ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፦ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ
ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ፡፡”
(ኤር.13፥23) በማለት፣ ስለይሁዳ ኃጢአት በከባድ ወቀሳ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ይሁዳ ተጠራርጋ በእግዚአብሔር ፍርድ
ልትጠፋ እንዳለች በእግዚአብሔር ስለተረዳ፣ ሚስትን ከማግባትና ልጆችንም ከመውለድ ተከልክሏል፤ (ኤር.16፥1-4)፡፡ ትዳር
ብቻም ሳይኾን ወዳጆቹም እጅግ ጥቂቶች ነበሩ፤ አኪቃም (26፥24)፣ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስና (39፥14) ኢትዮጲያዊው
አቤሜልክ ናቸው (38፥7)፤ የክፋቱ ጠጣርነት ከሰው በብዙ ስላገለለው ረጅም ዘመኑን ያሳለፈው በሐዘን ነው፡፡
የይሁዳ ኃጢአቶች የተገለጡና ለኹሉ የታዩ ነበሩ፤ “ይሰርቃሉ፥
ይገድላሉ፥ ያመነዝራሉ፥ በሐሰትም ይምላሉ፥ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ይገፋሉ፥ በቅዱሱም ስፍራ ንጹሕ ደምን ያፈስሳሉ፥
ስሙም በተጠራበት በቤተ መቅደሱ በፊቱ ቆመው፦ ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም ብለው ይክዳሉ፣ ስሙ የተጠራበት
ቤት በዓይናቸው ፊት የሌቦች ዋሻ አደረጉት፣ የቀደሙት አባቶቻቸው እግዚአብሔርን ተዉ፣ አመነዘሩ፣ አማልክት ያልሆኑትን ለራሳቸው
አማልክትን አድርገው፣ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም፥ ያስቈጡትም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል
አጠኑ፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን አፈሰሱ፣ ሕጉንም አልጠበቁም፤ እንዲኹም እነርሱም ከአባቶቻቸው ይልቅ ክፉ
አድርገዋል፤ እነሆም፥ ሁላቸውም እንደ ክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄደዋል እርሱንም አልሰሙትም” (7፥1-11፤ 16፥11፤ 20፤
22፥9፤ 23፥10፤ 32፥29፤ 44፥2፤ 23)፡፡ በዚህ ኃጢአታቸው እግዚአብሔርን ፈጽመው አስቆጥተውታል፡፡