በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለኪዳኑ ሕዝብ የተገለጠበት መንገድ እጅግ አስደናቂም፤ አስፈሪም ነበር፤ “… በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።” (ዘጸ. 19፥16) እንዲል፣ እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች ሲገለጥ፣ ማንም ሊቀርበው በማይችል መንገድ ነው፤ እንኳንና እግዚአብሔርን ርሱ የሚገለጥበትን ተራራ መንካት የማይታሰብ ነገር ነው፤ “… ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤” (ዘጸ. 19፥12)። እጅግ በሚያደንቅና በሚገርም መንገድ የፊተኛው ኪዳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንኳ፣ “በፍርሃት ተንቀጠቀጥሁ” ብሎአል፤ (ዕብ. 12፥21)።
መዝሙረኛው ስለ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ውስጥ ያለውን ግርማዊነት በመደነቅ
በዘመረበት ክፍሉ እንዲህ ብሎአል፤ “አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥
ውኆችም ጮኹ።ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር
ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም” (መዝ. 77፥16-18) እንዲል፣ አገላለጡ በሚያናውጥና በሚያንቀጠቅጥ መንገድ ነበር። ለአሕዛብም
እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበት መንገድ፣ “ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ።” (1ሳሙ. 14፥15)
እንዲል፣ እጅግ በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ መንገድ ነው።
ከዚህ የተነሳ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን “ሬቨረንድ” የሚል ስም
ተሰጥቶታል፤ ትርጓሜውም “የተፈራ ወይም እጅግ የተከበረ” ማለት ነው፤ (መዝ. 111፥9)። በርግጥም እግዚአብሔር እጅግ
የተፈራና የተከበረ አምላክና ገዢ ነው። “በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥”፣ “«አምላክህ እግዚአብሔር» የተባለውን
የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም”፣ “በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው።”፣ “ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥” (ዘጸ.
15፥11፤ ዘዳ. 28፥28፤ 1ዜና. 16፥25፤ ነህ. 1፥5) እኒህና ሌሎችም የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ይመሰክራሉ።
ይህ ገናና አምላክ ግን እኛን ስለ ማዳን የመጣበት መንገድ እጅግ
የሚደንቅና እጅን በአፍ የሚያስጭን ነው። ያ አስፈሪና በብዙ እሳትና ደመና፤ በዐውሎ ውስጥ ይገለጥ የነበረው ጌታና አምላክ፣
“[ቅድስት ማርያም ሕፃኑ ኢየሱስን]በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።”
(ሉቃ. 2፥7) ተብሎ ተነገረለት።
ባለጠግነቱ ሊነገር የማይቻለው፣ ከአንዲት ድኃ ሴት ተወልዶ ተገለጠ፤
ማንም ሊቀርበው ብርሃንና ጨለማ ውስጥ በኪሩቤል በተከከበና በከበረ ዙፋን የሚኖረው ጌታ፣ ከአንዲት በረት ውስጥ ከከብቶች
መካከል ዐደረ፤ እሳታውያን በኾኑት ኪሩቤል ጀርባ የሚቀመጠው ጌታ በአንዲት ሴት ክንድ ታቀፈ። ይደንቃል!
ስለ ሰው ልጅ መዳን ብሎ ክብሩንና መለኮታዊ ጥቅሙን ኹሉ ተወ፤
በፈቃዱ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥” (ፊል. 2፥7)፤ ከጥፋት ልጅ በቀር የጠፋውን ዓለም
ኹሉ ገንዘቡ ሊያደርግ፣ ሰውን ኾነ፤ በሰው መካከል ተመላልሶ የሰውን ኹሉ መከራና ስቃይ ይካፈል ዘንድ ሰው ኾነ፤ የታመሙትን
ሊያድን የሚታመም ሥጋን ለበሰ፤ ከኀጢአት በቀር ስለ እኛ ይፈተንና ድል ይነሣ ዘንድ እኛኑን ኾነልን፤ ተዛምዶ አዛመደን፤
አፍቅሮን እናፈቅረው ዘንድ ግድ አለን፤ በትህትና ተገልጦ ግርማውን አለበሰን፤ በበረት ተገኝቶ ወደ አባቱ ቀኝ ሳበን፤ ክብር
ለድል ነሺውና ለአሸናፊው ጌታና መሲሕ ኢየሱስ፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment