Sunday, 28 October 2018

ከ“ቄስ” በላይ መኮንንና ከኢዩ ጩፋ ጀርባ የቆመ የዘረኝነት ግንብ

Please read in PDF

   በዘመናችን ባለው ክርስትና ውስጥ፣ እንደ ዘረኝነትና መናፍቅነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተሰፋለት ነውር ኃጢአት ያለ አይመስልም። ኹለቱም መንፈሳዊ ካባ ለብሰው፣ ራሳቸውን ሸሽገው፣ ሾልከው ከመካከላችን ገብተው አሉ። ከኀጢአት ኹነኛ ባሕርያት አንዱ እንዳይታወቅ ራሱን መሸሸግ ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የዘር ምሳሌ ላይ ጠላት እንክርዳድን የዘራው፣ “ሰዎቹ ሲተኙ” ነው፤ (ማቴ. 13፥25) ይህም ማለት ጠላት ዲያብሎስ መልካሙ እርሻ መልካም ብቻ እንደ ኾነ እንዲዘልቅ ፈጽሞ አይፈልግም ማለት ነው።



  የዘሩ ባለቤት የዘራው መልካም ዘር ነው፤ “ጠላቱ ግን መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ” (ቁ. 25)፣ ሲዘራ አልታየም፣ ሲሄድም አልታየም፤ ነገር ግን ከስንዴው ጋር ሲበቅልና ሲያፈራ ታየ። የባለቤቱ ባሮች መከር እስኪደርስና ፍሬው እስኪያፈራ ድረስ የተመለከቱት አይመስልም። እንክርዳድ ወይም ኃጢአት በመልካም ነገር ውስጥ ራሱን ሸሽጎ መቆየት ይችልበታል። አንዱ የኃጢአት ባሕርይ ይህ ነውና። ዘርቶ ሂያጁ ሁል ጊዜ ጨለማን ለባሽ ነው፤ መሰወርን ይወድዳል፤ ተደብቆ ማድባትን ይመርጣል። ሾልኮ መግባትን ልማዱ ያደርጋል።

  ሰይጣን በተንኰሉ የሚያስተው (2ቆሮ. 11፥3)፣ የብርሃንን መልአክ መልክ የሚይዘው (2ቆሮ. 11፥14)፣ በበር ያይደለ በሌላ መንገድ የሚወጣው (ዮሐ. 10፥1) ሴረኛና አሳች ስለኾነ ነው። ራሱን በመደበቅ ውስጥ ኀጢአትን ሲሠራ እንዳይታወቅበት ጭምር ነው። ስለዚህም የማይፈርስ የማይመስልን ምሽግ በመሥራት ጠላት ወደር የለውም፤ ነገር ግን “የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤” (2ቆሮ. 10፥4) እንዲል፣ በወደቀው ዓለም ዘንድ ዕጹብ ድንቅ የተባሉና በሰዎች ትዕቢትና እብሪት የተመሠረቱ አይደሉም

  ምሽግ ስውር ሃሳብ ብቻ አይደለም፤ በግልጽ በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ የተነሣ ክርክርና ከንቱ ሃሳብ ነው፤ ቆሮንቶሳውያን አማኞችን ሐሰተኞች መምህራን ከንቱ በኾነ ዐሳብ እምነታቸውን ለመናድና ለማፍረስ ታጥቀው የተነሡበት ስልትና ብልሃት ነው። እናም ሁል ጊዜ ይህ ምሽግ መፍረስና መናድ ይገባዋል። ደግሞም ለዚህ ነው ደፍረን፣ “መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” (1ቆሮ. 2፥13-15) በማለት የምንናገረው

  በመንፈሳዊነት ውስጥ ራሱን ሸሽጎ ሲያታልል በግልጥ እያየነው ነው፤ በተለይም ደግሞ ነገሩን በትክክል እንዳናስተውል እውነትና ውሸትን ቀላቅሎ በማቅረብ ሃሳቡን በጣም ያወሳስባል፤ የመጀመርያይቱ ሴት ሔዋን የወደቀችው እንዲህ ባለ ጥበብ መኾኑን ዘንግተናል፤ “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” (ዘፍጥ. 3፥1) የሚለው የዲያብሎስ ንግግር እውነትና ሐሰት የተዋሰበበት ንግግር ነው፤ እግዚአብሔር አትብሉ ያለው አለ፤ ግን ኹሉንም አላለም፤ ለማጥመድ ግን ኹለቱን ሃሳቦች ፈትሎ አቀረበላት፤ በቀላሉ ወደቀች እኛስ ከብዙዎች ጋር እንዳንስት መጠንቀቅ አይገባንምን? (ማቴ. 24፥11)
   የጠላት ስልቱ በየዘመናቱ በጥቂቱ ይለያይ እንጂ፣ ምንጩ ያው አንድ ነው። በየዘመናቱም ሽሽግና ድብቅ ባሕርይን በመጠቀም የሚደርስበት የለም። ዛሬም እያየን ያለነው እውነት ይኸው ነው፤ እነ“ቄስ” በላይ “ኹሉም ሰው በቋንቋው፣ በ“ባህሉ” … ወንጌል ሊሰበክለት ይገባል” በሚለው ቅን ሃሳብ ውስጥ “በእገሌ ብሔር ስም ደግሞ ሲኖዶስ ሊቋቋም ይገባል” የሚል የመለያየትን መንፈስ በአንድነት ያቀርባሉ። ኢዩ ጩፋ ደግሞ ሐሰተኛ መምህር፣ አሳች ነቢይ መኾኑ እየታወቀ “ወደ ገዛ ወገኖቹ” ሲሄድ ግን በሚያሳፍር መልኩ በእልልታ ተቀብለውታል፤ ዘረኝነት፣ ብሔርተኝነት እንዴት ሽሽግ እንደኾነና ብዙውን ትውልድ እንዴት እንደጣለ መንፈስ ቅዱስ ከረዳው ሰው በቀር ካልኾነ ማን ሊረዳው፣ ሊያስተውል ይችላል?!


ትክክል አይደለም እንዳንል፣ ትክክል የኾነ ነገር አቅርበዋል፤ ሰው በገዛ ቋንቋው ሊማር ይገባል ይላሉና፤ ትክክል ነው እንዳንል ደግሞ፣ “ሲኖዶስ ይቋቋምልን” የሚል የልዩነትና የመለያየት፣ የሥልጣንና የፖለቲካ ነገርን በአንድነት “የክርስቶስ ልብ በሌላቸው ሰዎች” አሰንገው ያቀርባሉ። እንግዲህ እንዲህ ያለውን ውስብስብ ሴራ ማን መለየት ይቻለዋል? በጉያቸው እሳትን ታቅፈው እየነፈሩ አልተቃጠልንም ይሉናል፤ የአይሁድ ራቢዎች እንደሚሉት፣ ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዛፍ ለአዳም ስትሰጥ፣ “አዳም ባሌ ሆይ! አየኸው፤ እኔም በልቼ አልሞትሁም፣ አንተም ብትበላው አትሞትም” ብላ እንደሰጠችው፣ የሞትን ጦማር ሲሰጡን ከቃሉ ይልቅ የራሳቸውን ሃሳብ አሰልጥነው ያቀርቡልናል።

   ከ“ቄስ” በላይም ከኢዩ ጩፋም ጀርባ ስውር የዘረኝነት ዘር አለ፤ እኒህ ሰዎች እየተናገሩ ያሉት ለእግዚአብሔር ቃል መነገር፣ መታወጅ፣ መሰበክ … ቀንተው፣ ተቈርቁረው፣ እጅግ ናፍቀውና ተጠምተው አይደለም፤ ያ ቢኾን የዘረኝነት ክፉ ነገርን በኋላቸው ስበው ባላስከተሉ፣ በግልጥ ስህተት ውስጥ ወድቀው ከንስሐ ይልቅ በደጋፊዎቻቸው ባልታመኑ!!! እናም ስህተታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ውስጥ አስገብተው ያወሳስቡታል፤ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳይረዱ መንፈሳዊ በሚመስል ነገር ጨዋታቸውንና ንግግራቸውን ያረዝማሉ፤ ልክ እንደ አመንዝራ ሴት፤ አመንዝራ ሴት እንዲህ ታደርጋለች … “በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች። እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ። ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ። ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል፤ በጎዳናዋ አትሳት። ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው። ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።” (ምሳ. 7፥21-27)፣ እንኪያስ እኒህ ስሑት መምህራን ከዚህ የተሻለ ምን እያደረጉ ይኾን?

   እግዚአብሔር እንድንኖር የፈለገው ሕይወት ግልጽና ያልተወሳሰበ፣ የጠራና ኹሉ ቢያየው በትክክል ምን እንደ ኾነ የሚያስተውለውን ሕይወት ነው ትብትብና ውስብስብ ሕይወት እንድመራ አልተባለልንም፤ ውስብስብነትና ሽሽግነት የወደቀው ሰው ጠባይ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ሰውን ሲፈጥረው እንዲህ አልነበረም፤ ደግሞም ከዳንን፣ በክርስቶስ ከተቤዥን በኋላ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ሊታይብን፣ በልባችን ሊኖር አይገባም፤ ድነናል ካልን የዳንበት ዘር ብቻ እንጂ የተዳቀለ ነገር ሊታይብን እጅግ መታለልና ምስኪንነት ነው! ሰባኪው እንዲል፣ “እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጐ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስስብ ዘዴ ቀየሱ” (መክ. 7፥29 ዐመት)፤ መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ ቃሉ ነገሮችን ኹሉ እንድንመዝን፣ እንድንፈትሽ፣ እንድንዳኝ ይርዳን፤ አሜን

3 comments:

  1. እውነት ነው.እኔ ኦሮሞ ነኝ ከአማርኛ ይልቅ ኦሮምኛ ነው ሚገባኝ.ቅዳሴው መዝሙሩ ስብከቱ በኦሮምኛ መሆኑ እንደኔ ላሉት ሁሉ ትልቅ ደስታ ነው!ነገር ግን አዲስ ሲኖዶስ የሚለው ሃሳብ ትንሽ ሸፍጥ ያለበት ይመስለኛል.ቀሲስ በላይ ምርጥ የተዋዶ እና የኦሮሞ ኣባት ነው!

    ReplyDelete
  2. የተጠየቀው ጥያቄ ዘመኑን የዋጀ እና እውነተኛ ጥያቄ ሲሆን ለቀን ጅቦችና ለዘረኞች እንዲውም ኦሮሞ በራሱ ቋንቋ እንዳይማር እራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር ቀን ከሌሊት ለሚሯሯጡት ዉሾች ግን እራስ ምታትነው። ዘረኝነት ስትል አታፍርም ቤተክነትና ቤተመንግስት በስራተተክሊል ተጋብተው ለ27 ዓመት የኦሮሞን ስጫወቱበት እንደነበረ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው ጉዳይነው ካውን ቦኃላ በሐሰት ኦሮሞን መሸጥ አይቻልም
    የራሱ ቋንቋ የራሱ ባዕል ያለው ሰፊ ሕዝብነው ።እንኳን ለራሱ ለሌላውም ስለሚተርፍ አሃይማኖት ተቆርቃሪ መስለክ የጅቦችን አሳብ አናውንስ ከማድረቅ ተቆጠብ

    ReplyDelete
  3. አንቴም ብሎ ድያቆን፡ ምን አይነት ፍርፍር ጭንቅላት እንደ ተፈጠሬ እንዳሌ ካንቴ ዝቃጭ አስተሳሰብ ተረዳው

    ReplyDelete