የተሐድሶ ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰውም ኾነ አንዳች ተቋም አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ
ይህን የሚያደርገው ደግሞ በምሕረቱ ብዛት ነው። በባቢሎን ምርኰ ሳሉ እግዚአብሔር በተሐድሶ እንዴት ያለ ጕብኝት ለእስራኤል እንዳደረገላቸው፣
ነቢይና ካህን የነበረው ዕዝራ ሲናገር፣ “ … አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም የሕይወት
መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን
ዘንድ …” (ዕዝ. 9፥9) በማለት፣ የሕይወትን መታደስ ወይም የሕይወት ተሐድሶ የሚሰጠው ራሱ እዚአብሔር ብቻ እንደ ኾነ ገልጦአል።
እግዚአብሔር እንደ ወደደ ተሐድሶን ለሕዝቡ ይሰጣል፤
የተሐድሶ ጥሪ ደግሞ ለየትኛውም ቤተ ክርስቲያን የሚኾን መለኮታዊ ዐሳብ ነው። በእግዚአብሔር ቃል መሠረት የማትኖር የትኛዋም ቤተ
ክርስቲያን አካሄዷንና ትምህርቷን በእግዚአብሔር ቃል የማረም ጥሪ ሲደርሳት፣ ይህን ጥሪ የመታደስ ጥሪ ልንለው እንችላለን። ይህ
ጥሪ ደግሞ የእግዚብሔር ሥራ እንጂ፣ የሰው ሥራ ሊኾን አይችልም። እናም የተሐድሶ ባለቤቱ እግዚአብሔር ስለኾነ፣ ተሐድሶን እግዚአብሔር
ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው መልካም ዕድል አድርገን እንመለከታለን። እኛም እንኳ ሐዳስያን ነን ስንል፣ በፈቃዳችን ለእግዚአብሔር ዐሳብ
መገዛታችንን ለማሳየት እንጂ የተሐድሶ ጀማሪያን ነን ለማለት አይደለም። ደግሜ እላለሁ፣ የተሐድሶ ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው።
እናም ይን የተሐድሶ ጥሪ ዕድሉን ለማባከንም ኾነ
እኛ ባለቤቶቹ መስለን ለመታየት ምንም ዓይነት ጥረት አናደርግም። ለእግዚአብሔር ክብርና ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ቤተ ክርስቲያን፣
ወደ እግዚአብሔር ቃል በእውነትና በመንፈስ ወደሚደረግ አምልኮ እንድትመለስ ዘወትር በጸሎትና በእምነት ኾነን ዐሳባችን ዘወትር ባለመታከት
እናቀርባለን። “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የኾነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትኖ ለማወቅ በመታደስ
የተለወጠ ልብና ይህን ዓለም አለመምሰል” ያስፈልጋልና፤ (ሮሜ 12፥2)።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን በተደጋጋሚ
ይህን የከበረና የእግዚአብሔር ሥራ የኾነውን ተሐድሶ፣ ስትቃወምና ላለመቀበልም ሐዳስያንን ስታሳድድ መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም።
በተለይ ደግሞ በአርባምንጭ ከተማ ከዓመታት በፊት ይህን የተሐድሶ ዐሳብ በመቃወምና በአገልግሎት ላይ የነበሩትን ወንድሞችና እህቶች
በመደብደብ፣ የአካል ጉዳት በማድረስ፣ ንብረት በመዝረፍና ሰዎችን በማሳሰር “ተሐድሶን ላለመቀበል” ግልጥ የኾነ ተቃውሞ አሳይታለች፤
ከዚህም ባለፈ በግልጥ ማኅበረ ቅዱሳን በቲቪው እንደ ሠራው “ዘገባ”፣ “ተሐድሶ ከቶውንም በአርባምንጭ ከተማ ዳግም የመቀጠል አንዳች
ተስፋ እንደሌለው” በመዘበት ሲናገር ተደምጦአል።
እውነታው ግን ተሐድሶ አስቀድመን እንደ ተናገርን
የእግዚአብሔር ዐሳብ እንጂ የሰው ስላይደለ፣ ሰዎችም ኾኑ ማናቸውም የተደራጀ ተቋም ሊያግደው አይችልም። ለዚህም ነው ባለፉት ሳምንታት
ከአርባ ምንጭ ከተማ አልፎ በዙሪያቸው ባሉ ከተሞችና ወረዳዎች ጭምር የተደረጉት “የኦርቶዶክሳዊ ተሐድሶ” ጉባኤያት ተስፋፍተው ለብዙዎች
የወንጌል ብርሃን ማየት ምክንያት ኾኖ የምናገኘው።
ከጥንት ጀምሮ ወንጌልን በግልጥ የሚሰብኩ የወንጌል
ባላደራ ቅዱሳን፣ መከራን መቀበል የሚጀምሩት ከገዛ ወገናቸው ወይም ከሚያቀውቋቸው ዘመዶቻቸው ነው፤ ይህ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
እንደ ተናገረው፣ ወንጌል ልዩነት በማድረግ የምትታወቅ መኾኑን ትልቅ ማሳያ ነው። በአርባ ምንጭ የሚገኙ የማኅበረ አኀው የክርስቶስ
ቤተ ክርስቲያን አማኞችና የመንግሥቱ ባለሟሎችም በዚህ በረከት ስለ ተጐበኛችሁ፤ አኹንም እየተጐበኛችሁ ስለኾነ ስለ እናንተ እጅግ
ደስ ብሎናል፤ ጌታችን ኢየሱስ አብዝቶ ይባርካችሁ፤ አሜን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ
ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment