2.
በጋሻው ደሳለኝ
ተቀባሁበት ያለው “የኢየሱስ ቅባት”?!
መጽሐፍ ቅዱስ ስለቅባት ወይም መቀባት ግልጥና ምንም የማያሻማ ትምህርት
አለው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ነቢያት፣ ካህናትና ነገሥታት እንዲሁም ዕቃዎች ለአገልግሎት ስለመለየታቸውና ስለመሾማቸው በዘይት ይቀቡ
ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር ሥራ የተለዩት የብሉይ ኪዳን የመገናኛው ድንኳንና ዕቃው ተቀብተው ነበር፤ (ዘጸ.30፥22-29)፡፡
“ … ይህንን በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጥ ሰፍሮ እንመለከተዋለን፡፡
እኒህም ካህናት፣ ነገሥታትና ነቢያት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙት በቅዱስ ቅባት ከተቀቡ በኋላ ነበር፡፡ ለምሳሌም፦ ሙሴና ወንድሙ አሮን (ዘጸ.40፥13 ፤ ዘሌ.4፥3 ፤ 8፥1
-9፥1-8 ፤ መዝ.98(99)፥6)፣ አብያታር(1ሳሙ.30፥7 ፤ 1ዜና.15፥11፤ 27፥34)፣ … ካህናት፤ ሙሴ (ዘዳግ.18፥15
፤ ሐዋ.7፥37)፣ ናታን(2ሳሙ.7፥2)፣ ሳሙኤል (1ሳሙ.7፥15-17) … ነቢያት፤ ዳዊት(1ሳሙ.16፥13 ፤ 26፥11 ፤
2ሳሙ.5፥3፤ ሐዋ.13፥22)፣ ሰሎሞን( 1ነገ.1) እኒህና ሌሎችን ብናነሣ ካህናት፣ ነቢያትና ነገሥታት የሆኑትና ሕዝቡን በግልጥ
ያገለግሉ የነበሩት በአደባባይ በቅዱሱ ቅባት ተቀብተው ነበር፡፡ ይኸውም ለተለዩለትና ለተሾሙበት ሥራ በቅዱሱ እግዚአብሔር መለየታቸውንና
ለሥራቸው ብቁዐን አድራጊው በዘይቱ የተመሰለው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መኾኑን በምሳሌነት ያሳያል፤ …” [1]
|
በዚህ ዘመን
የሚነሡ የሐሰት መምህራን “ተቀባሁ ወይም ተቀብቻለሁ” የሚለውን ሃሳብ ይዘው የሚነሱት፣ ስለመቀባት የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ
ክፍሎችን “በሥልጣናዊ ቃልነት” የራሳቸውን ሃሳብ በማስገባት ሊጠቀሙባቸው በማሰብ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከእግዚአብሔር ተምረናል
ብለው የሚናገሩትን ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንቀበላቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእንከንና በሕጸጽ የተከበበውን ትምህርታቸውን “ትክክል
አይደለም” ብለን ብንሞግት፣ “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤” (መዝ.107፥14-15) የሚለውን በመጥቀስ እንዳፈለጋቸው ቢያጠፉና ቢያስቱ ምንም እንዳንናገራቸው፤
“በመቅሰፍታቸው ሊገስጹን” ስለሚፈልጉ ነው፡፡
ሁለቱንም አመለካከቶችና ከማናቸውም ወገን የተሰጠውን ማንኛውንም “ቃሉን
ጠቀስ” ትምህርት እንድንመዝንበት የተሰጠን የቅዱስ ቃሉ መርኅ አለን፡፡ “መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም
ያዙ፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ፤” (1ተሰ.5፥19-22)፣ “ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት
ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ
ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ፤”
(1ዮሐ.4፥1-3) የሚለው ቅዱስ ቃሉ ሁሉንም ነገር በቃሉ መሠረትነት እንድንፈትሽ እንድንመረምር ይመክረናልና ሁሉንም አመለካከቶቻቸውን
ያፈርሰዋል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ “ራሱንና ትምህርቱን ለትችት አጋልጦ”፣
ምናልባት አይሁድ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ካላቸው፣ “ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ
እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም?” (ዮሐ.8፥46) በማለት ተናግሯል፡፡ ራሱ እውነት የኾነ ጌታ፣ ይህን ያህል ራሱን ዝቅ ካደረገና
አይተነው፣ መርምረነው፣ ቀምሰነው… እንድንከተለው ከፈቀደ፣ እንስበካችሁ የሚሉን የዛሬዎቹ “ቅቡዐን” እና ተከታይ አጃቢዎቻቸው ትምህርታቸው፣
ሕይወታቸው፣ … ሁለንተናቸው እንደቃሉ ይመረመር ሲባሉ ለምን ይኾን የሚያኮርፉት?
በመዝ.105፥14-15 ላይ የተጠቀሰው ቃል ፈጽሞ እነርሱን ወይም የሚሉትን
ሃሳብ የሚደግፍ አይደለም፤ “አለመዳሰስ”፣ ሲሳሳቱ አለመወቀስ፣ ሲያስቱ ተዉ! አለመባል አይደለም፡፡ ቃሉ የተነገረው “ለልዩ ሕዝብነት”
ተመርጠው ለነበሩት ለሕዝበ እስራኤል ነው፤ (ዘፍጥ.12፥17-20 ፤ 20፥3 ፤ 26፥11 ፤ 35፥5 ፤ 1ሳሙ.12፥3 ፤ መዝ.9፥5)፡፡
የመነገሩም ምክንያት ለእስራኤላውያን የብርታትና የማደፋፈሪያ ቃል ሲኾን፣ ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደርስት አገር ሲሄዱ በዙርያቸው
ላሉ አሕዛብ ደግሞ እንዳይነኳቸው በብርቱ ማስጠንቀቂያ የተነገረ ቃል ነው፡፡ ለዚህም ነው የአብርሃም ዘሮች[እስራኤላውያን] በቁጥራቸው
እጅግ ጥቂት ቢኾኑም፣ ሁል ጊዜ በሚለዋወጠውና በሚነዋወጠው ፖለቲካዊና ምግባራዊ ሥርዓት ወድቀው ቢታመሱም ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ
በተጽዕኖው ሥር በመውደቅና ፍጹም በመዋረድ ያልተሸነፉት፡፡ እንደቁጥራቸው ማነስ ሳይኾን እንደታላቁ እግዚአብሔር ጥበቃና ትድግና
አልተጎዱም፤ በመቅሰፍትና በሕልምም አስጨናቂዎቻቸውን ነገሥታት “ገስጾላቸዋል”፡፡ በእርሱ ተቀብተው ተለይተዋልና፡፡
ሳዖል የተቀባና ለንግሥና የተለየ ነበር፤ ዳዊትን በክፉ ልብ ተነሣስቶ
ሊገድለው ሲፈልገው ሳለ፣ በአንድ ወቅት እግዚአብሔር ሳዖልን በእጁ ጣለው፤ ነገር ግን ዳዊት፣ “እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር
በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው” (1ሳሙ.24፥6)
በማለት እርሱም፤ ሌሎችም አንዳች ክፉ እንዳያደርጉበት እጅግ ተጠንቅቋል፡፡ ነገር ግን ይኸው ዳዊት ተቀብቶ ንጉሥ በኾነ ጊዜ ሲበድል፣
ሲስት፣ ሲያጠፋ … የሚወቅሰው፣ የሚገስጸው ነቢይ ናታን ከእግዚአብሔር እንደተላከ በመሄድ፣ “ … በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን
ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ … አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ?
ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል፡፡
ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም፤”
(2ሳሙ.12፥7-10) በማለት የተቀባውን ንጉሥ ዳዊትን በተግሳጽ ጠቅጥቆ ተናገረው፡፡
ንጉሥ ዳዊት ይህንን ግሳጼ ተቀብሎም ወዲያው ንስሐ ገብቷል፡፡ አምላኩንም፣
“ … አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፡፡ …ከፊትህ አትጣለኝ፥
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ፡፡” (መዝ.50፥4 ፤ 11) በማለት ፍጹም የንስሐ ጸጸቱን በእንባ በእግዚአብሔር ፊት
አፍስሶ ይቅርታና የእሺታ መንፈሱን ማልዷል፡፡ ናታን ዳዊትን እግዚአብሔር ተናገር ባለው ልክ ምንም ሳይሸሸግ በትክክል ተናገረ፤
ዛሬ ግን በአስባበ ባልንጀርነት የሐሰት ትምህርትንና ኃጢአተኝነትን መሸፋፈን ለምን እንደመረጥን፤ ለምን ለሐሰት መምህራኑም እንደምንከላከልላቸው፣
በሐሰት ትምህርታቸው መጽናታቸውን እያየን ስለእነርሱ ንጽህና ለምን ተሸሽገን እንደምንከራከር ግልጥ አይደለም፤ ምናልባት ከእነርሱ
ዓመጻና ከዓለሙ ጋር በስውር ለመተባበር ያሰብን ይመስላል!!! የሐሰት ነቢያትን መፍራት እንደሌለብን ቃሉ፦ “በልብህም፦ እግዚአብሔር
ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥
ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው፤” (ዘዳግ.18፥21-22) “ተብለናል”፤
ስለዚህ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የኾነ ትምህርትም ቢሆን፣ ማናቸውም ድርጊት ማንም ቢያመጣው የምንቀበለው አይደለም፡፡
በአዲስ ኪዳን ስለመቀባት ካነሣን በግልጥ ቃል ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ
የተነገረለት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ አንደበት፣ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ
ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ …” (ኢሳ.61፥1) ተብሎ የተነገረውን ቃል “የነቢዩንም የኢሳይያስን
መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ …”(ሉቃ.4፥17-19)
በማለት የትንቢቱን ቃል ጠቅሶ፣ “መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት
ነበር፡፡ እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር” (ሉቃ.4፥21) በማለት ለአገልግሎት፣ ለመሥዋዕትነት፣ ቤዛ
ኾኖ አለሙን ሊያድን የተለየ፣ የተሾመ፣ የተመረጠ፣ የተወደደ መኾኑን የተናገረው እርሱ ራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
በሌላ ሥፍራም፣ “በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና
አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ፤” (ሉቃ.4፥27-28)፣ “እግዚአብሔር የናዝሬቱን
ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ
ጋር ነበረና፤” (ሐዋ.10፥38)፣ “ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት
በትር ነው፡፡ ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል፤”
(ዕብ.1፥8-9)፡፡[2]
በሌላ መልኩ ምዕመናንና ምዕመናትም የተቀቡ መኾናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤
(2ቆሮ.1፥22 ፤ 1ዮሐ.2፥20 ፤ 27) የአማኞችን ቅቡዕነት በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን፤ በአንድ መልኩ የተቀበሉትና የተቀቡት[መንፈስ
ቅዱስን የተሞሉት]፣ መንፈስ ቅዱስ ድካማቸውን ያግዛል (ሮሜ.8፥26)፤ አንዳንዴ ግን ከብዙ ተቃውሞና ስደት ባያድናቸውም እንኳ፣
በየአገሩ ዞረው በመሰከሩት ምስክርነታቸው ሁሉ ድፍረትና ሞገስ ይኾናቸዋል፣ በክርክር ድል ነሺና አሸናፊ (ሐዋ.6፥10) ያደርጋቸዋል፣
ወደቤተ ክርስቲያን ብዙ ነፍሳትን እንዲጨምሩ በብዙ የቃሉን ኃይልና ሙላት ይሰጣቸዋል (ሐዋ.6፥7 ፤ 11፥24 ፤ 12፥24)፣ በሌላ
መልኩ ደግሞ አማኞች ተቀብተዋልና የሚነካቸው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተግሳጽ አያመልጥም፤ (ሐዋ.9፥5)፡፡
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምንም ያህል ቢቆረቆር ሲበድሉ ግን አይወቅስም ወይም
ሕዝቡ አይወቀሱም፣ አይነኬ ናቸው ማለት ፈጽሞ አይደለም፤ “ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያው ጴጥሮስን ለአይሁድ ስለማድላቱና ከአሕዛብ ጋር
አብሮ መኾንን ስለማፈሩ ፊት ለፊት ተቃወመው፣ ወቀሰውም፤ (ገላ.2፥11) ደግሞስ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ከሚሠራቸው ዋና ሥራዎች፣
“ስለ ፍርድም ዓለምን መውቀስ፤” (ዮሐ.16፥8) ነው፡፡ ወቀሳው ሁላችንን [አማኞችን ጭምር] እንጂ እንደሐሰት መምህራኑ አባባል
“ያልተቀቡትን ብቻ” የሚል ሃሳብ ፈጽሞ የለውም፡፡ ሁላችን በእርሱ ተቀብተናልና የፍቅርና የ“ከበደላችሁ ተመለሱ፣ በክርሰቶስ ደሙ
ታጥባችሁ ንጹ” የሚለው ወቀሳው ዘወትር ሊያገኘን ግድ ነው፡፡
እንዲሁም፣ “እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤
የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል” (ዮሐ.16፥13)፤ እንዲሁም፣ “እናንተም ከቅዱሱ
ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ” (1ዮሐ.2፥21) እንዲል ምዕመናንና ምዕመናት[ሁሉም አገልጋዮችም ጭምር] መካከል ምንም
አይነት ልዩነት ሳይኖር ከራሱ ከእግዚአብሔር የተማሩና የሚያውቁም መኾናቸውን የምናስተውለው ነው፡፡
ሁለቱም ሐዋርያት፣ “በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን”፣
“እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥” የሚለው ንግግራቸው ሁላችን በአንድነት ክርስቶስ ኢየሱስን በመቀበላችንና በማመናችን የተቀባን
እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ወይም አገልጋዮች በልዩነት የሚቀቡትና ለእነርሱ ብቻ የሚሰጣቸው ነገር ስለመኖሩ ምንም የሚጠቁመን ነገር የለም፡፡
ወደብሉይ ኪዳን አገልግሎት በግድ እንመለስ ካላልን በቀር፣ ለሁላችን በክርስቶስ ኢየሱስ የተደረገልን ነገር እኩልና የአንዳችን ከሌላችን
ፈጽሞ የማያንስ ደግሞም የማይበልጥ ነው፡፡ ጸጋን በተመለከተ ግን ቤተ ክርስቲያንን ስለማነጽ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥራ ስለማስቸኮልና
ስለመሥራት እንጂ ጸጋውን በግል ልንመካበትና በሌሎች ላይ ልንሰለጥንበት አልተሰጠንም፤ አይሰጠንምም፡፡ ጸጋ ኃላፊነትና አደራ እንጂ
ሌላውን እንበልጥበት ወይም እንድንበልጥበት የተሰጠ አይደለም፡፡
ደግሞም ከፍጡር ወገን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀባበት መንገድ ሊቀባ የሚችል
ማንም የለም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀባ ስንል ግን፣ “ብቃት ያለው አዳኝ” ስለመኾኑና ከእርሱም በቀር በዚህ ቅባት ሊቀባ
የሚችል እንደማይነሣ መጽሐፍ ደምድሞ ነግሮናል፡፡ በጋሻው “ኢየሱስ በተቀባበት በደስታ ዘይት”[በቅርቡ ሲናገር እንደሰማነው ደግሞ
በበቀል ቅባት[3]]
ተቀብቻለሁ ሲል ሰምተነዋል፡፡[4]
ለመኾኑ ክርስቶስ ራስ በኾነባት ቤተ ክርስቲያን ራሳችንን እንደልዩ አድርገን ማቅረብና መናገር ለምን አስፈለገ? “ክርስቶስ ኢየሱስን
ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን” (2ቆሮ.4፥5) እንዲል፣
ለምዕመናን “የኢየሱስ አገልጋይ ነን” ማለት ምነው የሞኝነት [“ወፍራም ቅባት” በሚያሳድዱት ዘንድ እንደሚባለው “እንደደረቅና ሞገስ
እንደሌለው ቀጭን ቅባት”] ያህል ለምን ተቆጠረ? አዎን! እኛ እንኳ “ተቀባን” ስንል የመቀባታችን ምስጢር አንዳችን ከሌላችን ሳንበላለጥ
ከቤተ ክርስቲያን ራስ ጋር በአካልነት አንድ ኾነን ስለመስማማታችንና ስለመሠራታችን እንጂ(1ቆሮ.12፥13) ስለሌላ ስለምንም ምክንያት
አይደለም፡፡
“ኢየሱስ በተቀባበት የደስታ ቅባት ተቀባሁ” የሚለው ንግግር ከልክ ያለፈ
ትዕቢትና ዓመጻ ከመኾን በቀር ምንም ሊኾን አይችልም፡፡ ፈቃዱን ለመፈጸም በክርስቶስ የሥጋ ሞትና ትንሣኤ የጸደቅንና በፊቱ የቀረብን
ልጆቹ መኾን በቂያችን፤ የአምልኮና ምስጋና ዋና ርዕሳችን ነው፤ ይህ በትክክል ከገባንና በልባችን ሞልቶ ከፈሰሰ፤ መንፈስ ቅዱስም
በጸጋው ከደገፈን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ለአባቱ፣ ለመንፈስ ቅዱስም የፈቃድ ባርያዎቹ፤ ፈቃዱን ፈጻሚ አገልጋይ ልጆቹ ነን፤
አዎን! “እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ”
(ሉቃ.17፥10) ብሎ ጌታችን ኢየሱስ እንደነገረን እንዲህ ባለ መታዘዝ እናምናለን፤ እንታመናለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
[3]
ለመኾኑ የበቀል
ቅባት ምንድር ነው? እንዲህ የሚል ትምህርት ከየትኛው መጽሐፍ ቅዱስ ይኾን የተቀዳው? በቀል ክፋትንና ብድራትን መመለስ ነው፤ ሶምሶን
ሊበቀል ቢነሣ (መሳ.15፥7) በእርሱ ድካም እግዚአብሔር ዐላማውን ሊፈጽም ቀድሞ አስቦ ነው፤ (መሳ.14፥4)፤ በኋላም ፍልስጥኤማውያንን
የተበቀለው በእግዚአብሔር ክንድና ስለቀደመው ዓላማው ነው፤ (16፥28)፣ የእስራኤል ልጆች ምድያማውያንን ቢበቀሉ በራሱ በእግዚአብሔር
ታዝዘው ነው፤ (ዘኊ.31፥1)፡፡ ኢዩ ኤልዛቤልን እጅግ ቢበቀል (2ነገ.9፥30-37) አክዓብ፣ “በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት
ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም” እንደተባለ፣ በአልዛቤል ሃሳብና ዕቅድ
ፈጽሞ በመሔዱ ምክንያት በእርሱና በቤተሰቡ ላይ ከባድ ነገርን ሊያመጣ እንዳለ ቀድሞ ስለተናገረ ነው(1ነገ.20፥24 ፤ 29)፡፡ እኛ ግን እንድንበቀል አልተባለልንም፤
የበቀል አምላክ ወይም በቀልን የሚመልስ[የሚበቀልልን] የተባለ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ “በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን
ሰው እኔ እበቀልለታለሁ” (ዘዳግ.18፥19)፣ “በቀልና ፍርድ የእኔ ነው” (ዘዳግ.32፥35)፣ “በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥
አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥” (2ሳሙ.22፥48)፣ “እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው፤ የበቀል አምላክ ተገለጠ” (መዝ.94፥1)፣
“አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው” (መዝ.99፥8)፣ “የበቀልንም
ልብስ ለበሰ” (ኢሳ.59፥17)፣ “እነሆ፥ እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤” (ኤር.51፥36)፣ “ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ
አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” (ሮሜ.12፥19)፣
“በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል” (ዕብ.10፥30) … እኒህና
ሌሎችም ምንባባት በቀል የእግዚአብሔር እንደኾነ ብቻ ነው፤ በተለይ በአዲስ ኪዳን እኛ የታዘዝነው ጠላቶቻችንን መውደድ፣ ለእነርሱም
ቸርነት ማድረግ፣ መራራት እንዳለብን ነው፤ (ማቴ.5፥44 ፤ ሮሙ.12፥20)፡፡
አንዳንዴ ተገዳዳሪዎች ቢነሡብንና ተቃውሞዓቸው እጅግ ቢበረታብን፣ የእግዚአብሔር
በቀል ባስጨነቁን ላይ እንድትደርስ መጠየቅ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፤ (መዝ.18፥47 ፤ 69፥22 ፤ ራእ.6፥10፤
19፥1) እንጂ ራሳችን የምንበቀልበትን “ዘይት” የምንቀባበትን ትምህርት ከየትም ልናገኝ አንችልም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እንኳ ስለስሙ
መከራን ተቀብለው፣ ታስረው፣ ተሰድበው፣ ተዝቶባቸው(ሐዋ.4፥20-23) “የበቀል ቅባታቸውን” መዥረጥ አድርገው ተቃዋሚዎቻቸውን፣
ያሠሯቸውን፣ የዛቱባቸውን አልተበቀሉም፤ ግን ወደእግዚአብሔር፣ “ … በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ፦ አሕዛብ
ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ
ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ፡፡ … አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው
ተመልከት፤” በማለት ነበር የጸለዩት፤ (ሐዋ.4፥24-31)፡፡ እናም የእግዚአብሔር በቀል በኃጢአተኞች ላይ የሚገለጠው እንደጽድቁ
ነውና ሥራቸውን በትክክል ይመልስላቸዋል፤ (ዘዳግ.32፥35) የዚያን ጊዜም፦ “ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል፤” (መዝ.58፥10)
የተባለው ቃል ይፈጸማል፡፡ ስለዚህም በቀል የእግዚአብሔር ብቻ እንጂ የፍጡር እጅ የለበትም፡፡ ምናልባት ደግሞ ሌላ ጥግ ለመያዝ
ታስቦ፣ “የምበቀለው ዲያብሎስንና ኃጢአትን ነው” ሊሉ እንደሚችሉ አስባለሁ፤ ይህም ቢኾን ዲያብሎስንና ኃጢአትን ያሸነፈው ራሱ ጌታ
ኢየሱስ ነው፡፡ [ስላሸነፈም የማሸነፉን ክብርና ሥልጣኑን መውሰድ ያለበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው!!!] ስለዚህም በክርስቶስ
ኢየሱስ በቤዛነቱ ሥራ የተደረገልንና በእርሱ ድል መንሣት ውስጥ ገብተን በማመናችን የተቆጠረልን እንጂ እኛ “የምንበቀለው በቀል”
አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ የአሕዛብ ሐዋርያ ኾኖ ሲላክ ወደአሕዛብ ሁሉ የሄደው በፍቅርና በሚራራ ልብ እንጂ ፈጽሞ በበቀል
ልብ አልነበረም፡፡
[4]
የእምነት ቃል እንቅስቃሴ መምህራን እንዲህ ባለ ራስን ከክርስቶስ ጋር
በሚያስተካክል ትምህርት ተውጠው እናገኛቸዋለን፤ ለምሳሌም፦ ኬኔት ኮፕላንድ “መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበት ጊዜ ኢየሱስ “እኔ ነኝ”
በሚልባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ፈገግ ብዬ “አዎን፤ እኔም ነኝ እላለሁም” ብዬ እመልሳለሁ” ብሎ በግልጥ ሲነገር፣ ቤኒ ሄን ደግሞ፣ “ክርስቲያን
ነን ስንል እያልን ያለነው መሲሕ[ኢየሱስ ክርስቶስ] ነን ነው፤ አማኝ ከኾንህ ሰው ብቻ መኾን አትችልም” በማለት እኒህና ሌሎችም
የእምነት እንቅስቃሴ የሐሰት መምህራን በዓመጻ ቃል ሲናገሩ ሰምተናቸዋል፡፡ ልንዘነጋ የማይገባው እውነት ቢኖር ግን በክርስቶስ አዳኝነትና ቤዛነት የምናምን
ሁላችን በዚህም መድር ኾነ በላይ በበጉ ሰማይ የበጉ ደቀ መዛሙርት፤ በጉን አምላኪዎችና በጉን አመስጋኞች እንጂ እንደበጉ ተመላኪና
ምስጋናን ተቀባይ በፍጹም አይደለንም!!!
wendeme betam tiru sra new. berta abo
ReplyDeleteጸጋ ይብዛልህ በጥሩ ትብ ብዕርህ አንቅተኸናል አስጠንቅቀኸናል
ReplyDeleteአንተ ራሱ የሱ ቢጤ ቀጣፊ ነህ እና ምን ይጠበስ??????
ReplyDeleteBegashaw bimar yishalew neber alememar kifu new. Agelgay eyetseleye simar yadgal. Alya endih mewdek ale. Egzaber yirdw
ReplyDeleteYigermal yeSilase theology collage temariwoch eskekirb gize dres eza esu ga yemihedu alu.kepentewochm ga metaw esu ga mimaru alu. Nigigiru bzu gze yekurat new. Yegeremegn lela neger በሪሁንና ያሬድ አጭሩ ከሱ ሲለዪ አላይም፡ ያሬድን ጉርሱም ባቢሌ ሐረር ለቲያንሽ ሥራ ሲመጣ ያስተምረን ነበር ግን ትምህርቱ አዲስ የማናውቀው ነበር ለካ ይህን ትምህርት ሲለማመድብን ኖሯል፡ አዲስ አበባም መጥቼ ሳገኘው ያንኑ ትምህርት ደጋግሞልኝ ነበር አሁን ነገረ ስራቸው ገባኝ፡፡ አቡbetam amesegnalew tru tmhrt new yastemarkegn berta gursumna babile yalutn lijochm astawsachew endaytalelu enem negerachwalew tebarek
ReplyDelete