Saturday, 27 December 2025

ወንድሞችን ለምን አምናቸዋለኹ?

 Please read in PDF

በአዲስ ኪዳን ወይም በመላው ክርስትና ውስጥ፣ እግዚአብሔር በብዙ ጸጋውን ያበዛለትና በወንጌል አገልግሎት ብዙ ሺህ ማይሎችን ተጉዞ በማገልገል እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ምሕረት የገነነለትና የተትረፈረፈለት ብርቱ አገልጋይ “ያለ አይመስልም”። የጽድቅ ቀናተኛ፣ የማያመቻምች፣ ባለ ብዙ ሐብተ ጸጋ፣ አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን የመሠረተ፣ የአዲስ ኪዳንን ግማሽ ያህል መጻሕፍት የጻፈ፣ አስደናቂና ተወዳጅ የእግዚአብሔር ምስጢራትን በትምህርትና በስብከት የመገበ፣ ክርስቶስን አክብሮና አስከብሮ በሕይወቱ ጭምር መስክሮ በጽድቅ መሥዋዕት የኾነ ሐዋርያ ነው።

ይህ ብርቱና ተወዳጅ ሐዋርያ፤ እንዲወደድና አሠረ ፍኖቱን ዛሬም እንድንከተል ከሚያደርጉን ሰናይ ምሳሌዎቹ መካከል፤ አብሮነትን መውደዱ፤ ብቻውን አለመሮጡ፤ ብዙዎችን ማብቃቱና መቀበሉ ጭምር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ምንም ጸጋ ቢበዛለት፣ ምንም ክርስቶስን በዓይነ ብሌኑ ያየ ቢኾን፣ ምንም እንኳ በኹሉ ጐዳናው ስኬታማ አገልጋይ ቢኾንም፤ አብረውት የሚያገለግሉትን ግን ወዳጅና አክባሪ፤ ተቀባይና ቀኝ እጁን ሰዳጅና አበርካች ነበር።

ለዚህ ኹነኛ ምስክር ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ቅኝት የተጻፉት መልእክቶቹ ናቸው፤ ቅዱስ ጳውሎስ ፌቤንን፣ “ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ የነበረች፥”፣ አቂላና ጵርስቅላን ደግሞ “በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ የሚሠሩ … ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት ያቀረቡ”፣ ኢሩባኖንን “በክርስቶስ አብሮ[ኝ]ን የሚሠራ”፣ ስለ ጠርሲዳም ሲናገር፣ “በጌታ ኾና እጅግ የደከመች”፣ “አብሮኝ የሚሠራ ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉቂዮስና ኢያሶን ሱሲጴጥሮስም” (ሮሜ 16) በማለት ስለ ተወደዱ ወንድሞቹና እህቶች በሚያስደንቅ መንገድ ያነሣል።

ቅዱስ ጳውሎስ ብቻውን እደሚያገለግል አያምንም፤ ምንም ብርቱ ቢኾን፣ “አንድ ብቻ ከመኾን ኹለት መሆን ይሻላል፤ … በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።” (መክ. 4፥9፡ 12) የሚለውን የመጽሐፍ ቃል በሚገባ የሚያስተውል እጅግ ብርቱ አገልጋይ፤ የክርስቶስ ባሪያ ነው። ክርስትና መሠረቱን በጣለበት ሕያው ድንጋይ ላይ የመንፈስ አንድነት እንጂ “የአንድ ብርቱ” ጨርሶውኑም የለም፤ አልነበረምም።



ኅብረታችን በአካል፤ እኛ በብልቶች በተመሰልንበት የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ውስጥ፣ አንዳችን ለሌላችን ፍጹም የምናስፈልግ እንጂ አንዳችን ለሌላችን “ዋና ወይም የበላይ” የኾንበት አይደለንም፤ ለዚህም ነው በኅብረት ጉዳይ ስሱ ሐዋርያ ሲናገር፣ “አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።” (1ቆሮ. 12፥26)በማለት የሚናገረው። አንዳችን የሌላችን ጤና፤ ሌላችን የሌላው ወገናችን ሰላምና ደስታ ነን።

ከዚህ የተነሣ እኔ ወንድሞቼን አምናቸዋለኹ፤ በነርሱ ጉዳይ ዘወትር ስስ ነኝ፤ ኅብረት “የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ መገለጫ ነው”፤ ኢየሱስ እንደ ነገረን፣ “እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ” (ዮሐ. 17፥22-23) ብሎ በመሲሐዊ ኑዛዜ እንደ ተናዘዘልን፤ የሥላሴ ኅብረት ፍጽምት ናትና እኛም ከዚያ የተማርነው የኅብረትን ስስነት ነው።

ስለዚህም አብረውኝ የሚያገለግሉኝን ወንድሞቼን አምናለኹ፤ አብረውኝ ሲያገለግሉ በደስታ ለስኬታቸውና ለምልአታቸው እተጋለሁ፤ ኅብረት የአንድ ወገን ጥረት አይደለም፤ እኛ እየፈለግን፤ ሌላው እየገፋ ኅብረት “ቊስል” እንጂ ኅብረት አይደለም። እናም ወንድምና እህቶቼ ይፈልጉኛል እፈልጋቸዋለኹ፤ ይይዙኛል እይዛቸዋለሁ፤ ይጠብቁኛል እጠብቃቸዋለሁ፤ ይመክሩኛል እመክራቸዋለሁ፤ ይገስጹኛል እገስጻቸዋለሁ፤ ይቆርሱልኛል እቆርስላቸዋለሁ … ስለዚህም ወንድሞቼንና እህቶቼን አምናቸዋለኹ!

ኢየሱስን በማይጠፋ ፍቅር ለምትወድዱ ኹሉ ምሕረትና ጸጋ ይብዛላችኹ፤ አሜን።

 

No comments:

Post a Comment