Saturday, 6 October 2018

አንተን ካየሁ ወዲያ

Please read in PDF

በፍርሐት ቆፈን ተይዞ
አልጋው በድካም ተከቦ
በሠርጉ እያለቀሰ

አለ ሲሉት እየፈረሰ …
በመርገም ዘር ተፀንሶ
ሕይወት በሞት ተገሶ
ሲኖር ትውልድ የደም ስልባቦት አርግዞ
እየዳኸ በጣዕር
አለመኖርን ሲኖር … 

ስምዖን ግን ተግቶ
ለተስፋው ቃል ተንበርክኮ
የጌታን መወለድ በትንቢት ታግሶ
እርጅና ሳይገታው በመንፈስ ታድሶ …
ለእስራኤል መጽናናት ለወገኑ ማረፍ
ዓይኖቹ ሳይፈዙ የዘመኑ ርዝመት - ራእዩን ሳያረግፍ
ሞትን ያህል ነገር እግዚአብሔር አስሮለት
ወጣ ወደ መቅደስ ሕፃኑን ለማየት፡፡
እንደ አንበሳ ደቦል እየተቻኰለ
እርጅናውን ረስቶ እየተቃጠለ
አቀፈው ናፍቶቱን የዘመናት ሕልሙን
ሳመው በከንፈሩ ብርሃን ጉንጮቹን፡፡
አረጋዊው አዲስ ሆነና ጐልማሳ
ትንቢት ተናገረ ለሕፃኑ ንጉሥ- ለይሁዳ አንበሳ፡፡
በእውነት ለሰው ሁሉ አንተ ነህ መዳኑ
ሁሉን የምትገልጥ የዓለም ብርሃኑ
ለእስራኤል ሕዝብህ ክብርና ሞገሱ
ለኔ ለባርያህም የእርጅናዬ ልብሱ፡፡
የስንብት ቃሌ የዓይኖቼ ማረፊያ
ውሰደኝ ወዳንተ ሕልም የለኝም - በቃ፣ አንተን ካየሁ ወዲያ፡፡

28/1/2001 ዓ.ም ምስራቅ ሐረርጌ፤ ኤጀርሰ ጎሮ ተጻፈ፡፡

No comments:

Post a Comment