በክርስትና ታሪክ ውስጥ “ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” እንደሚለው ያለ አስደናቂና አጽናኝ ቃል ጨርሶ የለም። ማቴዎስ ወንጌሉን ሲጽፍልን፣ ትንሣኤውን በልዩትነት መንገድ ነው። ይኸውም ስቅየቱንና መከራውን እንደ ዘገበ ወዲያው የትንሣኤውን ነገር ይነግረናል። ትንሣኤውንም የሚያቀርበው ልክ ክርስቶስን የሕግ ፍጻሜ ነው ብሎ (ማቴ. 5፥17) እንደሚያቀርበው እንደዚያው፣ ትንሣኤውንም የምድር አገልግሎቱ ማብቂያና መክተቻ፤ ፍጻሜ አድርጐ በውበት ያቀርበዋል።
ደቀ መዛሙርት በጊዜው
የነበሩበት ኹኔታ፣ በብዙ ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለ ነበር፣ የትንሣኤው ዜና ታላቅ የድል ብሥራታቸው ነው። ወንጌላዊው
ማቴዎስ መቃብሩ ባዶ መኾኑን አጽንዖት በመስጠትና መጥተው እንዲያ በመጋበዝ ቅዱሱን ወንጌል ማቅረቡ፣ ተስፋን በአዲስ መልክ በማለመልም
ትንሣኤው ዋና ነገር መኾኑን ምስክር ነው። መላእክትም ይህን እውነት በታላቅ ድምጽ አጕልተው ይናገራሉ።
በርግጥ መዘንጋት
የሌለብን እውነት፣ ትንሣኤው ታሪካዊ ክስተት ብቻ ሳይኾን የክርስትና እምነት አዕማድ ትምህርትና የማዕዘን ድንጋይ ነው የሚለውንም
ጭምር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ፣ የክርስቶስ መነሣት፣ ስብከታችን፣ እምነታችን፣ ምስክርነታችን፣
የኀጢአታችን ሥርየት፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ኹላ ከንቱ መኾናቸውን” በአጽንዖት ይናገራል፤ (1ቆሮ. 15፥13-17)። ስለዚህም
የክርስቶስ ትንሣኤ ለእምነታችን ኹለንተናዊነት ያለው ጠቀሜታ እጅጉን የጐላ ነው።
ማቴዎስ
ወንጌላዊ የክርስቶስ መነሣት ላይ ብቻ ሳይኾን፣ ክርስቶስ ተቀብሮበት የነበረውን ስፍራ ጭምር መትተው እንዲያዩ መልአኩ
የጋበዘውን ግብዣም በአብሮነት ያቀርብልናል። ይህ ግብዣ ትንሣኤውን ከመተረክ ያለፈ፣ ትረካውን የሚሰሙ ኹሉ ከሙታን መካከል
የተነሣውን መሲሕ ክርስቶስ በመገናኘት ከእውነቱ ጋር እንዲተባበሩ የሚጋብዝ አስደናቂ እውነት ነው። ተነሥቷል የምንለው ጌታ
በመቃብር የሌለ ብቻ መኾኑን እንድናምን ሳይኾን አይተን እንድንመሰክር የሚሻ መኾኑን እናስተውላለን።
ይህ አሰቃቂ
ስቅለቱን ለተመለከቱ ሐዋርያት ብርቱ የእምነት አቅም ነው፤ በተስፋ መቁረጥ ጨለማ ውስጥ ለነበሩት ሐዋርያት ከፍርሃት የሚገላግል
አስደናቂ የአሸናፊነት ዜና ነው። የሞት ፍርሃት፣ የመከራ ናዳ፤ የጣዕርና የስቅየት ድምጽ … አኹን አቅም አይኖረውም፤ ይህን
ኹሉ የሚሽር የትንሣኤ ኃይል በክርስቶስ ተገልጦአልና። ዛሬም በብርቱ ሐዘን ለተከበባችሁ፣ በማናቸውም ክስተት በተስፋ መቁረጥ
ውስጥ ላላችሁ ኹሉ፣ በማመንና በእውነት ለሚቀበሉት ይህ የትንሣኤ ብርሃን ኹለንተናን የመለወጥ አቅሙ አልደከመም፤ ሕያው ነው።
ከተነሥቷል ዜና
ጋር የተያያዘው ትእዛዛዊ ቃል፣ “የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” የሚለው፣ አማኞችን ኹሉ የሚጋብዝ ቃል ነው። ለማመን ማየት
የሚያስፈልግ ከኾነ እነሆ የክርስቶን መቃብር ማየት ብቻውን በቂ ነው። እምነት በማየት ከኾነ፣ ይኸው የመቃብሩን ስፍራ እዩ፤
ባዶ ነው፤ አንዳችም የለበትም። ምክንያቱም በደል አልባው መሲሕ ሞት ሊይዘው ስላልቻለ ከሙታን መካከል ተነሥቶአልና።

No comments:
Post a Comment