Wednesday, 29 April 2026

“በወንጌል ሕይወታችን ኾነ”

 

“በወንጌል ሕይወታችን ኾነ” በሚል መሪ ቃል፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገር አቀፍ የወንጌል ቀን ለሦስተኛ ጊዜ ባለፉት ኹለት ቀናት አክብራ አሳልፋለች። ይህም በዋናነት ትኵረት ያደረገው፣ የወንጌልን ትምህርት በቋንቋ ተደራሽ ለማድረግ ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ በተለየ ኹኔታ በማሰብ እንደ ኾነ ተገልጦአል። የቦሌ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዳሉትም፣ “የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ ምዕመናንን በቃለ እግዚአብሔር ወንጌል አንፆ ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ማዘጋጀት እንደ መኾኑ መጠን፣ ሰባክያን ምሳሌ ባለው ሕይወት ሊያገለግሉ ይገባል።” ብለዋል። ተያያዥነት ባለው መልኩ፣ በተለይም ወንጌል ለሚያገለግሉ ሰባክያን ልዩ ትኵረት እንዲሰጥና፣ ሰባክያኑም አገልግሎታቸው “ተልእኮ ተኰር” እንዲኾን ከታዳሚው በተደጋጋሚ ተጠቅሶአል።

ሐዋርያዊ ተልእኮ ከተደራሽነት አንጻርም ብዙ ክፍተቶችና ጉድለቶች ያሉበት በመኾኑ፣ እንደ መፍትሔና የአቋም መግለጫ፣ በብዙ ቋንቋ፣ ከከተማ ይልቅ ወደ ገጠር በማድላትና ዓለም ዓቀፍ ይዘት እንዲኖረውም በሚያሳስቡ መልእክቶች ታጅቦ ቀኑ ተከብሮ ወይም ታስቦ ውሎአል። በመርሐ ግብሩ መጨረሻ ላይም፣ ለረጅም ዓመታት ቤተክርስቲያንን በታማኝነት ላገለገሉና አርአያ የሚሆን ተግባር ለፈጸሙ አባቶችና አገልጋዮች የተለያዩ ሽልማቶችን በማበርከት ጉባኤው ተጠናቅቆአል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ያለኝን አድናቆትና ትዝብት ላጋራ፣

  1. “በወንጌል ሕይወታችን ኾነ” በሚል መሪ ቃል ይህ መርሐ ግብር መዘጋጀቱ በራሱ፣ እጅግ ይበል የሚያሰኝ ነው፤ ምክንያቱም ያለ ወንጌል ሕይወት ሊኾን ጨርሶ አይችልምና። ጌታችን ኢየሱስ “ሕይወት እኔ ነኝ” አለ (ዮሐ. 11፥25)፤ ርሱ የሚሰጠን የዘላለም ሕይወት ደግሞ ለዘላለም የማይጠፋ ነው (ዮሐ. 10፥28)፤ ላመኑት ደቀ መዛሙርትም፣ “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።” (ዮሐ. 10፥10) በማለቱ፣ ክርስቶስ የተትረፈረፈ ሕይወት መኾኑን ነገረን። በርግጥ አማናዊው ወንጌል ክርስቶስ ሕይወታችን ኾኖአል። ክብር ይኹንለት።

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህ “ሕይወት በዚህ ልክ” መታሰቡ፤ በእምነት መነገሩ፤ መሪ ቃል መኾኑ፣ ሰዎች ስለዚህ ሕይወት ብቻ በማናቸውም መንገድ ሲወያዩ ማየት  ከልብ ያረካል። ዛሬም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ርቱዕ በኾነ መንገድ “በወንጌል ብቻ ሕይወት እንዲኾን” ከልብ እንመኛለን፤ እንጸልያለን፤ እጅግ በጣም እንናፍቃለን!





  1. ለረጅም ዓመታት ቤተክርስቲያንን በታማኝነት ላገለገሉና አርአያ የሚሆን ተግባር ለፈጸሙ” በሚለው መርኅ ውስጥ ከተካተቱት አንዷ ፋንቱ ወልዴ ናት። ትዝብቴ ከርሷ መመረጥ ይጀምራል። ፋንቱ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት “ስሟ ከወንጌል ነቀፋ ጋር” ሲነሳ ነበር። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ “ስለ ወንጌልና ስለ ክርስቶስ ብቻ” የሚዘምሩ ወንድሞችና እህቶችን በማሳደድ፤ በማስኮብለል፣ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ በማድረግ፣ ብሎም በዓውደ ምሕረት ጭምር በአደባባይ በማሸማቀቅ የተጠመደች ሴት ናት። ከዚህ የተነሳ እውነት ለመናገር “ታማኝነትና አርዓያነት” ከርሷ ይታያል ብሎ መጠቀሱ ለትዝብት ይዳርጋል። ከርሷ እጅግ በተሻለ ይህ መስፈርት “የሚገባቸው” አሉና ይህ ለወደፊቱ ቢስተካከል ብዬ አምናለኹ።

ከዚህ በዘለለ ስለ ወንጌል ሕይወትነት በማናቸውም መንገድ መነገሩ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን “ለሕይወትና ለመዳን በሚኾን ወንጌል ያጥለቅልቃት”፤ አሜን።   

No comments:

Post a Comment