Thursday, 23 April 2026

“በመንፈስ ተመላለሱ” (ገላ. 5፥16)

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ “የሥጋ ምኞት በመንፈስ ላይ፣ መንፈስም በሥጋ ላይ ነውና፤ ልታደርጉ የምትወዱትን እንዳታደርጉ እነዚህ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ” ይላል።  በዚህ በወደቀው ዓለም ውስጥ ስንመላለስ፣ ምንም እንኳ በክርስቶስ ኢየሱስ በደሙ ቤዝወት ከኩነኔና ከዘላለም ሞት ድነን፣ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ የታጠብን፣ የተቀደስን፣ የጸደቅን" (1ቆሮ. 6፥11) ብንኾንም፣ በውስጣችን ግን የእግዚአብሔር በኾነውና በኀጢአት መገኘት ምክንያት ታላቅ ጦርነት አለ። በአንድ ማንነት ውስጥ ያሉ፣ ርስ በርሳቸው ደግሞ የሚቀዋወሙ ባላንጣዎች! የሥጋ ምኞታችን በማናቸውም መንገድ ለእግዚአብሔር አይታዘዜና እንዳንገዛ ከልካይ ነው። 

የሥጋ ምኞት ዘወትር በመንፈሳዊ ነገራችን ላይ መሰልጠን ይፈልጋል፤ ሳያቋርጥም ይመኛል። በዚህም የምንወደውን እንዳናደርግ ይከላከላል። ከሕግ በታችም ገዝቶ ሊይዘንም ይጥራል። ቅዱስ ጳውሎስ እኒህ የሥጋ ምኞቶች ወይም ሥራዎች በስፋት ዘርዝሮአቸዋል፤ በነዚህ የሥጋ ምኞቶች መመላለስ ከመንፈስ ወደ ኋላ ይስበናል፤ ለዚህም ሐዋርያው፣ “በመንፈስ ተመላለሱ” ይለናል። ሰው ከሥጋ ምኞት ጋር በመጋደል ከተመላለሰና የመንፈስን ነገር ዘወትር አጥብቀን ከያዝን መንፈሳዊ ፍሬዎችን እንደምናፈራ ይመክረናል።

በሌላ ንግግር ቅዱስ ጳውሎስ አብዝተን የምንመገበውን ያንኑ ፍሬ እንደምናፈራ ይነግረናል፤ በሥጋ ምኞት የሚመላለሱ፣ የሥጋ ሥራዎች ይበዛላቸዋል፤ በመንፈስ የሚመላለሱ ደግሞ የመንፈስ ፍሬዎችን በጽድቅ ያፈራሉ። የምንመገበው ያው ምግብ ሰውነታችንን ይገነባዋል፤ የምመላለስበት ያው ጎዳና ፍጻሜያችንን ይተልመዋል፤ ሰውነታችንን በምን እያጐለመስን፣ ደግሞ ምን መግበን እየገነባን ነው?

“የማይደክም” ባላጋራ፤ “የማይታክት” ባላንጣ፤ “ካልጣለ የማይለቅ” የክፋት አበጋዝ፤ የኀጢአት አባት “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ‘በዙሪያችን’ የሚዞር” (1ጴጥ. 5፥8)፤ ከኋላችን የማይታጣ (ማቴ. 16፥23) በጐአችንን የማይሻ ጥንተ ጠላት አለብን። ርሱን መርታት የሚቻለን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ስንመላለስ ብቻ ነው፤ ለዚህ ነው ሐዋርያው “በመንፈስ ተመላለሱ” የሚለን። በመሲሑ ደም፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነጻ ከወጣን ወዲያ፣ አርነታችንን ለሥጋ ዕድል መጠቀምም የለብንምና።

በመንፈስ ለመመላለስ ነጻነት ተሰጥቶናል፤ ነጻነታችንን እንዴት እየተጠቀምነው ነው? ታላቁን ጦርነት በድል የሚያጠናቅቁት በመንፈስ የሚመላለሱት ብቻ ናቸውና። ተዋግቶልንም፤ ድል ነሥቶልንም ከሚያኖረን ጋር የክብር ፍጻሜ እንዲኖረን ጸንቶ መቆም፤ በመንፈሱ መዓዛ ፍጹም መታዘዝና መመላለስ ይኹንልን፤ አሜን

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment