የሐሰት መምህራን ክርስትና ከመጀመሩ በፊትም የነበሩና ያሉ፣ በእኛም
ዘመን እንግዳ ኾነው የተከሰቱ ያይደለ ሲኾን፤ ትምህርታቸውም ከታየበትም ጊዜ ጀምሮ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሐሰት ትምህርታቸውን
ሳይታገሱ ፊት ለፊት የተቃወሙ መኾናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይነግረናል፡፡ ሐዋርያት በዘመናቸው ይሠራጭ የነበረውን የሐሰት ትምህርትና
አስተማሪ መምህራንን ትምህርታቸውንና ስማቸውን ጠቅሰው ተቃውመዋል፤ የሰማርያው ጠንቋዩ ሲሞን (ሐዋ.8፥9)፣ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ[እስክንድሮስ
የተባለው ምናልባት የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ ሊኾን ይችላል (2ጢሞ.4፥14)] (1ጢሞ.1፥20)፣ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ (2ጢሞ.2፥17)፣
ዴማስ(2ጢሞ.4፥10)፣ ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ (3ዮሐ.9) እና ሌሎችንም “ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረው ሐሰተኞች
ሆነው ባገኟቸው” ጊዜ እንደለዩዋቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክርልናል፤ (ራእ.2፥2)፡፡
በኋለኛውም በቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘመን፣ ቤተ ክርስቲያን የተነሡባትን
የኑፋቄ ትምህርቶች እንደጉባኤ ኒቂያ፣ ቁስጥንጥንያ፣ ኤፌሶንና ሌሎችንም ጉባኤያትን በመሥራት ከኢቦናውያን እስከ ግኖስቲካውያን፣
ከሲሞን መሠርይ እስከ አርዮስ፣ መቅዶንዮስ፣ አቡሊናርዮስ፣ አውጣኪ፣ ንስጥሮስ፣ ቫሲለደስ፣ መርቅያን … ድረስ ያሉትን መናፍቃንን
በየዘመኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መዝና ትቃወም፤ አልመለስ ያሉትንም አውግዛ ከመካከሏ ትለይ[ለሰይጣን አሳልፋ ትሰጥ (1ቆሮ.5፥5)]
እንደነበር ታሪክ ምስክራችን ነው፡፡


