Thursday, 28 December 2017

የማይለወጠው ዥንጉርጉሩ ነብርና የኢትዮጲያዊ መልክ

 ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፦ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ፡፡” (ኤር.13፥23) በማለት፣ ስለይሁዳ ኃጢአት በከባድ ወቀሳ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ይሁዳ ተጠራርጋ በእግዚአብሔር ፍርድ ልትጠፋ እንዳለች በእግዚአብሔር ስለተረዳ፣ ሚስትን ከማግባትና ልጆችንም ከመውለድ ተከልክሏል፤ (ኤር.16፥1-4)፡፡ ትዳር ብቻም ሳይኾን ወዳጆቹም እጅግ ጥቂቶች ነበሩ፤ አኪቃም (26፥24)፣ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስና (39፥14) ኢትዮጲያዊው አቤሜልክ ናቸው (38፥7)፤ የክፋቱ ጠጣርነት ከሰው በብዙ ስላገለለው ረጅም ዘመኑን ያሳለፈው በሐዘን ነው፡፡
     የይሁዳ ኃጢአቶች የተገለጡና ለኹሉ የታዩ ነበሩ፤ “ይሰርቃሉ፥ ይገድላሉ፥ ያመነዝራሉ፥ በሐሰትም ይምላሉ፥ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ይገፋሉ፥ በቅዱሱም ስፍራ ንጹሕ ደምን ያፈስሳሉ፥ ስሙም በተጠራበት በቤተ መቅደሱ በፊቱ ቆመው፦ ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም ብለው ይክዳሉ፣ ስሙ የተጠራበት ቤት በዓይናቸው ፊት የሌቦች ዋሻ አደረጉት፣ የቀደሙት አባቶቻቸው እግዚአብሔርን ተዉ፣ አመነዘሩ፣ አማልክት ያልሆኑትን ለራሳቸው አማልክትን አድርገው፣ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም፥ ያስቈጡትም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል አጠኑ፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን አፈሰሱ፣ ሕጉንም አልጠበቁም፤ እንዲኹም እነርሱም ከአባቶቻቸው ይልቅ ክፉ አድርገዋል፤ እነሆም፥ ሁላቸውም እንደ ክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄደዋል እርሱንም አልሰሙትም” (7፥1-11፤ 16፥11፤ 20፤ 22፥9፤ 23፥10፤ 32፥29፤ 44፥2፤ 23)፡፡ በዚህ ኃጢአታቸው እግዚአብሔርን ፈጽመው አስቆጥተውታል፡፡

    ኤርምያስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ባየው ኃጢአትና እየኾነ በነበረው ነገር ኹሉ እጅግ ልቡ ተሰብሯል፤ የኤርምያስ የልቡ ሕመምና ከፍ ያለው የነፍስ ቁስሉ፣ ከገዛ ቤተሰቡ፣ ከመሪዎች፣ ከሕዝቡና እንደሐናንያ ካሉ ሐሰተኛ ነቢያት(28፥1) ጭምር የተነሣ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ኃጢአትና በደል መፋቅ የማይችል እስኪመስል ድረስ ያለፈባቸው መንገዶች ከባድና መራር ናቸው፡፡
     በሚደረገው ሃይማኖታዊ የአምልኮ ሥርዓት እግዚአብሔር ፈጽሞ ደስተኛ አልነበረም፤ “የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያሉ በሐሰት ቃል ይታመኑ (7፥4)፣ በሚያደርጉት በማናቸውም መንገዳቸው ከመቅደሱ ሳይለዩ በአምልኮአቸው ኹሉ ግን መሥዋዕት ቢሠዉም፣ ዕጣን ቢያጥኑም፣ ቁርባን ቢያቀርቡም … ከሽንገላና ከግብዝነት የጠራና ለእግዚአብሔር ክብር በማድላት የቀረበ አይደለምና፣ እየኾነ የነበረው ነገር አስቀያሚና አስፈሪ ነበር፡፡
    በዚህ መንፈስ ውስጥ የነበረችውን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን በተመለከተ ጥያቄያዊ ትንቢትን ተናገረ፡፡ ትንቢቱ፣ ከኃጢአትዋ ብዛት የተነሣ የልብሷን ዘርፍ ገልጦአል፣ ተረከዟንም ገፍፎአልና፣ “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ፡፡” የሚል ነው፡፡ ጥያቄው መልስ የሚጠብቅ አይደለም፤ ምላሹ አሉታዊ መኾኑ የታወቀ ነውና፡፡ ኤርምያስ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ኃጢአት ለመግለጥ የተጠቀመው የታወቀ ምሳሌን ነው፡፡
   ይሁዳ በኃጢአት ፈጽሞ ከማትመለስበት ደረጃ ደርሳ ነበር፤ እርሷን በንስሐ ከመመለስ ይልቅ የኢትዮጲያዊውን መልክና የነብርን ዥንጉርጉነቱን ማስለቀቅ ወይም የተፈጥሮን ሕግ የመለወጥ ያህል ኀጢአቷ እጅግ ሥር የሰደደና ንስሐ የመግባት ተስፋዋ ፈጽሞ የተሟጠጠ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የንስሐ ጥሪውን ደጋግሞ አኹንም ድረስ ቢያቀርብም እንኳ፣ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ፈጽሞ ካለመመለስ ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር፡፡ ተፈጥሮን ለመለወጥ የማይቻለውን ያህል[እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት ራሱ ስለማይክደው] እግዚአብሔር ነጻ ፈቃዳችንን ፈጽሞ አይቃረነውም፤ ወይም በመገደድ መልካሞች እንድንኾን አያደርገንም፡፡
   ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ በክፋት መጽናትና በንስሐ ራስዋን ለመለወጥ አለመዘጋጀት በንጽጽር የቀረበው፣ ኢትዮጲያዊ መልክና የነብር ዥንጉርጉርነት ነው፡፡ ኢትዮጲያዊ መልክ ጥቁር፣ በበረሃ ዋዕይ የበለዘ መልክን የሚያመለክት ነው፡፡[1] ይህ መልክ ከግብጽ በስተደቡብ ጥቁር ዐባይና ነጭ ዐባይ እስከሚገናኙበት የነበረውን አገርና መንግሥትን የሚያካልል እንደኾነ ይታመናል፤ እኒህ ወገኖች መልካቸው መለወጥ የማይችል ተብሎ ተተርጉሞላቸዋል፤ ልክ እንደነብር ዥንጉርጉርነት፡፡ በዚህ ዓውድ ኢትዮጲያዊነት የታወቀና ሊለወጥ የማይችል መልክን በምሳሌነት ከመግለጥ አንጻር እንጂ ሌላ ምንም ምስጢራዊ ፍቺ የለውም፡፡

    ኤርምያስ በእውነተኛ ንስሐ ቢመለሱ ሊመጣ ያለውን ፍርድና ቅጣት ሊያስቀር እንደሚችል፣ ደጋግሞ በማስጠንቀቂያ ጭምር ለከተሞቹ ቢያመለክትም፣ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ግን ሊመለሱ ፈጽመው አልወደዱም፡፡ ኀጢአት በተደጋጋሚ ሲሠራ ነጻ ፈቃድ  ጭርሱን ይጠፋል፡፡ ኀጢአትም የኑሮ ዘይቤ፣ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ይኾናል፤ ከተፈጥሮም ይልቅ ኹለንተናን ይገዛል፡፡
    እግዚአብሔር ሕዝቡ ኃጢአት ለመሥራት የወደዱትን ምርጫቸውን አልከለከላቸውም፤ በዚያ አለመከልከል ውስጥ ደግሞ የኀጢአት ነጻነታቸውንና ሊመጣ ያለውን ውጤቱንም እንደሚቀበሉት ተናገራቸው፡፡ አለመለወጥ መብት ነው፤ ያለመለወጥን ውጤት መቀበል ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ የእስከመጨረሻ እንቢተኝነት ፍጻሜው አደገኛ ቅጣትና ውርደት ነው፡፡ የጥያቄው ምላሽ ይህን በሚገባ ያስረዳል፤ “ክፋትን የለመዳችሁ” የሚለው የጥያቄው ምላሽ ውስጥ ያለው ሐረግ ልማድ የቱን ያህል ኀይል እንዳለውና በራስ ለመላቀቅ የማይቻል መኾኑን ያሳያል፡፡ በንስሐ ለመመለስና ለመለወጥ አለመውደድ ፍጹም የተንኰለኝነትና እጅግም ክፉ የመኾን ጠባይ መገለጫ ነው፤ (17፥9)፡፡
     በዳዊት መዝሙር ውስጥ የድፍረት ኀጢአት በታላቅነቱ ተጠቅሷል፤ “የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ” (መዝ.19፥13)፣ የልማድም ኃጢአት ብዙ ጊዜ የሚደረገው በፍጹም ድፍረትና በትዕቢት ነው፡፡ ኃጢአትን ተላምደነው የኑሮ ዘይቤ ስናደርገው የማንላቀቀው ባሕርያችን ይኾናል፡፡  ስለዚህም ኤርምያስ ይህ አደገኛ ልማድ ከኹለንተናቸው እስከመጨረሻው እንዲወገድ በብርቱ ቃል ይናገራቸዋል፡፡
   ይህ ኾኖ ባይመለሱ ግን ሊመጣ ያለው ፍርድ አደገኛና ማንም የማይመልሰው ነው፡፡ “ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፡፡” (ኤር.17፥24) ይህ አስፈሪና ከባድ ፍርድ ነው፤ ነፋስ ብትንትኑን እንደሚያወጣው ገለባ(እብቅ)፤ ኀጢአትን እንደኑሮ ዘይቤያቸው አድርገው ጸንተው ለሚኖሩ ክፉዎች፣ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው ነው፤ “ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው፡፡” እንዲል መዝሙረኛው፤ (መዝ.1፥4)፡፡
   ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከወናዎች ኮረብቶች የሚመጣው የበረሃ ነፋስ(4፥11) የሚጠብስ፣ እጅግ ደረቅ፤ አሸዋና አቧራ አዝሎ የሚጓዝ ሞቃትና ፈጣን ሲኾን፤ አደጋ አድራሽነቱ ከባድና ታላቅ ነው፡፡ እንደኢትዮጲያዊ መልክና እንደነብር ዥንጉርጉርነት በኃጢአት ፈጽሞ መጽናት፣ ለመለወጥ አለመፈለግ፣ ኃጢአትን የኑሮ ዘይቤ አድርጎ መኖር ፍጻሜን እንዲህ በውድቀትና በታላቅ ጥፋት ያመሰቃቅላል፡፡
   ኢትዮጲያዊ መልክ በሚለው ነገር ዙርያ እግረ መንገድ አንድ ነገር ላንሣ፦ አኹን ኢትዮጲያ ያለችበት ኹኔታ “የነበረ መልካችንን” የሚያጠለሽና በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት ዳርቻው አስፈሪ ይመስላል፡፡ ማኅበረሰባዊ ኀጢአታችን ከፊት ይልቅ በቤተ መንግሥትም በቤተ ክህነትም በግልጥ እየታየ ያለበት ጊዜ ቢኖር አኹን ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ የቆየ ቁርሾ፣ የተጠበቀ ቂም፣ “ከዚህ ቀደም ተረግጫለሁኹና ይበቃችኋል” የሚል ውስጥ ውስጡን የመረቀዘ የበቀል መግል፣ … ካልፈነዳኹ እያለ ምልክቱን እዚህና እዚያ ሲያሳይ ተመልክተናል፤ ግላዊ ጠቦች ሁለት ብሔርተኞችን ካናተፈና ካባላ፣ ከተማን ካዘረፈና ለሌሎችም ንጹሐንም ሞት ምክንያት ከኾነ፣ ሰላማውያን እንመስል ነበር እንጂ የለየልን ጠበኞች ነበርን ማለት ነው፡፡
    ሰባራ ቀን ጠባቂው ጠባያችን የክፋትን ዕድል ኹሉ አሟጦ ሊጠቀም የተነሣው ድንገት አይደለም፡፡ ቁጣችን ድንገት የገነፈለ አይደለም፤ ዘረኝነትና መንደርተኝነታችን የራሴን ወገን ሳይና ቋንቋውንም ስሰማ እንጂ ሌላውን ብሔር ቋንቋ መስማትና መልኩንም ማየት “ይነስረኛል” ካልን፣ ፈቅደን አልያም ተታለን በስመ ፖለቲካና ሃይማኖት በትልቁ የተሠራብን የኀጢአትና የክፋት ድርና ትብ አለ ማለት ነው፡፡ ይህን አስተውሎ ከበደል አለመመለስና በዚያው በተጀመረበት መንገድ መቀጠል ግን ጠቡ ሰዋዊና ማኅበረሰባዊ መኾኑ ቀርቶ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ይኾናል፡፡
    ልክ “እንደታወቀው መልካችን”፣ የታወቅንበት ኢትዮጲያዊ “ሌላም መልክ” አለን፤  ባለብዙ ብሔርና ባለብዙ ቋንቋ ነን፤ አንዳችን ለሌላችን መኖር ጌጥና ሞገስ ነን፤ የቱም ብሔር ከየትኛውም ብሔር አያንስም፤ አይበልጥምም፤ ከምንም በላይ ሰው-ነታችን የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ነው፡፡ ማናቸውንም ሰው የሚጠላ፣ የሚንቅ፣ የሚገድል … ሰው ካለ የሚጠላው፣ የሚንቀው፣ የሚገድለው በእርሱ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መልክና አምሳያ ነው፡፡
     በተለያዩ የአገራችን ከተሞችና በአኅጉራችን የሚደረጉ ዘርና ብሔር ተኰር ንቀቶች፣ ስድቦች፣ ደም ማፍሰሶች፣ ግድያዎች፣ ንብረት ውድመቶች … ሰውን በሰው-ነቱ ላለመቀበል የሚደረጉ ዓመጾች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ይህን አምርሮ ይጠየፋል፡፡  ወደበጐነትና መቀባበል እንመለስ፣ እንያያዝ፣ ለዓመጽና ለክፋት ከምናድም፣ ከምናምጽ ለፍቅርና ለመያያዝ፣ ለመከባበርና ለመቀባበል ንስሐ እንግባ፤ ይህ የኑሮ ዘይቤያችን ይኹንልን፤ በዚህ ብንጸና ግን አግዚአብሔር ከኃጢአት ጋር አይመቻመችም፤ ደግሞም ሳይቀጣን አይቀርም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ለሕዝብህ ማስተዋልን አብዛ፤ አሜን፡፡





[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ.163

5 comments:

  1. Geta yirdan lk neh bzu neger tru tru ayshetm

    ReplyDelete
  2. Amen Geta mastewalun yabzaln.

    ReplyDelete
  3. ምንም አለውቅም ብትል አይሻልም?መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስንትት ጊዜ ኢትዮጵያ ተጠቅሳለች?በቁራንስ?ረክሰህ ሐገራችንን አታርክስ::

    ReplyDelete
  4. አውቃለሁ በሚል ከፍታ ያለማወቅ ዝቅታን በአደባባይ!ዱያቀን አብ የእነሱ ዘር አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ: በአለም ላይ ሚሊዮን እምነቶች አሉ እነሱም እንደየእምነት ስርአታቸው አንድ አምላክ አለ ይላሉ:: ቢሆንም ብዙ እምነት አለ እና ብዙ አምላክ አለ አይባልም: ስለዚህ ሁሉም ውሸታም ሆኖ አንድ እምነት ግን ትክክለኛ አምላክ ያለው አለ ማለት ነው:: እናም አንተ የምታምነው እምነት ትክክል ነው ካልክ ከሌላው በተለየ መልኩ ትክክለኝነቱን አሳይ(+) ዝም ብለህ እንዳትመልስ ጥናት ይፈልጋል

    ReplyDelete