Saturday, 2 December 2017

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፭

ü  ዘፍጥ.2፥7 
     ህ ክፍል የምዕ.1 ሌላ እይታ ወይም ማብራሪያ እንጂ ከስድስቱ ቀናት ውጪ ቀጣይ ታሪክን በራሱ የያዘ አይደለም፡፡ የፍጥረትን ታሪክ በተመለከተ ከሁለት አቅጣጫ በመመልከት ወይም የምዕ.1ን የአፈጣጠር ሁኔታ ለማብራራት የተቀመጡ እንጂ፣ ሁለት የተለያዩ ዘመናት ታሪኮችና ክስተቶች አይደሉም፡፡ ይህ ደግሞ የቅዱሳት መጻሕፍት ባሕርይ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ሰው “ከመሬት ተነሥቶ” አራቱ ወንጌላት ይበዛሉና ይቀነሱ ቢል፣ ጤናማ ሃሳብ ነው ብለን አንቀበለውም፤ ምክንያቱም የአንዱን የጌታችን ኢየሱስን ትምህርትና ሕይወት ከአራት ወንጌላውያን እይታ አንጻር አይተው አስፍረውታልና በደስታ ተቀብለነዋል፡፡ በዘፍ.1 እና 2 ላይም አንድን የፍጥረት ታሪክ በሁለት እይታ መስፈሩን ማስተባበል አንችልም፡፡ 
    አልያ ግን አሁንም ሌላ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፤ “እግዚአብሔር ፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ አልጨረሰም” ወደሚል አንድ እንግዳ ጫፍ ይወስደናል፡፡ ስለዚህ ምዕ.2 የምዕ.1 ማብራሪያ ወይም ሌላ እይታ ነው፡፡[1] ይህንንም እንዲህ በአጭሩ ማሳየት እንችላለን፤
ü  ለሰማይና ምድር፦
v ምዕ.1፥1-2 በአጭሩ፣ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይላል፤
·        ምዕ.2፥4-6 ላይ ይኸንኑ ሲያብራራ፣ “እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው፡፡ የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፣ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤ ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር” ይላል፡፡

ü  ለሰው አፈጣጠር
v ምዕ.1፥26-27 በአጭሩ፣ “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ …እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል፤
·        ህ በሦስት ዓይነት መንገድ ተብራርቷል ብለን መናገር እንችላለን፤
-       “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፤” (2፥7) በማለት የሥጋና ነፍስን የት መጣ ሲነግረን፣
-       “እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፡፡ ... እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፡፡ አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል፤” ሲል የሴትን የት መጣ ይነግረናል፡፡
     ምክንያቱም እንዲሁም፣ “ወንድና ሴት” ተደርገው የተፈጠሩት ሰዎች እንዴት ተፈጠሩ? ብንል ሁለተኛው ምዕራፍ፣ “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ሥፍራውን በሥጋ ዘጋው፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት፤” (2፥21-22) በማለት ያብራራልናል፡፡ ከዚህም የተነሣ የሰው ነፍስና ሥጋው በተለያዩ ጊዜያት መፈጠራቸውን የሚያሳይ አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልን ማንሳት አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረበት ቀን ሥጋውንም ነፍሱንም[መንፈሱንም] በአንድነት ፈጥሮታል፤ ስለዚህም ሰው ስንል ሥጋና ነፍስ ያለው ወይም ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ያለው ማለታችን ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይመሰክርልናል፡፡ንደገናም፣
-       “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና፤” (ዘፍ.3፥19) ላይ ያለውን የፍርድ ቃል ከምዕ.1፥26 ላይ ቆመን ሥጋ ከወዴት መጥቶ ተፈጠረ ብንል ምንም ምላሽ የለንም፤ ነገር ግን እኛስ ምዕ.2፥7 ላይ ተብራርቶልናልና ግራ አይገባንም፡፡
     እግዚአብሔር በምዕ.1 ላይ እንፍጠር ብሎ በመልኩና በአምሳሉ መፍጠሩን የሚነግረንን፣ ምዕ.2፥7 ላይ ደግሞ፣ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” በማለት “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያውን ይሰጠናል፡፡
ü  ለፍጥረት ተፈጥሮ መጨረስም፣
v ምዕ.1፥31 “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን፡፡” ይላል፡፡ “ያደረገውን ሁሉ” ሲልም፣ የተፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ ማለቱ ግልጥ ነው፡፡
·        2፥1-4 “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ፡፡ እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው፤” በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
     ሁለቱም ምዕራፋት ስለአንድ ነገር የሚያወሩ ከኾነ፣ ሁለተኛው ምዕራፍ የአንደኛው ሌላ እይታ ወይም ማብራሪያ ነው፡፡ እንዲህ፤ እንዲህ እያልን ብዙ መመሳሰሎችንና አንዱ የሌላው ማብራሪያ መኾኑን በሚገባ ማዛመድ እንችላለን፡፡ በተጨማሪም በምዕራፍ.1 እና 2 መካከል ያለውን ፍጹም ዝምድና ቄስ ኮሊን በመጽሐፋቸው እንዲህ አስቀምጠውታል፤
     “እግዚአብሔርን በተመለከተ ምዕራፍ አንድ፥ በመፍጠሩ ልዕልናውን፥ ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ለሰው አስፈላጊውን ሁሉ ማዘጋጀቱን ያሳያል፡፡ ሰውን በተመለከተም ምዕራፍ አንድ ሰው የፍጥረት አክሊልና መጋቢ መኾኑን ሲያመለክት፥ ምዕራፍ ሁለትም ምድራዊ አኗኗርን ያሳያል፡፡ በአጭሩ የምዕራፍ አንድ ፍሬ ነገር ፍጥረት ሲሆን፥ የምዕራፍ ሁለት ደግሞ ገነት ነው፡፡ ሰው በምዕራፍ አንድ የፍጥረት ራስ፥ በምዕራፍ ሁለት የገነት ባለቤትና ጠባቂ ነው፡፡
      ምዕራፍ አንድ የሰማያትንና የምድርን ታሪክ ሲተርክ፥ እግዚአብሔር በልዕልና እየተናገረ ሁሉን ለሰው እንዳዘጋጀ ይገልጣል፡፡ ሁሉም ከተዘጋጀና ልዩ አምላካዊ ምክክር ከተደረገ በኋላ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ከፈጠራቸውም በኋላ ባረካቸው፤ በዓለም ላይ ሾማቸው፤ በዓለምም እንዴት ሊጠቀሙ እንደሚገባቸው ነገራቸው፡፡”[2]
ሰው ሥጋም አለው፤
    “ጋ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ነገርን ሊያመለክት ይችላል፤ ከእኛ ርእስ ጋር ብቻ የሚዛመደውን ብንወስድ፣ “(1) ከአጥንት በቀር የሰው ወይም የእንሰሳ ክፍል፣ (ዘፍጥ.40፥19)፤ (2) ጠቅላላው ግዙፍ የሰው አቅዋም፣ (ያዕ.2፥26)፤ (3) የሰው ሁለንተና (ዮሐ.1፥14 ፤ 1ዮሐ.4፥2) ይህም ደካማ ነው፤ (ማቴ.26፥41 ፤ ሮሜ.6፥19) …” በማለት መዝገበ ቃላቱ[3] ያስቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ ሥጋ ስንል የሚታየውን፣ የሚዳሰሰውን፣ የሚያዝና የሚጨበጠውን፤ ውጫዊውንና ውስጣዊውን የሰውነታችን ክፍል ማለታችን ነው፡፡
     ሥጋ በእግዚአብሔር ከምድር አፈር የተበጀ ነው፤ “አቤቱ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን(ኢሳ.648) ሲል፣ የሥጋ ማንነታችንን ያሳየናል፡፡ ስለዚህም ሰው የፍጥረት አክሊል ነው፡፡ ክቡርና ከምናየው ዓለም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነትን የምናደርግበት፣ እግዚአብሔርንም ለማምለክና ለማክበር በቅድስና ልናቀርበው የሚገባን ሰውነት(ሮሜ.12፥1-3) ነው፡፡ ደግሞም ይህ ሰውነታችን፣ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ፤” (1ቆሮ.3፥16)፣ “እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና” (2ቆሮ.6፥16) በማለትም ያጸናዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሰውን ሥጋነት[ሥጋ ስለኾነው ተፈጥሮው] የሚያስረግጡ እጅግ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤ 
ü  “እግዚአብሔርም፦ መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ” (ዘፍጥ.6፥3)
ü   “ከዝሙት ሽሹ፡፡ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል፡፡ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፤” (1ቆሮ.6፥18-20)
ü  “ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም” (መዝ.38፥3)፤
ü  “ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ” (ሰቆ.2፥11)
ü  “በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው” (ፊልጵ.1፥23-24)
ü  ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፤ (ቈላ.2፥22)
    እኒህና ሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ሰው ሥጋን ገንዘቡ ያደረገ ክቡር ፍጥረት መኾኑን ይመሰክራሉ፡፡
ሰው ነፍስም አለው፤
    ሰው ነፍስ፣ “ … በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (2፥7) እንዲል፣ የሰው ሁለተኛ ክፍል ኾና የተነገረችው ናት፡፡ አንዳንዶች የሰውን ነፍስ መንፈስ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ነፍስና መንፈስ[4] በየራሳቸው የተለያዩ ናቸው ይላሉ፡፡ ነፍስ የራሷ ማንነትና አካል[5] ያላት ስትኾን፣ ልክ እንደሥጋ በድካምና በኃጢአት ልትያዝ እንደምትችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስቀምጣል፤ “እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ፥ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች፤” (መዝ.78፥8)፣ “በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፥ የሚያጕረመርሙም ትምህርትን ይቀበላሉ” (ኢሳ.29፥24)፣ በአዲስ ኪዳንም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” (2ቆሮ.7፥1) በማለት መንፈሳችንም ሊረክስ እንደሚችል ነገር ግን ቅድስናን ፍጹም በማድረግ በእግዚአብሔር ፍርሃት መንጻት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡
     ከዚህም ባሻገር ነፍስም[መንፈስም] መኖርዋን የሚያስረግጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፤ እኒህም፦
ü  “በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤” (1ሳሙ.1፥15)
ü  “አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ” (መዝ.25፥1)
ü  “ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና” (መዝ.62፥1)
ü  “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” (ሉቃ.1፥46)
ü  “እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤” (1ቆሮ.5፥3-4)
   መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ሁለንተና ሰውነት በሚገባ አብራርቶ አስቀምጧል፡፡ የሰውን ነፍስነት[መንፈስነት] ብቻ ነጥሎ ማቅረብና ማስተማር ሰውን ለሌላና እንግዳ ለሆነ ትምህርት በሚገባ ወልውሎ፤ ወና አድርጎ ጠርጎ ማሰናዳት እንደኾነ ግልጥ ነው፡፡ ደግሞም ሥጋን መጣልና ሥጋን አልለበስኩም ማለት ለብዙ ክህደት ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ሰው ማለት ሥጋ፣ ነፍስ ወይም መንፈስ ነው፡፡ እንዲያው በምሳሌነት ብንጠቅስ፦ ሰው ሲሞት ነፍስና ሥጋው ይለያያሉ፤ ነፍሱን ብቻ ሰው አንልም፤ ሥጋውንም ብቻም ሰው አንልም፡፡ የሁለቱ በአንድነት መኾን ግን ሰውን ሰው ያሰኘዋል፡፡
    የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን በዚህ ዙርያ የሚሉት ብዙ ነገር አላቸው፡፡ በእርግጥ እነርሱ ሊሉ የፈለጉትን በግልጥ እስከመጨረሻው ለጥጠው ተናግረውታል፤ የሰውን ልጅ ደረጃ ወደፈጣሪነት ከፍ ለማድረግ [“እኛም የእግዚአብሔር እኩዮች ነን” በማለት] የትምህርታቸውን መሠረት የሚጥሉት “ሰው መንፈስ ነው” በሚለው አስተምኅሮ ነው፡፡ ምንም ሳያፍሩም በመታበይ ቃል፣ “እግዚአብሔር እኛን ያመጣን[ወደዚህ ምድር] ራሱን ሊያበዛ ፈልጎ ነው” (ጆን አቫንዚኒ እና ሞሪስ ሴሬሎ) እና ሌሎችም “መንፈስ ነን” የሚለውን ትምህርት እዚህ ድረስ ለጥጠውታል፡፡
“መልክና ምሳሌ” የሰው ኹለንተና ነው!
   እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደምሳሌው የፈጠረው፣ ሰውን ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ አይደለም፡፡ ሰው ጾታው ወንድና ሴት ተደርጐ የተለየውና ምሉእ ኾኖ የተፈጠረው፣ በዚያው በተፈጠረበት ቀን እንደኾነ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክርልናል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን የሚመስለው መልክና ምሳሌው የሰው-ነታችን ኹለንተናው[ቁሳዊው ሥጋችንና ነፍሳችንም ጭምር] ነው፡፡ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” (1ተሰ.5፥23)፤ በሚለው ንባብ ውስጥ፣ “ሁለንተናችሁን” የሚለው ቃል የሰውን ነፍስንም፣ሥጋንም እንደሚያካትት መንፈስን ብቻ እንደማይል ግልጥ ነው፡፡
    ይህንን ሰው እንዲያደርግና እግዚአብሔርን እንዲመስልበት ከተሰጠው ሥራ ጋር ማዛመድ እንችላለን፡፡ ሰው፣ “ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” (ዘፍ.1፥28) የሚለውን ሥልጣን ከእግዚአብሔር በውክልና ተሰጥቶታል፡፡ ግዑዛን የኾኑትን ፍጥረታት፣ ሰው በመንፈሱ ብቻ ይገዛቸዋል፤ ያስተዳድራቸዋል ማለት ራስን መካድ ብቻ ነው የሚኾነው፡፡ የመግዛትን ምሳሌ ቀለል አደርገን ብናነሣ፣ አንዲት ትንሽ ሕጻን ታላቁን ፈረስ ስትነዳ፣ ወይም ለጉማ ይዛ ስትሄድ ከማየት የበለጠ የመገዛትንና የመግዛትን መግለጥ አይቻልም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ “ቅድስና ለመንፈስ ብቻ” የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የለም፡፡ ሥጋም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንዲገዛ[እንዲመስል]የጸና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አለን፡፡ እግዚአብሔርን ከምንመስልበት ነገራችን አንዱ ቅድስና ነውና፡፡ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ፤”፣ “ … እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ፡፡ ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤” (ዘሌ.19፥2 ፤ 1ጴጥ.1፥16) በሚለው ንባብ ውስጥ ቅድስና ከእግዚአብሔር የተካፈልነው ባሕርይ ኾኖ እንመስለው ዘንድ ተጠርተናል፡፡
     ስለዚህም መንፈሳችን ብቻ ሥጋችንም ለእግዚአብሔር መቀደስ አለበት፤ “… ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል፡፡ ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም፡፡ ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና፡፡ ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው፡፡ ከዝሙት ሽሹ፡፡ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል፡፡ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፤”(1ቆሮ.6፥13-20)፣ “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፤” (ሮሜ.12፥1)፣ “እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤” (ሮሜ.6፥11-12) የሚሉት ንባባት ሥጋ ለእግዚአብሔር መቀደስ እንዳለበት ያሳስባል፡፡
    ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ፣ “ቅድስና የሌላቸው” ብንባል (1ጢሞ.3፥3)፣ “ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች ቢኖሩን” (2ጴጥ.2፥14)፣ ሥጋን በመጨቆን የራስብ ጽድቅ ለማቆም ማሰብ (ቈላ.2፥23)፣ በሥጋ በኩል ጻድቁን ማጥቃት (ኢዮ.2፥7-9)፣ በሥጋ ተገንነት ሰዎች ዓይናቸውን ከእግዚአብሔር እንዲያነሡ ማድረግ (ይሁ.8-9)[6] ከባድ በደል ነው፡፡ ለዚህም ኃጢአትን በተመለከተ የቀደመውን ዓለም ሲያጠፋ፣ “በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” (2ጴጥ.2፥9) እንዲል፣ እንዲህ ያሉ መናፍቃን ወደፍርድ መምጣታቸው የማይቀር መኾኑን ይነግረናል፡፡ እናም በሥጋችንም መከራን በመቀበል ኃጢአትን ልንተው (1ጴጥ.4፥1)፣ ከምንም በላይ ደግሞ፣ “ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል፤” (1ጢሞ.4፥8) እንዲል፣ ሥጋዊ ልምምድ አካላችንን ጤነኛ እንደሚያደርገው እንዲሁ መንፈሳዊ ልምምድም በሥጋችን፣ በነፍሳችንና በመንፈሳችን ፍጹም ጤነኞችና “ብቁዓን” ያደርገናል፡፡ በሥጋችንም መልካም እያደረግን “… ነፍሳችንን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ብንሰጥ” (1ጴጥ.4፥19) መልካም አድርገናል፡፡ ደግሞም፣ “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው፤” (ያዕ.3፥2)፡፡
    እንደሦስተኛ ፍሬ ነገር ብንናገር፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለተፈጠረ፣ በማናቸውም መንገድ ሊገደል አይገባውም፣ (ዘፍ.9፥6)፡፡ ሁለንተናችን ነፍስና ሥጋ ወይም መንፈስ፣ ሥጋና ነፍስ መኾኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤” (ማቴ.10፥28) ብሎ ባስተማረው ትምህርቱ፣ ሥጋና ነፍስ ያልተነጣጠሉ መኾናቸውን ነግሮናል፡፡ ስለዚህም ሰው ከመግደልም ባሻገር ሊናቅ፣ ሊሰደብ አይገባውም፣ (ማቴ.5፥22)፣ ሊረገምና አድልዎ ሊደረግበትም አይገባም፣ (ያዕ.3፥9)፡፡ ሥጋ ይህን ያህል የማያስፈልግም ቢኾን ይህን ያህል አክብሮት፤ ከለላም ባልተደረገለት ነበር፡፡
    በሥጋችንም እግዚአብሔርን እንመስለዋለን ወይ? የሚል ጥያቄ ብናነሣ፣ አዎን ብለን ለመመለስ እንደፍራለን፡፡ እንዳይገደል፣ እንዳይናቅ፣ እንዳይሰደብ፣ እንዳይረገም የተባለው ነፍሱ ወይም መንፈሱ ብቻ ሳይኾን ሥጋውም ጭምር ነው፡፡ አትግደሉ፣ አትናቁ፣ አትሳደቡ፣ አትርገሙ የተባልነውም የሰውን ኹለንተና ነው፡፡ ይህ ውስን ሃሳብ ግን እግዚአብሔርም ቁሳዊ ነው ለማለት ከሚንደረደር የስንፍና ሃሳብ ጋር አይዛመድም፡፡
    ኹለንተናችን በሰማይም በምድርም ያው እንጂ፣ ወደሰማያት ስንሄድ የሚለወጥ አንዳችም ነገር የለም፡፡ በሁለተኛው ትንሣኤ መንፈሳዊ አካል እንለብሳለን እንጂ ሰውነታችንን አንጥልም፤ እንባዎቻችን ሁሉ የሚታበሰው. (ራእ.7፥17)፣ “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤” (ራእ.21፥3) እንደተባለውም ሰውነታችን በሰማያትም ያው ነው፡፡
    በዚህ ምድር ቅዱሳን ሲኖሩ ፍጹማን ሲባሉ በእምነትና በመንገዳቸው አካሄድ የበሰሉ፣ ያደጉ፣ የጠነከሩ ወይም እየበሰሉ የሚሄዱ እንጂ እንከን አልባ ናቸው ማለት አይደለም፤ (ፊል.3፥12 ፤ 1ዮሐ.1፥8)፤ በሰማያት ደግሞ ወደፍጹም ሰውነት እንጂ ወደመንፈስነት አናድግም፤ (ኤፌ.4፥13 ፤ ቈላ.1፥28)፡፡ ኹለንተናችን እግዚአብሔርን ይመስላል፤ ራሱ እግዚአብሔርን ግን አይደለንም፡፡ ወደፍጹም ሰውነት ብናድግም እግዚአብሔር ወዳሰበልን፤ እንድንኾንም ወደፈቀደልን ምሉእ ሰው-ነት እንጂ መለኮታውያን[ራሱ እግዚአብሔርን] አንሆንም፡፡ እግዚአብሔር ያሰበልንና ያለን ነገር ብቻ እውነትና ትክክል ነው፤ ከዚያ ያለፈው የሰዎች ሃሳብ የነፍሳችን ወጥመድ እንጂ አንዳች የሚረባን ነገር አይደለም፡፡ [7]ጌታ መንፈስ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፤ አሜን፡፡ 
ይቀጥላል …





   [1] እንዲያውም አንዳንዶች ምዕ.1 እና 2ን የተለያዩ ሰዎች መጻፋቸውን ይገልጣሉ፡፡ ይህም ቢኾን እንኳ ነቢዩ የፍጥረት አፈጣጠር ሁለቱንም ታሪኮች በትክክል አስቀምጧቸዋል ማለት ነው፡፡
   [2] ትምህርተ ክርስቶስ ገጽ.16
   [3] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ.66
    [4] ሰው ስላለው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች  ዘንድ ሁለት ዓይነት አመለካከት አለ፤ ይኸውም ሰው ነፍስና ሥጋ ነው፤ ሰው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ነው የሚሉ ወገኖች ናቸው፡፡ የሰው ተፈጥሮው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ነው የሚሉ ወገኖች ከሚጠቅሷቸው የመጽሐፍ ቅዱሶች አንዱ፣ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” (1ተሰ.5፥23) የሚለውን ቃል በመያዝ ነው፡፡ የነፍስና የመንፈስን ልዩነትንም ሲያስረዱ፣ ነፍስ የሰውን አእምሮ፣ ስሜትና ፈቃድን የሚያመለክት ሲኾን፣ መንፈስ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በአምልኮትና በጸሎት የሚገናኘውን አመልካች ነው ይላሉ፡፡ የዚህ ትምህርት ተከታዮችም የሦስትዮሽ መላምት(Trichotomists) ተከታዮች ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሦስትዮሽን ትምህርት ተከታዮች፣ “ ሰው መንፈስ ነው” ለሚለው ትምህርት ተጋላጭ መኾናቸውን ቄስ ኮሊን ማንሰል፣
   “ … የተወሰኑት ደግሞ መንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ክፍልና ከአእምሮ፥ ከስሜትና ከፈቃድ የተለየ ክፍል እንደሆነ በማሰብ፥ መንፈሳዊ ሰው ብዙ ማጥናት የማያስፈልገው መሆኑን ማሰብ ይጀምራሉ፡፡ ከዚህም ጋር በክርስቲያናዊ ኑሮ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናትና ከማንበብ ይልቅ መንፈሳዊ ተመክሮና ስሜት የሚበልጡ ይመስላቸዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች “እኔ መንፈስ ነኝ” በማለት ሊፎክሩ እንደሚችሉ አይተናል፡፡” (ቄስ ኮሊን ማንሰል፣ ትምህርተ ክርስቶስ፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ ገጽ.41) በማለት ተናግረዋል፡፡
   ነገር ግን የሦስትዮሽን መላምት የሚከተሉ ሁሉ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ይቀበላሉ የሚለውን እንዳልኾነ ማስታወስን እወዳለሁ፡፡
      [5]  “አካል” ማለት ከግዑዝ ወይም ከሚዳሰስና ከሚያዝ ነገር ጋር የሚያያዝ ሳይኾን ሰምቶ ከሚመልስ፤ ዕውቀትና ፈቃድ ካለው ነገር ጋር የሚያያዝ እንጂ እንደበጋሻውና ዋና የቃል እምነት መምህራን አስተምኅሮ ምናብና የማይታይ ነገር ሁሉ አይደለም፡፡ ነፍስ፣ መላእክት፣ ነፋስ፣ መለኮት  … እና ሌሎችም አካል አላቸው፡፡ የነፍስን አካላዊነት አለቃ መሠረት እንዲህ ገልጠውታል፦
    “ነፍስ ሦስት ከዊን አላት ሲባል፣ ሦስት አኋኞች አሏት፡፡ እነርሱም ልብ ቃል እስትንፋስ ናቸው፡፡ በእነዚህ በሦስቱ ኋኝ ሆና አካልነቷን ትገልጻለች፡፡ ይኸውም ኋኝነትዋበዐለመ መንፈስ ይዘት አካል ለማሰኘቱ ብቁ እንደመሆኑ፥ በስመ ህላዌያት ሥርዓተ ምጣኔ አንድ አካል ትሰኛለች፡፡” (ሥላሴ በተዋሕዶ፤ ገጽ.174)፡፡
በማለት ገልጠዋል፡፡ ስለዚህም የራሷ አካል ያላት እንደነበጋሻውና የእምነት ቃል መምህራን በራሷ ምንም ማድረግ የማይቻላት ላስገዛላት ሁሉ የምትሸነፍ ብቻ አይደለችም፡፡
     [6] በዚህ የይሁዳ መልእክት ላይ ሰይጣን ሙሴ በሞተ ጊዜ የሙሴን በድን ፈልጐት ነበር፤ ሙሴ በእስራኤል ልጆች እጅግ የተወደደ ከመኾኑም እንደዋና የሚታይ ሰው ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን ይህን በእስራኤል ልብ ያለውን ነገር ሙሴን ወደማምለክ እንዲደርስ ለማድረግ ሥጋውን እንዲያመለኩት እጅጉን ይሻ ነበር፡፡ ዲያብሎስ “ሥጋውን ሊወስድ በመጣ ጊዜም” ነበር፣ ቅዱስ ሚካኤል በመቃወም “እግዚአብሔር ይገስጽህ” በማለት የተቃወመው የሚል ትውፊታዊ ትርክት አለ፡፡ 
[7]  ይህ ለበጋሻው ደሳለኝ በዚህ ርእስ ሥር ከተመለሰው መልስ ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበ ነው፡፡

5 comments:

  1. በጣም መፀልይ ተገቢ ነው ጌታ ኢየሱስ አይነ ልቦናቸውን ያብራላቸው;; tru melkt new enamesegnalen aben bertaln eski ante እንኳ

    ReplyDelete
  2. Amharic Bible verse

    (ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ. 10)
    ----------
    9፤ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤

    10፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።

    11፤ መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።

    12፤ በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤

    13፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። wegeney be Eyesuse sm emenu Ye E/r mhret yag'gnach'u yensha hywet geta ysxach'u.

    ReplyDelete
  3. አስተማሪነቱ ምንም አያጠያይቅም እና ቢያንስ ለምን አታሳጥረውም? ብዙ ጊዜ ሰዎች ባክነው ስለሚያነቡት ወንድሜ በአጭር በአጭሩ ብታደርገው እጅግ መልካም ነው፡፡ ደግሞ ፒዲኤፍ አንዳንዶቹ ጽሁፎችህን ስለማይገለብጡ ስትጭነው አስተካክልልን፣ የጽሁፍ አያያዝህ ከሌሎች ብሎጎች አንጻር ቶሎ ቶሎ በማውጣት የተሸለ ቢሆንም ጽሁፉ ተሰባስቦ በመጽሀፍ መልክ ሊወጣ ቢችል መልካም ነው፤ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን በርታ፡፡

    ReplyDelete
  4. ገና ከኢትዮጲያ ምድር ተነቅላችሁ ትጠፋላችሁ፤ አንተም አቤንኤዘር ተቀላቀልካቸወ እንዴ ያሳዝናል፡፡ደግሞ በቅርብ ከሁሉም የኢትዮጲያ ከተሞች ተለቃቅማችሁ ትወጣላችሁ

    ReplyDelete