4.
“የኢየሱስ ክርስቶስን
አምላክነት መካድ፣ በመጽሐፉ ቃል ላይ “የራስን ሃሳብ” መጨመር፤ የቃል ትእዛዝና፣ የገዢነት ሥልጣን”
“ … ፊተኛው አዳም “lose”
ያደረውን ነገር ሁሉ ኋለኛው አዳም መልሷል፤ ፊተኛው አዳም ምንድርነው lose ያደረገው? የተፈጠረበት “purpose” ምን የሚል
ነበረ? ምድርን ግዛ፣ ባሕርን ግዛ፣ የሰማይ አእዋፍን ግዛ የሚል ነው፤ ያን ገዢነት ለእኛ መልሷል፤ ሁለተኛው አዳም በዚህ ማንነት
ነው የተገለጠው … እያንዳንዱን ነገር አስተካክሏል፤ ለምሳሌ ባሕርን ግዟት አለ፤ በባሕር ውስጥ ያሉት ዓሦች አሉ፤ ኢየሱስ በአንድ
ወቅት ግብር ክፈሉ ሲባል፣ ከዛ ጴጥሮስን ምን አለው? ወደባሕር ሂድ፣ ከዛ ዓሳ ታገኛለህ፣ ዓሣ ውስጥ ምን አለ ዲናር አለ፤
እርሱን አንዱን ለእኔ፣ አንዱን ላንተ ትከፍላለህ አለው፤ … ኢየሱስ ለማስደነቅ ምናምን ተአምር ያደረገ ይመስላችኋል? ዓሣ ውስጥ
ያ ዲናር ከየት መጣ? …
ኢየሱስ ሲናገር ዓሳ ውስጥ
ዲናር ሲሠራ ነበር፤ በዚህ ቃል ነው ዓለምን የፈጠረው፤ … ምድርን ሲፈጥር እኮ ከነዳይመንዷ ነው የፈጠረው፤ አሁን አይግረምህ
… ዓሳው የሆነ ቦታ ዲናር ውጦ አይደለም፤ ይኼ አንተ ያለህ ቃል የሚሠራ ነው፤ የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚጠራ፤
የሚያመጣ ነው፤ አዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ይህ ነው፤ ምንም ነገር በቃሉ … [የበለሲቱን ምሳሌ አንስቶ]… የማትፈልገውን ትናገራለህ
ይደርቃል፤ የምትፈልገውን ትናገራለህ ይለመልማል፤ የአዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ነው ይኼ፡፡
አዲሱ ፍጥረት ዓሣን ብቻ
ማዘዝ እንዳይመስልህ ወዳጄ፤ ባሕሩ ላይ መራመድ ካስፈለገህ ትራመዳለህ፤ ይኼ [ኢየሱስ]አምላክ ስለኾነ አይደለም ያደረገው፤ ገና
born again ያላደረገው ጴጥሮስን ተናገር ብሎታል፤ “born again” ያልተወለደው ከተራመደ አንተ እንዴት?[አትችልም?]
ያኔ ጀልባ ስላለ ላያስፈልግ ይችላል፤ ጭንቅ ቢኾን ትሞታለህ እንዴ? [ሰሚዎቹ በጣም በሚጮኽ ድምጽ አልሞትም ሲሉ በተደጋጋሚ
ይሰማል፤] ትራመድበታለህ፤ በባህር ላይ እንድትራመድ የሚያደርግህ “Divine thecnology” ባንተ ላይ ይገጠማል፤ እምነት
ይባላል፤ … ”
|
በጋሻው በዚህ ትምህርቱ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ይስታል፤
1.
በጋሻው፣ “ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በባሕር የተራመደው አምላክ ስለኾነ አይደለም” ይለናል፡፡ እንዲህ በማለት፦ “... ባሕሩ ላይ መራመድ
ካስፈለገህ ትራመዳለህ፤ ይኼ [ኢየሱስ]አምላክ ስለኾነ አይደለም ያደረገው፤ ገና “born again” ያላደረገው ጴጥሮስን ተናገር
ብሎታል፤ “born again” ያልተወለደው ከተራመደ አንተ እንዴት?[አትችልም?] ያኔ ጀልባ ስላለ ላያስፈልግ ይችላል፤ ጭንቅ ቢኾን
ትሞታለህ እንዴ? [ሰሚዎቹ በጣም በሚጮኽ ድምጽ አልሞትም ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል፤] ትራመድበታለህ፤ በባህር ላይ እንድትራመድ የሚያደርግህ
“Divine thecnology” ባንተ ላይ ይገጠማል፤ እምነት ይባላል፤ … ”
የመጽሐፍ ቅዱሱ ንባብ ግን እንዲህ ይላል፤
“ … ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው
ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው፡፡ ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፡፡ በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ
ነበረ፡፡ ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር፡፡ ከሌሊቱም በአራተኛው
ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፦ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ
በፍርሃትም ጮኹ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው፡፡
ጴጥሮስም
መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው፡፡ እርሱም፦ ና አለው፡፡ ጴጥሮስም ከታንኳይቱ
ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ፡፡ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ
ብሎ ጮኸ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው፡፡ ወደ ታንኳይቱም
በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ፡፡ በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት፤”
|
ይህ ታሪክ የሚገኝበት ክፍል የማቴ.14፥22-33 ነው፤ ክፍሉን በጠቅላላ
ስንረዳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ሺህዎችን በመመገቡ ምክንያት ሰዎች ሊያነግሡት ፈልገው ነበር፤ (ዮሐ.6፥14)፤ ጌታችን
ግን ይህንን ስላልፈለገ ከዚያ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ዘንድ ወደተራራ ወጣ፤ (ማቴ.14፥23)፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሻግረው
እንዲቀድሙት[ወደቤተ ሳይዳ ማር.6፥45] አዟቸው ነበርና፣ እነርሱ ገና እየተሻገሩ ሳለ በባሕሩ መካከል ከነፋሱና ከጨለማው ብርታት
የተነሣ ሲጨነቁ አይቶ፣ ወደእነርሱ መምጣቱንና ማጽናናቱን፣ ባሕሩን መገሰጹንና ከፍርሃታቸው ነጻ እንዳወጣቸው እናነባለን፡፡
ከዚህ በኋላ ማለትም፣ ከታላቁ ተአምራት በኋላና የተአምራቱም ባለቤት ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ከተረዱ በኋላ፣ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ
አለው፡፡” ጌታችን ና አለው፤ ጴጥሮስ በጌታችን ቃልና ሥልጣን በመታመን በባሕሩ ላይ መራመድ ጀመረ፤ መራመድ ጀምሮ ግን የነፋሱን
ኃይል አይቶ ፈራ፤ ጴጥሮስ ቀድሞውንም በራሱ ሥልጣን መራመድ አልጀመረምና፣ እንዲራመድ ካዘዘው ጌታችን ኢየሱስ ዓይኑን ማንሳት ሲጀምር
መስጠም ጀመረ፤ ወዲያውም ጌታችን እጁን ዘርግቶ ይዞ ወደጀልባው አወጣው፡፡
ጴጥሮስ ልክ መስጠም እንደጀመረ መልሶ ዓይኖቹን ወደጌታ ኢየሱስ በመመለሱና፣
“ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ በመጮኹ” ጌታችን ታደገው፡፡ በዚህ ክፍል ጴጥሮስ በራሱ በባሕሩ ላይ መራመድ እንዳልጀመረ እንዲሁ፣ ራሱን
ለማዳንም ሙከራ አላደረገም፤ ስለዚህም “ጌታ ሆይ” ብሎ እርሱን በመጣራት የሚያድነው የጌታ ኢየሱስ እጅ ተዘረጋለት፡፡ ደቀ መዛሙርቱ
በኾነው ነገር ሁሉ እጅግ ተገረሙ፤ “በጥቂት እንጀራና ዓሳ ብዙዎችን እንደመገበ አላስተዋሉም ነበር፤ (ማር.6፥52)፤ አሁን እንኳ
ያደረገውን ነገር ከፍርሃት የተነሳ እጅጉን ተገረሙ፤ አላመኑበትምም፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደዘገበልን ደግሞ በታንኳው ውስጥ የነበሩት
ሁሉ ጌታችን ወደታንኳው በመግባቱ ማዕበሉ ጸጥ በማለቱ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት” በማለት የጌታ ኢየሱስን
የእግዚአብሔር ልጅነት እንደተረዱ ይነግረናል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን መሲሐዊ ልጅነት ወይም አምላካዊ ልጅነት በትክክል
ከሚያስረዱ ክፍሎች አንዱ ይህ ወንጌላውያኑ በአንድነት የጻፉት ጌታችን ኢየሱስ በባሕር ላይ የተራመደበት ክፍል ነው፡፡ ለአንድ አይሁዳዊ
“የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መስገድ ማለት፣ ለራሱ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮአዊ ስግደትን የሚያመለክት ነው፡፡ ታሪኩን
የጻፉልን ወንጌላውያንም ሊነግሩን የፈለጉት እውነት የእግዚአብሔር ልጅነቱን በባሕር፣ በማዕበልና በጨለማ ላይ ያለውን አምላካዊ ሥልጣን
በመግለጥ ጭምር ነው፡፡
በጋሻው በግልጥ ይህንን እውነት ይክዳል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ
ስለኾነ አይደለም ይህን ተአምር ያደረገው በማለት ያሽሟጥጣል፤ ጴጥሮስም የተራመደው በራሱ እንጂ በጌታችን ኢየሱስ የሥልጣን ቃል
እንዳልኾነ በድፍረት ይናገራል፡፡ እርሱም ኾነ ሌሎች ሊያደርጉት የሚችሉት “ተራ ነገር” እንደኾነም ተከታዮቹን በማደፋፈር ሲናገር
እንሰማዋለን፡፡ ነገር ግን አሁን በባሕር ላይ የማይኼዱት ጀልባና መርከብ ስላለ እንጂ፣ ጭንቅና ችግር ሲመጣ ግን ሊያደርጉት እንደሚችሉ
በጽርፈት ቃል ይናገራል፡፡[1]
ይህን ያህል ግን በሃሳብ መርመጥመጥ ለምን አስፈለገ? ሰውነትን ጥሎ፣ በጥፋት እየባሱ በትዕቢት መታጀል ፍጻሜው አስፈሪ ውድቀት
ነው፡፡
2.
በጋሻው፣ በቅዱስ ቃሉ ላይ
የሌለ ነገር ይጨምራል፤ እንዲህ በማለት፦ “ ... ኢየሱስ በአንድ ወቅት ግብር ክፈሉ ሲባል፣ ከዛ ጴጥሮስን ምን አለው?
ወደባሕር ሂድ፣ ከዛ ዓሳ ታገኛለህ፣ ዓሣ ውስጥ ምን አለ ዲናር አለ፤ እርሱን አንዱን ለእኔ፣ አንዱን ላንተ ትከፍላለህ አለው፤
… ኢየሱስ ለማስደነቅ ምናምን ተአምር ያደረገ ይመስላችኋል? ዓሣ ውስጥ ያ ዲናር ከየት መጣ? … ኢየሱስ ሲናገር ዓሳ ውስጥ ዲናር ሲሠራ ነበር፤ በዚህ ቃል ነው ዓለምን የፈጠረው፤
… ምድርን ሲፈጥር እኮ ከነዳይመንዷ ነው የፈጠረው፤ አሁን አይግረምህ … ዓሳው የሆነ ቦታ ዲናር ውጦ አይደለም፤ ይኼ አንተ ያለህ ቃል የሚሠራ ነው፤ የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚጠራ፤ የሚያመጣ ነው፤ አዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ይህ ነው፤
ምንም ነገር በቃሉ … [የበለሲቱን ምሳሌ አንስቶ]… የማትፈልገውን ትናገራለህ ይደርቃል፤ የምትፈልገውን ትናገራለህ ይለመልማል፤
የአዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ነው ይኼ፡፡ አዲሱ ፍጥረት ዓሣን
ብቻ ማዘዝ እንዳይመስልህ ወዳጄ፡፡”
የቅዱስ ወንጌሉ ንባብ ግን እንዲህ ይላል፤
“ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ
ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና፦ መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር አይገብርምን? አሉት፡፡ አዎን ይገብራል አለ፡፡ ወደ ቤትም
በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ፦ ስምዖን ሆይ፥ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን
ወይስ ከእንግዶች? አለው፡፡ ጴጥሮስም፦ ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ፦ እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው፡፡ ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥
ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና
ስለ አንተ ስጣቸው አለው፤” (ማቴ.17፥24)፡፡
|
በቅዱስ ቃሉ ንባብ ውስጥ፣ “ጌታችን ኢየሱስ ሲናገር
በዓሳ ሆድ ውስጥ ዲናር ይሠራ ነበር የሚል ቃል አለን? ከሌለ የራስን ሃሳብ እንዲመች አድርጎ መጨመር ስለምን አስፈለገ? ዓውዱስ
ማንኛውም ሰው ልክ እንደጌታችን ኢየሱስ ቢናገር ለማዘዝና ለማድረግ፣ ለማድረቅና ለማለምለም የሚያበቃ ነገር እንዳለው ለማመልከት
የተጻፈ ነውን? … የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎችን ብናነሣ የምናገኘው መልሱ አይደለም የሚለው ምላሽ ነው፡፡
የእምነት እንቅስቃሴን ትምህርት በጠቅላላው ስናጠና ግን በጋሻው ሊናገር
የፈለገው ነገር ምን እንደኾነ ፍንትው ብሎ ይታየናል፤ የቃል እምነት እንቅስቃሴ[2]
ለሚናገሩት ቃላቸው የሚሰጡት ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በጋሻው ይህንን ነው፣ “ … ይኼ አንተ ያለህ ቃል የሚሠራ
ነው፤ የሌለውን እንዳለው አድርጎ የሚጠራ፤ የሚያመጣ ነው፤ አዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ይህ ነው፤ ምንም ነገር በቃሉ … [የበለሲቱን ምሳሌ አንስቶ]…
የማትፈልገውን ትናገራለህ ይደርቃል፤ የምትፈልገውን ትናገራለህ ይለመልማል፤” በማለት የሚናገረው፡፡ የእምነቱ መምህራን ይህን ማወጅ
ወይም መናገርን እንደዋና የእምነታቸው መገለጫ ይጠቀሙበታልም፤ ጥቂቶቹን ብንጠቅስ፦
“እግዚአብሔር ባለጠጋ ሊያደርጋችሁ
እንደሚፈልግ ማወቅ አለባችሁ፡፡ ይህ ለእናንተ ተዘጋጅቷል፡፡ በግልጽ ለመናገር በድፍረት ባትካፈሉ ደደቦች ናችሁ፤” (ኬኔት ኮፕላንድ)
“የሰው የመፍጠር ችሎታው
የሚመጣው ከመንፈስ ነው፡፡ መንፈሳዊው ዓለም ላይ የሚሠሩ መንፈስ የኾኑ ቃላትን ይናገራል፡፡ እነዚህ ቃላት ግዑዙ ዓለም ላይም ተጽዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ እግዚአብሔር ገና ከፍጥረት
መጀመርያ ላይ ቃልን ተናግሮ እንደኾነለት ሁሉ ሰውም መንፈስ የኾነ ቃል በመናገር ተጨባጭ ነገሮችን ሊፈጥር ይችላል፤” (ቻርልስ
ካፕስ)
“እኔ ስለምፈልጋቸው ነገሮች የእምነት አዋጅ አውጃለሁ እንጂ እንደሃይማኖተኞች
ጌታ ሆይ ፈቃድህ ከኾነ አልልም” (ኸርል ፖልክ)
“የአየሩን ጠባይ በእምነት ቃላችን ልንቆጣጠርና እንደምንፈልገው ልናስተካክል
እንችላለን፤” (ግሎሪያ ኮፕላንድ) …
|
እና ሌሎችም ልክ እንደኢየሱስ ሁሉን ማዘዝ የሚችልና ማስተካከል የሚችል
ሥልጣን እንዳላቸው ያምናሉ፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስናጠና ግን ፈጣሪ ቃል፣ አስገኚ ቃል፣ አድራጊ ቃል … የተባለለት ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን
ብቻ ነው፤ እርሱም ከአባቱ ጋር በመጀመርያ የነበረ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥
ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፡፡ የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው፡፡ … እርሱ
ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም፤” (መዝ.33፥6-9)፣ “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው
ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን፤” (ዕብ.11፥3) በማለት የእግዚአብሔር ቃል[አካላዊ ቃል ክርስቶስ ኢየሱስ]
ሁሉን አድራጊነት ይነግረናል፡፡ በእግዚአብሔር የምናምን እንኳ ታላላቅ ተአምራትን ብናደርግ በስሙ ሥልጣንነትና በእርሱ ላይ ጽኑ
እምነት ታመነን እንጂ ከራሳችን አንቅተን ፈጽሞ አይደለም፡፡
ትምህርታቸውን ለማጽናት ከሚጠቅሷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንዱ፣ “የሰው
ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል፥ ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል፡፡ ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ፤”
(ምሳ.18፥20-21) የሚለውን ነው፡፡ ይህ ቃል ግን የእምነት ቃል መምህራን ለራሳቸው እንደሚጠቅሱትም ያይደለ፤ የአፋችን ቃልም
ፈጣሪና ዕጣ ፈንታችንን ወሳኝ እንደኾነ የሚናገር አይደለም፡፡ ከሰዎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት በከንፈራችን ሰዎችን ልናሳዝና
ልንበድል እንዲሁም ደስ ልናሰኝ እንደምንችል የሚናገር ክፍል ነው፤ ይህንን ጠቢቡ በብዙ ክፍሎቹ ላይ ገልጦታል፤ “የሰው ነፍስ ከአፉ
ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል፤” (ምሳ.12፥14) ልክ ገበሬ በድካሙ መልካም አዝመራን
እንደሚያፍስ በጥበብ የሚናገርም መልካም ፍሬን እንደሚያገኝ፣ በምዕ.18፥4 ላይም እንደተነገረው፣ “የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ
ነው፥ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው፤” የጠቢብ ንግግሮች እንደጥልቅ ውኃና ፏፏቴው እንደማያቋርጥ እጅግ ጠቃሚ፣ አስተማሪ፣ የጥበብ
ምንጭም እንደኾነ ይነግረናል፡፡
ስለዚህም ውጤታማና ጤናማ ንግግር ሰዎችን ያረካል፤ ቃላት በሰዎች ግንኙነት ላይ መልካምም ኾነ መጥፎ ነገሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤
መናገርን የሚወድዱ ሰዎች እንደንግግራቸው መጠን ፍሬያቸውን ሊያዩ ይችላሉ፡፡ በጎና ገንቢ የኾነ ነገር ቢናገሩ መልካም ፍሬን ተቃራኒውን
ቢናገሩ ደግሞ እንደዚያው ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህም በማናቸውም ጊዜ ሲናገር ለሚናገረው ነገር እጅግ አብዝቶ ሊጠነቀቅ ይገባዋል፡፡
ይህ ክፍል ከቃል ፈጣሪነትና ሁሉን አድራጊነት ጋር ምንም የሚያያዘው ነገር እንደሌለ ልናስተውል ይገባናል፡፡
በጋሻው ሌላም በንግግሩ ውስጥ የጠቀሰው ቃል አለ፤ ይኸውም፤ “የሌለውን
እንዳለው አድርጎ የሚጠራ፤[አጽንዖት የእኔ] የሚያመጣ ነው፤ አዲሱ ፍጥረት ማንነቱ ይህ ነው” የሚል፡፡ ይህ ቅዱስ ቃል ተጽፎ የሚገኘው በሮሜ.4፥16 ላይ ነው፤ ቃሉም፣
“ስለዚህ ከሕግ
ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦
ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ
ፊት የሁላችን አባት ነው፤” ይላል፡፡
በእርግጥ ግን በጋሻው ለጠቀሰው ቃል ሊውል የሚገባው ነውን? ብለን ግድ
ያስፈልገናል፡፡ “ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ” የተባለው አዲሱ ፍጥረት ነውን? ቃሉ የተነገረው ለአባታችን
አብርሃም መነገሩ ግልጥ ነው፤ ሁላችን እንደምናውቀው አብርሃምና ሣራ ዕድሜያቸው ጃጅቶ መውለድ ባልቻሉበት ጊዜ ለሙታን ሕይወትን
የሚሰጠው ጌታ(ዮሐ.5፥21) የተወደደውን ልጅ ይስሐቅን ሰጣቸው፤ (ዘፍ.17፥5)፡፡ ስለዚህም የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ
ጌታ(ኢሳ.48፥13) ከምንም አንድን ነገር ሲፈጥር አይተነዋል፡፡ ይህ ለእግዚአብሔር ከተነገረበት አውርዶ ለሰው መስጠት ፍጹም ዓመጽና
አለመታዘዝ አይደለምን? የእግዚአብሔር የተነገረውና የኾነው ለእኔ ይኹን ማለት የቀደመው አዳም የወደበት ጽኑ አዘቅት አይደለምን?
3.
በጋሻው፣ የፍጥረትን ገዢነት
“ሥልጣን” እጅግ በጣም ለጥጦታል፤ ለብልጽግናም እንዲውል መሻቱን ያስቀምጣል፡፡ ይህንንም በትምህርቱ፣ “ ... ፊተኛው
አዳም lose ያደረውን ነገር ሁሉ ኋለኛው አዳም መልሷል፤ ፊተኛው አዳም ምንድርነው lose ያደረገው? የተፈጠረበት
purpose ምን የሚል ነበረ? ምድርን ግዛ፣ ባሕርን ግዛ፣ የሰማይ አእዋፍን ግዛ የሚል ነው፤ ያን ገዢነት ለእኛ መልሷል፤ ሁለተኛው
አዳም በዚህ ማንነት ነው የተገለጠው … እያንዳንዱን ነገር አስተካክሏል፤ ለምሳሌ ባሕርን ግዟት አለ፤ በባሕር ውስጥ ያሉት ዓሦች
አሉ፤ ...” በማለት ተናግሯል፡፡
አዎን! ሰው፣ “ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር
ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” (ዘፍ.1፥28) እንዲል ዓለምን ሊገዛም ተፈጥሯል፡፡ ይህም እንዲኾን የተፈለገበት ዋናው ምክንያት
ግን የእግዚአብሔር እቅድ እንዲፈጸምና የእግዚአብሔር ክብር እንዲገለጥ ነው፡፡ ሰው በፍጥረት ላይ ያገኘውን ገዢነት ዳዊት፣ “…
በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥
የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ፡፡” (መዝ.8፥6-8) በማለት ይገልጠዋል፡፡ ይህም የተሰጠውን
ክብርና ሞገስን ያሳያል፡፡ ነገር ግን ማስተዋል ያለብን ነገር ይህ አገዛዝ ፍጹምና ነጻ አለመኾኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ሰው ፍጥረትን
የሚገዛው በእግዚአብሔር ሥልጣንነት ሥር ኾኖ እንጂ በራሱ አይደለም፡፡ እናም የተሠጠው ኃላፊነት የስጦታ እንጂ የመብት ጉዳይ አይደለም፡፡
ስለዚህ በሰውና በፍጥረት መካከል ያለው ግንኙነት ሚዛናዊና አግባብ ያለው
ሊኾን ይገባዋል፡፡ ሰው ፍጥረትን ሲገዛ የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያበራባቸው፣ በአግባቡ ሊገለገልባቸው፣ ሊያስተዳድራቸው … ተሹሟል፡፡
ነገር ግን ዘወትር ማስተዋል የተጠራነው ፍጥረትን ልንገዛ እንጂ በፍጥረት[በተለይም በቁሳዊ ነገር] ልንገዛ አልተጠራንም፡፡ ምክንያቱም
ሰው ግቡ ሰማያዊ ዘላለሙ ከፍጥረት ጋር ያይደለ ከእግዚአብሔር ጋር ነውና፡፡
እነበጋሻው የፍጥረትን ገዢነት ሲያነሱ ለዲናር፣ ለዳይመንድና ለእስታቴር
መገኛ መንገድ ሊያሳዩ እንጂ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ክብሩን እንገልጥበት፤ እንመሰክርበትም ዘንድ በማሰብ አይደለም፡፡ “ግዙ” መባላችን
ቁሳዊውን ዓለም እንድናሳድድ፣ እንድናመልከውም፣ እንድንገዛለትም[እንድንበረከክለትም] አይደለም፤ ይህን መንገድ ጌታችን ኢየሱስ፣
“የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” (ሉቃ.12፥15) በማለት ኰንኖታል፡፡ በእርግጥም
የፍጥረት ዋናው ቁም ነገር ሰዎች፣ “ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር
ይሉ ዘንድ ወንጌልን ለመስበክ” እንጂ፣ “መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና
በደስታ ሊሞላው” ብቻ አይደለም፤ (ሐዋ.12፥15 ፤ 17)፡፡ ይህን ብቻ የሚያስቡም፣ “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን
ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን” (1ቆሮ.15፥19) እንዲል ከሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ናቸው፡፡
በጋሻውን ስለትምህርቱ መጠየቄና የመለሰልኝ ምላሽ
የሐሰት መምህራን ከተኩላ ይልቅ በሚመሳሰል “ወንጌል ቀመስ ወጥመዳቸው”፣ ተዘልለው
የተቀመጡትን ብዙዎች ለማጥመድ ያለከልካይ ሲመላለሱ እናያለን፡፡ እንዳለመታደል በጋሻው ደሳለኝ የአዲሱን እምነት እንቅስቃሴ ትምህርት
እንደሚያስተምርና ምስክርነትም እየሰጠ እንደሆነ ቀድመው ከሰሙት አካላት ከመጀመርያው ተርታ እንደምመደብ አስባለሁ፡፡ እንደሰማሁም
የነገሩን እውነታነትና “የአዲሱን እምነት እንቅስቃሴ” ትምህርት አምኖበት ስለማስተማሩና ስላለማስተማሩ ለማጣራት በቀጥታ ወደእርሱ
የደወለ የመጀመርያው ሰው እኔ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
በጠየቅሁት ጊዜ ግን ፈጽሞ እንዳላስተማረና ትምህርቱን ጭምር እንደማያውቀው
በሙሉ ልብነት ነበር የመለሰልኝ፡፡ ነገር ግን ድምጹ ውስጥ አንዳች ነገር ስለመኖሩ በውስጤ ጥርጣሬ ስላደረ፣ በንግግሬ ማሳረጊያ
“እንግዲህ ካንተ ከጸጋውና ከመዳን ወንጌል ውጭ ሌላ ምንም አዲስ ነገር አልጠብቅ?” ብዬ በጠየቅሁትም ጊዜ ሌላ ነገር እንደማይመጣ
ተለሳልሶ ነበር የመለሰልኝ፡፡ ነገር ግን አመላለሱ አንዳች ነገር ውስጤ ስላጫረ ዝምማለትን አልወደድኹም፡፡
ነገሩ ከልብ፣ ልቤን ስለከነከነኝ ካለሁበት ከተማ ተነስቼ፣ እርሱ ይህን
ትምህርት አስተምሮባታል ወደተባለችው ከተማ በማግስቱ ተነስቼ ሔድኩ፤ ከዚያም ያስተማራቸውን ሰዎች ማግኘትና ማናገርን እንደመጀመርያ
አማራጭ አድርጌ ወሰድኩ፡፡ የሚያሳዝነው እኛው በቅርብ የምናውቃቸውንና እርሱም “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳለ በወንጌል ያገለገላቸውን
ሰዎች” እንጂ፣ ሌሎችን እንዳላገለገለ ስረዳ እጅግ ነበር ያዘንኩት፡፡ ከዚያም ሲያስተምር የቀዱትን ስብከቱንና “ከእርሱ ጋር አብረውት
የሚያገለግሉትን ይኸንኑ ትምህርቱን የሚያራምዱት” ከእኒህ እህቶችና ወንድሞች ጋር እርሱና ባልንጀሮቹ የተላላኳቸውን የስልክ የጽሁፍ
መልእክቶችን ተመለከትሁ፤ ከዚያም በጋሻው ደሳለኝ በስልክ ሳናግረው ከመለሰልኝ መልስ ጋር አዛመድሁት፤ ፍጹም እንደዋሸኝና ትምህርቱን
በዓላማ እንዳስተማረ ለምን በግልጥ ሊነግረኝ እንዳልፈለገ ማሰላሰል ጀመርሁ፡፡
እናም ትምህርቱንና እርሱ፣ የእርሱ ባልንጀሮች የተላላኩትን የጽሑፍ መልእክቶችን
በተደጋጋሚ ተመለከትኳቸው፤ የትምህርቶቹ ስህተትና አስከፊ ክህደትነት ፍንትው ብለው ታዩኝ፡፡ በድጋሚም በጋሻውን ስለማናገር ወሰንኩ፡፡
እናም ከሁለት ቀናት በኋላ መልሼ ላናግረው ወሰንኩ፡፡ ስንገናኝም በመጀመርያ ትምህርቶቹን አንስቼ ማስተማሩንና አለማስተማሩን ጠየቅኹት፡፡
ማስተማሩን ነገረኝ፤ ባለፈው ግን አለማስተማሩን ለምን እንዳልነገረኝ ስጠይቀው፣ ድምጹም ቃላቱም ተቀይረው አግባባዊነትና ከእርሱ
ፈጽሞ የማይጠበቅ ነበሩ፤ “የቤተ ክህነት ወይም የቤተ ክርስቲያን ተቀጣሪ ስላልሆነ” የሚዋሽበት ምክንያት እንደሌለው በድፍረት ተናገረ፡፡
ነገር ግን እኔም የቤተ ክህነት ወይም የቤተ ክርስቲያን ተቀጣሪ አለመኾኔን፣ ነገር ግን ተቀጣሪ አለመሆኔ እርሱ እያስተማረ ያለውን
የኑፋቄ ትምህርት ለማስተማር መብት እንደማይሰጠኝ በግልጥ ተናግሬ፣ ትምህርቱን ማስተማሩንና በትክክል እንደሚያምንበት ደጋግሜ ስጠይቀውም
አምኖበት የሚያስተምረው መኾኑን በግልጥ ነበር ደጋግሞ የመለሰልኝ፡፡
ከዚያም በኋላ፣ ደጋግሜ ብደውልም ሊመልስልኝ ፈጽሞ ፈቃደኛ ስላልኾነ ይህን
የኑፋቄ ትምህርት ስሙን ጠቅሼ እንደምጽፍ በስልክ መልእክት ብልክለትም ምንም ምላሽ ሊሰጠኝ አልወደደም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ በወኪልነት
የሚከራከሩለት አካላት ይህን ማድረግ እንደሌለብኝ በብዙ ሞግተውኝ፤ እንዳላደርገውም “ማስጠንቀቂያ ቢጤ”ና የእኔን ጀርባ ለማጥናት
ጥቂት መቃተታቸውን አስተውያለሁ፡፡ ከዚህም ባሻገር በእምነት የበረቱ
ሌሎችም ወንድሞችና አባቶች ሊያናግሩት ብዙ ጥረት እያደረጉ እንደኾኑ በመስማቴ የጻፍኩትን ጽሁፍ አዘግይቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱም
ጋር የነበረው ነገር በአሉታዊ መንገድ በመጠናቀቁ፣ በትምህርቱ በመጽናቱና ማስተማር በመቀጠሉ ጽሁፉን ለማውጣት ወስኛለሁ፡፡[እጅግ
ቢዘገዩም አንዳንዶች አሁንም ለማናገር በብዙ እየጣሩ መኾናቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ቢሳካ እጅግ ደስተኛ ነኝ! እንዲሳካም ጸሎትና ምኞቴ
ነው!]
በብዙ የታዘብኩት ነገር ቢኖር፣ ብዙዎች አገልጋይ ሰባኪዎች [የነገረ
መለኮት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሳይቀሩ] ከእርሱ ጋር ያላቸው ባልንጀርነት እንዳይበላሽባቸው ትምህርቱን ክህደት መኾኑን እያወቁ
ዝምታን መርጠው አብረው መኾናቸው ነው፡፡ ይህ እጅግ አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ብዙዎች የሚሰናከለው ሰው ምንም የታያቸው ወይም የብዙዎች
ምእመናን ነፍስ ከአንድ “አገልጋይ” እንደማይበልጥ ቀለል አድርገው ሲያዩት ተመልክቻለሁ፡፡ አንዳንዶችን “ወንጌል ስለመረዳታቸው
ጭምር እጅጉን ተጠራጥሬያለሁ”፡፡ ክርስቶስ ጌታችን ከእኩያ ፍቅር ካልበለጠብን የምንኖረውና የምናስተምረው ለየቅል ነው ማለት ነው፡፡
ማጠቃለያ
በጋሻው ዛሬ በንስሐ ቢመለስና ንስሐውንም በተግባራዊ መንገድ ቢገልጠው፣
በዚሁ የጡመራ መድረክ ለመግለጥ ዝግጁ ነኝ፤ ምክንያቱም እንደሰውነቱ ከበጋሻው ጋር ምንም ጠብ የለኝም፤ የምንቃወመው፤ ትግልና ሙግቴ
እኛው መካከል ተቀምጦ የመዳንን ወንጌል እንሰማለን ብለው ለሚመጡ ምዕመናንና ምዕመናት ከሚያስተምረው ኑፋቄው ጋር ብቻ ነው፡፡ የማልስማማው
ከኑፋቄ ትምህርቱ ጋር ነው! የምቃወመው በጌታችን ኢየሱስ ስም ደሙንና መንፈሱን በማክፋፋቱ፣ በመናቁና በድፍረት ስለተራመደበትም
ነው፡፡
ስለዚህም “የእምነት እንቅስቃሴ”ን በተመለከተ በተከታታይ ትምህርታቸውንና
ኑፋቄያቸውን በወንጌል ቃል እንመዝናለን፤ እንኰንናለንም፡፡ በጋሻውም አሁን በሚሔድበት መንገድ የሚሄድ ከኾነና ራሱን ሰውሮ እንዲህ
ያለ አስነዋሪ ነገር የሚያደርግ ከኾነ ሥራዎቹን ከመቃወም አናቋርጥም፡፡ እውነት ከኾነው ጌታችን ጋር ስለመቆማችን አንዱ ምስክር
የሐሰትን መንገድ ፈጽሞ መቃወማችንን በማሳየት ነው፡፡ ከእኛ ተለይተው በዚህ ትምህርት “ራሳቸውን ከገለጡ” [መሹለክለክን ትተው
በትክክል የቃል እምነታቸው ከተገለጡ] ስማቸውን አንስተን የምንናገርበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ በጠቅላላው ግን በክርስቶስ ላይ
የሚነሣውን የትኛውንም የኑፋቄ ትምህርት እንቃወማለን፤ ለሚያስተምሩት አካላት በሚራራ ልብ ስማቸውን እየጠራን እንጸልያለን፤ እንማልዳለን፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ የሐሰት መምህራንንና ትምህርትን መቃወም የምንችልበትና አቅምና ማስተዋል ያድለን፤ አሜን፡፡
ዋቢ መጻሕፍት
o የኢትዮጲያ መጽሐፍ
ቅዱስ ማህበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ
እትም፤ 2002 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
o ምኒልክ አስፋው፤
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ርእሰ
ጉዳዮችና ተግዳሮቶች፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ራእይ አሳታሚ፡፡
o
ኮሊን ማንሰል (ቄስ) ፤ ትምህርት መንፈስ ቅዱስ 3ኛ እትም፤ 2007 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ
ማተሚያ ድርጅት፡፡
o
ኮሊን ማንሰል (ቄስ)፤ ትምህርት ክርስቶስ 2ኛ እትም፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
o ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፤ የኢትዮጲያ
ሊቃውንት እንደተረጎሙት፤ 1988 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡
o የቅዱስ ጳውሎስ ንባብና ትርጓሜ፤ የኢትዮጲያ ሊቃውንት
እንደተረጎሙት፤ 1988 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ
ማተሚያ ድርጅት፡፡
o
ተካልኝ ነጋ፤ የጸሎት - የንግድ ቤት?!፤ ዓ.ም እና የታተመበት ሥፍራ ያልተጠቀሰ፤ ርኆቦት አታሚዎች የታተመ፡፡
o Charles
E. Hummel, Fire in the Fire Place
(Ivp, 2nd ed,1993)
o ከጸሐፊው ያልታተመ
መጽሐፍ፡፡
o የበጋሻው ደሳለኝ
በአዋሳ የተደረጉ የቃል ስብከቶች፡፡
ወንድማችን በጋሻውን እንወደዋለን ግንእንዲህ መሆኑ ያሳዝናል፡፡እንጸልይለታለን ጌታ ይድረስለት ይህ ከባድ መናፍቅነት ነው
ReplyDeleteErsu gn endih yale tmhrt ket agegne? dimtsu sitefa yet hede eyalkuu asb neber. Egzabher yasbew
ReplyDeleteየእምነት እንቅስቃሴ ትምህርት ግን በብዛት ማንን ነው ሚያጠቃው? ሳስበው አማኞችን ይመስለኛልና ባካችሁ ተጠንቀቁ፡፡ አቤኔዘር በዚህ ዙርያ ካንተ ብዙ እንጠብቃለን በርታ ጌታ ይርዳህ
ReplyDeleteበጋሻው ደሳለኝ ቀስ ቀስ ክርስቶስን የሚያስክድ ትምህርት የሚያሰርፅ ከሆነ ማንም የሚሰማው የለም... እናመሰግናለን ስለጥቆማው!
ReplyDeleteባለፈው ሳምንት በጋሻው ዘንድ ሔደን ከሰማነው ትምህርት አንድ ነው፡፡ በጣም አዝነን ነው የተመለስነው፡፡ እንደውም ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብሐል፡፡
ReplyDeleteአንተ የጌታ ባርያ ድፍረትህ የጌታ ወታደር መሆንህን ያሳያል አደራ ተጠንቀቅ እኒህ ወሮበሎች ካገኙህ አይምሩህም
ReplyDeleteይህን ያህል ግን በሃሳብ መርመጥመጥ ለምን አስፈለገ? ሰውነትን ጥሎ፣ በጥፋት እየባሱ በትዕቢት መታጀል ፍጻሜው አስፈሪ ውድቀት ነው፡፡ ewnet new betam yasznal.Geta Eyesus yirdaw
ReplyDeleteይህን ያህል ግን በሃሳብ መርመጥመጥ ለምን አስፈለገ? ሰውነትን ጥሎ፣ በጥፋት እየባሱ በትዕቢት መታጀል ፍጻሜው አስፈሪ ውድቀት ነው፡፡ ewnet new betam yasznal.Geta Eyesus yirdaw
ReplyDeleteፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥
ReplyDeleteወደ ኤፌሶን ሰዎች 5 : 11Endetebale melkam sra new berta
እንደኔ እምነት በጋሻው ከመጀመሪያው ለስብከት ሲመጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በምታምነውና በምታስተምረው ዶግማም ሆነ ቀኖና ላይ እምነት ያልነበረው እንደነበር እታዘብ ነበር።
ReplyDeleteበዚህ ነገር ተጠልፎ መሄዱ ቢያሳዝንም ነገር ግን ቤተክርስቲያን መምህር ሄደባት ተብሎ ሊነገር አይችልም ፤ምክንያቱም እሱ ቤተክህነቱ ባለበት ውስብስብ ችግር ምክንያት መድረክ ያገኘ ደፋር ተናጋሪ እንጂ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ለማብቃት የምትሰጣቸውን ትምህርቶች አንዱንም ያልተማረ/እሱም አሁን እንደገለጠው/ ተራ ግለሰብ ነው።
ReplyDeletewe have not place for ariyos and begashaw similarly for hom followers.
ReplyDeletewehave not place for ariyos and begashaw similarly for him followers.
ReplyDeleteአደገኛ ሐራ ጥቃ
ReplyDeleteBalefew ጉባኤ esu ga heden neber.ena sewochn eyemeretu yasgebu neber.betam gragebtogn siketatel endaygebu yemikelekelu kalu bye sitebk neber.hulet lijoch simelesu ayehu.timhrtachewm bzu aygebam.botaw lay chuhet yibezal grgr alew betam yasaznal
ReplyDeleteKoy enezih sewoch mekari yelachewm ende
ReplyDeleteEne begashaw eko bzu rikew ayhedum enepiter mading erdata yakomu ken enesum yibetenalu ... lenegeru timhrtachew rasu yemot menged new
ReplyDelete