በዘመናዊው ዓለም ኢየሱስ በኪደተ እግሩ ከሰማርያ እስከ ኢያሪኮ የሚፈልጋቸው ሳምራዊቷ ሴትና የጤሜዎስ ልጅ በርጠሚዎስ፣
ወይም በቅፍርናሆም ያገኛት ደሟ ቀጥ ያለላት ሴት፣ ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ጥሩ የስብከት ርዕስ እንጂ በወንድምነት ወይም በእህትነት
የሚፈለጉ አይመሰለኝም። በቀላል ንግግር ሰውነት በዚህ ዘመን ከአገልግሎት አይበልጥም የተባለ ይመስላል።
የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ካመጣብን መዘዝ አንዱ፣ አርዓያ ሥላሴ ያለበትን ክቡር ሰው አርክሶ፣ አርዓያ ነገሥታት
ያለበትን ቊስ እናመልክ ዘንድ “ጥበብና ዕድገት በሚል ተላላነት አዋዝቶ በማቅረብና በማሳመን” ዘርሮናል። የሰው ሞት አንሶብን፣
ክብርና ብዕል በልጦብናል፤ የድኻ መመንገል ጥቂት ሳይሰቅቀን፣ ሞቱም “የትንኝ ሞት ያህል
ሳይከብደን” ተደላድለናል፤ አይረቤው የኳስ ወሬና ሌላም ሌላም “እንቶ ፈንቶ” ግን ብዙ ያስጮኸናል። ይህን በነፍስ ተወራርደው እግዚአብሔርን
የማያገለግሉ ቢናገሩ አይደንቅም፤ አገልጋይ ነን ያሉቱ ለዚህ ዐሳብ ሎሌ ሲኾኑ ግን ይሰቅቃል።
የተጠራነው እግዚአብሔርን ለማክበር እንጂ በተባ ብርዕ ለመጻፍ አልያም በአንደበተ ርቱዕነት ለመስበክ አልነበረም።
እግዚአብሔር ስለ ገፋኸው፤ ባልንጀራህን ችላ ብለህ ስለ ተውኸው፤ አልያ “እኔ ዘንድ መቼም አይደርስም” ብለህ ስለ ናቅኸው ወንድምህ
እንጂ ስለ ተደራጀውና ብዙ ተከታይ ስላፈራው አገልግሎትህ ግድ የለውም። ጆን ስቶት የተባሉ አባት፣
“በአንድ ጊዜ ታማኝም ዝነኛም
መኾን አትችልም፤ አንዱን ለአንዱ ትሠዋለህ።”
እንዳሉት።
በአገልግሎት ዝነኛና ታዋቂ መኾን፣ ርሱ'ኮ “ኢየሱስን ሲሰብክ” ደስ ይላል ማለትና በታማኝነት ለኢየሱስ ትምህርት፣
ሥራና ሕይወት መታዘዝ እጅግ የተለያዩ፤ የማይገናኙም ናቸው። እንደ ሰናዖር ሰዎች የራስን ስም ለመገንባት መጣር ያደክማል፤ በኹሉ
ነገር እንደ አብርሃም ለእግዚአብሔር መገዛት ግን የትውልዶች አባት ያደርጋል። ከአገልግሎት ይልቅ ወንድምነት ይበልጣል፤ ቃሉም፣
“በብርሃን አለሁ
የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።” (1ዮሐ. 2፥9) እንዲል።
የ“ትልልቅ” አገልጋዮችና ጉባኤያት ውድቀት በመጋቢ አልባ ሕይወት ማገልገላቸውና መገልገላቸው ነው። አገልጋይ በኹሉ
ነገር ብቁም፤ ንቁም አይደለምና፣ ሳምራዊቷና በርጠሚዎስ ለስብከት እንጂ በእውነታ ሕይወት የማይፈለግባቸው፣ ዓውደ ምሕረቶችና “ፑልፒቶች”
በዝተዋል፤ የነርሱ ወንድምነትና እህትነት ተገፍቶም “አገልግሎት ዋና ኾኖአል”፤ ምን ርሱ ብቻ፣ በአገልጋዮች መካከል እንኳ፣ “ደረጃ
መዳቢ” በዝቶአል፤ እናም “እባካችን” አገልግሎቱ ይቆየን፤ ወንድምነቱ ይቅረበን!
እናም”
“ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1ቆሮ. 10፥12 ዐት)።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:
Post a Comment