ማሳሰቢያ - ረጅም ንባብ ነው!
እነ አባ ገዳ ተሾመ እንዲያው ዝም ብለው ብቻቸውን፣ “የኦሮሚያ ሲኖዶስ ይቋቋም” ለማለት አይደፍሩም፤ ደግሞም ሥልጣንም የላቸውም። ነገር ግን የራሷ “የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እጅ” እንዳለበት እርግጠኛ ኾኖ መናገር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የነ“ቀሲስ” በላይ እጆች ረጅም ብቻ ሳይኾኑ፣ እሬቻዊ አምልኮ በግልጥ ከክርስትና ጋር ለመስፋት የሚጥሩ ናቸው። “ቄስቻው” በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ይንቀሳቀስ እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንጥፍጣፊ ፍቅርና ለክርስትና ደንታ እንደሌለው፣ የዛሬ ሦስት ዓመት በOBS የኦሮሚኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በ“harka fuune” (ቤት ለእንቦሳ) በሚለው ዝግጅት ላይ ከጋዜጠኛ አብዲ ገዳ ጋር “ረዥም” ቃለ መጠይቅ ማድመጥ በቂ ማሳያ ነው። “የኦሮሚያ ሲኖዶስ የመቋቋም ጥንስስም” ጅማሮው የሰነበተ መኾኑን ማስተዋል አይከብድም፤ ይህን ቃለ ምልልስ ከሰማሁት በኋላ ሊያስተምርና ሊያወያይ እንደሚችል ስላሰብኩበት ተርጉሜው ለማቅረብ ወደድኹ። ይህን ቃለ ምልልስ አንብበው፣ ቃለ ምልልሱ በኋላ “ኦርቶዶክሳዊ ሃሳብ ነው” የሚሉ ይኖሩ ይኾንን? ብዬ መጠየቅ እፈልጋአለሁ፤ አይደለም የምትሉ ደግሞ እንግዲያው “ዘርን ወይም አንድን ክልል ማዕከል ያደረገ ሲኖዶስ” ጥንስሱ ዛሬ እንዳልኾነ፣ አባ ገዳ ተሾመም ኾኑ ሌሎች ይህን እንዲሉ አነሳሽ ኀይላት ከጀርባ እንዳሉ ማሳያ ይኾናል በማለት ነው። የ“ቄስቻው”ንም ማንነት በዚያውም መመልከት ተገቢ ሳይኾን አይቀረወም፤ መልካም ንባብ እላለሁ።
አብዲ፦ ከልጅነት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል። በተለይም በኦርቶዶክስ ቤተ እምነት በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች (ኃላፊነቶች) በመሥራት ዛሬ የሥራ ድርሻቸውን የጠራንበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። … እንኳን ወደ ሚድያችን በሠላም መጡ።
ቀሲስ፦ እንኳን ቸር ጠበቃችሁኝ።
አብዲ፦ እስኪ ከግል ታሪካችሁ ላይ እንነሳና ተመልካቾቻችን “ቀሲስ በላይ ማን ነው?” ቢሉ ቀሲስ በላይ ከልጅነታቸው፣ ከወጣትነታቸው፣ ዛሬም ባሉበት በሥራ ድርሻቸውም ቀሲስ ማን ናቸው የሚለውን እስኪ ከእርስዎ እንስማ።
ቀሲስ፦ በጣም ጥሩ ነው፤ እኔ የተወለድኩት ሰሜን ሸዋ ዞን፤ ኩዩ ወረዳ፤ ሊበን ኩራ ቀበሌ ውስጥ ነው። አባቴ መኮንን ባለሚ ጅማ፤ የገመዳ ቤተሰቦች ይባላሉ። እናቴ ዓመለወርቅ ፍሬ ገለቱ ትባላለች። የእርሷ ትውልድ ወረጃርሶ፤ የእርሱ ደግሞ ኩዩ ነው። ከኹለቱ ወረዳዎች ተጋብተዋል።
የተወለድኩት 1962 ኅዳር አሥራ ኹለት፤ የሚካኤል ቀን ብለው ይነግሩኛል። እንደተወለድኩ ፈጥኜ እንዳደግሁና ፈጥኜ መናገር እንደቻልኩ ቤተሰቦቼ ይነግሩኛል። ስወለድም ጠንካራና ትልቅ እንደ ነበርኩ፤ ያበረታቱኝም ነበር። በተለይም አያቴ ባለሚ ጅማ እኔን የሚተካኝ እርሱ ነው ብሎ ይደሰታል፤ ሴት አያታችን ኦቦላ ያያ ትባላለች፤ ከእነርሱ 13 ወንድና 1 ሴት ናቸው፤ ባለሚ ጅማ እኒህ ሁሉ ልጆች ዘንድ እየሄደ እንዴት እንደሚበሉና እንdሚጠጡ፤ አስተዳደጋቸውን ይቈጣጠራል። ለምን? ቢሉት የእኔ ዘሮች(ትውልዶች) ምን አይነት ምግብ ነው የሚጠቀሙት፣ እያለ ሁሉንም በጣም ይቆጣጠራል። እንዲህ ካደጉት መካከል እንዱ እኔ ነኝ።
አብዲ፦ እኒህ ሽማግሌ እንዲህ የሚቆጣጠሯችሁ ከእናንተ ምን ፈልገው ነው?
ቀሲስ፦ እኒህ ሽማግሌ የሚፈልጉት ነገር (1) ሰው ጠንካራ ካልሆነ ጭቆናን ከራሱ ላይ መከላከል አይችልም፤ ልጆቹንም ሲያጋባ ረጃጅምና ግዙፍ እየፈለገ ያጋባቸዋል፤ ምነው? ሲባሉ፣ “qalaa mana guddaatu nama guddaa dahaa” ይላል። በአማርኛ (ትልቅ አቋም ያለው ትልቅ ሰው ይወልዳል) እንደማለት። ስለዚህም ሲያድጉ ከእያንዳንዳቸው ዘንድ በመሄድ ይቆጣጠር፤ ጭቆናን ይከላከሉና አይችሉ እንደሆን በማለት የሚመገቡትን ይቆጣጠራል። በዚህ ዘመን ሕግ አለ እንጂ፣ በዚያ በእነርሱ ዘመን ጎሰኝነትም ሆነ ባላባትነት የሚመጣው በጀግንነት ይመስለኛል፣ ሽማግሌው ምን አለ፤ … ጃሌ ጐሣ ነበር ድሮ የወሰደው፣ አሁን ግን የገመዳ ጐሣዎች ናቸው የወሰዱትና (የእኛ ጎሳ ነው)፤ “የገመዳ ጎሳዎች ባላባትነትን መልሱ” ቢባሉ፣ “የበግ ቆዳ ነው ወይ አውልቄ የምመልስልህ?” ብሎ ሲመልስ ልጅ ሆኜ እሰማ ነበር።
የንግግር ችሎታን ማወቅ ሥልጣን ያመጣል። እንቢ ብሎ አልፎ የመጣውን ለመመለስና ለመመከትም ይረዳል። ሽማግሌው ይላል፦ በእኔ ዘመን ይላል ሽማግሌው፣ ሰው ሁሉ ወደ አርሲ ሸሽቶ ሲሄድ ቶርበን በዳቱ የሚባሉት የገማዳ ልጆች ሠላሌ ወደ አርሲ ተፈናቅሎ ሲሸሽ እኛ ጭቆናን ተከላክለን ነው እዚህ የቀረነው ሲሉ ሰማለሁ።
አብዲ፦ በምንድር ነው የተፈናቀሉት?
ቀሲስ፦ የተፈናቀሉት ነፍጠኞች ስላፈናቀሏቸው ነው። በዚያ ዘመን አይደል እነአምዴ አበራ ሲያፈናቅሉ፣
“kunoo si deemne si demnee yaa Hamdee Abarraa
Yoo mujjaan olla sii ta’e yoo jaldeesssi daboo si dhufee
Si baanee kaa biyyaa si baanee” ተብሎ ሠላሌ ከአገር የወጣው።
ትርጉም፦ ሐምዴ አበራ ሆይ ሄድንልህ ሄድንልህ
ዝንጀሮ ደቦ ወጥቶ ሙጃ ዘመድ ከሆነህ
ይኸው ወጣንልህ ወጣንልህ።
አብዲ፦ የዚያኔ እሳቸው እዚያ ቀሩዋ?
ቀሲስ፦ ሽማግሌው በጉልበት ተከላክዬ እዚያው ቀረሁ ይላል። ለአባቱ አደረግሁ ይላል፤ ብዙ ወጣቶች ስለነበሩት ከአንድ ሚስት አሥራ አራት ልጆችን ወልዷል። ጭቆናን በዚህ መልክ ነው የተከላከልነው ይላል፤ የእኛ ሽማግሌ እንደሚለኝ ወደአርሲ ሸሽቶ የሄደና አይቶ የመጣ ዘመዱ እንደነገረው፣ አርሲ በዚያ ዘመን እንደሠላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ሰላሌን ተቀበለው፤ ሰላሌ ደግሞ ወደዚያ የሄደው የነፍጠኛን አገዛዝ በመቃወምና በመከላከል አብሮ ለመዋጋት ወደባሌ ጋላቢ ፈረሱን ትቶ ነው ይላል። ስለዚህም የእኛ ሽማግሌ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ቁጭ ብሎ ታሪክ ይነግረናል። ታሪክ ይነግረናል፤ ወኔ ያለው ሰው በእግዚአብሔርም መታመን ይገባዋል ይላል፤ ወደእምነትም እንድመጣ ያደረገኝ ይኸው ሽማግሌ ነው። ከአባቴም ይልቅ ወደእምነት እንድመጣ ያደረገኝ አያቴ ባለሚ ጅማ ነው። ምን ይላል? በእግዚአብሔር ያልታመነ ሰው ጭቆናን አይከላከልም። ወኔ ያለው ሰው ማለት ያመነ ሰው ነው፤ በእግዚአብሔር ያላመነ ሰው ውሸታም፤ ለማኝ፤ ሌባ ነው። ሽማግሌ የሚነግረን ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፤ በራሱ የሚተማመንና በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ጭቆናን ይከላከላል እግዚአብሔርም ይረዳዋል። እንዲህ ነው እንግዲህ ያደግሁት።
እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ መንደራችን ድረስ ቄስ አምጥተውልን ተማርን። ከተማሩት ሰዎች ቄስ እስከመኾን የደረሰ እኔ ብቻ እንጂ ወንድሞቼም ሆኑ ሌሎች ከተማሩት ውስጥ ማንም ቄስ የሆነ የለም። ወደአስኳላው የሄዱ አሉ፤ እኔ ግን ሁለቱንም ጎን ለጎን ይዤ ሄድኩኝ። ይህን የቄሱን ትምህርት ተምሬ ደብረ ሊባኖስ በመሄድ ቄስ ሆንኩኝ፤ ከዚያ ተመልሼም ኩራ ገብርኤል የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ተቋቋመ፤ ደብረ ሊባኖስም በሕጻንነቴ ታምሜ አስገቡኝ፤ የኔታ ወልደሰንበት ደምሴ የሚባሉት ሰው ቀንና (እዚያው እየዋልኩና እያደርኩ) ማታ ስድስት ወር አስተማረኝ። ከዚያ መሠረተ ትምህርት ሲመጣ ቀድሜ ድቁና ስለተማርኩ፤ ልክ ዘመቻ ሲመጣ ከስድስት ወረዳዎች ተወዳድሬ አንደኛ ወጣህ ተብዬ ተሸለምኩኝ። ታላቅ እህቴም እዚያው ትማር ነበርና በኩዩ ወረዳ ካልተማረ ብላ አባቴን አጥብቃ ያዘችው፤ እኔንም እንድማር ገፋፋችኝ። ከአባቴ ተደብቄም ትምህርት ቤት ገባሁ። ትምህርት ቤት ስገባም ኹለት ዓመት ሳልማር 1973 ዓ.ም በቀጥታ ሦስተኛ ክፍል ገባሁ። ሦስተኛ ክፍልም ስድስት ወር እንደተማርኩ ጥር ላይ ደብል የሚባል ነገር አለ፤ ከዚያም አራተኛ ክፍል በዚያው ዓመት ገባሁ። ክረምቱን ደግሞ አምስተኛ ክፍል ተማርኩ። እንዲህ እያልኩ ቶሎ ቶሎ ጨረስኩ። ... አዎን። ለምን መሰለህ የቤተ ክርስቲያኑን በጣም ስለተማርኩኝ ቶሎ ይገባኝ ነበር። እንዲያውም ፈተና እመልስ የነበረው፣ የቃል ትምህርት የሚባል አለ፣ እንዲሁ ይነበብና ትናገረዋለህ። ለምሳሌ፦ ፖለቲካል ሳይንስ የሚባለውን ትምህርት አራትና አምስት ገጽ እጽፍ ነበር። ውዳሴ ማርያም በቃል ነበር የተማርነው በዓይናችን አናይም፤ ቀን የተማርነውን ማታ ተቀምጬ አነባለሁ ከዚያም በቃሌ እይዛለሁ። ፈተና ሲመጣ ደግሞ በቃሌ እጽፋለሁ። ከቤተ ክርስቲያን መማሬ ልምድ ሆነኝ፤ … በፍጥነትም አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ጨረስኩ።
አሥራ ኹለት እስከምጨርስም በዚህ በኩራ ገብርኤል እቅድስ ነበር፤ እየቀደስኩም ሳለ ሊቀ ዲያቆንነት የተሾምኩት ዲያቆን ሆኜ ኹለት ወር ሳልሠራ ነው። በዕድሜም ሁሉን በልጬ ሳልሆን፣ ዲያቆን የሆንኩ እለት አያጀቴ በሬ አርዶ ቄሶችን አበላቸው። ሁለተኛው ደግሞ እናቴ ምግብ አዘጋጅታ ይዛ ትሄዳለች፤ እኔ ሳልሆን የተመረጡት ቤተሰቤ ነው። በቤታችን ድግስ ይዘጋጃል።
በአከባቢያችን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በብዛት ይገኛል። እኔ ከቅዳሴ ስወጣ ሰው ጎንበስ ብሎ መሬቱን ይስማል። ሽማግሌው ምን ይላል? ገባባ (የጅማ አባት) ክርስትና አልተነሳም፣ የባለሚ አባት ጅማ ራሱ ካደገ በኋላ ነው ክርስትና የተነሳው። ባለሚ ክርስትናውን ሲይዝ ስላጠነከረ መሰለኝ ሁሉንም ልጆቹን ክርስትና አስነሳ። እኛም ከልጅ ልጆቹ ተላልፎልን ይህን እምነት እንድናጸና ሆነ።
አብዲ፦ ሁሉ ቤተሰብ ከዚህ የተነሳ አጸና ማለት ነው?
ቀሲስ፦ አዎ! ጸንቷል። ሽማግሌው ዋሽተው ሥራ የሚሰሩትም ሰዎች አይወድም። ልጅ ሆኜ የማስታውሰውና የረሳሁት ነገር ለሙግት ወደፍቼ ሄጄ መንገድ አድሮ ጠዋት ይገባል። ሴት አያታችን ደግሞ የያያ ወንድሞች ልጆቿን በአዳራሽ ሰብስባ ሰው ፍርድ ተብሎ ሲጠራ ምግብ ከሁሉም አይነት ተዘጋጅቶ ሽማግሌው ሲመጣ ሁላችንም ተቀምጠን፤ ወጣቶች ከአባቶቻችን ጋር ተቀምጠን ሳለ ሽማግሌው ለእርሱ በተዘጋጀ ቦታ ተቀምጦ ቀጥሉ ይላል። እንደ ጠንቋይ በዚህ ቦታ ያለው ሰው የሆነ ነገር ይናገራል (እንደ ጠንቋይ እያጓራ)። እኛ እውነት የሚሰራ መስሎን ነበር። ጠቋር ነህ፣ አባ ቡሌ ነህ አንተ ማነህ? ይለዋል ጠንቋዩ። ሽማግሌው የዚህ ጊዜ “እኔ የባለሚ ልጅ ነኝ” ብሎ በሽመል ነረተው። ይህ ማታለል ነው ይላል።
በኦሮሞ ባህል ያምናል፤ ለምሳሌ ሴቶች ወደ ወንዝ ወርደው ለምለው፤ አምልከው ሲመለሱ ሽማግሌው ይህንን በጣም ያደንቃል። ልጆችን ይዘው፤ ሲንቄ ጨብጠው ለእሬቻ ሲሄዱ (እኔ እሬቻ መሄድን የምወደው ሕጻን ሆኜ ሴት አያቴ መካከል ተቀምጣ እናቴ፣ የፈዬ እናት የአጎቶቼ ሚስቶች እርሷን ከበዋት ይሄዳሉ። ሄደውም እዚያ ምግብን ተመግበው በተመገቡበት ደግሞ ውኃን ቀድተውበት ከዚያም ገንፎ፣ ቂንጬ ይዘጋጅበታል። ሌላ የሚሠራበት ነገር የለም፤ ራስን ስቶ መውደቅም የለም፤ ይህ ባህል ነው።
ጨሌውን ደግሞ ሴት አያቴ ስትነግረኝ፣ “ይህ የእናቴ የበዳቱ ነው፣ ይህ ደግሞ የእናቷ የአያንቱ ነው፣ ይህ ደግሞ በዚህ ዓመት ብላ (ለእርሷ ካላንደርም ወይም ዘመን መቁጠርያም ስለሆነ) … ይህ ደግሞ የባለሚ እናት ትላለች። ሁሉንም በየመልካቸው ታውቃቸዋለች፤ ታሳየናለችም። ማስቀመጫ ሙዳዩንም ስትከፍተውም መዓዛ አለው፣ ይሸታል። በአለባበስም ዛሬ ለበስን ተጌጥን ከሚሉት የበለጠ የሴት አያቴ ሳጥን ሲከፈት በጣም ይሸታል። በጣምም ሰውን ያስደስታል። አሁን ቤተ ክርስቲያን ብገባም፣ እዚያ ባለ ሥልጣን ብሆንም ከውስጤ አልወጣም ብሎ ወድጄው እንድቀር ያደረገኝ አስተዳደጌ ይመስለኛል።
ሌላው ትምህርቴን በሚገባ አጽንቼ በግዕዙም በአማርኛውም ሳይ ቄሶች የሚያወሩትና መጽሐፉ የሚለው የተለያየ ነው።
አብዲ፦ እውነቱና ያለው ነገር …
ቀሲስ፦ እንዲያውም የሚያስተምሩን ባህላቸውን ሃይማኖት ብለው ነው። ሃይማኖት ያልሆነን ባህል ለራሳቸውም አልገባቸውም። በዚህ ቤተ እምነት ወደ ወንዝ መውረድን ቀሳውስቱም ጳጳሳቱም ያወግዛሉ። ስልጣን እስክይዝ እኔ ይህ ነገር ያመኛል፤ ሥልጣን አጊኝቼ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ስሆን መሄድ አለብኝ ብዬ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልብስ ለብሼ ሄድኩኝ። ለምን? ሲሉኝ ለአቡነ ጳውሎስ በደንብ ነገርኳቸው። “አምላከ ባህር ወቀላያት”፤ ኦሮሞም የባህርና የገደል አምላክ ይላል፤ በግዕዝም እንዲሁ ነው የሚለው። ድሮ ክርስትና ሳይፈጠር በብሉይ ኪዳን የሚያመልኩ ሰዎች ወደ ወንዝ፤ ወደ አድባር ሄደው ይለምኑ ነበር። ለምሳሌ፦ አብርሃም ልጁን ለመስዋዕት ሲያቀርብ ወደአድባር ወጥቶ ነበር፤ በዚያ አድባርም እግዚአብሔርን አነጋገረው ይላል፤ በእኛ ጊዜ ወንጀል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አድባር የሚለው ሙሴና አብርሃም እግዚአብሔርን ያነጋገሩበት ነው። በእኛ ጊዜ ወንጀል ያደርጉታል፤ ወደ ወንዝ ስንሄድ ወንጀል ያደርጉታል።
ጨሌውም ደግሞ እኔ ሰው ይዞ እንዲገለገልበት ማድረግ ኋላ ቀር ባህል ነው፤ ራስን መተው፣ መጣል፤ በግድግዳና ከመሬት ጋር ራስን ማላተም ባህል ሳይሆን ኋላ ቀር ባህል ነው። ግን የውበት፣ የጌጥ ጨሌ የምትሰራበት ነገር የለም፤ ለእኛ ካላንደርም ውበትም ነው። የሚጠፋም ደግሞ አይደለም። ለምሳሌ፦ ይህ ልብስ ያልቃል፤ ጨሌ ግን አያልቅም፤ ክሩ ቢያልቅ ክሩ ይቀየራል፤ በቤተ እምነታችንም መቁጠርያ ብለን ይዘን እንጠቀማለን። የእነርሱ ጊዜ ይለምኑበታል፤ ለጸሎት ይውላል፣ የእኛ ጊዜ ይቃጠል ይላሉ። እንደው ሌላው ነገር ቢሆን ሊነገር የሚገባው ተሳስተው የሚያመልኩትን ተሳስታችኋል ማለት ነበር። እኔ ለሁሉም የኦሮሞ ተወላጅ ማለት የምለው እናትና አባቶቻችን ጨሌንና አምላኩን ለይቶ ያውቃል።
ለጨሌ የሚሰግድ፣ የሚጸልይ፤ ጨሌውንም አምላክ ነው የሚል ሰው ካለ ተሳስቷል። እናትና አባቶቻችን እንዲህ አላደረጉም። ደግሞም አላዋቂነት ነው። በየትኛውም ዘመንም ለውበት፣ የራስን ባህል ለማንጸባረቅ አስፈላጊ ነው።
ወደ አድባርም ስንመጣ ሾላ ሥር ይመጣሉ። ሾላ በዚህ ዘመን እንጂ ሰው በቤት አይቀመጥም፤ እንደ ዓለም የሰው ልጅ በዋሻና በጥላ ሥር ይኖራል። ኦሮሞ ደግሞ በተለይም በሾላ ስር አምላኩን ይለምናል፤ ያስታርቅበታል፤ ሥርዓተ ጋብቻን ይፈጽማል፣ ሕግ ያወጣል፣ ይፈታል፣ ያጠፋውንም ሰው እዚያው ይቀጣል፣ ማደርያውም እዚያው ነው። ዝናብም ጸሐይም ይከላከልለታል። ልክ ቤት ጸሐይና ብርድ እንደሚከላከልልህ። ቤት መሠራት የጀመረው በቅርብ ነው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ባህሉን ያልምድ የነበረው ከዚያ በፊት ነው። ከክርስትና በፊትም ነበር።
አብዲ፦ እስኪ እንመለስበታለን … ግለ ታሪኮትን እየተከተልን ብዙ ራቅን። እኔ ምን አስተዋልኩ፣ መሰልዎት ከአስተዳደግዎ አንድን ነገር ዳራውን ማጥናት እንደሚገባ ነው። ዛሬ ካህን በላይ የደረሱበትን … አሥራ ሁለተኛ ክፍል ካቋረጡበት እስኪ ወደትውልድዎ ይመለሱና ያጫውቱን ..
ቀሲስ፦ አሥራ ሁለተኛ ክፍል እስክጨርስ ትምህርቴንና የሃይማኖቱን ሥራ ጎን ለጎን እያስኬድኩ ሳለ ነርስ ነበርኩና ጎንደር ደረሰኝ። ያኔ የጎንደር ሚድካል ኮሌጅ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሥር ነበር እዚያ ስማር አንተ ኦሮሞ ሆነህ እንዴት የነፍጠኛ ሃይማኖት ትከተላለህ ብለው የኦሮሞ ልጆች ሆነው ኦርቶዶክስ ያልሆኑቱ ጠየቁኝ፤ ተው ማን ሰጣቸውና ሃይማኖት የተቀበለውን ሰው ይወክላል፤ እስኪ እናንተም አስተምሩን ፕሮቴስታንቱም፣ ሙስሊሙም ብለን እንወያያለን። ስንወያይ ከሁሉም ላይ የምወስደው አለኝ።
ከዚያም ከመጣሁ በኋላ በነርሲንግ ስላልቀጠልኩ ዳኛ ሆኜ ደግሞ ሐረርጌ ተሸምኩ። በዚያም ዳኛ ሆኜ ስሾም የምዕራብ ሐረርጌ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕረዘዳንት ነበርኩና ቤተ ክርስቲያንንም ጎን ለጎን እያገለገልኩ ሳለ አቡነ ጳውሎስ ከአባቶች ጋር ተማክረው መመለስ አለብህ ብለውኝ ቤተ ክርስቲያንን እንዳገለግል አደረጉኝ። ለምን በጎንደር ወንጌል አስተምር ስለነበር ብዙ ሰዎችም እንዲያምኑ አድርጌያለሁ በቤተ እምነቱ ኖረው የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ትተው የራሳቸውን ነገር ሊያለማምዱና ሊያስተምሩ የሚያስቡትን ሁሉ በአግባቡ መልስን ሰጣቸው ነበር።
በዚህ ቤተ እምነት ውስጥ ጉልበት የሆነኝ ነገር የሚመስለኝ (1) ከዚያ ስመጣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሕግ ክፍል ነው የተመደብኩት፤ አባ ጳውሎስ የሕግ ክፍል ኃላፊ እንድሆን ቢፈልጉም እኔ ግን ቀድሜ ባለሙያ ሆኜ ምን እንደሚሠራ ቤቱን ማወቅ አለብኝ ብዬ እንቢ አልኩኝ። (2) ተምሬ ስለመጣሁ በተለይም አስራ ሁለተኛ እስክጨርስ ክረምት፤ ክረምት ዝዋይ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ እየሄድኩ እማር ነበር። ለምሳሌ፦ ሰኔ ትምህርት ሲዘጋ እኔ ሐምሌና ነሐሴ እዚያ ሄጄ እማራለሁ፤ ሽማግሌው (አቡነ ጎርጎርዮስ) ትምህርት እንደሚገባኝ አይቶ የተለየ ትምህርት ይሰጠኝ ነበር፤ ሽማግሌው ትልቅና የወሎ ሰው ነው፤ ልክ እኔን ይመስላሉ፣ እንዲያውም ከኋላ ሳጠናቸው ኦሮሞ ይመስሉኛል፣ (1) ሰው እኮ አንድ ነው፤ አንድ ነን ይለኛል ሽማግሌው፤ ኦሮሚኛም ጥቂት ጥቂት እሰማለሁ፤ ቤተሰቦቼ ያውቃሉ ሲባል እሰማለሁ አሉኝ ሽማግሌው። ልክ እንደ አባት እኔን ያቀርበኛል። እንግዲህ በዚያ ቤት እኔ ኦሮሞ ነኝ ብሎ በግልጥ መናገር አይቻልም፤ እኔ ብቻ ነኝ የጀመርኩት።
አብዲ፦ ለምንድር ነው አንድ ነን ብለው የሚናገሩት የሚጠራጠሩት ነገር አለ?
ቀሲስ፦ እነርሱ አንድ ነን የሚሉት እኔን አትጠርጠር ይህን ቋንቋ ተናገር ሊሉኝ ፈልገው ነው። ለራሳቸው አይናገሩም ነገር ግን ይከላከሉልኝ ነበር፤ ለምሳሌ ጥያቄ ሳነሳ አማርኛ በትክክል አልናገርም ነበር፤ የኦሮሚኛውን ዘዬ እየቀላቀልኩ ሰባብር ነበርና፤ የዚህን ጊዜ አንዳንዶች “እርሱ ያጨማለቀውን ከምናዳምጥ ይቅርብን” ሲሉ፣ ሽማግሌው ደግሞ፣ “አያይ፣ እኔ ደግሞ እርሱን እሰማለሁ፤ ማስተማር የሚገባኝ እንደእርሱ አይነቱን ነው፤ የቋንቋ ችግር እንጂ እርሱ ከእናንተ በላይ ያውቃል” ይሉ ነበር።
አብዲ፦ እርስዎ በእውነት ለማሳመን ይጥሩ ነበር?
ቀሲስ፦ አንዳንዴ ሲነሳብኝ ሽመል አነሳለሁ። ለምሳሌ፦ ከዚህ ልነሳና፣ 1988 ዓ.ም ልክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደገባሁ ለጊዜው ባለሙያ (ኤክስፐርት) ሆኜ ብገባም በ1999 ዓ.ም በሕግ ክፍል ኃላፊነት ተመደብኩ፤ ኹለት ዓመት ሳይሞላኝ ደግሞ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆንኩ። ይህ ሊሰጠኝ የቻለው ከጎጃም ከሸዋ የመጡት ከእኔ ጋር ሊሾሙ በሲኖዶስ ቀርበው አንዱ ጎጃሞቹ የጎጃሙን፣ ሸዋዎቹ ደግሞ የሸዋውን ወገኑ። በዚህ ጊዜ አንዱ የሚያውቀኝ ተነሳና “እንዲያውም ይህንን ሥፍራ ማሟላት የሚችለው በላይ መኮንን እዚህ ነውና ያለው ለምን አንሾመውም?” ብሎ አስተያየት ሰጠ። በዚህ ጊዜ አቡነ ጳውሎስ፣ “እንዲያውም ዘንግቼ ነበር እንኳንም አስታወስከኝ” ብለው ወዲያው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆንኩኝ። ይህ ትልቅ ሥልጣን ነው።
ከእኔ በላይ ያለው አንድ ሊቀ ጳጳስ ብቻ ነው፤ እርሳቸውን የሚመለከተው የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ነው፤ የአስተዳደርና የፋይናንስ ጉዳይ በውጭም ቢሆን በአገር ውስጥ በቀጥታ የሚመለከተው እኔን ነው። በዚህን ጊዜ በመምሪያ ላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሰባስበው የእኔን መሾም አይሆንም ብለው ቃለ ጉባኤ ይዘው ተቃወሙ። ይህ እውነት ነው፤ ቃለ ጉባኤው በእጄ አለ፣ ለዚህም ሳልፈራ በግልጥ እናገራለሁ።
ሲኖዶስ ወሰነውን አንድም ጊዜ የተቃወመ አካል አልነበረም። አማራም ይሁን፣ ትግራይ ሌላውም ብሔር ቢሆን ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ የአስተዳደር ሰዎች ቃለ ጉባኤ ይዘው ተቃውሞ አያውቅም። እኔ ይህን ስሾም አስተዳደሩ ቃለ ጉባኤ ይዞ ለሲኖዶስ ደብዳቤ ጻፈ።
አብዲ፦ ለመጀመርያ ጊዜ ማለት ነው?
ቀሲስ፦ አዎን ለመጀመርያ ጊዜ አይሆንም የሚል። ይህን እንደሰማሁ ወዳደግሁበት ወደደብረ ሊባኖስ ሄድኩ። እዚያም ሄጄ “ጌታ ሆይ ይህ ነገር ካንተ ከሆነ ከእኔ ጋር ሁን፣ ካልሆነ ደግሞ ከዚህ ነገር ከልክለኝ” ብዬ አለቀስሁ። እኔ እንዲያውም አላሰብኩትም ነበር፤ በኋላ ግን ሽማግሌው(አቡነ ጳውሎስ) የት ሄድክ? አሉኝ፤ ለጸሎት ሄድኩ ብል ራሴን እንደጻድቅ መቁተር ይሆናል ብዬ፣ “ቤተሰብ ልጠይቅ ሄጄ ነበር” አልኩት።ከዚያም “ፈጥነህ ቶሎ ና” አሉኝ።“ከዚያ በፊት ግን እንወያይ አልኳቸው፦ እኒህ ሰዎች አብሮ አደግ ባልጀሮቻችሁ ናቸው እንዲህ ከሚቃወሙኝ እኔ ሥልጣኑ ቢቀርብኝስ? ይህ ስላደረጋችሁልኝ ደግሞ አመሰግናለሁ” አልኳቸው። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው (አቡነ ጳውሎስ) አብዶ፤ ካባውን ጥሎ፦ “ለካ አንተ ነህ የምታደራጅብኝ፤ ለካ አንተ መንገድ ከፍተህላቸው ነው?” ብለው ተቆጡ። እኔም “እስኪ ተቀመጡ፤ እሺ እናወራለን” አልኳቸው።
“እኔ ለእናንተ ብዬ ነው እንጂ አርጅተው እግራቸውን ማንሳት የተሳናቸውን በጥፊ ከዚያ ውስጥ አባርሬ ለራሴ መቀመጥ አያቅተኝም” ስላቸው “ታዲያ እንዲያ አትልም፤ እንደዚያ በላ” አሉኝ። ከዚያም “እንዴት እንደምትፈጽመው ብቻ ንገረኝ አሉኝ” እኔም “እነርሱ ለጻፉት ለዚህ ደብዳቤ መልስ ስጡና ለእኔም በግልባጭ አሳውቁኝ፤ ይህን ካደረጉ አመሰግናለሁ አልኳቸው” ተደረገ። ከዚያም ሄድኩ፤ ከዚያ በሩን ዘጉ። ከዚያ ነጋሽ ባልቻ የሚባል ኦሮሞ አለ፤ከዚያ የታሸገውን በር በእግሬ ረግጬ ከፈትኩት፤ አዲስ ቁልፍ አስገዛሁኝና ቆለፍኩት።
ዋናው ትግል እዚያ ነበር፤ ከዚያ ጠራኋቸው። እንዲህ አልኳቸው፦ ቤተ ክህነት ማለት እኔ ነኝ፤ የምትታዘዙ ትሠራላችሁ፣ እንቢ ያላችሁ በጥፊ ከዚህ ትወጣላችሁ” አልኳቸው። ይህን አቋሜን ሰምቶ ጳጳሱ ተደብቆ ወጣ። ከዚያም አንድ ወር ሙሉ ከቢሮ ቀረ። ከዚያ ኹለት ሦስት ቀን መቅረታቸውን ሳይ ሊቀ ጳጳሱ እስኪመጣ ወና ሥራ አስኪያጁም እኔ ነኝ አልኳቸው። ሕጉም ምን ይላል መሰለህ? ዋናው ሥራ አስኪያጅ በሌለበት ጊዜ ወክሎ ሳይሆን ተክቶት ይሠራል ነው የሚለው። አንድ ሰው ግን ተቃወመኝ፤ እሱን አስወጣሁት፤ በኋላ ከኹለት ሳምንት በኋላ በእኔ ላይ የተፈራረሙት ሰዎች ሁሉ ይቅርታ ጠየቁኝና ሥራችንን ቀጠልን። ከዚያ በሥራ ሲያዩኝ ማንም ያልሠራውን ሥራ ሠራሁ። ደመወዝ ጭማሪ በፊት በዝምድና ነበር፤ በፊት እገሌ ጳጳስ ዘመድ አለው ይባል ነበር፤ ሥራ እንደ ጀመርኩም ዘመናዊውንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ማእከላዊ ያደረገ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከፋይናንስና ከሕግ ክፍል የተውጣጣ ወዲያው ኮሚቴ አዋቀርኩ። የደመወዝ እስኬል እንዲዘጋጅ አደረግሁ። ከዚያ በፊት የተፈራረሙብኝ ሁሉ ተሳሳትን ብለው አደነቁኝ።
አብዲ፦ እውነት አሸነፈች ማለት ነው፤
ቀሲስ፦ አዎን እውነት አሸነፈች። ይህን ማለት የፈለግሁት፣ እውነት ነው የምነግራችሁ እዚያ ቤት ለትግሉ ሽመል ነው ይዤ የገባሁት ማለት ይቻላል። እንግዲህ እዚያ ቤት በተለያየ ጊዜ ያለውን ተግዳሮት ለማሳየት ነው። የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን እያለሁም ሠላማዊ ሰልፍ ወጡ። በግልጥ መወራት ያለበት በትውልዳቸው ወለጋ ሆነው ከጅማ የመጡ አባ ገብረ ማርያም ነጋሳ የሚባሉ አባት ሰብሳቢ ሳለሁ፤ ጳጳሱም ከእኔው ጎን ነበሩ፤ ፈተና እየሰጠን ሳለ ተፈታኞችን ጠርተን እንጠይቃለን፤ ሁሉም መምህራን ነጥብ እንይዛለን፤ እርሱ ተፈትኖ ሲወጣ ውጤቱን አንድ ላይ እንሰበስበዋለን፤ እና የእርሱን አየሁት፣ አንዳንዶቹ ከአሥር ዜሮ፤ ሌሎቹ አንድ ሰጥተውታል፤ ከዚያ ተሳሳትኩኝ እንዴ ብዬ ቆይ እስኪ ይመለስ አልኩኝ፤ አያይ አያይ ምን ያደርጋል ብለው ተጯጯሁ፤ ተመለሰ፤ ከዚያ ቅዳሴ ይህ ነው የፈተነው፤ አልመለሰም?... ይህንንስ አልመለሰም? አልኳቸው። ከዚያ በመጨረሻ እንመለስበታለን ብዬ ወደሌላ ሰው ተላለፍን። እኔ ግን ልቤ እዚያው ነበር። ነጋሳ የሚለውን ስም አይተው ማለት ነው። ኦሮሞ ከእኔ በቀር እዚያ ውስጥ ማንም የለም። ይህ ነገር ታሪክ ነው ብዬ ዝም ማለት አልወደድኩም። ልክ ፈትነን ሁሉን ነገር ከጨረስን በኋላ የሙያ ሥራ ጨርሰናል፤ ቴክኒካልና አስተዳደራዊ የሆነውን ደግሞ ለእኔ ተዉ ብዬ አስወጣኋቸው። ከዚያ እርሱን አንደኛ አድርጌ አስገባሁኝ።
ይኸው አባ ገብረ ማርያም ነጋሳ በአንደኛ ሴምስተር ማብቂያ ላይ ሁሉንም ትምህርት A+አመጣ፤ ሁለተኛም ሴምስቴርም እንዲሁ። በሁለተኛው ዓመትና ሲመረቁም አራት ነጥብ አምጥተው ተመረቁ። ፈተና ስሰጥ ደግሞ ምን አደርጋለሁ መሰለህ? ኮድ ሰጠቡት፤ መምህሩ ማረም እንጂ ፈተናው የማን እንደሆነ አያውቀውም፤ ዩንቨርሲቱ የሕግ ትምህርት ቤት ሳለሁ ስለኮድ ስለማውቅ አደረግሁት። በዚህ መንገድ እንግዲህ በዚህ ቤተ እምነት ውስጥ ኦሮሞ ባዳ ነው፤ የነፍጠኛ ቤተ ክርስቲያን ነው ይላሉ። ኦሮሞ የእኛ አይደለም ያለው፤ እኛ ብቻ አይደለንም፤ የደቡብ ሰዎችም የእኛ አይደለም ያሉት ለዚህ ነው።
ወደ እኔ ስመለስልህ እኔ ፊት ለፊትና በግልጽ እንድናገረው ያደረገኝ አያቴ ነው ብዬ አስባለሁ። እርሱ ይመክረኝ ነበር፤ ... ለምሳሌ ምን ይላል? ሊቀ ዲያቆን ሆኔ ሚስት ሳላገባ 16 ዓመት ሆኖኝ ኩራ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አለቃ ሆንኩኝ። ልክ አለቃ የሆንኩ እለት ሽማግሌው አያቴ ምን እንዳለ ታውቃለህ? መጀመርያ አትናገር አለኝ፤ ሰው ሲናገር ስማና የምትናገረውን ነገር ሰው ሁሉ ካልተቀበለው እንዳትናገር አለኝ፤ የሚቀበሉህ ከሆነ ተናገር አለኝ። ይመክረኛል ሁሌም ማታ ማታ። አንዳንድ ቀን ደግሞ ስብሰባ ሲደረግ መጥቶ ከመካከል ይቀመጣል። በእኔ ሕይወት የእርሱ ድርሻ ይህን ያህል ነው የምለው አይደለም።
ይህ ነው እንግዲህ እርሱን እንድወድ፤ ባህሉንም እንድወድ አደረገኝ። ሽማግሌው እንዲሁ ነው የገባው። ተምሮ አይደለም። ግን አባቱ ጅማ ዳኛ ወይም ነጭ ለባሽ መጣ ሲባል እያረሰ ካለበት እርሻው የጠመደውን በሬዎች ጥሎ ይሸሻል አሉ፤ ባለሚ ሲወለድ ግን እርሱ ጠበቃ ይሁን፤ የቢሮ ሰው ይሁን፤ አዋቂ ይሁን ብለው ላኩት። ኦሮሞ አዋቂ አይመርጥም፤ እገሌ ሥራው ይህ ነው ብለው አክብረው ይሰጡታል እንጂ። ባለሚ እርሻ አላረሰም፤ እነርሱን ብቻ ያስተዳድራል እንጂ። ታናናሾቹን፣ እናቱን፣ አባቱን ... ማስተዳደር ነበር። እኔም ከልጅነት ጀምሮ አስተዳዳሪ ሆንኩኝ።
ሌላው (የጠየቅኸኝን ሁሉንም ልመልስልህ ሌላም ልትጠይቀኝ ትችላለህ) በዚህ ቤተ እምነት አይ የነበረው ንጹህ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፤ እነርሱ ወደሥልጣን አይመጡም፤ ይህን ተግዳሮትም መጋፈጥ አይፈልጉም ወደ ዳር ኾነው ቆመው ያያሉ፤ ወይጥለው ገዳም ይገባሉ። ወደ ሥልጣን የሚመጡት ሰዎች ፦ (1) ሠርተው ሳይሆን በዘረኝነት፣ በጥቅም ተደራጅተው ነው ወደ ሥልጣን የሚመጡት። እኔን እዚያ ውስጥ እንድቆይ ያደረገኝ፦(1) ዲያቆን ሆኜ ስቀድስ ብቆይም ከዚያ በኋላ የመንግሥት ሠራተኛ መሆኔ ጉልበት ሆኖኛል። (2) ፊት ያሳለፍኩት ሕይወት ለምሳሌ፦ፓርላማ ሳለሁ አቡነ ጳውሎስ ደስተኛ አልነበሩም። ምክንያቱን በኹለት ልከፍለው እችላለሁ አንደኛውበቀናነት ካየነው ለምን ከእጄ ወጣ?፤ እዚህ ማገልገል እየቻለ ሊሉ ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ከባለ ሥልጣናት ጋር እንድታይ አይፈልጉም። ከእርሱ ጋር ብቻ አንድሆን ነው የሚፈልገው። ሌላው በቋንቋ ችሎታዬ አሰናካይ የሆኑትን በተለይም ሽማግሌው ይህ ነገር ይሠራ ብሎ ዛሬ ካዘዘ (አቡነ ጳውሎስን) ይመጡና የሆነ የሆነ ነገር ብለው ያደናቅፋሉ እንጂ እርሱ ፍላጎት ነበረው። ወንጌል እንዲሰበክ፣ እውነት ለመናገር በተለይም የኦሮሞ ጳጳሳት ሲሾሙ ከማንም በላይ አቡነ ጳውሎስ ሊመሰገኑ ይገባል።
አብዲ፦ መልካም እንግዲህ ወደፊት ልጠይቆት ያሰብኩትን እግረ መንገድ መልሰውታል፤ በሥራ የገጠምዎትንም አብራርተው በጥሩ ሁኔታ ነው የመለሱልኝ። ሌላው ይህ በእጄ የያዝኩት በእርስዎ የተዘጋጀው መጽሐፍ የተወሰነውን ያህል አንብቤዋለሁ። ከርዕሱ ጀምሮ ብነሳ እስኪ በአጭሩ ይዘቱን ምን ማለት እንችላለን? ርዕሱ (Kiristiyanummaa fi Oromo Dur irraa hanga ammaatti jedha) “ክርስትና ከጥንት ኦሮሞ እስከ አሁን” ይላል። የጻፉትም እርሶ ሊቀ አእ... ካህን በላይ ... (ሲያነብ ሲኮላተፍ)
ቀሲስ፦ ሊቀ አእላፍ ካህን በላይ ይላል ...
አብዲ፦ እንዲህ አይነት ታሪክ ሲጻፍ ይህ የእርስዎ የመጀመርያ ነው ወይስ ከዚህ በፊት የተሞከረ ነገር አለ? የመጀመርያ ከሆነ ደግሞ ደግሞ ቄስ በላይ ከምን ተነስቶ ነው ይህን መጽሐፍ ሊጽፍ የቻለው? የመጽሐፉንም ይዘት ቢነግሩን።
ቀሲስ፦ እንዲህ አይነት ሲጻፍ የመጀመርያ ነው። የመጽሐፉ ሽፋን ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልብስ ከቅዳሴ እንደወጣሁ እንዲህ አጊጬ ለብሼ ያኖርኩበት ሰዎች ባዩት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት አይደለም እንዳይሉና እንዲገነዘቡም ነው። ሁለተኛው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆኑት ደግሞ የመጽሐፉን ይዘት አይቶ ማን እንደሆንኩ ያውቃሉ።
መጽሐፉ የመጀመርያ ነው ብዬሃለሁ፣ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ደግሞ አንደኛ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያስተዳድሩ ባለ ሥልጣናት ማንነቱንና ባህሉን ፈጽመው ይረግማሉ፤ ያወግዛሉ፤ ሁሉንም ነገሮን ሰይጣን አደር ይሉታል። የሚያቀርበውን ምግብ ይበሉለታል፣ ጮማ፣ ጠላ፣ አረቄ፣ (የገጠሩን ነው የምነግርህ) ይዞ ሲሄድ ይበሉለታል፣ ይጠጡለታል፤ ጠላና አረቄውን፤ ጠጁንም ያደንቃሉ። ለቄስ በሬ ታርዶ ወጡ በልዩ ሁኔታ ነው የሚሠራው። ይህን ያደንቃሉ፤ ከዚህ ሲያልፍ ግን፣ ለምሳሌ፦ የእኔ ስም ኦልአና ነበር፤ የኔታ አስራት የሚባል ሰው ኦልአና ማለት ምን ማለት ነው? አለኝ፤ በላይ ማለት ነው አልኩት። ከዚያም እርሱ ነው ስምህ አለኝ፤ እኔም ተጠራሁበትና በዚያው ቀረ።
አብዲ፦ ተተርጉሞ በዚያው ቀረ ...
ቀሲስ፦ አዎ! እውነቱን ነው የምነግራችሁ። የኔታ አስራት ገብረ ጉራቻ መድኃኒዓለም አለቃ ነበሩ። “እንዲህ ያለ ስም እያለ እንዲህ እንዴት ትላለህ?” አሉኝ። እኔም የዚያኔ እውነት መሰለኝ። አሁን፤ አሁን ግን ... በሌላ በኩል የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ ይህ ሃይማኖት የጠላት ነው፤ የነፍጠኛ ነው ብሎ ይራገማል። እኔ ሁለቱንም እወዳለሁ። ይህን ሁለቱን ማስታረቅ አለብኝ ብዬ ከብዙ ጊዜ በፊት አስብ ነበር፤ ይህን መጽሐፍም ማዘጋጀት ከጀመርሁ ስድስት አማታት አስቆጥሯል። በመጀመርያ እኔ ማስተላለፍ የፈለግሁት መልዕክት በየትኛውም ዓለም ብሔር ይበላለጥ ይሆናል እንጂ የባህሉን ክብር ያጣ የለም። የኦሮሞ ባህል ከየትኛውም ዓለም የሚበልጥ ነው ብል የዓለም ጸሐፍት ይህን አረጋግጠዋል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ስበኩ ብሎ ደቀ መዛሙርትን ሲልክ የሕዝቡን ባህል አክብራችሁ በሕዝቡ ቋንቋ አስተምሩ ብሎ ነው የላካቸው። ከእነርሱ ባህልና ቋንቋ ይልቅ የሕዝቡ ባህልና ቋንቋ እንዲያከብሩ አዟቸዋል። የእኛ ካህናት የሕዝብን ባህል ሲረግሙ ይውላሉ፤ ወንጌሉ እንዲያ አይልም፤ ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርትን ሲልክ የተናገረው ሌላ እነርሱ ደግሞ የሚሉት ሌላ ነው። .... ለምን መሰለህ እነርሱ የተሳሳቱት? ማንነቱን ይዞ ነው ክርስቶስ የእርሱ እንዲሆኑ ያዘዘው፤ እነርሱ ደግሞ ማንነቱን ሰርዘው የእነርሱን ማንነት ወስደው ክርስቲያን ይሆናሉ። ይህ ትልቅ አላዋቂነት ነው። .... በእርሱ ማንነትና ባህል ነው የሰበኩትና የነገሩት። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ ነው የሚገለገሉት። እዚህ እኛ ዘንድ ሲመጣ ግን የኦሮሞን ይፈራሉ። ለምን እንደሚፈሩ አላውቅም፤ ይህ ለሁሉም ምስጢር ነው። አሁን እነዲህ ብዬ የምገልጠው የለኝም፤ በግምት ማለት ፈልጋለሁ ግን አያስፈልግም። ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአንድ ሕዝብ ባህል መከበር አለበት ይላል።
ባህልና ሃይማኖት ተደባልቋል። ስንለብስ ባህል ነው፤ ሃይማኖትህንም በአለባበስ ትገልጥበታለህ እንዲሁ ባህልህንም ትገልጥበታለህ።
አብዲ፦ እንግዲህ እንኳንም አገኘኋችሁ እስኪ የምፈልገውን ጥያቄ ልጠይቆት። የአብዛኛው ሰው ስም፤ ከሂደት በኋላ ስሙ መቀየሩን የምታውቀው አለ፤ በአብዛኛው ብዙ ኦሮሞ ገብረ ምናምን ... ወልደ ምናምን ... ሃብተ ምናምን የሚባሉት በሂደት ከጊዜ በኋላ የተሰየሙ ናቸው። እንደ ገናም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሆነህ የአማርኛ ስያሜ ያላቸው እኒህ ተቀጽላዎች አይቀጸልባቸውም፤ ገብረ፣ ወልደ፣ሃብተ... ተብሎ የሚጨመረው ከሌላ ብሔር ለመጡ የሚቀየርላቸውና የሚጨመርባቸው እውነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ያለ ነው ወይስ እንዲሁ በግል የተፈጠረ ነው?
ቀሲስ፦ ጥሩ ነገር አነሳህ። ይህ ስያሜ ከክርስትና ከተነሳ የክርስትና ስም ነው ይሉሃል፤ ክርስትና የሚያነሳው ቄስ የኦሮሚኛን ቋንቋ አያውቅም፤ እርሱ የሚያውቀው አማርኛ ነው።ለዚህ ነው ስም የሚሰይመው፤ ወደሰሜን ስትሄድ ስሙም፤ የክርስትና ስሙም ያው ነው። ክርስትና የተነሳ እለት ያንኑ ስሙን ያደርገዋል። የክርስትና ስሙን ሲረሳ “መምሬ ስሜን ረሳሁት ንገሩኝ” ይላል። ሰው የገዛ ስሙን ይረሳል፤ ለምን ሆኖ መሰለህ? ያ ልጥፍ ስም ሕጋዊ ስላልሆነ ነው። በፊትም አሁንም የምናገረው ነገር ጳጳሳቱም ራሳቸው ደቡብ ይሁኑ ምዕራብ በጥንት ስም ነው የሚሰየሙት። ...ሁሉም። የትግራይ ይሁን የአማራ፣ የኦሮሞም ሁሉም። ግን ሲሰየም የትግራዩም ሕዝቡ በሚሰማውና በሚተረጉመው ስያሜ ቢሆን በጣም ጥሩ ነው። ለምሳሌ፦ አቡነ ሄኖክ፣ ኤዎስጣቴዎስ፣ ሳዊሮስ ... አቡነ ጳውሎስ ሰብስበዋቸው ሲኖዶስ ሰብስበው ጳጳስ አድርገው ሲሾሙዋቸው ሁሉም ይህንን ስያሜ ሲሰይሙ እጄን አውጥቼ እንዲህ አልኩ፦ በጊዜው ሰው ቢስቅብኝም ለእኔ ግን እውነት ነው፤ በተለይም አቡነ ኤዎስጣቴዎስ የመጀመርያ ስማቸው አባ አራርሳ ነበር፤ ኤዎስጣቴዎስ የሚባለውን እንኳን ሕዝቡ እኔ ራሴ መጥራት አልችለውም፤ ለምን ሰው መጥራት የማይችለውን ስም ትሰይማላችሁ? አልኩ። ማን ይባል ትላለህ? አሉኝ። እኔ ልንገራችሁ አልኳቸው፤ አቡነ ዋቅጅራ፣ አቡነ አራርሳ .. ቢባል ምን ይሆናል? እግዚአብሔር ይቀየማል? አቡነ ጳውሎስን፦ በአገራችሁ አቡነ ሐጐስ ቢባልስ? ስላቸው ሽማግሌው(አቡነ ጳውሎስ) ደንገጥ አሉ። ለምሳሌ የአማርኛውንም እንውሰድ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲባል ምድሩ ይንቀጠቀጣል፤ ለምን መሰለህ? ሕዝቡ ትርጉሙን ስለሚያውቀው ነው። በአማራ ብሔር ዘንድ ሄደህ ተክለ ሃይማኖት እንደሚባለው ሰላሌ ደግሞ አቡነ ተክሌ ይላል። ልለምን መሰለህ ትንሽ ትንሽ ስለሚረዳ ነው። እንደው ሰው ትርጉሙን የማያውቀውን ስም ትተን አቡነ አራርሳ፣ አቡነ ዋቅጅራ ብንልስ ስል፦ ሽማግሌው ዋቅጅራ ማለት ምን ማለት ነው አሉኝ፣ “ዋቅጅራ ማለት እግዚአብሔር አለ፤ አማኑኤል” ብዬ ትርጓሜ ሰጠሁት። አራት አምስት ትርጉም ሰጠሁት፤ “አራርሳ ማለትስ?” ሲሉኝ፣ “በአማርኛ ልተርጉመው?” አልኳቸው። አዎ ሲሉኝ፣ “አስታረቀ፣ አንድ አደረገ፣ አስማማ፣ ምህረት አደረገ ማለት ስላቸው ... እርሱስ ጥሩ ነበር ሲኖዶሱ እሺ ቢል አለ ሽማግሌው። ትርጉሙ በጣም ያስደስታላ፤ ይህን ያለው እኮ ሲኖዶስ ውስጥ ነው።
አቡነ ስምዖን የሚባሉት ደግሞ፦ “ሲኖዶሱን መጫወቻ አደረጋችሁት እንዴ?” ብለው ተቆጡ። ሳቅ .... “ምን ያድርግ ... የእውቀቱን ያህል ነዋ ሽማግሌው!” ሽማግሌውን(አቡነ ጳውሎስን) ነው የተቆጣው፦ ይኼ ልጅ ዝም ብሎ በሲኖዶስ ይጫወታል? ብሎ በጣም ተቆጣ። ቁጣ አይሁን ቆይ እስኪ ብዬ ተውኳቸው። ግን የዚያን ቀን አልተሳካም፤ እነርሱ ያሉት ስም ነው የተሰየመው። ከዚህ በኋላ ግን አቡነ ዋቅጅራ፣ አቡነ አራርሳ፣ አባ አራርሳ፣ አባ ዋቅጅራ መባሉ ... ሕዝቡ አባ ዋቅጅራ ቢባል እስላምና ፕሮቴስታንት መጥቶ አባታችን ይል ነበር፤ ይህ ነው የሚፈልገው። ስም ብቻ አይደለም ቋንቋም መቻል አለበት፤ ቋንቋ ብቻም ሳይሆን ፍላጐትም ሊኖረው ይገባል። ይህ ከሆነ ሃይማኖቱም ተስፋፋ፤ እነርሱም ተወደዱ፤ ሕዝቡም አንድ ይሆናል ማለት ነው።
በኦሮሚኛ ስጽ እኔ ዓላማዬ የመካነ ኢየሱሱ ቄስ ዶክተር ዋቅስዩም፣ ሼክ አመዲንና እኔ ሆነን ተቀምጠን አወራን። ጸሎት እስላምም ፕሮቴስታንትም ኦርቶዶክስም ካቶሊክም ሁሉም በኦሮሚኛ ቢጸልይ አንድ ይሆናል እኮ አልኳቸው። አንድ ቋንቋ ነውና እስላም፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት መሆኑን ይረሳ ነበር። በኦሮሚኛ ዋቀ(ፈጣሪ)፣ እኔም ፈጣሪ ነው ምለው ሁላችንም እንዲህ ብናደርግ ሳይታወቅ አንድ እንሆናለን። እውነቴን ነው ይህ ወደፊትም መሆን ይገባዋል።
አብዲ፦ ሕዝቡ ከገዛ ፍላጎቱ ተነስቶ ማለት ነው?
ቀሲስ፦ አዎን ይህን ሁሉ በማካተት። ግን አስከአሁን በአግባቡ አልሄድንበትም፤ ሁሉንምም ላያስደስትም ይችላል። ወደመጽሐፉ ይዘት ስንመጣ ይህም ከእርሱ ጋር ይያያዛል፤ እዚህ ላይ ኹለት ታላላቅ ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለሁ። አንደኛው ይህን ሃይማኖት ሽፋን በማድረግ ይህን ሕዝብ ሲሳደብ የነበረ ሰው መልስ ማግኘት ይገባዋል። ሁለተኛው ደግሞ የእኒህ ሰዎች አባባል ቤተ ክርስቲያኒቱን መወከል አይችልም።
ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባባል መልስ ሳይሰጡ ዝም ያሉ ሰዎች ከቅጣት ሥር ያመልጣሉ ብዬ አላምንም። እግዚአብሔርም ሰውም ይጠይቃቸዋል። ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም አይደለም ብለው መመለስ ነበረባቸው። ለምሳሌ፦ የአለምን ሕዝብ የትውልድ መነሻ በአጭሩ አንድ ነገር አስቀምጫለሁ። ከአዳም ጀምሮ ያለውን አንስቼ ከእርሱ ቀጥሎ ብዙ ሰው ከተወለደ በኋላ በጥፋት ውኃ ሁሉም ትውልድ ጠፋ። በዚያ በጥፋት ውኃ ሁሉም ትውልድ በጥፋት ውኃ ተወሰደ። ኖህ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅ ስለነበር እርሱ ብቻ ቀረ። ኖህ ደግሞ ሦስት ልጆች ነበሩት። ሴም፣ ካምና ያፌት።ስምና ያፌትን ትቼ ወደካም መጣሁ። ለምን ብትለኝ ኦሮሞን ፍለጋ።
የካም ልጆች ደግሞ አራት ናቸው፤ ኩሽ፣ ሚስራ፣ ፉጥና ከነዓን። ኦሮሞ ከኩሽ ልጆች የመጀመርያው (የበኵር) ልጅ ነው። ይህን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው የወሰድኩት።
አብዲ፦ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተቀምጧል ማለት ነው?
ቀሲስ፦ አዎ! ተቀምጧል።
አብዲ፦ እስከ ኦሮሞ ድረስ ስም ጠቅሶ?
ቀሲስ፦ አዎ! ኦሮሞም ሌላው ብሔር እንደተወለደው ነው የተወለደው። ከዚህ ውጪ አይደለም። ምን ይላል? እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። የሕይወት እስትንፋስን ካገኘ በኋላ ሰው ሕያው ፍጡር ሆነ። ይህ ለአዳም ትውልድ ሁሉ የተሰጠ ነው። ነጭም፣ ኦሮሞም ቢሆን። እንዲህ የተወለደውን ሰው አለቃ ታዬ “ኦሮሞ ከውኃ ውስጥ ወጣ” ብለው ጻፉ። መጽሐፋቸው በእጄ አለ። ይህ መልስ ማግኘት አለበት። ብዙ ሰዎች ዘንድ ሄጄ ይህ ምንድር ነው? ትክክል አይደለም ብዬ ለጳጳሳቱ፤ ለሽማግሌውም ጭምር(አቡነ ጳውሎስ) ነገርኳቸው። ሽማግሌው ይሁን፤ ይውጣ ይላል። በኋላ ግን አምስት ይሁኑ አራት ጳጳሳት ገብተው ይህን አታሰሙ ብለው ከለከሏቸው። ሲኖዶስ ሲነሳ ትልቅ ሥልጣን አለውና ሽማግሌው የሲኖዶስን ስልጣን እየጠበቁ መሄድ ይፈልጋሉ። እነርሱ ሲያጓትቱት እኔ መልስመስጠት አለብኝ ብዬ ጻፍኩ።
አብዲ፦ ሰዎቹ እንዲህ ነገርን በማጣመም የሚያገኙት ምን ትርፍ አለ? ፍላጎታቸውስ ምንድር ነው?
ቀሲስ፦ ፍላጎታቸው ለኔ ኹለት ነገር ነው። አንደኛው ችሎታ የላቸውም፤ አእምሮአቸው ጤነኛ አይደለም፤ ይቅርታ አድርጉልኝ አእንጂ በአማርኛ ደንቆሮ የሚባሉ አሉ አይደል፤ ከእነዚያ ሰዎች አንዱ እነርሱ መሰሉኝ። ኅሊና ኖሮት ደህና ነገር የሚያስብ ሰው የሰው ልጅን እንዴት ከውኃ ተገኘ ብሎ ያስባል? ... ቤተ ክርስቲያንን አፍርሷል፤ ይህ ሰው የኦሮሞ ጠላት ነው። ሁለተኛ ለዚህነግ ማን ነው መልስ መስጠት ያለበት እኔ በቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ድርሻዬ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ነኝ፤ ይህ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ነው፤ ስለዚህም መልስ መስጠት ያለብኝ እኔ ነኝ ብዬ ጻፍኩለት። ሰዎቹ ዛሬ ነገ እያሉ አጓተቱት እኔ ግን መቀበል አልቻልኩም።
አብዲ፦ ለዚህም ሰው የመለስከው መልስ እዚሁ ውስጥ አለ?
ቀሲስ፦ አለ። ምን አልኩት መሰለህ? ይህ ሰው፤ ሰው ተብሎ ሊጠራ አይገባም፤ ቤተ ክርስቲያንን መወከል አይችልም። አንዳንድ ሰዎች በዚህ ጽሁፍ ቢደሰቱም እርሱ ቤተ ክርስቲያንን መወከል አይችልም። ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበት መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ እንዲህና እንዲያ ይላል። የዚህን ተቃራኒ የሚናገር ሰው የሐሰት ሰው፤ ወይም ልብወለድ ጽሁፍ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ እርሱ ወንጀለኛ፤ጥፋተኛም ነው። ይህንንም አይተው መልስ ሳይሰጡ የተቀመጡም ከተጠያቂነት አያመልጡም። ያላዩ ሰዎች ግን ይኖራሉ ያላዩ ከሆኑ አይጠየቁም። እኔ የሕግ ሰው ነኝ አይጠየቁም። ካላዩ ካልሰሙ ተጠያቂዎች መሆን አይችሉም። ይህን አንብበው ዝም ያሉ ግን ችግር አለባቸው። ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም ሊሉ ይገባል። እንዲህ መልስ ማግኘት አለበት ብዬ ይህን መልስ ሰጠሁ።ሁለተኛው አባ ባሕርይ ነው፤ ብዙ ሰዎችን ማንሳት ይቻላል፤ ይህን ሁሉ ከጻፍን አስር መጽሐፍም ላይበቃ ይችላል። የማነሳው ትልልቆቹን ብቻ ነው። አባ ባሕርይ ደግሞ ምን አለ፤ ኦሮሞ መሬትም አገርም የለውም ይላል። እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት ነው እንዲያገለግል ነው የተመረጠውም፤ የተሾመውም።የሰው ልጅ እንዴት ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ ይወጣል። ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሁሉ እስከምድር ዳርቻ ሄዳችሁ አስተምሩና ደቀቀ መዛሙርት አድርጉ አለ እንጂአንተ መሬት አለህ፤ አንተ የለህም እያለ በእግዚአብሔር መንግሥት ስለምድራዊ መንግሥት ማውራት አይገባም ነበር። እርሱ መሬት አዳይ የቀበሌ ሹም አይደለም፤ የዚህ ዓለም ካድሬ አይደለም፤ ለዚህ መልስ መስጠት አለብኝ ብዬ መልስ ሰጠሁት። እንዲበቃው አድርጌ በበቂ ሁኔታ። አሁንም ለዚህ መልስ ያልሰጡ ሰዎች ተጠያቂነት አለባቸው።
ይህ መጽሐፍ በውስጡ ብዙ ነገርን ይዟል። የኦሮሞን .... እምነትም ጭምር።
አብዲ፦ ባለፉት ዘመናት የነበሩት ነገሥታት
ቀሲስ፦ እውነት ነው፤ አንደኛ ተጠቅመዋል። አሁን በኃይለ ሥላሴ ብቻ ሳይሆን ወደኋላም ተመልሰን በዚህ እምነት ተጠቅመው ሲገዙ ነበሩ። ለእምነቱም መስፋፋት መሰናክል የሆነው ይህ ይመስለኛል። ሃይማኖትና መንግሥት መለያየቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፊትም (ከሥጋዌ በፊት መሆኑ ነው) እንደዳዊትና ሰሎሞን ያሉ ነገሥታት ንጉሥም የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። ከጌታ ልደት በኋላ ግን የቄሣርን ለቄሣር፤ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ አለ። አሁን ምን ሆነ ሊገዙበት ሃይማኖትን ሽፋን አደረጉት። ከቅርቡ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ብንነሳ ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ብለው ከአይሁድ ወገን ራሳቸውን ሾሙ። የአይሁድ ዘር የላቸው፤ ኦሮሞ ላይ እንጂ ለኦሮሞ አልሠሩም። የኦሮሞ ዘር ነው ያላቸው፤ አባታቸው መኮንን ጉዲሳ ነው፤ግን አማራይዝድ ሆነው የዘዚያን ጊዜውን ሥርዓተ መንግሥት ብቻ አይተው ... ምን አለ አንድ ጃገማ ኬሎ፣ ኃይለ ሥላሴ በአማርኛ ይናገራል፤ ጃገማ ይተረጉምለታል፤ ጃገማ ሲተረጉም ሽማግሌው ያልተናገረውን ተረጎመ፤ ጃገማ እኛ እንደዛ አላልንም አለው። ዛሬም ኦሮሞ ሆኖ ኦሮሞ ላይ የሚሰራ ኦሮሞ አይደለም፤ ጠላት ነው። ኦሮሞ ሳይሆን ደግሞ ለኦሮሞ የሚሠራ ካለ ሊወደድ ይገባዋል።
አሁን ሥርዓተ መንግሥቱ እንጂ ሰዉ ብቻ አይደለም፤ በዚያ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ሰዎች ድርሻውን መወጣት ነበረባቸው። ይህ መጽ ሐፍ እንዲወጣ ሲመክሩኝ የነበሩ ሰዎች ምነው ተው ይቅርብህ፤ ቢሆንም በኦሮምኛ አትጻፈው፤ በላቲን ሳይሆን በአማርኛው ለምን አትጽፈውም? አሉኝ።እኔ የምፈልግ ከእናንተ ጋር ጭንቅላቴን መበጥበጥ ሳይሆን ጨቅላ ወጣቶችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያሉትን፤ ነገ ደግሞ ዛሬ እየተወለደ ላለው እነርሱ እንዲያነቡትና ሃይማኖትና በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንዲረዱት ለማድረግ ነው።
ማብራራት የፈለግሁት ነገር እኒህ ሰዎች ጸረ ቤተ ክርስቲያንና ጸረ ሕዝበ ኦሮሞ ናቸው። ቤተ ክርስቲያንንም አይወክሉም። አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን በግልጥ ማወጅ አለባት ... ይላሉ። እውነት ነው፤ ግን እኔም ባለሁበት የሥልጣን ደረጃ ላይ ሆኜ መልስ መስጠት እንደቤተ ክርስቲያን እውቅና ሊያገኝ ይገባል ብዬ አምናለሁ። ለምን መሰለህ ልዩነት ስላለ ነው። በፖለቲካ ውስጥም እኮ ልዩነት ይኖርሃል። ልዩነትህን እንዳለ ይዘህ ትሄዳለህ። እነዚያኛዎቹ ትክክል ቢሆኑም እኛ ኦሮሞ የሆንን ደግሞ እንዲህ ልንወስደው ይገባናል።
ሌላው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዲገለጥ የፈለግሁት ኢሬቻ ከሄዱ በኋላ ቤተ ክርስቲያን መሄድን ደግሞ ወንጀል የሚመስላቸው አሉ። ይህ ለኦርቶዶክሳውያን ራሳችንን ማወቅ ነው፤ ራሱን የሚያውቅ ፈጣሪውንም ሃይማኖቱንም ያውቃል። ችግሩንም ጠላቱንም የሚለየው ... ሌላው ደግሞ ኦሮሞ እንዴት እንደተስፋፋ፣ የጥንቱ ኦሮሞ አንድ ነው፤ ይቅርታ ያድርጉልኝና አንድ ነን ብሎ ያስባል፤ እስኪ የጥንቱን ገዳ እናንሳ፤ ዛሬ እንደዚያ ልንግባባ እንችላለን? ይህንንም ደግሞ ብጽፍ አንዱ ለሌላው ያስተላልፍ እንደነበር ዓለም እጅግ ያደንቀው ነበር።
ሌላው በኦሮሞ ዘንድ ውሸት የለም። ዛሬ ፍርድ ቤት ሄዶ የተፈረበትና የተቀጣ ሰው ሲዋሽ ነው የሚውለው። ተከሶም፣ ሽማግሌ ሆኖም፣ ለምስክርም ቢሄድ ይዋሻል። አንድ ነገር ልንገርህ በሐረርጌ ዳኛ ሆኜ የሰው ምስክር ሳስምል ወደእኔ ዞረህ ሳይሆን ወደሐጂውና ወደ ሼኪው ዙና ቁርአኑን ይዘህ ማል እላለሁ፤ አያይ እንደ ሕጉ ነው የማደርገው ሲለኝ፣ ሂድ እኔ ነኝ ያዘዝሁህ እንዳልኩህ አድርግ እለዋለሁ። እሺ አይልም ይቃወማል። እንዲያውም ምስክርነቱ ቢቀርብኝስ ብሎ ይናገራል። አትችልም ትገደዳለህ እለዋለሁ። ዘወር ብሎ አቦ ያንን የተማከርነውን ትቼዋለሁ እውነት ነው የምናገረው ብሎ ይምላል። መቃብሬ ብቻዬን ነው፤ ፈጣሪ ይጠይቀኛል፤ አላደርገውም፤ ዛሬ ይሁን ነገ ሞቴን አላውቀውምና ይላል።ኦሮሞ ይህን ያህል ፈጣሪውን ይፈራል።
ቦረና ስትሄድ አሁን የሆነውን አላውቅም አንድ ጓደኛ አለኝ፤ እዚያ ተመድቦ 1984 ዓ.ም ስድስት ወር ተቀምጦ ነበር ተመድቦ የሄደው። እንዴት ነው ቦረና ብዬ ጠየቅሁት፤ ኸረ ሕጉን ረሳሁት አለኝ። የሚሟገት ሰው የለም፤ ቢመጣም የሚዋሽ ሰው የለም። የሕጉን አንቀጽ ለማየት አልሄድም፤ ሕጉን ረሳሁት አለኝ። ምክንያቱም አይዋሹም፤ እውነትን ብቻ ነው የሚናገሩትና። የተከሰሰውም እውነት ነው የሚናገረው፤ በክርክር ጊዜ አይቃጠልም፤ ገንዘብ አያልቅም፤ ሠላም እንጂ።
አብዲ፦ አሻጥርም የለም ...
ቀሲስ፦ አዎን የለም። እዚም እዚያም ማምታታት የለም። መጽሐፉ ይህንና ሌሎችንም የሚያሳይ ነው። የኦሮሞ ትውልድ እንዴት እንደተባዛ፤ የማደጎ ልጅ፣ተገዶ የተደፈረ ልጅ...
አብዲ፦ የኦሮሞን ታሪክ በጥልቀት አይታችሁት ... ለምን የሃይማኖት አባት ሆነው ብዙ ነገር ሠርተዋል፣ ብዙ ነገሮችንም ለውጠዋል፤ ይህንን እንግዲህ መልሱን ለታሪክ ነው የምንተወው። እናንተ የአንዳንድ ሰዎችን ታሪክ ስናነሳ ነገም መነሳቱ አይቀርም። አሁን ምን ላይ ነዎት፤ ወደ ፊትስ ምን ያደርጋሉ? ያቀዱትና ያሰቡት ነገር ካለ ቢነግሩን?
ቀሲስ፦ ወደ ፊት እኔ ያቀድሁት ነገር ኦሮሞ በባህሉና በሃይማኖቱ ላይ ተገናኝቶ መወያየት አለበት። ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ዛሬም... የሚያደርጉ ካሉ ቁሙ ሊሏቸው እንደሚገባ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በኦሮምኛ የተዘጋጀውን ቅዳሴ ካለው ክፍል ላይ አቡነ ሔኖክ ፍትሐት ዘወልድን ሲያነብቡ አይተህ ከሆነ እንደሚመች አየኸው? ሁሉም ይቻላል። ለምሳሌ፦ አማርኛ ለዜማ አይመችም፤ ኦሮሚኛ ግን ለዜማ ይመቻል። ከግዕዙም ጋር ይመሳሰላል። ለምሳሌ ላንሳ፦ የባህር አምላክ በኦሮሚኛ የሚለውን ብናነሳ፤ አምላክ የሚለው በግእዙም፤ በኦሮሚኛውም ይቀድማል። አማርኛው ግን ይገለብጠውና የባህር አምላክ ይለዋል። ለዜማ የሚሆነው ግዕዝና ... ለምሳሌ፦ ብርድ የሚለውን በግዕዙም በኦሮሚኛውም አንድ ነው። አማርኛው ባለቤትን አያስቀድምም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ ቃላት ከኦሮሚኛ ጋር አንድ ናቸው። ስለዚህም በኦሮሚኛ ቋንቋ ቅዳሴውን ብቻ ሳይሆን ዜማውንም መሥራት ይቻላል። ዘፈኑንም ብናነሳ ደስ የሚለው ለዚሁ ነው። የአማርኛ ዘፈኖችን ሰዎች አንድ ዓመት ያህል ጥናት ያደርጉበታል። የእኛ ልጆች የሚዘፍኑት የሚዘምሩት ሲነግሩኝ ግን ግጥሙንና ዜማውን አንድ ጊዜ ከሰሙ ወዲያው በአንድ ቀን ይይዙታል። በዚህ ሥራ ላይ ሁሉም ኦሮሞዎች ቢሰማሩ እስላሞችንና ፕሮቴስታንቶችን ማንም አያልፋቸውም። በመስጊድ ውስጥም በሌላ ቋንቋ ሳይሆን በኦሮሚኛ ቢጸለይ(ቢያመልክ) ሁሉም ሰው ቆሞ ይሰማል። ... ፓርላማ ተመርጬ አባጋሪ ኦሮሚያ ሆኜ ስመረጥ ወይም የአበጋር መሥሪያ ቤት በበላይ ኃላፊነት ስመደብ ወይም ስሾም ላለፉት ስድስትና ሰባት ወራት ይሆናል። የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ አማኞች በዚህ የአገልግሎት ድርሻህ ብትቀጥልበት ይሉኛል፤ እዚያ እንዳልገኝ የሚፈልጉት ደግሞ ፊት ለፊት ባይሉኝም የማይፈልጉ አሉ። እኔም በተቻለ መጠን ሕጉን ጠብቄ ነው የምሄደው:: ስለዚህም እኔ የማደርገው ፦ (1) እንደ ኦሮሚያ ክልል ቤተ ክህነትን ማቋቋም እፈልጋለሁ። ልክ እንደ ሕገ መንግሥቱ ማለትም ለምሳሌ የእስላም፣ የፕሮቴስታንት፣ ካቶሊካውያኑም አላቸው። ይህንን ኦርቶዶክሳውያኑ ግን ጆሯቸው መስማት ኤፈልግም። ሳነሳባቸው ይህማ ተለያየ ማለት ነው ይላሉ። አሁን ግን በራሴ ጥረት እንደ ኦሮሚያ ምክር ቤት ያለውን ጽ/ቤት ማቋቋም ሲሆን፤ (2) በኦሮሚያ ባሉት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መጀመርያ እዚያው ባሉበት እንዲደራጁ፤ ከዚያም መጣቶችና ዲያቆናት ሰልጥነው እንዲገቡበት ማድረግ እንችላለን። ባለ ሃብቶች፣ የኦሮሞ ምሁራን ደግሞ በዚህ ዙርያ ላይ እገዛ ሊያደርጉልን ይገባል።ሊረዱን ፍላጎት ያሳዩንም አሉ።
አበጋርን ከመምራት ጋር በተጨማሪ ይህንንም እሠራለሁ። እንግዲህ ያለሁበት ሁኔታና ዓላማዬ ይህን ይመስላል። እዚህ ማንሳት የማልፈልጋቸው እጅግ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። ይህ ተግዳሮት ሂደት በሂደት እየተፈታ የሚሄድ ነው።
ይህ ዛሬ የተደረገው አዋጅ መሰናክል ሊሆኑ የተዘጋጁ ሰዎችን ባሉበት እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል። ተደብቀው ያደርሱት የነበረው በደል ስላልሆነ ማለት ነው። ግን እኮ ይወደዱ ነበር፤ ለምሳሌ፦ ከግብጽ ሰዎች ጋር ስንገናኝ እንግባባለን፤ እነርሱም እኔም ኦርቶዶክስ ነን፤ ቋንቋችን ግን የተለያ ነው። ቀኖናችንም ዶግማችንም አንድ ነው፤ ቋንቋችን ግን የተለያየ ነው። አሁን ግን የቋንቋ አሁን አሁን ምን እንዳስተዋልኩ ታውቃለህሰ? ቋንቋ፤ ቋንቋ ብቻ አይደለም። ቋንቋህ ማንነትህ ነው፤ በቋንቋህ የራስህን ነገር ስትናገርና ... አሁን የሆኑ ሰዎችን አያለሁ የትርጉም ሥራ እንሠራለን የሚሉትን፣ “መጀመርያ በአማርኛ የነገርንህ ነገር እኮ በኦሮሚኛ እንዲህ ማለት ነው” ብለው ይነግሩሃል። ይህ አይሆንም። ይህ ማለት ምን ማለት ነው መሰለህ ገና ይተረጉሙታል፤ አንተ በባህልህ አትረባም፤ ምንም አታደርግም ... መጀመርያ የነገርንህ ይህን ለማለት ነው እንዲህ ያልነው ይሉታል። ይህ እርባና አይሰጥም።
ቀኖናውንና ዶግማውን ትቀበላለህ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ራስህ ቀይረኸው(አዛምደኸው) ትቀበላለህ። ክርስትናው ይስፋፋ እንጂ (እንዲስፋፋ) ጌታ ኢየሱስ ሌላ ምንም አይፈልግም። ስለዚህ ይህን ማስፋፋት ነው። አሁን አበጋር የምሠራበት መሥሪያ ቤት ከቤተ እምነትም ጋር ይያያዛል። አባ ጋሪ ማለት የሃይማኖት ሰው ማለት ነው፤ አልቅሶ የመጣን ሰው በአማርኛው እንባ ጠባቂ እንደ ማለት ነው። የሚያለቅስን ሰው አጽናንተኸው፤ እንባውን አብሰህ፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አስተዳደር ላይ ላሉት የዚያ ተበዳይ ሰው ሕግ ከተጣሰበት ሕግ ጥሰሃል፤ አስተካክልለት የሚል ነው። ተበዳዩም ከተሳሳተ እርሱንም ማስረዳት ነው። የተጣሰብህ ሕግ የለም፤ አስተዳዳሪውም አልበደለህም፤ ግባ ብለን እንመክረዋለን። መልካም አባት የሚያደርገውም ይኸው ነው።
ስለዚህም እርሱ ተመችቶኛል። ትንሽ ከኃይማኖት ተቃራኒ አይደለምና። ስለዚህም በመጨረሻ የማስተላልፈው መልእክት (1) ይህን ነገር ለማድረግ ባለሃብቶች፣ ምሁራን ሊረዱን ይገባል ብዬ አምናለሁ። ወጣት ምሁራንም ሊደማመጡ፤ ሊቀባበሉ፤ አብሮ መወያየት ይገባቸዋል። አሁን ከጠላት ጋር መጣላት አያስፈልግም፤ ለራስ ተወያይቶ ... አሁን ወለጋ ዩንቨርሲቲ አንድ የተሠራ መልካም ነገር አለ፤ ከአዲስ አበባ የሄዱ ልጆች፣ “ለምን በአማርኛ አንጸልይም?” ሲሏቸው፣ “በማናውቀው ቋንቋ አንጸልይም እንቢ ካላችሁን ተውትና ኑ” ብለው በግል ለራሳቸው ጸሎትን ተለይተው አደረጉ። በደንብ በማንሰማው ቋንቋ አንጸልይም፤ መጸለይም አንችልም ብለው። መሥራት እንግዲህ ይኸው ነው።
ይህ የሚቃወም ሰው ካለ “ዘወር በል” ብሎ መቃወም ነው። መልካም ያደረገ ሰውን ደግሞ ባትሰማውም፤ ባያገለግልህም መልካም ነው ካለህ እርሱን አትቃወመው። አይችልም ምን ታደርገዋለህ ታዲያ? በሃሳቡ ምንም ይኑር የሃይማኖት አባት ሆኖ መልካም ነው ብሎ ከተቀበለህ እሺ በእጄ ብለህ እንደአባት ትቀበለዋለህ። ይህ ትክክል አይደለም፤ የጠላት ነው፤ በቋንቋህ አታድርገው የሚልህ ከሆነ ሂድ፤ ወግድ አንተ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነህ ልንለው ይገባናል። ወንጀለኛም ስለሆነ በግልጥ መናገር ነው።
ቋንቋህን የፈጠረው ፈጣሪ ነው ። እያልኩ ያለሁት ቋንቋ የፈጠረህን ፈጣሪ የምታመሰግንበት ነው። ለዚህም ነው ጌታ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ሲልክ “ፈጣሪ በፈጠረለት ቋንቋ እኔን እንዲያመልኩ፤ ፈጣሪን መለመን፤ ማምለክ የሚቻላቸው እግዚአብሔር በፈጠረላቸው ቋንቋ ሊሆን ይገባል። የአሁኑም የመንግሥት ፖሊሲ ለሰው የሚመቸው ለዚህ ነው።
አብዲ፦ እኔ በበኩሌ በንግግርዎ እጅግ ረክቻለሁ። ከእርስዎ መማር የፈለግሁትን ብዙ ነገር አጊኝቻለሁ። ተመልካቾቻችንም ብዙ እንደሚያገኙ አምናለሁ። እንደ አንድ ሰው እኔ በበኩሌ ያለኝን ጥያቄዎች ስለጨረስኩ በኦቢኤስ አማካይነት የሚያስተላለፉት መልእክት ካለዎት ማስተላለፍ ይችላሉ።
ቀሲስ፦ ገዳ በውስጡ ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ነው። ሁሉም በገዳ ጥላ ሥር ነው ያለው። ይህ ጸሐፍት ሊጽፉት ይገባል፤ ... ሊሳተፉበት ይገባል። ኦሮሞ ደግሞ መተሳሰብ፤ ተቀምጦ መወያየት፤ አብሮ መወያየት ያግባባል፤ ሲግባቡ ተስማምተው በአንድ ጎጆ ይገቡ፤ ኦሮሞ መቻቻል፤ መስማማት፤ መተሳሰብ አለበት እላለሁ።
እኔ ይህን መጽሐፍ የጻፍኩት ገንዘብ ላገኝበት ብዬ አይደለም። ለማሳተም፣ አርትዖት ለመሥራት በኮንፒውተር ስጽፍ ከአንዳንድ ነገር በቀር መፍጠን አልችልም፤ በዚህ ላይ የረዳኝም ሰው የለም። ሰው ሊገዛው ይገባል። ዋጋውም ሃምሳ ብር ነው፤ ገዝተውም ቢያዩት ጥሩ ነው፤ በሌላ መንገድ ደግሞ ለእነዚያ ሕትመቶች መልስ ይሆናል። ሌላም ለማሳተምም በዝግጅት ላይ ስላለሁ ይረዳኛል ብዬ አስባለሁ። ሰዎች ይህን ቢገዙት በጣም እወዳለሁ። ክበሩልኝ እላለሁ።
አብዲ፦ መልካም። በኦቢኤስ ስም እጅግ አድርገን እናመሰግንዎታለን።
ቀሲስ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሐሰት መምህራን ይጠብቅ፤ አሜን።
ምን ችግር አለው ቢቋቋሞ ቤተ ክርስቲያኗ በኦሮሚያ ክልል ያን ያህል እንቅስቃሴ እያደረገች አይደለም ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በስተቀር በኦሮሚያ ክልል የፕሮቴስታንትን ያህል እንቅስቃሴ አለማድርጓ ለነዚህ ወገኖች በእነሱ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚቃረን መስሎ ስለሚታያቸው ቤተክርስቲያኗ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንድታቋቅም አይፈልጉም ስለዚህ ቤተክርስቲያኗ ይህንና የመሰለውን ተግዳሮቶች አልፋ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል
ReplyDeletebetaam yasaznal
ReplyDeleteOrtodox befitm eko kenesu gar nat
ReplyDeleteገራሚ ነው በየክልሉ ከሆነ 9 ሲኖዶስና አንድ ፌዴራል ሲኖዶስ ሊያስፈልገን ነው በየቋንቋው ከሆነ ደግሞ 84 ሲኖዶስ
ReplyDelete