ሳሉ፣ የእስራኤልን ጥልቅ ውድቀትና መንፈሳዊ ቅዝቃዜ በማየት፣ እስራኤል ዘሥጋ ትነቃቃና ታበራ፤ ትጌጥና ትፈካ ዘንድ የነቢያቱን የተስፋ ቃል በማወጅ፤ እንደገና በማስታወስና አጽናንቶ በማበረታታት ይታወቃሉ።
እስራኤል ለወደቀችበት ጥልቅ ውድቀት፣ ትንሣኤና ብርሃን የኾንዋት እኒህ የተሐድሶ ምርጥ ቅሬታዎች(remnants) ናቸው። እውነተኛ
ሐዳስያን ኀጢአትንና ክፉ ውጤቱን በትክክል ያያሉ፣ ደግሞም ያሳያሉ፤ ለእግዚአብሔር ክብር መጉደል በብዙ ይቀናሉ፣ የእግዚአብሔር
ስም መሰደብና የመቅደሱ መርከስ ይከነክናቸዋል፣ የሕዝቡ መማረክና በወደረኞች እጅ መያዙ ያሳዝናቸዋል፣ የቅድስቲቱ ከተማ ቅጥር
አልባነትና የአሕዛብና ያላመኑ ኹሉ መመላለሻ መኾንዋ ዐይናቸውን በእንባ ይመላዋል።
አማናዊው ሐዳሲና ፍጹሙ መምህር መሲሑ ኢየሱስ፣ ሕጉንና ትእዛዛቱን ለራሳቸው ክብርና ጥቅም በማስቀደም፣ በሕዝቡ ላይ መንፈሳዊ
እርጅናና ንቃቃት ያስከተሉትን “ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንን” በወቀሰበት ክፍሉ፣ “... የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን
ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። ... ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል።” (ማር. 7፥8-9) ብሎ በመውቀስ ሐዳሲነቱን በአደባባይ ናኝቶአል።
ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በአጭር ቃል፣ "የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር
ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።" (ሮሜ 12፥2) በማለት
“የሕይወት ተሐድሶ” ዕለታዊ ወይም ዘወትር የሚኾን እንጂ የሚጠላ እንደ ኾነ አይነግረንም፤ ደግሞም ይህን መናገር ጨርሶ
የሚያሳፍርም አይደለም።
ደግሞም ሐዳሲነት ንግግር[ስብከት] ብቻ ሳይኾን ግብርም ያነገበ “የሕይወት ደቀ መዝሙርነት” የሚሻ ነው። በዚህ መንገድ
መመላለስ ደግሞ፣ የትኛውንም ዕድፈትና ነቅ የማየት ንስራዊ ዕይታን ያጐናጽፋል። ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “...
አሕይዎና (መንፈሳዊ መነቃቃት) ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ
በተቀመጠው ሥርዓት (Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው
ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ‘መለወጥ አለበት’ የሚሉትን ለመለወጥ ቈርጠው ሲነሡ ደግሞ
ታላቅነታቸው ወደ ገናናነት ያድጋል። ትውልድም አገሪቱ የነጻ ሐሳብና የምርምር ሰዎች እንደነበሯት ሲያውቅ ይኮራል። ...”
(ጌታቸው ኃይሌ(ፕሮፌሰር)፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ፤ 2010 ዓ.ም) በማለት የገለጡት።
በርግጥ ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ ሐዳስያን የሚያደርጉትን ተሐድሶ፣ በግልጥ ቃል “ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዓት
(Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ የሚያይ”
ብለው በተባ ብርዐቸው ቢጠቅሱም፣ ነገሩን ከመንፈስ ቅዱስ ነጥቀው በሰዋዊ ዕይታ ላይ ብቻ መወሰናቸው
ድካማቸው ነው ብዬ አምናለኹ። ሊስተባበል የማይችለው እውነታ፣ ሐዳሲነት “ቅዱስ ዕይታንና ታላቅ ቅንአትን” ስለ መፈለጉ ሊሸሸግ
አይችልም።
የተሐድሶን ሥራ የሚቀሰቅስ፣ የሚጠብቅና የሚያበዛ ርሱ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የክርስቶስ ሙሽራ ቅንነቷ፣ ንጽሕናዋ፣
ተልእኮዋ ተጠብቆ እንዲኖር፣ ክርስቶስ ራሱ በመንፈሱ ሁልጊዜ ሊያድሳት ይቀናል፤ ይሠራል። ከእኛ የሚጠበቀው ከላይ
እንዳልነው ራሳችንን በትጋት እያዘጋጁ መቆየትና መጠባበቅ ብቻ ነው።
ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በዚህ መንገድ ከተመላለሰች የእግዚአብሔር
መንግሥት ትሰፋለች፤ ምዕመናንና ምዕመናት ፍጹም ወደ መንፈሳዊ ዕረፍት ይመጣሉ፤ ከዚህ የተነሳ፣ በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር
ፈቃድ በሰዎች ልብ ኹሉ ትፈጸማለች፤ አሜን።
“እንግዲህ #ምሕረትን_እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ #የሚረዳንን_ጸጋ_እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”ዕብራውያን 4፥16
ReplyDelete