እግዚአብሔር
አምላክ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ከወጡ በኋላ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር በተቃረቡ ጊዜ በተደጋጋሚ የተናገራቸው
ቃል ቢኖር እንዲህ የሚል ነው፤ “… ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን
እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤” (ዘዳግ. 8፥11፤ 4፥9፤ 6፥25)። የታዘዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ሊረሳ የሚችልባቸውን ምክንያቶችንም
ሲያስቀምጥ እንዲህ ይዘረዝራቸዋል፤
“ከበላህና ከጠገብህ
በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ
በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና
በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም
አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን
ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። ነገር ግን ዛሬ እንደሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት
ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ።” (ዘዳግ. 8፥12-18)






