“ … በሕዝብ ሁሉ ዘንድ
የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥
እንዲህም አላቸው፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። … ከእግዚአብሔር እንደ
ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። ሰሙትም፥…” (ሐ.ሥ.
5፥34-35፡ 39-40)
“… በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ
እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ።” (ሐ.ሥ. 22፥3)
እኒህ ኹለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ገማልያል ማንነት በትክክል
የሚነግሩን ነገር አላቸው። ገማልያል በኹለቱም ክፍሎች እንደ ተጠቀሰው አስደናቂ የሕግ መምህርና በሕዝቡ ኹሉ ዘንድ ቅቡል የኾነ
ሰው ነበር፤ ይኹን እንጂ በዚህ ወቅት ገማልያል፣ ርቱዕ ክርስትናን ስለ መቀበሉ የሚነግረን አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል
የለም።
“በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር” ገማልያል ምንም እንኳ
ክርስትናን ባይቀበልም፣ ሐዋርያት የመሲሑን የመንግሥት ወንጌል በመስበካቸው ምክንያት ስለ ገጠማቸው ተግዳሮትና መከራ የሰጠው
ምክር ግን እጅግ አስደናቂ ነው። አስቀድሞ ለክሱ ምክንያት የነበሩት ሰዱቃውያን ናቸው፤ “ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን
ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው።” (ሐ.ሥ. 5፥17) እንዲል። ያለ ፈሪሳውያን ምክር ሰዱቃውያን
ብቻቸውን ሐዋርያትን እንዲገድሉላቸው ሮማውያንን መጠየቃቸው “ፖለቲካዊ ሞኝነት” ነበር። ብቻቸውን ለማጥቃት መሞከራቸው በራሱ
አደገኛ ቢኾንም፣ ውጤታማ አለመኾናቸውን የሐዋርያት ሥራ የጻፈልን ሉቃስ ወንጌላዊ፣ “ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።”
በማለት በወቅቱ የነበረውን ነገር በትዝብት ያስቀምጥልናል (ቊ. 26)።
አስደናቂ በኾነ መንገድ፣ የሰዱቃውያን ሃይማኖተኛ ቡድን በሰው ፊት ሲታዩ
እጅግ የተሳካላቸው ነበር፤ ነገር ግን በሐዋርያት የሚደረገውን ትምህርትና ድንቅ ተአምራት የሚቃወሙና የሚያቃልሉ ነበር፤ በሰው
ፊት መደመጥ መቻል፤ አያሌ አጃቢና አጋፋሪ ማግኘት ርሱ የመጨረሻው የእውነት መለኪያ አይደለም፤ ኾኖም አያውቅም። ገማልያል በሚገባ
ስላስተዋለ፣ ለእውነት በማድላት ራሱን ገለጠ።
በርግጥ የሕግ መምህሩ የገማልያል መንገድ በተወሰነ መንገድ ነቀፋ
የሌለበት አይደለም፤ “…ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ
ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።” ብሎ ኢየሱስንና ሐዋርያትን በሚጠሉአቸውና ሊገድሉአቸው በሚፈልጉ ሰዎች
ፊት መናገሩ ግን ቀላል አይደለም። የኢየሱስ ከሙታን መካከል መነሣትና ደቀ መዛሙርት ከሚያደርጉት ተአምራት በላይ ሌላ ምስክር
ባያሻም፣ ገማልያል ይህን “ፈራ ተባ እያለ”፣ “ከእግዚአብሔር ከኾኑ ልታጠፉአቸው አትችሉምና ከእግዚአብሔር ጋር እንዳትጣሉ
ምናልባት ተጠንቀቁ” ሲል እንሰማዋለን። የተናገረው እምብዛም ምስጋና የሚገባው ባይኾንም፣ ግና ፍጹም እውነትና የማይለወጥ ሐቅ
ነው።
ኢየሱስ ከሙታን መካከል ተነሥቶአል፤ ሊስተባበል አይችልም፤ ሐዋርያትም፣
“… በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም
ይፈወሱ ነበር።” (ሐ.ሥ. 5፥16) እንዲል፣ የሐዋርያትንም ፈውስ ማስተባበል አይቻልም ነበር፤ ግን ይህን እውነት ላለማየት
ሰዱቃውያን ታውረው፤ ገማልያል ለጊዜው ከማመንና ከመቀበል ዘግይተው ነበር።
ዛሬም ይህ እውነት አለ፤ በብዙ ድጋፍና አጀብ፤ በአጋፋሪና ሆይታ፤
በቲፎዞ ብዛት እውነት መሳይ ሐሰትን ለማቆም የሚጥሩ አሉ። ጥቂቶች ግን ምናልባትም ድምጻቸው ሳይሰማ ለእውነት ጨክነው የቆሙ ጽኑዕ
ሃያላን አሉ፤ የገማልያል ማስተዋል ለጊዜው ሰሚ ቢያገኝም፣ ግን አልጸኑበትም። ከጀማው ጋር አላበረም፤ ተነጥሎ ወይም ተገልሎ
መከራቸው፤ ሰሙት ግን አልተከተሉትም።
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ገማልያል ቊጥሩ ካመኑ ቅዱሳን መካከል ነው፤
በልበ ሰፊነት ተነጥሎ ማሰቡ ጠቀመው፤ ከቡድንተኛ አስተሳሰብ መላቀቁ ወደ መሲሑ ማኅበረ ሰብ ሳበው። የምንሰማውን በቃሉ
መፈተሽ፣ የምናደርገው ነገር ከሰው ጋር ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ያጣላኝ ይኾን? ብሎ ማሰላሰል፣ ለጀማችን ከመታመን ይልቅ
ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ ሥራ ማድላት እውነተኛነትና ገማልያላዊ ማስተዋል ነው።
ኢየሱስን በማይጠፋ ፍቅር
ለምትወድዱ ኹሉ ምሕረትና ጸጋ ይብዛላችኹ፤ አሜን።

No comments:
Post a Comment