Thursday, 7 December 2017

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፮


Please read in PDF
የእምነት ቃል አገልጋዮች የሰውን ሰው-ነት ለመካድ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች
   መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሥጋም መኾኑን ቢናገርም፣ የቃል እምነት አገልጋዮች ግን ይህን እውነት ከዓውድ ውጪ አጥምመው “ሰው መንፈስ ነው ለማለት” የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች አሏቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን ከዚህ በታች እያነሣን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ እንሰጥበታለን፡፡
·        ፍ.1፥26-27 እና 2፥7፦ እኒህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ተመልክተናልና የቀደሙትን ክፍሎች እንድትመለከቱ በመጋበዝ አልፌዋለሁ፡፡ “ሰዎቹ” ሰውን “መንፈስ ነው” ለማለት ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል መኾናቸውን ግን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡
·        ሐ.3፥1-13፦ ሰውን አመናፋሾቹ የሐሰት መምህራን ከዘፍጥረት መጽሐፍ ቀጥለው የሚንደረደሩት ወደዚህ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ እንግዲህ ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዓውዳቸው ለማያጠና ተማሪ፣ “እምነትና በጎ ሕሊናውን ያስጥሉታል፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር እንዲጠፋ ያደርጉታል፤” (1ጢሞ.1፥19)፡፡ ስለዚህ “ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ እንደማይችሉ ሞኞች ሴቶች፣ ከተነዳላቸው ወደየሞት ወጥመዳቸው ሰተት አድርገው ያስገቡታል፤ እኛ ግን ስለምንሰማው ነገር ልንጠነቀቅ፤ ባለማስተዋልም ልንዘለል አይገባንም፤ (2ጢሞ.3፥6-7)፡፡

    ቅዱስ ዮሐንስ እያስተማረን ያለው ስለዳግም ልደት ነው፤ (ዮሐ.3፥1-13)፡፡ ትምህርቱ የተሰጠው ለአይሁድ ሊቅ ለነበረው ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ከጌታችን ኢየሱስ የሰማው የዳግም ልደት ትምህርት ግራ አጋብቶታል፡፡ ጌታችን ከላይ መወለድን ከሥጋዊ ውልደት ጋር ነጥሎ በማንሳቱ ደግሞ ይበልጥ አልገባህ አለው፡፡ ዳግማዊው ልደት ከቀዳማዩ ልደት እኩል፣ በሥጋ ከእናት አባት እንደምንወለደው መስሎትም፣  “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” (ዮሐ.3፥4) ጥያቄን አንስቷል፡፡
     ጌታችን ግን ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ሥራ እንጂ ከሰው አለመኾኑን በነፋስ ምሳሌ አስረድቶታል፡፡ የነፋስ አመጣጡ እንደማይታወቅ ነገር ግን ሥራው እንደሚታይ እንዲሁ፣ ከመንፈስ ቅዱስም መወለድ እኛ አናውቀውም፤ ጌታችን ኢየሱስን አምነን (ዮሐ.1፥12፤ ሮሜ.8፥16፤ ገላ.3፥26)፣ ሕይወታችንን አሳልፈን በመስጠት በተጠመቅን ጊዜ መወለዳችንን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይመሰክርልናል፤ ከመንፈስ ተወልደናልና መንፈሱ ይመሰክርልናል፤ (ሮሜ.8፥16)፡፡
    ከቀዳማዊው ልደትና ኑሮ ባሻገር፣ አዲስ የኾነ ዳግመኛ ልደትና ቅዱስ ኑሮ ያለን መኾኑን ጌታችን ኢየሱስ ተናገረ፡፡ ዋናውና የታሰበልን ዓለም በቀዳማዊ ልደት የምናየው አይደለም፤ ዋናውና ጌታ ያዘጋጀልን ዓለም በዳግም ልደት የምናየውና የምንኖርበት ነው፡፡ ያ ዓለም ግን ክርስቶስን በማመን የምናገኘውና በዚህ ምድር በመኖር የምንለማመደውም ነው፡፡ በዚህ ዓለም ዳግም ተወልደው የኖሩለት ልጆቹ ብቻ ናቸው፣ በሰማያትም የሚያከብሩትና የሚያመልኩት፡፡ በክርስቶስ ቤዝወት አምነን ልጆቹ መኾናችንና ከመንፈሱ መወለዳችን ግን ሰውነታችንን አያስጥልም፡፡
    “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን” (ቲቶ.3፥5) እንዲል፣ ሲያድነን ከአሮጌው የኃጢአት ሕይወት በመውጣት በሚያስመሰክር ሕይወት እንኖር ዘንድ ድነናል ወይም ተወልደናል፡፡ የሕይወት ሽግግራችን በሥጋና በነፍስ(መንፈስ) እንጂ በመንፈስ ብቻ አይደለም፤ (2ቆሮ.5፥17፤ ገላ.6፥15፤ ኤፌ.4፥23)፡፡ አስተውሉ ኃጢአተኝነትን የሚክደው(ቲቶ.2፥12)፣ ዳግም የሚወለደው የሰው-ነት ሁለንተናችን ነው፡፡ ስለኾነም ነው፤ ሥጋ ኃጢአትን የኑሮ ዘይቤ እንዳያደርግ የተከለከለው፤ (ገላ.5፥19፤ 1ዮሐ.3፥9)፡፡
    ይህን ክፍል ለጥጠው ሲያስተምሩም፣ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፤” (ዮሐ.4፥24) ከሚለው ሃሳብ ጋር በመስፋት፣ መንፈስ ነንና ለእግዚአብሔር የምንሰግድለት በመንፈስ ነው በማለት ያስተምራሉ፡፡ ዮሐ.4 ላይ ያለው እውነተኛ አምልኮ በቦታ ሳይወሰኑ ከመንፈስ ቅዱስ በኾነ ማንነት፣ በምን ዓይነት ግንኙነት ሊፈጸም እንደሚገባና አንድ ሰው በፍጹም ቅንነት ከመንፈስ ቅዱስ በኾነ ትጋት አምልኮውን ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባው ለማመልከት የቀረበ መኾኑን ከዓውዱ እናስተውላለን፡፡ ስለዚህም ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በየራሳቸው ዓውድ ሲጠኑ፣ የእነርሱን ሃሳብ ፈጽሞ የማይደግፉ መኾናቸውን እናስተውላለን፡፡
·        2ጴጥ.1፥4፦ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን፤”(2ጴጥ.1፥4)፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የቃል እምነት መምህራን “የመለኮትን ባሕርይ ከመካፈል ይልቅ ሙሉ ለሙሉ መኾናቸውን” ይናገራሉ፡፡ “ተካፋዮች” የሚለውን ቃል አይቀበሉትም ወይም መካፈልን አያመለክትም፣ ሙሉ ለሙሉ መኾንን እንጂ ብለው ፈጽመው ይክዳሉ፡፡ የቃሉ ዓውድ ከእነርሱ በተቃራኒ የቆመ መኾኑን ምንም ክርክር የለውም፡፡
    ቅዱስ ጴጥሮስ እያስተማረን ያለው፣ ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ውስጥ ካለው ዓለማዊና የጥፋት ሕይወት በማምለጥ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንዲኾኑ፣ “በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን” ሰጥቶናል፡፡ ከመለኮቱ ባሕርይ ተካፋዮች እንኾን ዘንድ የጸጋን፣ የኃጢአት ይቅርታን፣ ከመንፈስ ቅዱስ የኾነ የአዲስ ሕይወትንና የእግዚአብሔር ልጅነትን ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ይህ ታላቅና የከበረ ነገር የተሰጠን በቅድስና እንመስለው፣ ይኸንኑ ባሕርይውን እንካፈል እንጂ መለኮትን እንኾን ዘንድ አይደለም፡፡ አዎን! የተሰጠንና እንድንኖርለት የሚገባን ነገር አለ፤ ከቅድስናው ባሕርይው እንካፈል ዘንድ የሚያስችለንን ጸጋ፣ መለኮታዊ ኃይሉን ይሰጠናል፤ (ኤፌ.3፥20፤ ፊል.2፥13፤ 4፥13)፤ በእውነትም መንፈሳውያን እንኾን ዘንድ ከርኩሰት ሁሉ ያስመልጠናል፤ (1ተሰ.4፥7)፡፡
   “ባህርይ”፣ በዚህ ክፍል ዕድገትንና ያለንበትን ሁኔታ [ስብእና ወይም ጠባይን] ለመግለጥ ተጠቅሷል፡፡ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስለሚያድር፣ ኃጢአትን የማድረግ ዝንባሌ አይኖራቸውም፤ (ዮሐ.14፥17፤ 1ዮሐ.3፥9)፣ ኃጢአተኞች ግን ኃጢአትን የሚያደርጉት በውስጣቸው ካለው የኃጢአት ባሕርይ የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች እንዲህ ካለ እግዚአብሔር ከሚጠየፈው የኃጢአት ዝንባሌ በመራቅ ወይም በማምለጥ፣ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ በሰማያዊ ቅዱስ ጥሪ ይጠራሉ፡፡ ደግሞም እንድንካፈለው የተባለልን ነገር አለን፣ እርሱ፦ “ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል” (ዕብ.12፥10)፣ መከራውንም አብረን እንካፈል ዘንድ ይገባናል፣ (1ጴጥ.4፥13፤ 5፥1)፡፡ ስለዚህም ከዓለማዊ ርኩሰት አምልጠን የቅድስናውን ባሕርይ ተካፍለናልና እንደእርሱ በተመሰከረለት ጽድቅ ልንመላለስ ይገባል፡፡
    የቃሉ ዓውድ በትክክል እንዲህ ሊታይ ሲገባው፣ በድፍረት ቃል ራሱ እግዚአብሔርን ወደመኾን ለማደጋችን ማስረጃችን ነው ብሎ መጥቀስ የራስን መሻት ከመናገር አይዘልም፡፡ ምክንያቱም እኛ መቼም ቢኾን ሰውነታችንን ጥለን መለኮታዊ አካል ወይም ባሕርይ አንለብስም፤ በዚሁ የሰውነት አካልና ባሕርይ በሰማያትም የምንቀጥል መኾናችንንና አካላዊ ማንነት ያለን መኾኑን ጌታችን ኢየሱስ፣ “በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም” (ማቴ.22፥30) በማለት አስተምሮናል፡፡
·        ሜ.8፥28-29፦ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፤ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና...”፡፡ እኛ መንፈስ ወይም ጌታ ኢየሱስን እንመስላለን ተብለው ከሚጠቀሱት ጥቅሶች አንዱ ይህ ነው፡፡
    በተለምዶ፣ “ነገር ሁሉ ለበጎ ነው”፣ እየተባለ በግንጥል፣ አለቦታው ከሚጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጥቅሶች አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን “ነገር ሁሉ ለበጎ ነው”፣ የሚለው ቃል እውን የሚኾነው፣ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት” ታዛዥ ልጆቹ ብቻ ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ለአማኞች ያለው የመጨረሻ ዓላማም የልጁን መልክ እንድንመስል ነው፡፡ እርሱ ገና በእጆቹ ከመሠራታችንና ከመፈጠራችን በፊት ያውቀናል፡፡ ከመጀመርያውም ለእያንዳንዳችን እግዚአብሔር ዓላማና ዕቅድ ነበረው፤ (ኤፌ.1፥4)፡፡
   እግዚአብሔር፣ ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስን እንድመስል ታላቁን ሥራውን የጀመረው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልክ እንዳመንን ነው፡፡ በማናቸውም መከራና ስደት ውስጥ ብናልፍም፣ አስቀድሞ የመረጠን ልጆቹን ሁሉ እግዚአብሔር የልጁን መልክ እስክንይዝ ይሠራናል፡፡ እርሱ ሠሪያችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ወደመንግሥተ ሰማያት እስክንሄድ ድረስና በመንግሥተ ሰማያት በመንፈሳዊው አካል ሰውነታችን እስኪገኝ[እስከፍጽምናችን ድረስ] በውስጣችን ያለመታከት ይሠራናል፡፡
    የልጁን መልክ የመያዛችን ዋናው ምክንያም ክርስቶስ ባመኑት ልጆቹ መካከል እንደበኩር ይታይ ዘንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ትልቁ ዓላማም ሁላችን “የክርስቶስ ወንድሞች” እንኾን ዘንድ ነውና፡፡ በብዙ ወንድሞች መካከል ደግሞ ክርስቶስ እርሱ በኩር ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የክርስቶስ በኩርነት ባለቤትነቱን፣ ምንጭነቱን፣ የሁሉ ነገር ጀማሪነቱን፣ ከሁሉ በፊት ዘላለማዊ ኗሪነቱን ለማመልከት የተነገረ ነው፡፡
    “ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን” (1ዮሐ.3፥2) እንዲል፣ አሁን ክርስቶስን በትክክል ባንመስልም፣ የእግዚአብሔር ልጆች መኾናችንን እናውቃለን፡፡ እርሱ ሲመጣና ወደራሱ ሲወስደን ግን የዚያን ጊዜ የእርሱን መልክ በትክክል እንይዛለን፤ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤” (2ቆሮ.3፥18) እንዲል፣ ክብሩም በውስጣችን ይገለጣል ይላል እንጂ እርሱን መኾንን ወይም ሰውነትን መጣልን ፈጽሞ አይናገረንም፡፡ አሜን ማራናታችን ኢየሱስ እንዲህ ባለ ክብር እንድትመጣ ና! ቶሎ ና! ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኾነን እንጠራሃለን፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል …

7 comments:

  1. የልጁን መልክ የመያዛችን ዋናው ምክንያም ክርስቶስ ባመኑት ልጆቹ መካከል እንደበኩር ይታይ ዘንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ትልቁ ዓላማም ሁላችን “የክርስቶስ ወንድሞች” እንኾን ዘንድ ነውና፡፡ በብዙ ወንድሞች መካከል ደግሞ ክርስቶስ እርሱ በኩር ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የክርስቶስ በኩርነት ባለቤትነቱን፣ ምንጭነቱን፣ የሁሉ ነገር ጀማሪነቱን፣ ከሁሉ በፊት ዘላለማዊ ኗሪነቱን ለማመልከት የተነገረ ነው፡፡geta yihn endnastewl yirdan

    ReplyDelete
  2. የክርስቶስ ወንጌል የብልፅግና ወንጌል ነው!!!
    ከመንቀፍ እውነቱን ሟወቅና ባወቁት እውነት መኖር:
    ወንጌል ብልፅግና ነው!!
    ‘‘አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ
    ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል።’’ # ማቴ . 6፥33
    በዚህ ቃል ውስጥ ሁለት ነገር አለ።
    አንደኛው የእግዚአብሔር መንግስት፣ ሁለተኛው የእግዚአብሔር
    ጽድቅ።
    በክርስቶስ ስትሆን የእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትገባለህ።
    ጽድቅ ደግሞ በእምነት የምትቀበለው የራስህ ያልሆነ
    የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው።
    ሮሜ. 10፥3-10 ‘‘የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም
    ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።
    ……….. ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል…’’ ሮሜ. 3፥21-22 ‘‘አሁን
    ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ
    ህግ ተገልጧል እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ
    በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው’’
    በአዲስ ኪዳን የተገለጠው ጽድቅ የራሱ የእግዚአብሔር ጽድቅ
    ነው። ስለዚህ በክርስቶስ ስትሆን የትንሳዔው መንፈስ ይሰጥሃል
    ይህም በውስጥህ ያለው ከእግዚአብሔር የተወለደው አዲሱ
    ሰው ነው። አዲሱ ሰው ብሩክ፣ ባለጸጋ፣ ጤነኛ፣ ጻድቅ ነው።
    ጽድቅ ከእግዚአብሔር በመወለድ የተካፈልነው ማንነት እንጂ
    መልካም ሰርተህ የምትቀበለው ስም አይደለም።
    ወንጌል የባለጠግነትም አሊያም የድህነትም ጉዳይ አይደለም።
    ወንጌል የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በመስቀል የሰራው ስራ
    ጉዳይ ነው። በዚያ ዋጋ መክፈል ውስጥ ታዲያ የተሻሩ አሊያም
    የተሸነፉ ነገሮች አሉ። ልክ እንደ ኃጥያት፣ እንደ ሞት፣ እንደ
    ሴጣን ስልጣን፣ እንዲሁ ድህነትም፣ በሽታም ተሽሮአል፣
    ተሸንፎአልም። ብሩክ የተባለው ማንነትህ እንጂ ኪስህ ወይንም
    ጤንነትህ አይደለም። ወገኖቼ ባለጠግነት የብር ጉዳይ ወይንም
    ብዙ ሃብት የማከማቸት ጉዳይ አይደለም። ሰው ብርም ይዞ ድሀ
    ሊሆን ይችላል። ባለጠግነት ትርጉሙ ፍሬያማ አይምሮ፥ የልብ
    መከናወን ስለሆነ ነው።
    ገንዘብ፣ ጤንነት፣ ስኬት እንደ አህዛብ የምንከተለው ክብራችን
    ሳይሆኑ እኛን የሚከተሉን ተጨማሪ ነገሮች ናቸው። እግዚአብሔር
    ባለጠግነት ልታገኝ የምትችለው በዚህ በኩል ብትሄድ ነው
    ይላል፤ ዓለም ደግሞ ባለጠግነትን ማግኘት የምትችለው በዚህ
    በኩል ብትሄድ ነው ትላለች። በሁለቱ መካከል ደግሞ ትልቅ
    ልዩነት አለ። አለም ማንነትን ነጥቃ ገንዘብን ትሰጣለች፤ ይህ
    ደግሞ ትልቅ ውድቀት ነው። ሰው ሊረዳው የተገባው ነገር ቢኖር
    የሰው ልጅ ክቡር እንደሆነ ነው። እናንተ ከብር፣ ከወርቅ፣
    ከአልማዝ ወይንም ደግሞ በዚህ አለም ላይ አለ ከሚባል ነገር
    ሁሉ ይልቅ ውድና ክቡር ናችሁ። ጌታ ኢየሱስ ሲናገር ‘‘ሰው
    አለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል’’
    አለ። ምንም አይጠቅመውም። ስለዚህ ከብር ወይም ከወርቅ
    ይልቅ የከበርን ስለሆንን ባለጠግነት ልንከተለው ወይንም
    ልንገዛለት የሚገባ ነገር ሳይሆን ሊከተለንና ሊፈልገን የሚገባው
    እርሱ ነው። ጌታ ‘‘አህዛብ እንዲፈልጉት እናንተም በእነርሱ
    መልክ አትፈልጉት ማስቀደም ያለባችሁን ካስቀደማችሁ እነዚህ
    ሁሉ ይከተሏችኋል’’ ብሏል። ይህም ማለት ክርስትና
    ከድህነትም፣ ከብልጽግናም፤ ከበሽታም፣ ከጤንነትም
    አይጀምርም ማለት ነው።
    ጤነኛ የምትሆነው በክርስቶስ ጤነኛ ስለሆንክ ነው ።
    ባለጸጋ የምትሆነው በክርስቶስ ሙሉ ስለሆንክ ነው።

    ReplyDelete
    Replies
    1. የፌስቡክን አስተያየት ወዲህም ማምጣቱ አግባብ ከኾነም የዚያኑ መልስ እዚህም ይኸው፤ ጥቅሶች ከዓውዳቸው ወጥተው እንዲህ ሲተረጎሙ የገዛ ሀሳብን እንጂ የቅዱስ ቃሉን ሀሳብ እንደማያውቅ ጤናማ ትምህርት ያለው አይስተውም፡፡ እንጂማ ብልጥግናን እንዳልተጠየፍን እንዳልተጠየፍን፤ ፈጽመን እንዳላናናቅን ዳሩ ግን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ስለእላቂ ጨርቅና ለድቃቂ ሳንቲም ብለን እነደማንሰብክና እንደማናስቀድመውም ከእግዚአብሔር የኾነ ብቻ እንዲሰማን እናውቃለን፡፡
      ጤና ባይኖረኝም እንደቅዱስ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ጥሮፊሞስ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ፣ ጻድቁ ኢዮብ ...፤ ድኅ ብኾንም እንደድንግል ማርያም፣ እንደድንኳን ሰፊው ጳውሎስ ... ደግሞም ጤና ቢበዛልኝ፣ ሀብት ቢትረፈረፍልኝ ...ሁለቱም ሁኔታዎች ከክርስቶስ ጌታዬ ጋር ላለኝ ግንኙነት የሚጨምሩት፤ የሚቀንሱት አንዳች ነገር የላቸዉም፡፡ ቢኖረኝም ባይኖረኝም፤ ቢጎድልም ቢመላም ክርስቶስ ጌታዬን በምልአቱና በሁሉን ቻይነቱ አውቀዋለሁ፤ አምነዋለሁ፡፡ የሚገርመኝ ነገራችሁ ወዲህ ሰው መንፈስ ነው ትሉና ትመናፈሳላችሁ፤ ወዲያ ደግሞ ሥጋን ማምለክና ማግነን ስትፈልጉ ደግሞ የአለሙ ብልጥግና የኛ ነው ብላችሁ ትንጫጫላችሁ፡፡ ደግሞ ምድራዊ ብልጥግና ለመንፈሳችን ነው እንዳትሉና እንዳልስቅ¡¡ ብትሉስ ትንሣኤ ሙታንን አታምኑ ነገር ምን ገዶኝ፡፡

      Delete
  3. የነበጋሻው ደቀመዛሙርት ራሳቸውን በዚህ ትምህርት በደንብ እየገለጡ ነው፡፡ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡ በባለፉት ጊዜያት ብቻ ከየአገራቱ ልጆች ጠርተው በክፉ ትምህርታቸው የአመራረዝ ስልጠና ሰጥተዋቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ክፉዎች ናቸው፡፡ አሁንም ራሳቸውን በወንጌልምክንያት እንደተገፉ ይቆጥራሉ፡፡ በክህደታቸው ስለጸኑ፡፡ አቤንኤዜር አንተ ደፍረህ ይህን ነገር በመናገርህ መልካም አደረክ፡፡ እግዚአብሔር አጽራረ ክርስቶስና መጽሐፍ ቅዱስን ያስታግስልን፡፡

    ReplyDelete
  4. ነገሮችን ለምን እንደሚያወሳሰስቡ ግልጥ አይደለም የእምነት እንቅስቃሴ ሰዎችለኔ ትምህርታቸው ግራ ነው፡፡ አይደለም ሌላው ቀርቶ ስለሰው ያላቸው ግንዛቤ ግራ ከመሆኑ ባለፈ ሰውን ያመናፍሳሉ ራሱን እንዲስትና እግዚአብሔርን እንዲሆን ያበረታታሉ ትምህርታቸውም ይህን ይደገፋል፡፡ እግዚአብሐየር ያጠፋቸዋል ከዚህ በፊትም ተነስተው አጥፍቷቸው ነበርና

    ReplyDelete
  5. ጌታ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይርዳህ፤ በርታ የአገልግሎት ዘመንህ ይባረክ፡፡ የሚጠቅመንን ብዙ መልእክት አስተላልፈህልናልና፡፡

    ReplyDelete
  6. ኢየሱስ ከብልጽግናም በላይ ነው፡፡ ክርስቲያኖችኮ በጌታችን ባለጸጎች ነን፡፡ ይህ ያልገባቸው፡ ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉ የዚህ ዓለም ነገርን ያረገዙ ሆዳሞች ተረት ተረት ነው፡፡

    ReplyDelete