Please read in PDF
ኹሌም የቤተ ክርስቲያንን ችግር
አንስተን ከብዙ ወገኖች ጋር በግልም በጋራም ስንወያይ፣ ውስጤን የሚነካኝና የሚያስጨንቀኝ ነገር ይህ ነው። ወደ ዋናው የችግሩ መንስኤ
መሄድን አንፈልግም። በደፈረሰው ወራጅ ላይ እንከራከራለን፣ የወራጁን ምንጭ የማጥራት ሥራ ላይ ለመረባረብ እንገፋፋለን እንጂ መሠረታዊውን
ችግራችንን፣ ከምንጩ ያፈነገጠውን ነገራችንን አጢነን፣ አስተውለን በልበ ሰፊነት ልናይ፣ ልንወያይ፣ በልበ ሰፊነት ተነጋግረን …
መፈለግንም ማድረግንም (ፊልጵ. 2፥13) ከሚሠራው ጋር ለመሥራትና ለመቃናት አንተባበርም። ምንጩ ሲጠራ ወራጁም እንደሚጠራ እናውቃለን
እንጂ አምነን ለመነሣት ለክፋት ጨካኞችና ለእግዚአብሔር ፍጹም ያደላን አይደለንም። ከዚህ የሚከፉት ይልቅ ያሉትን ችግሮች ብናይ
በአሁን ሰዓት በግልጽ ከሚታዩት ችግሮች አንዱና ዋናው፦
1.
እግዚአብሔርን
ብቻ አለማምለካችን ነው፤
የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር እያለ፥ እግዚአብሔርን አዝኖ
የተከተለበት ጊዜ እንዳለ ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል። እግዚአብሔር የመጽናናት አምላክ ነው፤ ከእርሱ ጋር ሆኖ ማንም ያዘነ የለም።
እርሱ “የርኅራኄ አባት የመጽናናት አምላክ” (2ቆሮ. 1፥3)፤ “ኃዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክም ነውና” (2ቆሮ. 7፥6) ከእርሱ
ጋር ሆኖ ምንም አላዘነም። ሁሉም የእግዚአሔር ቅዱሳንና አማኞች በዚህ ዓለም ሳሉ በመረረ ጥላቻና በከባድ መከራ በተከበቡ ጊዜ አጽናኛቸውና
ሁሉን ነገር ተክቶ ከጐናቸው የቆመላቸው አጽናኙ እግዚአብሔር ነው።
በነቢዩ ሳሙኤል ዘመን የነበረውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሁኔታ ጸሐፊው
ሲገልጠው፣ “… የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ” ይለናል፣ (1ሳሙ. 7፥2) በዚህ ቃል ውስጥ ኹለት ከባድ አገላለጦች
አሉ፤ አንዱ የእስራኤል ሁሉ እግዚአብሔርን መከተል ሲሆን፤ ኹለተኛው ግን እግዚአብሔርን እየተከተሉ ማዘን የሚሉት ናቸው። መንፈሳዊ
ኀዘን እንኳ ከልክ ባለፈ ወይም በሚበዛ ኀዘን መዋጥ አይደለም (2ቆሮ. 2፥7)፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያዘኑት መንፈሳዊ ኀዘን
ሳይሆን ከኃጢአታቸውና ከበደላቸው የተነሳ ያዘኑትን ኀዘን ነው ታላቁ መጽሐፍ የሚነግረን።
የእግዚአብሔር ታቦት ለሐያ አመታት በስደት በነበረበት ወራት ሳዖል ይህንን
የእግዚአብሔር ኪዳን የመፈለግ ሃሳብ በልቡ አልነበረም፣ ይልቁን ወደጣዖታት ልቡን አዘነበለ እንጂ፣ በኋላ ላይ ዳዊት ደግሞ እንደ
ሥርዓቱ አልፈለገውም። ለዖዛ መቀሠፍና ለቤትሳሚስ ሰዎች በመቅሰፍት መመታት (1ሳሙ. 6፥19፤ 2ሳሙ. 6፥7) ዋናው ምክንያት የታቦቱ
ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ውጪዳዊት ያዘዛቸው ከእስራኤል የተመረጡት ሠላሳው ሺህ ሰዎች እንደ ሥርዓቱ ከፍልስጥኤማውያን እጅ ወደ እስራኤል
አለማምጣታቸው ነው። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ታቦት ከአንድ ሥፍራ ወደሌላ ሥፍራ እንዲንቀሳቀስ የታዘዘው በላሞች (በበሬዎች) ትከሻ
እንዲጫኑ ሳይሆን (1ሳሙ. 6፥12) በሌዋውያን ካህናት ራስ ላይ በማድረግ እንዲጓጓዝ ነበር። ስለዚህም ታቦቱ በበሬዎቹ ጫንቃ ተጭኖ
ሳለ በሬዎቹ ፋነኑ፤ በፋነኑ ጊዜ ዖዛ ታቦቱ ሊወድቅ ያለ መስሎት ሊደግፍ ሲል ተቀሰፈ። የቤት ሳሚስም ሰዎች የሆኑት እንዲሁ ነው።
ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ሥርዓቱ በሬ ሳይኾን አሠራሩ ራሱ ካህናቱ እንዲሸከሙት በሚያመች መልኩና እነርሱም እንዲሸከሙት
ነበር ትዕዛዙና የተደነገገው ሥርዓት፤ (ዘጸአ. 25፥1-22፤ ኢያሱ 3፥6)።
አገልጋይ ሊያገለግል ተጠርቶ ሳለ የአገልግሎቱን ሸክም ለሌሎች እንደ ማሸከም
ያለ ፈሪሳዊ ደንታ ቢስነት የለም። የአገልግሎቱን አደራ በሌሎች ጫንቃ እያሸከሙ “የአገልግሎቱን ፍሬ የክብር ሽልማት” ላይ ግን
በጋራ ለመሸለም መቅረብ ግብዝነት ነው። ዳዊት የቃል ኪዳኑ ታቦት
በአሕዛብ ምድር ያደረገውን ተአምራት ሲሰማ ታቦቱን ለመቀበል ፈርቶ በመጀመርያ በአሚናዳብ ቤት ተወው፤ ከዚያ ደግሞ ሊወስደው ባለ
ጊዜ እንደ ሕጉ ሳይኾን እንደአሕዛብ ልማድ በግዕዛን ላሞች አሸክሞ ለመውሰድ ሰዎችን ላከ። ሕያው አምላክ ሊገለገል የወደደው፣ ሕያዋን
በሆኑት ፍጡራን በሰውና በመላዕክት ነበር። የሰው ልጅ ግን ሕያው አምላክ በእርሱ ሳይሆን በግዑዝ ፍጡር እንዲመለክ ወደደ።
ከዚህ የተነሳ የእስራኤል ልጆች የጣዖታቱን ሥርዓት ለታቦቱ እንዳደረጉት እንዲሁ
የአህዛብ ልማድ የሆነውን የጣዖት አምልኰንም ተለማምደው፤ ወርሰው ያመልኩም ነበር። ስለዚህም ታላቁ መጽሐፍ “ሳሙኤልም የእስራኤልን
ቤት ሁሉ፦ በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር
አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ …” (1ሳሙ. 7፥3) አላቸው ይላል።
የእስራኤል ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ሆነው የማዘናቸው ምስጢር ጣዖትን በጉያቸው
ይዘው እግዚአብሔርን ለማምለክ ማሰባቸው ነው። እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ ብቻ አለማክበርና አለማመስገን የሚያስተውለውን
ልብ ያጨልማል፤ (ሮሜ 1፥21)። በእርግጥም የቃየል ልብ ጨልሞ የነበረው፥ አቤልን ቀድሞ ለመግደል በማሰቡና በመግደሉ ምክንያት
ነው። ቃየል ግን ልቡን አጨልሞ መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት ይዞ ቀረበ፤ (ዘፍ. 4፥7)። የልብ አለመብራት በጨለማ ሥራ በኃጢአት
መመላለስን ያሳያል፤ የእስራኤል ልጆች በብርሃኑ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጠው ጨለማቸውን ማየት አልተቻላቸውም። ይህ ከባድ ድንዛዜ
ነው።
ቅዱስ ነቢይ ሳሙኤል ይህን የጨለማ ሥራ ስለመስበር አወሳ። ከእግዚአብሔርን
እየተከተሉ እንዲያዝኑ ካደረጋቸው ከንቱ የጣዖት አምልኰ እንዲርቁ አስጠነቀቃቸው። ሳሙኤል ልከኛ አገልጋይ ነው፤ የሕዝቡን ነውር
አይቶ አልተደራደረም፤ አልሸቃቀጠምም። ከእግዚአብሔር የለያቸውን ነገር በግልጥና ምንም ሳይፈራ ነው የተናገረው። ለእግዚአብሔር ያደላ
እውነተኛ መሪ ሕዝቡን ይመራል እንጂ በሕዝብ አይመራም፤ መከራን ሊያመጣ በአይኑ ለተንኰልና ለአድማ አይጠቅስም፤ ሰላምን ሊያደርግ
ደፍሮ ይገስጻል እንጂ (ምሳ. 10፥10)። ስለዚህም “የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ”
(1ሳሙ. 7፥4)፣ እግዚአብሔርን ብቻ ማምለክ ማለት ከእርሱ ውጪ ማንንም አለማየት፤ ለእርሱ ብቻ መገዛት ማለት ነው። የእስራኤል
ልጆች እግዚአብሔርን ብቻ ማምለካቸውና በፊቱም መሥዋእትን ለማቅረብ ውኃን ማፍሰሳቸው (ፍጹም በመዋረድ ንስሐ መግባታቸው) እግዚአብሔር
“አቤንኤዘር” ሆኖላቸዋል፥ ጠላቶቻቸውን እንደአንድ ሰው ተፈጥሮ ሠራዊት ሆኖ መትቶላቸዋል።
ልክ እንዲሁ፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር ብቻ አለመመለኩ
የወለዳቸው የራሱ ከባባድ ችግሮች አሉ። እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና (ዘጸአ. 20፥6) በእርሱ ትይዩም ሆነ ከእርሱ በታች
ማናቸውም ፍጡር ሆነ እርሱን የሚተካከለው ያይደለ እንግዳ ነገር እንዲመለክ ፈጽሞ አይፈልግም። ከእግዚአብሔር ውጪ ብዙ ነገሮች በሕይወታችን
ጌቶች ሊሆኑ ይችላሉ ፤ ነገር ግን ለሁለት ጌታ መገዛትና በሁለት አምላክ ማነከስ አንችልም፤ (1ነገ. 18፥21፤ ማቴ. 6፥24)።
እግዚአብሔር ግን ከእኛ ጋር ፍጹም በአገልግሎት የሚሠራው በቅድስና በፊቱ መቆም ሲቻለን ነው። ጌታችን ኢየሱስ ሕይወትን በተመለከተ
ከእኛ ምንም አልፈለገም፤ ጠላቶች፣ ደካሞች፣ ኃጢአተኞችና የማይገባን ሆነን ሳለን ተቀብሎናል፤ አገልግሎትን በተመለከተ ግን በፍጹም
ንጽዕና እንድንቆም ማዘዙን በብሉይ በዘሌዋውያን የቅድስና መጽሐፍ ላይ ስናይ፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከቃል (ከትምህርት) ይልቅ በሕይወቱ
ጌታ ኢየሱስ አስተምሮናል።
ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ሙሽራዋን ማስደሰት የምትችለው ያለዕድፈት
፣ ያለነቀፋ ፣ ያለፊት ማጨማደድም ቅድስትና ነውር የሌለባት ሆና በፊቱ መቆም ሲቻላት ነው፤ (ኤፌ. 5፥27) ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን
ዋጋ ስለከፈለላት አብሯት ሊኖር ሙሉ መብት አለው። ቤተ ክርስቲያንም ሙሉ ዋጋ በስሟ ክርስቶስ ከፍሎላታልና ከእርሱ ጋር የመኖር
ግዴታ አለባት። ደግሜ እላለሁ፥ ከእርሱ ጋር ብቻ የመኖር ግዴታ ነው ያለባት።
ቤተ ክርስቲያን ለሞተላት ጌታ ራስዋን በፈቃድዋ አሳልፋ ባትሰጥ አስጨንቆ
ለሚገዛት ክፉ ራሰዋን አሳልፋ ትሰጣለች። የክፋት አሠራርና ፍጹም ኃጢአተኝነት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነግሰው ወይም የመስቀሉን
የማዳን ሥራ እንዳታይ በዓይኗ ላይ አዚም ረቦ የሚጋርዳት ከሙሽራዋ ክርስቶስ ጋር፤ ከአጽናኝዋ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ስትለያይ ወይም
ከእርሱ ፊቷን ዘወር ስታድርግ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን
ብቻ አለማምለኳ ብዙ ኃጢአቶቿ በአገልጋዮቿና በተከታዮቿ መካከል ለብዙዎች መሳለቂያ ሆናለች። እኛ እኒህን ግልጥ ነውሮች የምናነሳው
ብዙዎች ይህንን የአደባባይ ገመና ሰፋፍነው የአኹኑን የቤተ ክርስቲያን ችግር ከዚህ ስለማይጀምሩት ነው። እውነት ለመናገር እኒህ
ኃጢአቶችና ነውሮች ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን ብቻ ባለማምለኳ ያገኟት ናቸውና ይመለከቷታል፦
ይቀጥላል …
ወደ ዋናው የችግሩ መንስኤ መሄድን አንፈልግም። በደፈረሰው ወራጅ ላይ እንከራከራለን፣ የወራጁን ምንጭ የማጥራት ሥራ ላይ ለመረባረብ እንገፋፋለን እንጂ መሠረታዊውን ችግራችንን፣ ከምንጩ ያፈነገጠውን ነገራችንን አጢነን፣ አስተውለን በልበ ሰፊነት ልናይ፣ ልንወያይ፣ በልበ ሰፊነት ተነጋግረን … መፈለግንም ማድረግንም (ፊልጵ. 2፥13) ከሚሠራው ጋር ለመሥራትና ለመቃናት አንተባበርም። tebarek Abeni
ReplyDeleteችግሩ የታወቀ ነው ግን ማን ደፍሮ ያስተካክል? ጌታ ያስበን እንጂ ያለንበት ጉድ ብዙ ነው
ReplyDeleteGBU more and more!
ReplyDeleteGod bless you! It's Amazing message.
ReplyDelete