Friday, 19 October 2018

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 1)

Please read in PDF

መግቢ
   “ … በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ላይ ሂስ ማድረግ እንደ ክህደት ስለሚቈጠር ብዙ አስተያየት አልዳበረም። ይህ ባህል ቅዱስ መጽሐፍን ተመራመሩ የሚለው መሠረተ ሐሳብ ተመራመርና እመን ከሚለው ንድፈ ሐሳብ በተቃራኒ እመን ግን አትመራመር ከሚል ንድፈ ሐሳብ ላይ ይመሠረታል።”[1]



      በእርግጥ ዶ/ር ዲበኩሉ ዘውዴ ያቀረቡት ይህ ሐሳብ፣ “እንደ ኢትዮጵያ ልምድ ስለ ፍትሐ ነገሥት ዝግጅትና የትርጉም ሥራ ላይ አብርሃም ወልደ ሐናናጥያን ምንም ሚና እንዳልተጫወተ እየታወቀ አለመተቸቱንና እንደ ወረደ መቀበላችንን በግልጥ ለመናገር ወይም ለመተቸት በማሰብ ነው። እውነታው ግን ለፍትሐ ነገት ብቻ ሳይኾን፣ በጠቅላላው አሁን ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ማለትም አስተምህሯዊ ችግሯን፣ አምልኳዊ ጉድለቷን፣ ሥነ ምግባራዊ ውድቀቷን … በጐላና በተረዳ ጎኑ የሚያጸባርቅ ነው።
      ቤተ ክርስቲያን በትውልድና በዘመን መካከል የምታልፍ፥ ሕያው የክርስቶስ አካል ናት። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በተኩላው ጨካኝ ዓለም መካከል እንጂ፣ ከዓለም በማውጣት አይደለም፤ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ፦ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም” በማለት ጸልይዋል፤ (ማቴ. 10፥16፤ ዮሐ. 17፥15)። ቤተ ክርስቲያን በክፉው ዓለምና በጠማማው ትውልድ መካከል ከክፋትና ከጥመቱ ሳትተባበር (ሐዋ. 2፥40)፣ ራስዋን “ለአንድ ወንድ በድንግልና እንደ ታጨች ንጽሕት ሴት በቅድስናና በንጽሕና በሐሰተኞች ትምህርት ያልተበከለች ሆና ራስዋን ለክርስቶስ ልታቀርብ ይገባታል።” (2ቆሮ. 11፥2) ቤተ ክርስቲያን ለአማኞቿ እናትም አባትም ናት። ለእርሷ ልጆች እንደ መኾናችን መጠን (2ቆሮ. 6፥13) ስለልጆቿ የኅሊና አምልኰ ቅድስና አብዝታ ልትተጋ፤ እንዲበዛላቸውም በመስቀሉ ርኅራኄ ልትለምናቸው፤ ልትለምንላቸውም ይገባታል።
    ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ታበራ ዘንድ “በተራራ ላይ ያለች ከተማ ናትና ልትሰወር አትችልም” ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ለዓለሙ ሁሉ ልታበራ ሥፍራዋ ከፍታ እንጂ ዝቅታ አይደለም፤ (ማቴ. 5፥14)። በብርሃን፤ በከፍታ፤ በተገለጠ የሕይወት ምስክርነት የምትመላለስ ቤተ ክርስቲያን በጨለማ ልትመላለስ አልተባለላትም፤ አልተፈቀደላትምም፤ (ዮሐ. 8፥12)። በፍጥረት መጀመርያ እግዚአብሔር “በጥልቁ  ጨለማ ላይ ብርሃን ይብራ” (ዘፍ. 1፥3) እንዳለ እንዲሁ፣ በአዲሱና ከማይጠፋው ከእርሱ በተወለደችው ልደት (1ጴጥ. 1፥3) “የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራውን የክርስቶስን ወንጌል” (2ቆሮ. 4፥6) እንዳይበራ ጨለማ የሆነውን ያለመታዘዝና የኃጢአትን ሕይወት ድል ለመንሳት፤ ለማፍረስም (1ዮሐ. 3፥8) የተገለጠው ጌታችን ኢየሱስ አገልጋይና ሙሽሪት ናት።
   እንዲህ ያለች ኾና ሳለ ቤተ ክርስቲያን ራስዋን ከተራራው ከመከበርና ከልዕልና ብታወርድ፣ የሚገጥማት መጣልና መናቅ፤ መረገጥም ጭምር ነው፤ (ማቴ. 5፥13)። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን የመፍራት ምሳሌ ሆና ከመታየቷም ባሻገር የማህበረሰቡ አምልኰ እንዳይበላሽና እንዳይነቅዝ የመጠበቅ ኃላፊነት አለባት። ነገር ግን በተቃራኒው “ዘመነኛነዋ” ቤተ ክርስቲያን ሥር በሰደዱና አስነዋሪነታቸው በግልጥ ለሚታዩ ችግሮች አሳልፋ ራስዋን ስትሰጥ እያየን ነው። በዚህ አጭር ጽሑፍ ይህን የተጋረጠ ልጎምራ ባይ ችግርን በመንቀስ፣ በመግለጥ ከቅዱስ ቃሉ መንፈሳዊ መፍትሔን እንበጃለን፤ እናመለክታለንም።
የችግሩ ዋና ምንጭ
   ዛሬ ላይ አግጦና አፍጥጦ፣ ፍንትው ብሎ ለሚታየው የቤተ ክርስቲያን ችግር፣ በአብዛኛው የሚጠቀሰው፦ “ሥነ ምግባራዊና አስተዳደራዊ ችግር” እንደ ኾነ ብቻ ነው። ለዚህም ችግር “አብርሖታዊና መዋቅራዊ ሽግግርን (Structural Transformation) መሠረት በማድረግ የትንሣኤ (Renaissance or Revival) ሥራ ከተሠራ፣  ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመ ክብሯ እንደምትመለስና የሐዋርያትን ዘመን ቤተ ክርስቲያን ልትመስል እንደምትችል የሚናገሩ አሉ።”[2]
   በተለይም ደግሞ ከዘውዳዊው ንጉሥ መውረድ በኋላ ስለተስፋፋው ዓለማዊነትና “እግዚአብሔር የለሽነት” አስተምህሮዎችንም “… በዚህ ወቅት እግዚአብሔር የለም የሚለው የክህደት ፍልስፍና በብዙዎች የሠለጠንን ነን በሚሉ ወገኖች በመሰበኩና ካህናትን ጨምሮ ብዙ ክርስቲያኖችንም የዚሁ ፍልስፍና ሰለባ በመሆናቸው ብዙ ክርስቲያናዊ ዕሴቶች ከማኅበረሰቡ ውስጥ ተደምስሰዋል ማለት ይቻላል”[3] በማለት፣ በግማሽም ቢሆን የእውነተኛ አስተምህሮ ችግር እንዳለም የተጠቆመበት ጊዜ አልጠፋም።
  በእርግጥም ይህም ችግር የቤተ ክርስቲያን አንዱና ትልቁ የችግር አካል ነው። ነገር ግን ለምን ዋናውንና ምንጭ የኾነውን ምክንያት እንደምንሸሸው ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም መዋቅራዊ ችግሮችን በማጥናት፥ እጅግ ውብ በሆነ መልኩ ነገሮችን ማደራጀት ይቻላል። በተለይ አሁን ያለንበት ዘመን፣ የቴክኖሎጂው ጫፍ የተደረሰበት ዘመን ነውና፣ በብዙ ሰው የሚሠሩ ሥራዎችን በጣም በጥቂት ሰዎችና በቀላል ጉልበት መሥራት የሚቻልበት ዘመን ላይ ነን። የሰው ኃይል አደረጃጀትን፣ የበጀት አመዳደብን፣ የሰው ኃይል ሥምሪትን፣ የቢሮና የመጓጓዣ አደረጃጀትን፣ ምንኩስናንና አሰጣጡን፣ ብህትውናውንና አኗኗሩን፣ የበዓላት ብዛትንና አከባበራቸውን፣ ድንጋጌያቸውን፣ የጳጳሳት አመራረጥና አሿሿምን፣ በመቀራረብና በመተዋወቅ አሠረ ክህነት መሰጣጠትን፣ የዳታ ቤዝ አለመኖርን፣ በየቤተ ክርስቲያኑ ሥር የሰደደው የመልካም አስተዳደር እጦትን፣ በሥነ ምግባር የመዝቀጡና የመውረዱን ነገር፣ በየሐገረ ስብከቱ የካህናትና የዲያቆናት ምዝገባ አለመኖርን … እነዚህና ሌሎች ነገሮችን በራሳቸው የአሁን የቤተ ክርስቲያን አባባሽ ችግሮች ወይም የዋናው ችግር ፍልቃቂ መገለጫዎች እንጂ ዋናና የችግሮቹ መነሻ ምንጭ አይደሉም።




[1] ዲበኩሉ ዘውዴ(ዶ/ር)፤ ፍትሐ ነገሥት ፡ ብሔረ ሕግ ወቀኖና ፤ 1986 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ። ገጽ 82
[2] ዲ.ን ዳንኤል ክብረት፤ ስማችሁ የለም ፤ ነሐሴ 2006 ዓ.ም፤ አሳታሚ አግዮስ ህትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኀላ. የተ. የግል ማኅበር፤ ገጽ 16-17
[3] ሐመረ ተዋህዶ ዘዕሥራ ምእት፤ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ሐምሌ 2000፤ አዲስ አበባ። ገጽ 76

No comments:

Post a Comment