Monday, 20 November 2017

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፫

2. ታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ የተናገረውንና የተነገረለትን ልክ ለመለኮቱ እንደተነገረ ተቆጥሮ ሲካድ እንመለከታለን፡፡ ለዚህም እንደዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት፣ “የክርስቶስን ከዘላለም የእግዚአብሔር ልጅ አለመኾኑን” ሁለት ሃሳቦችን በአንድነት በመስፋት ነው፡፡ እንዲህ በማለት፦ “አብና ወልድ …እኩል አይደሉም፤ አብ ወልድን ይበልጣል፤ … ገብርኤል እንዳለው ስሙ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ ከዛ በፊት አባታችን ነው፤ ሌላ ማስረጃ በዕብ.2 ላይ “ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱም እንዲሁ በሥጋና በደም ተካፈለ፤ ማን ተካፈለ? አባታቸው፡፡ ስሙ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል በሚል የእግዚአብሔር ልጅ ብሎታል፤ ከዛ በፊት ልጅ አልነበረም ወይ? ልጅ አልነበረም፤ አባታችን ነው፡፡ አባትና ልጅ መሆንም አይችልም፡፡ … ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ልጅ ከነበረ ለዘለዓለም ከአብ ያንስ ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሥጋ የለበሰው መች እንደኾነ እናውቃለንና፤ ሥጋ የለበሰው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ከድንግል ማርያም በተወለደበት ጊዜ ነው ልጅ የኾነው፡፡ ያን ጊዜ “officially”[በግልጥ ወይም በይፋ ለማለት ይመስላል] እግዚአብሔር የነበረው ሥጋ ሲኾን፣ አብ ከእኔ ይበልጣል፤ ብታምኑስ አብ ከእኔ ይበልጣል ብሏል፤ አብ ስለሚበልጠው እንደውም በሁሉ ነገር ይጸልይ ነበር እንደማንኛውም ሰው፤ እርሱ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ከኾነ “somehow”[እንደምንም] የኾነ ቦታ ተወልዷል ማለት ነው፤ …የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር አይደለም፡፡”[1] በማለት፡፡
    “ኢየሱስ ከአብ ጋር አይተካከልም” ለማለት መናፍቃኑ የሚጠቅሱት ጥቅስ፣ በእውኑ ክፍሉ እነርሱ እንደሚሉት ሃሳባቸውን ይጋራልን? እውን ቃሉ እነርሱ እንደሚሉት የኢየሱስን የመለኮታዊ “ታናሽነት” ይናገራልን? የጌታችን ኢየሱስ ልጅነት ወይም አባቴ ብሎ መጥራቱ የእርሱን አምላክ አለመኾንን ያመለክታልን? ዓውዱስ ያንን የሚል ነውን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብር እንደሌለው የሚያመለክት ነውን? … እና ሌሎችንም ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት መመርመር ይኖርብናል፡፡
ብ ከእኔ ይበልጣል” የማለቱ ምክንያት
   ንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እጅግ በተደጋጋሚ የክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችንን ከአብ ጋር ተካካይነት ሲገልጥልን አይተነዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደአባቱ እንደሚሄድ በተናገራቸው ጊዜ ልባቸው ታውኳል፣ (ዮሐ.14፥1)፣ ደግሞም ፈርተዋል፤ (ቁ.27)፡፡ ስለዚህ መፍራትና መሸበር እንደሌለባቸው በሚያጽናና ቃል ተናገራቸው፡፡ እንደውም የእርሱ ወደአብ መሔድ የተሻለ መኾኑን ስለሁለት ምክንያት ተናገራቸው፤ (1) “ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤”(ቁ.15-16)፣ (2) ጌታችን ኢየሱስ ወደአባቱ በመሄዱ አብ እርሱን ያከብረዋል፤ (ዮሐ.17፥5)፡፡ ደቀ መዛሙርቱ እኒህን ታላላቅ ምክንያቶች ያስተዋሉ አይመስሉም፡፡ ስለዚህም ለራሳቸው እጅግ ከማሰብ የተነሣ በራሳቸው ሃሳብና ኀዘን ውስጥ ተዋጡ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እነርሱ በዚህ ዓይነት ድብልቅልቅ ስሜት ውስጥ እያሉ፣ “የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” በማለት ተናገራቸው፡፡ ይህንንም ስለሁለት ነገር ተናግሯቸዋል፡፡ እኒህም፦

1.     ታችን ኢየሱስ እኛን ሊያድነን ወደዚህ ምድር ሲመጣ፣ አምላክነትን እንደመቀማት ሳይቆጥር ክብሩን በመተው፣ ሰውነትን ጨምሯል፤ (ፊል.2፥6-8)፣ በዚህ ነገር ከአብ ያንሳል፡፡ ከአብ ጋር ተካካይ የነበረው አምላክ ለተወሰነ ጊዜ እኛን ስለማዳን ያንን እኩልነት በመተውና የሰውን መልክ በመያዙ ምክንያት አብ እርሱን ይበልጣል፡፡ በምድር ሳለ ከአባቱ አንሷል፤ ነገር ግን ከሙታን መነሣት በኋላ በፍጹም እየከበረ ሄደ፤ (ዮሐ.7፥39 ፤ ፊል.2፥9-11)፡፡
    ስለዚህም እኛን ለማዳን ዝቅ ብሎ በመምጣቱና በታላቅ መዋረድም መከራን መቀበሉን ያሳያል፡፡ እርሱ ስለእኛ ሲል “ድኻ ኾነ”(ማቴ.8፥20 ፤ 2ቆሮ.8፥9 ፤ ፊል.2፥6)፣ አገልጋይ ኾነ (ማር.10፥45)፣ ታዛዥም ኾነ(ፊል.2፥8) … አብ እንዲህ ያለውን ነገር ማለትም፣ እንደጌታ ኢየሱስ ሥጋ ኾኖ አልተገለጠም፤ ወልድ በተለየ አካሉ ይህን በማድረጉ ብቻ እንጂ በመለኮታዊ ማንነቱ ማነሱን የሚያመለክት ሃሳብ ፈጽሞ የለውም፡፡ ስለዚህም አብና ወልድ በመለኮታዊ ማንነት ፈጽሞ አይበላለጡም፡፡
2.    ታችን ኢየሱስ ወደሰማያት በመሄድ ካልከበረ በቀር፣ ሌላው አጽናኝ ልክ እንደእርሱ መለኮት የኾነው መንፈስ ቅዱስ አይመጣም፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ከሃዘናቸው አይጽናኑም፣ ከፍርሃታቸው አያርፉም፤ እናም አሁን ከአብ በሚያንስ ማንነት ያለው ወልድ፣ “አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” የሚለው ጸሎት በተሰማለት ጊዜ፣ “ ... ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤” (ኤፌ.1፥20-21)፡፡
    ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት ኢየሱስ በአምላክነቱ ላይ ሥጋን በመጨመሩ ምክንያት ከአብ ጋር ያለው መለኮታዊ ግንኙነቱ ስለመለወጡ የሚናገሩት ምንም ነገር የላቸውም፡፡ “እንግዲህ በዮሐንስ ወንጌል ትምህርት መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥
1)     ፍጹም አምላክ መሆኑ፥
2)    ከዘለዓለም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ፥
3)    ከአብ ጋር የሚተካከል መለኮት ያለው መሆኑ፥
4)    በምድር ሳለ ከአብ ጋር እንደቀድሞው ያለው ግንኙነት ያለው መሆኑ፥
5)    በምድር ሳለ ሰውን ለማዳን የአገልጋይን ስፍራ መውሰዱ፥
6)    የአገልጋይን ስፍራ በመውሰዱ ከአብ ጋር የማይለወጥ አምላካዊ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታያሉ፡፡ ሆኖም ከግብር ተገዢነቱ ተነሥተን ስለሕላዊያዊ ተገዢነት ለማስተማር የሚያደፋፍር ምሳሌ ወይም ምክንያት በወንጌል አይገኝም፡፡ ይህን ስንልም ክርስቶስ ልጁ ነውና በልጅነቱ ለአብ የሚገባውን ክብር ሁልጊዜ መስጠቱን እናውቃለን፡፡”[2]
     “ከእኔ አብ ይበልጣል በማለት ክርስቶስ የተናገረውን በመያዝ በስህተት ትርጉም እንዳትሰናከሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል (ዮሐ.14፥28)፡፡ ይህ አነጋገር የክርስቶስን አምላክነት አይመለከትም፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጐ በተዋሐደው ሥጋ በምድር ላይ ሳለ የነበረበትን የሰውነቱን ሁኔታ በማስመልከት የተነገረ ቃል ነው፡፡ “ክርስቶስ አባቴ ከእኔ ይበልጣል ቢል ይህ አነጋገር ሰው ለመሆኑ የሚስማማ ነው” በማለት ቅዱስ ቄርሎስ ያስረዳናል፡፡ ስለዚሁም ጉዳይ እንደሚከተለው ገልጧል፡፡ “ያልተፈጠረ፣ ዓለም ከመፈጠሩ በፊትም ሥጋ ያልነበረ እሱ፣ በኋላ ዘመን ሥጋ ባሕር ሆነ፤ ከመፈጠሩ በፊትም ሥጋ ያልነበረው እሱ፣ በኋላ ዘመን ሥጋ ባሕርዩ ሆነ፤ ፍጹም ሰው በመሆኑም በዚህ መልክ ሰው ተባለ፤ ስለዚህም በእውነት አባቱን ከእሱ የሚበልጥ ይለዋል፤ ስለመታመሙ፣ ስለመሞቱ ከመላእክት ጥቂት አነሰ ተብሎ የተነገረለት እሱ ነው፡፡ እሱ አባቱን በእውነት “ከእኔ ይበልጣል” ይለዋል፤ እሱ መላእክትን ፈጥሮ የሚገዛ ሲሆን ስለተዋሐደው ሥጋ ይህን ቃል ቢናገርም፣ በተዋሐደው በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ አምላክ የተዋሐደው ሥጋን ከፍጡራን መካከል የሚተካከል ምንም የለም” (ሃይማኖተ አበው፣ ገጽ.585)፡፡
    እንግዲህ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ ከእኔ አብ ይበልጣል ያለበት ምክንያቱ ፈተናና ችግር ሕማምና ሞት ያለበትን የተዋረደውን የፍጡርን ሥጋና ነፍስ መዋሐዱን ለማመልከት መሆኑን እያስተዋልን፣ እርሱ ግን በመለኮቱ ከአብ ጋር እኩል መሆኑን እንመን፡፡”[3]

3.    መጣበትም ዓላማም ተክዶ እናስተውላለን፡፡ ክህደታቸውንም ሲናገሩ፣ “ኢየሱስ ራሱን አንድም ቦታ እኔ አምላክ ነኝ በማለት የተናገረበት ቦታ የለም፣ ተከታዮቹ እንጂ እርሱ ራሱን አላለም” ብለውም ይሞግታሉ፡፡ ነገር ግን አስቀድመን እንደተናገርነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን በትምህርቱና በሥራዎቹ ሁሉ ገልጧል፡፡ ለዚህም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻለናል፦
1.     ታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ባስተማረው ትምህርቱ፣ እግዚአብሔር አብን አባቴ[4] ብሎ በመጥራቱና ራሱን ከእርሱ[ከእግዚአብሔር አብ] ጋር አስተካክሎ በመጥራቱ አይሁድ እጅግ በጣም ተቆጡ፤ (ማቴ.26፥63 ፤ ዮሐ.5፥17-23 ፤ 8፥58 ፤ 10፥38)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ አብን “አባቴ” ያለበት ዓውድ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሎ እንደተናገረው፣ ያላቸውን ጥብቅ ግንኙነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አይሁድ “እግዚአብሔር የሁሉ አባት” እንደኾነ ያምናሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን በቅርበትና በተካካይነት ራሱን በመግለጡ ፍጹም ተቃውመውታል፡፡ ከኢየሱስ በቀርም እጅግ በማቅረብ “አባቴ” ያለና የጠራውም ማንም የለም፡፡
    ለክርስቶስ የተነገረው አንድያ የእግዚአብሔር ልጅነትም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተብራራው፣ ራሱ እግዚአብሔር ወይም የአብ የባሕርይ ልጁ እንደኾነ በሚገልጥ መልኩ ነው፡፡ “ … ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ…” (ዮሐ.20፥31) በሚለው ንባብ ውስጥ፣ በእግዚአብሔር ልጅ ማመን የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ፣ ስሙም ሕይወትን የሚሰጥ መኾኑን፣ በጥምቀቱ ጊዜና በደብረ ታቦር አባት የነበረው እግዚአብሔር ወልድ(ኢሳ.9፥6) በተለየ አካሉ ሥጋ በኾነ ጊዜ አብ፣ “ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት” (ማር.1፥11 ፤ 9፥7) ብሎ ስለጌታ ኢየሱስ የባሕርይ ልጅነት መናገሩን፣ ይኸው የእግዚአብሔር ልጅ በልዩና ፍጹም አንድነትን በሚያንጸባርቅ መንገድ መገለጡን፤ (ዮሐ.1፥14 ፤ 1ዮሐ.4፥9)፣ ሊያድነን መምጣቱን፤ (ዮሐ.3፥16 ፤ ሮሜ.5፥10 ፤ 8፥3 ፤ ቈላ.1፥13 ፤ 1ተሰ.1፥10)፣ የእግዚአብሔር ልጅ የኾነውም(ሉቃ.1፥35) ለመዳናችን ሲልና ለአባቱ ክብር እንደኾነ፣ “እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” (ዮሐ.13፥13)፣ “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” (ዮሐ.17፥4)፣ የሚሉትንና ሌሎችንም ምንባባት መመልከት እንችላለን፤ (ፊል.2፥6 ፤ ዕብ.1፥4 ፤ 3፥1-6)፡፡ ስለዚህም ይህን በማድረጉ እግዚአብሔርነቱን ይገልጣል፡፡
   ጌታችን ኢየሱስ ራሱም በአንደበቱ ፈሪሳውያንን፣  “ …. ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የዳዊት ልጅ ነው አሉት፡፡ … ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል?” (ማቴ.22፥41-45) ብሎ በመናገሩ፣ ከቅድስት ድንግል ከመወለዱም በፊት የእግዚአብሔር ልጅ እንደነበርና አምላካዊ ልጅነቱ የዘላለም እንደነበር ተናገረ፡፡ “…የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” (ገላ.4፥4) እና “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤” (ዕብ.1፥3) በሚሉት ንባባት ውስጥ፣ “ልጁን” እና “በልጁ” ሲል፣ ከዘላለም የነበረውን ልጅና በኋላ ከቅድስት ድንግል ሥጋን የነሣውን ጌታ እንደሚያመለክት ግልጥ ነው፡፡
    “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” (ቁ.19) የሚለው ንግግርም፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጥረት በፊትም ሆነ በኋላ በማናቸውም ኹኔታ ከአባቱ ተለይቶ ያደረገው አንዳች ነገር አለመኖሩንና ማድረግም እንደማይቻለው የተናገረበት ክፍሉ ነው፡፡
2.    መዋዕለ ሥጋዌው ባደረገው ሥራዎቹም አምላክነቱን ገልጧል፡፡ አምላክ ያሕዌ ብቻ የሚያደርገውን ሥራ ጌታችን ኢየሱስ ማድረጉን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ ጌታችን በአንድ ወቅት ሽባውን ሲፈውስ፣ “አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” (ማር.2፥5) በማለቱ ፍጹም አምላክነቱን ገለጠ፡፡ ይህን በማድረጉም “ከጻፎችም አንዳንዶቹ ... በልባቸውም፦ ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” አሉ፡፡ ይህን ያደረገበትን ምክንያት፣ “ ... ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ወንጌላዊው አጽንዖት ይሰጣል፡፡
   በግልጥ ቃል በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የያህዌን ሥራ[ኃጢአትን ማስተሥረይ] በመሥራት የያህዌንም ክብር ለራሱ ወስዷል፡፡ ይህን በማድረጉ አይሁድ እግዚአብሔርን እንደመሳደብ ቆጥረው በልባቸው አስበዋል፡፡ በአካላዊ ቃል አምላክነቱ ፈጣሪና አስገኚ፣ ደጋፊና አኗሪ ነው፤[5] (ዮሐ.1፥3 ፤ ቈላ.1፥16 ፤ ዕብ.1፥1-3 ፤ ራእ.4፥11)፣ በሁሉ የሚፈርድ ጻድቅ አምላክ ነው፤ (ዳን.7፥23 ፤ ዮሐ.5፥22 ፤ 27 ፤ 9፥39 ፤ ሐዋ.10፥42 ፤ 17፥31 ፤ 2ቆሮ.5፥10 ፤ 2ጢሞ.4፥1)፣ ሙታንን ማስነሣቱና ሕይወትን ሰጪ መኾኑም አምላክነቱን ያሳያል፣ (ዮሐ.1፥4 ፤ 5፥21 ፤ 25 ፤ 6፥40 ፤ 10፥10 ፤ 11፥25 ፤ 17፥2)፣ እረኝነቱና በጎቹን ከእርሱ የሚነጥቅ አንዳች አለመኖሩ አምላክነቱን ያሳያል፤ (ዮሐ.6፥37 ፤ 10፥29 ፤ 17፥12 ፤ ዕብ.13፥20) እና ሌሎችም ብዙ ሥራዎቹ አምላክነቱ በብዙ ምስክር የሚያስረዱ ናቸው፡፡
3.    ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ባሕርያቱም አምላክ መኾኑን የሚገልጡ ናቸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ልዩ ጠባያት አሉት፤ እንደያህዌ ዘላለማዊ ነው፤ (ዳን.12፥2 ፤ ሚክ.5፥2 ፤ 2ጴጥ.3፥8 ፤ ራእ.1፥17) አለመለወጡ፤ (ዕብ.1፥8 ፤ 13፥8)፣ ስግደትና አምልኮ መቀበሉ፤ (ማቴ.2፥11 ፤ ማቴ.15፥21 ፤ 14፥33 ፤ ዮሐ.9፥38 ፤ ፊል.2፥10 ፤ ዕብ.1፥6 ፤ ራእ.5፥12)፣ መላእክትን ማዘዙና ገንዘብ ማድረጉ፤ (ማቴ.13፥41 ፤ 2ተሰ.1፥7)፣ ኹሉን አዋቂነቱ፤ (ማር.2፥8 ፤ ዮሐ.1፥48 ፤ ዮሐ.2፥24-25)፣ በኹሉ ቦታ መገኘቱ፤ (ማቴ.18፥20 ፤ 28፥20 ፤ ኤፌ.1፥23) ... አምላካዊ ባሕርያቱን ገላጭ ነው፡፡
     ስለዚህም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በሁሉ የኾነ አምላካችን ነው፡፡ የእርሱን አምላክነት ወይም መለኮታዊ ማንነት የሚክዱ ሁሉ ከእግዚአብሔር መንግሥት በአፍአ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ መናፍቃኑ፣ “ትምህርተ ሥላሴን እናምናለን” እያሉ የሚናገሩ ቢኾኑም፣ “ሦስቱም አካላት አባት ናቸው፣ ያው አንዱ አባት ሥጋ ሲለብስ ልጅ እንደተባለ እንጂ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ የአብ የባሕርይ ልጁ ከቅድስት ድንግል ሥጋን አልነሣም” በማለት ሽምጥጥ አድርገው ትምህርተ ሥላሴን ሲክዱ እንመለከታለን፡፡ ለዚህም ነው መናፍቃን፣ “እንዲህ እናምናለን” የሚሉትን የትኛውንም ትምህርታቸውን ሲያብራሩ ይክዳሉ የምንለው፡፡ እኛ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን፣ ከአብ በተለየ ልዩ አካላዊ ቃልነቱ ከቅድስት ድንግል ሥጋ መንሣቱን፣ ለእግዚአብሔር አብም የባሕርይ ልጁ፣ ከአብም ከመንፈስ ቅዱስም በምንም በምን የማያንስ ፍጹም አንድ የኾነ መለኮትና አምላክ ነው እንላለን፡፡ ይህን ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ የመሰከሩልንን፤ እናምናለን፤ እንታመናለን፤ አሜን ወአሜን፡፡
ይቀጥላል …





[1] ቤተልሄም ታፈሰ፣ ከኃይሉ ዮሐንስ ጋር በExodus Tv፣ ተሾመ ዳምጠው ከኃይሉ ዮሐንስ ጋር ሲከራከርና በጋሻው ደሳለኝ በግል ካስተማረው ትምህርቶች በአንድነት ተቀናብሮ የተወሰደ ነው፡፡
[2] ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርት ክርስቶስ 2 እትም፤  1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ (ገጽ.224-225)
[3] ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ አባ)፤ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡ ገጽ.104-105
    [4] በጌታችን ትምህርት ውስጥ የእግዚአብሔር አባትነትና የክርስቶስ ኢየሱስ ልጅነት ፍጹም እኩልነትን እንደሚያመለክት አይሁድ አስተውለዋል፡፡ በተደጋጋሚ ይህን ትምህርት በማስተማሩም እጅግ ተቆጥተው፣ ተቃውመውታል፡፡ እግዚአብሔርንም እንደመሳደብም ቆጥረውታል፡፡ በልዩ መንገድ አባትና ልጅ ተካካይ መኾናቸውን፣ እርሱና እግዚአብሔር አብ አንድ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው መኾኑን በክርስቶስ ንግግር ውስጥ አይተዋል፡፡ ከቁ.19-30 ባለው ክፍልም ጌታ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አባቱ ጋር ተካካይ መኾኑን ተናገረ፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ አይሁድ አምላካዊ መተካከል እንዳለው በትክክል አውቁ፡፡
    አንድ አይሁዳዊ አባት ልጁ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው፣ ወገኖቹን ዘመዶቹን በአቅራቢያው ያሉትን ሁሉ ጠርቶ ትልቅ ድግስ ደግሶ ያከብረዋል፤ የማክበሩ ምክንያትም፣ “ልጁ እርሱን ወክሎ ልክ እንደእርሱ ማናቸውንም ሥራ ሊሠራ እንደሚቻለው ለሁሉም ያሳውቃቸዋል፤” ስለዚህም ልጁ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቱን በተመለከተ ማናቸውንም ሥራ የሚሠራው ልክ ከአባቱ ጋር በተካከለ ሥልጣን ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ አብን “አባቴ” ሲል፣ ልጅነቱ ማነስን ሳይኾን ፍጹም እኩልነትንና የባሕርይ አንድነት ያላቸው መኾኑን አመልካች ነው፡፡ አይሁድ ይህን ሲረዱ፣ ፍጹም የባሕርይ አንድነት መኖሩን በማወቅ ነውና አብዝተው ተቃወሙት፤ ሊገድሉትም ፈለጉ፡፡
    አይሁድ ይህን ታሪክ በሚገባ ያውቁ ነበርና፣ ሲቃወሙትም ከእግዚአብሔር ጋር ራሱን እንደማስተካከል በማየታቸውም ጭምር ነው፤ (ማቴ.21፥45 ፤ 26፥63 ፤ ዮሐ.10፥36)፡፡ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ.10፥30) ሲልም፣ “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን” (ዮሐ.10፥24) ላሉት ጥያቄ ጌታችን ኢየሱስ መሲሕ ብቻ ያይደለ፣ መሲሕ አምላክ መኾኑን አጽንቶ ተናገረ፡፡ በሌሎች ሥፍራዎችም ይህንን ትምህርት በተደጋጋሚ ተናግሮታል፡፡
   [5] በዘፍጥረት 1፥1 ላይ ያለውን “በመጀመሪያ እግዚአብሔር[ኤሎሂም] ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” የሚለው  “ኤሎሂም”፣ ሥላሴን አመልካች ነው፡፡ የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ግን አንዱ አባት የኾነው እግዚአብሔር አባትም፣ ልጅም ኾነ ስለሚሉ እውነታውን ይክዳሉ፡፡ የሚክዱትም ለሥላሴ ባሕርይ በማይጥም መልኩ ትንታኔን በመስጠት ወይም ትምህርትም በማቅረብ ነው፡፡ ሥላሴ ስንል፣ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው፡፡ አብ ያልተፈጠረ ነው፤ ወልድም የባሕርይ ልጅነቱ ከቅድስት ድንግል ሲወለድ አይደለም፡፡ መናፍቃኑ እንደሚሉት ያይደለ፣ ያልተፈጠረው አብ ከጊዜ በኋላ ልጅነትን ካገኘው ወልድ ጋር “ኤል - ኤሎሂም” መባል አይቻለውም፡፡ “ኤሎሂም” ፍጥረትን ከማስገኘት፣ ከፈጣሪነት፣ ከመጋቢነት፣ ከተቆጣጣሪነት፣ ከባለቤትነት እንዲሁም የዓለማትና የሰው ዘር ገዥ መኾኑን ከሚያመለክት ማንነት ጋር የተዛመደ ነው፡፡
    ኢየሱስ ልጅነትን ከድንግል ማርያም በመወለድ ያገኘ ከኾነና የኾነውም ከፍጥረት መፈጠር በኋላ ከኾነ፣ ካልተፈጠረው አብ ጋር “ኤሎሂም[ፈጣሪና አካል ያለው እግዚአብሔር]” ኾኖ ሊጠራ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ያልተፈጠረውን እግዚአብሔር አብንና ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ ወልድን አንድ ላይ እንጠራ ዘንድ የሚፈቅድልን ምንም አምክንዮታዊ ምክንያት የለንም፡፡ ፍጡርና ፈጣሪን አንድ ላይ ማስተካከል ባዕድ ትምህርት ነውና፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው ማቴዎስ፣ “ … በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም …” (ማቴ.28፥20)፣ ሲልና “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤” (ኢሳ.6፥3)፣ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ” (ራእ.4፥8) የሚለውን ሰማያዊ ቅዳሴና ውዳሴ ስንሰማ፣ ሦስቱም አካላት እኩልና ፈጽሞ የማይበላለጡ፤ የማይተናነሱም መኾናቸውን አመልካች ምስክር ነው፡፡

11 comments:

  1. ምርጥ ዓቃቤ እምነት

    ReplyDelete
  2. ተባረክ ግሩም ማስተዋልና እውነትም ዕውቀትም የተሰጠበት መልስ ነው ዘመንህ ይባረክ።

    ReplyDelete
  3. Ewunet tebarek wondim. Degegna meleikt new.

    ReplyDelete
  4. Ewunet tebarek wondim. Degegna meleikt new.

    ReplyDelete
  5. Ewunet tebarek wondim. Degegna meleikt new.

    ReplyDelete
  6. Remain blessed and be blessings for others dear

    ReplyDelete
  7. መስከረም(Dalls,Tx)25 November 2017 at 22:27

    የተወደድክ ወንድሜ እግዚአብሔር በረዳህ መጠን ትውልዱን ለመድረስ በብዙ እየተጋህ ነው አሁንም እግዚአብሔር ይርዳህ!! የድንግልም ምልጃ እና ፀሎት አይለይህ።አንድ ነገር ልበል የዚህን ሁሉ ውጥንቅጥ እኮ የችግሩን መሰረት አለመረዳት ነው። ድሮ ማርያም አታማልድም፥ እየሱስ ብቻ በቂ ነው እረ ስንቱ.እኛም ደሞ በደንብ ሰማናቸውና ተከተልናቸው, ለአሉን ሁሉ አሜን ይሁን አልን የከፍታ ዘመን መጣ አልን, ኢትዩጵያዬ ዘመንሽ ሁሉ በእየሱስ ስም ይቀየር ብለን ዘመርን። በዚው ትውልድ ክርስቶስን አላገኛችሁትም ብለው የልጅነት ጸጋ ካገኘንበት አስወጥተውን ይህው ትውልድ ሳያልፍ 3 አስርት አመታት እንካን ሳይሞላቸው እየሱስ ጌታ ነው እያሉ ያለእየሱስ ሊያስቀሩን እየሰሩ ነው። ይህንን ደሞ ለማወቅ ትምህርታቸውን ማዳመጥ ማዳመጥ በቂ ነው።እስኪ ወንድሜ አቤነዘር በደመወዝ ጎሽሜ የተጻፋ መጻፍ(ዓሥራ ሥድሥት)የፍጥረት ናፍቆት የሆነው የድል ነሺው ድምፅ የሚለውን መጻፍ ካላነበብከው እባክህ ፋልግና አንብበው።ስለብርታትህ ሁሉ ልዑል እግዚአብሔር ይመስገን!!! እኛስ ሀይማኖት ለዋጮችንና ስራቸውን እንጠየፍለን። እኛስ እየሱስ ከርስቶስ ከድንግል ማርያም በነሳው ስጋ እንደተዋሀደ(መለኮት) እናምናለን ለዘላለም በዚ እውነትና መሰረት ለይ ተሰርተናል። አሜን !!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. እህቴ መስከረም ሰላምና ፍቅር በክርስቶስ ይብዛልሽ! ደጋግሜ ሳይሽ አስተያየት ስትሰጪ አንድ ወገንን በመውቀስ ነው፡፡ እርግጥ ነው በነዚያ ዘንድ ብዙ ስህተት አለ፡፡የዚያኑ ያህል እኛም ጋ ስህተት አለ፡፡ክርስቶስ በቂያችን መሆኑ አያከራክርም፡፡ይህ ማለት ቅዱሳንን ጻድቃንን መጥላት መናቅ አይደለም፡፡ ኢየሱስ በቂ ነው ያሉሽ ሰዎች በግል ድካማቸው ስለወደቁ የኢየሱስን ብቻ በቂነት አትጠራጠሪ፡፡ቃሉ ሕያው ነውና፡፡

      Delete
  8. እህቴ መስከረም ሰላምና ፍቅር በክርስቶስ ይብዛልሽ! ደጋግሜ ሳይሽ አስተያየት ስትሰጪ አንድ ወገንን በመውቀስ ነው፡፡ እርግጥ ነው በነዚያ ዘንድ ብዙ ስህተት አለ፡፡የዚያኑ ያህል እኛም ጋ ስህተት አለ፡፡ክርስቶስ በቂያችን መሆኑ አያከራክርም፡፡ይህ ማለት ቅዱሳንን ጻድቃንን መጥላት መናቅ አይደለም፡፡ ኢየሱስ በቂ ነው ያሉሽ ሰዎች በግል ድካማቸው ስለወደቁ የኢየሱስን ብቻ በቂነት አትጠራጠሪ፡፡ቃሉ ሕያው ነውና፡፡

    ReplyDelete
  9. Thank you so much

    ReplyDelete
  10. እኛ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን፣ ከአብ በተለየ ልዩ አካላዊ ቃልነቱ ከቅድስት ድንግል ሥጋ መንሣቱን፣ ለእግዚአብሔር አብም የባሕርይ ልጁ፣ ከአብም ከመንፈስ ቅዱስም በምንም በምን የማያንስ ፍጹም አንድ የኾነ መለኮትና አምላክ ነው እንላለን፡፡ ይህን ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ የመሰከሩልንን፤ እናምናለን፤ እንታመናለን፤ ጌታ በነገር ሁሉ ማሰስተዋልን ይሥጠን

    ReplyDelete