Friday, 10 April 2026

“እነሆ ሰውዬው” (ዮሐ. 19፥6)

 Please read in PDF

ይህን ቃል የተናገረው ጴንጤናዊው ጲላጦስ ነው። የተናገረውም ስለ ስቁዩ ሎሌ መሲሕ ኢየሱስ ነው። የተናገረበትም ምክንያት፣ ቊ. 1 ላይ እንደምናነበው፣ ጲላጦስ ራሱ ኢየሱስን ገርፎታል፤ የያዙትም ሰዎች “ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤” (ሉቃ. 22፥63) እንዲል፤ መግረፉንና “ለመግረፉ ድጋፍ ለማግኘት” የተናገረው ይመስላል፡፡ ክፍሉ በክርስቶስ ሕማማት ትረካ ውስጥ ወሳኝና ጌታችን በገዛ ወገኖቹ ፍጹም አለመቀበልን እንደ ገጠመው እንመለከታለን። ከምንም በላይ ደግሞ ሰዎች ኢየሱስን አሳልፈው ሲሰጡ፣ ምን ያህል ለጥቅማቸውና ለክብራቸው፤ ለሥልጣናቸው እንደሚጨነቁና አብ የተወደደ ልጁን በሚሰጠው ፍቅሩ ውስጥ ሰው ምን ያህል ኀጢአተኛ እንደ ኾነ በጥልቀት የምናይበት ነው።

ጲላጦስ ይህን ሲናገር፣ “የካህናት አለቆችና ሎሌዎች” ለሥልጣናቸውና “ለሕጉ” ካላቸው ቅንአት የተነሣ ኢየሱስን ፍጹም ተቃውመውታል። የጳንጦሱ ጲላጦስ ደግሞ የአይሁድ መሪዎችንም ኾነ ሕዝቡን ለማርካት በሚሞክርበት ውጥረት ውስጥ “ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤” እንዲል፣ ፍትሕ ከማድረግና ቅን ፍርድን ከመፍረድ ታቅቦ ሰውን ለማስደሰት፤ ዐመጸኞችን ለማርካት ሲናውዝ እናየዋለን።

ጲላጦስ አሳዛኝ ሰው ነው፤ የኢየሱስን ንጹህነት በተደጋጋሚ ባደረገው ምርመራ ቢያውቅም፣ ሕዝቡን በመፍራትና የሮማዊ ቄሳርን ሥልጣን ለመጠበቅ ሲል ያለ ሕጉ በንጹሁ ላይ ሊፈርድ ጨከነ። ስለዚህም ኢየሱስን የሚያድን አንዳችም እርምጃ እንደማይወስድ የታወቀ ኾነ። ድርጊቱ ብዙውን ጊዜ በፖለቲካና በኅብረተ ሰብ ጫና ስር የሚፈፀመው ኢፍትሃዊነትን አጕልቶ ከማሳየቱም ባሻገር፣ በታሪክ ውስጥ ይህ እውነታ ተደጋግሞ መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ነው።

ጲላጦስ የኢየሱስን እውነትነት ቢረዳም፣ አንድን ወንጀለኛ እንደሚቀጡበት ልማዳቸው (ሐ.ሥ. 22፥24)፣ ኢየሱስን በተደጋጋሚ ገረፈው፤ አስገረፈው። አይሁድም ቢኾኑ ይህን መደገፋቸው የሚያስደንቅ ነው፤ ነገር ግን የሕጉ መጽሐፍ፣ አንድን ሰው ጥፋተኛ ለማለት በኹለት ምስክሮች ምስክርነት ካልተፈረደበት በቀር ከባድ ቅጣቶችን ከልካይ ነበር፤ (ዘዳ. 17፥6፤ 19፥15)። ነገር ግን አይሁድም፤ አሕዛብም ለእውነተኛ ፍትሕ ጆሮ መንፈጋቸው የፍጥረተ ዓለሙ “በጠቅላላ መበላሸትን” የሚወክሉ ነበሩ።

ጲላጦስ ከገረፈው በኋላ፣ የአይሁድን ፈቃድ ፈጽሞአልና ምናልባት እንዲደሰቱ በማለት ወደ አደባባይ አውጥቶ “እነሆ ሰውዬው” አላቸው። የተገረፈ የደማ፤ የተሳቀየ ብዙ መከራን የተቀበለ፤ በግርፋት ብዛት ሰውነቱ በደም የተነከረ፤ ለሰው ልጆች ኹሉ ክብርና “መጌይተይ” ሲል፣ ተዋርዶና ተጎሳቁሎ የቆመውን መሲሕ፣ ጲላጦስ “እነሆ ሰውዬው” ወይም “ይኸውላችሁ ሰውዬውን ተመልከቱት” ሲል እንመከተዋለን። ፍትህ በማጣት የተገረፈው መሲሕ፣ ዛሬ ፍትሕ ላጡ ኹሉ ወክሎና በፈቃዱ መከራ ተቀባይ ኾኖ ተገለጠ።

ውርደታችንን በክብር ሊለውጥ ተዋረደ፤ በኀጢአት ስቅየት፤ በሰይጣን አለንጋ በዓመጻ ለተገረፈው ሰው ፈውስና መድኃኒት ይኾነው ዘንድ “ይኸው ሰውዬው” ተብሎ ከነግርፋቱ በአደባባይ ታየ። ጆን ፓይፐር ስለዚህ ታላቅ የመስቀል ሥራ እንዲህ ብለዋል፣    

“የመስቀሉን ክብር ካልያዝን፣ ሕይወታችን መቅኖ ቢስ ኾኖ (ባክኖ) ቀርቷል ማለት ነው። እንደ ውድ መዝገብነቱ (ሀብትነቱ) ደስ ተሰኝበት፤ ከየትኛውም ደስታ በላይ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው እንደ መኾኑ ተጠጋው። በማንኛውም ሕማምህ ጊዜ ደስታን ቅዳበት፤ በአንድ ወቅት ለእኛ ለሰዎች ሞኝነት ይመስለን የነበረው የአምላክ መስቀል ጥበባችን፣ ኀይላችንና በዚህ ዓለም የቀረን ብቸኛው ትምክሕታችን መኾን አለበት።”

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment